በአዲስ አበባ ከሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንዱ በሆነው ብርሃንህ ዛሬ የሚታየው ሁኔታ፣ የሀብታም ልጆችን ከሚያስተምሩ የከተማዋ ትምህርት ቤቶች ሲነፃፀር ልዩነቱ እጅግ ሰፊ ነው፡፡
እዚያ ባለፀጋ አባቶችና እናቶች ልጆቻቸውን በተሽከርካሪ የሚያመላልሱ ሲሆን፣ ጠዋት እጅግ ውብና ውድ ከሆኑት መኪኖች የሚወርዱት ሕፃናት ከመጠናቸው ጋር የሚቀራረበው በጀርባቸው የሚያዝሉት ቦርሳ በሚወዱት የካርቱን ገፀ ባህሪ ያሸበረቀ ነው፡፡ በውስጡ ደግሞ የሚመርጧቸው የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን የያዙ የምሳ ዕቃዎችን ያገኛሉ፡፡
በአንፃሩ የብርሃንህ ዛሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ግርግር በበዛበት የትምህርትና የሥራ መግቢያ ሰዓት በጠባቡ የሃያ ሁለት መንገድ በእግራቸው ሲራወጡና ሲጣደፉ ይታያሉ፡፡ የለበሱት ሰማያዊ ሹራብና ጥቁር ሰማያዊ ሱሪ የትምህርት ቤቱ ዩንፎርም ሲሆን በአብዛኛው የተቀዳደደ ነው፡፡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ለማድረስ ያጀበ ወላጅ ማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ልጆቹ ቀኑን ሙሉ ትምህርት ቤት የሚውሉ ቢሆንም፣ ከፊሎቹ ልጆች ግን የምሳ ዕቃ የላቸውም፡፡ ከልጆቹ ገጽታ የባለፀጋ ልጆች እንዳልሆኑ መለየት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ልጆች መካከል ምን ያህሉ በትምህርት ገበታቸው ለመቀጠል ዓመቱን ይጨርሳሉ የሚለውን ለመመለስ አዳጋች ነው፡፡
‹‹ባለፈው የትምህርት ዘመን ብቻ 74 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፤›› ያሉት ወ/ሮ ፋንቱ ኃይሉ ሲሆኑ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የብርሃንህ ዛሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡ ትምህርታቸውን ያቋረጡት ተማሪዎች ወይ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ካልሆነም ቤተሰቦቻቸው ሊመግቧቸው የተሳናቸው ናቸው፡፡
የምግብ ፕሮግራም ሕፃናት ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሕፃናትን ቁጥር ለመቀነስና የትምህርት ውጤታቸውን ለማሻሻል መንግሥታት የቀረፁት ስትራቴጂ ነው፡፡
በኢትየጵያ ለሕፃናቱ በትምህርት ቤቶች ምግብ የማቅረብ ፕሮግራም ከአሥር ዓመት በፊት በዓለም የምግብ ፕሮግራምና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር የተጀመረ ነው፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር በሚመራው ፕሮግራም በመላው አገሪቱ በ1,200 ትምህርት ቤቶች 650,000 ተማሪዎች እንደሚረዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ተማሪዎቹ በቀን አንድ ጊዜ በቫይታሚን የበለፀጉ የተለያዩ ምግቦች ይቀርቡላቸዋል፡፡ በተጨማሪም በአርብቶ አደሮች አካባቢ ለሚገኙ 153,000 ሴት ሕፃናት ወደ ቤታቸው የሚወስዱት የአትክልት ዘይት ይከፋፈላል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሴት ሕፃናት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማበረታታት ይህን ዘይት የሚሰጠው ከ80 በመቶ በላይ በትምህርት ገበታቸው ላይ ለተገኙት ብቻ እንደሆነ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፕሮግራሙ ያለው ‹‹በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉና ዝቅተኛ የቅበላ አቅም ያላቸው ቦታዎች›› በሚባሉት በአፋር፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ብሔራዊ ክልሎች ነው፡፡
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች በፕሮግራሙ ያልተካተቱ በመሆናቸው፣ ደሃ ሕፃናት በዕርዳታ ድርጅቶችና በበጎ አድራጊ ግለሰቦች ካልተረዱ በቀር ትምህርታቸውን ለመቀጠል ይቸገራሉ፡፡ የእነዚህ አካላት ተደራሽነትና ውጤታማነት ደግሞ ከፕሮግራሙ ጋር ሲነፃፀር ደካማ ነው፡፡
ይሁንና በቀደማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ የተመራው ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በተያዘው የትምህርት ዘመን ለሕፃናቱ በትምህርት ገበታቸው ላይ ምግብ ሊያቀርብ እንደሆነ ተገልጾ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታትም ፕሮግራሙን በአዲስ አበባ ለመጀመር የተለያዩ ጥናቶች ተደርገው ውይይቶችም ተከናውነው ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይለ ሥሳሌ ፍስሐ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ያለውን ችግር እንረዳለን፡፡ ችግሩን በተቀናጀና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመቅረፍ ዝግጅት እያደረግን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ዕቅዱ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በተያዘው የትምህርት ዘመን 730 ተማሪዎችን የመዘገበው ብርሃንህ ዛሬ ትምህርት ቤት ግን መጠበቅ የሚችል አይመስልም፡፡ አዲሱ የትምህርት ዘመን ከተጀመረ ገና አንድ ወር ብቻ የተቆጠረ ቢሆንም፣ ሁለት ተማሪዎች ግን አስቀድመው ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡
‹‹እዚህ የመጡት ትምህርት ለመማር ነበር፡፡ አሁን ግን የጎዳና ተዳዳሪ ሆነዋል፤›› ሲሉ ወ/ሮ ፋንቱ አክለዋል፡፡ የትምህርት ቤታቸው ችግር በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በሚገባ እንደሚታወቅ ያመለከቱት ወ/ሮ ፋንቱ፣ ‹‹የሚበሉት ስላጡ ሕፃናቱ ትምህርት አቋረጡ የሚለውን መስማት በጣም የሚያሳዝን ነው፤›› ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በፕሮግራሙ የሚካተቱ ተማሪዎችን ማንነትና ቁጥር ለመለየት እያጠና መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 216 የሕዝብ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው ብርሃንህ ዛሬ ይህንን ጥናት ለመደገፍ የሚያስችል ኮሚቴ እንደሚያቋቁም ይጠበቃል፡፡ ኮሚቴው እንደሌሎች ትምህርት ቤቶች ሁሉ ከሴቶች ብቻ የሚዋቀር ሲሆን፣ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ተማሪዎች ይለያል፡፡ የመምረጫ መሥፈርቶቹ በትምህርት ቢሮው የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ትምህርት ቤቱ ከአጠቃላይ ተማሪዎቹ 41 በመቶ የሚሆኑ 300 ተማሪዎችን በታቀደው የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራም ሊካተቱ እንደሚገባ ለይቷል፡፡ ይህ ቁጥር 20 በመቶ የሚሆኑ ክርስቲያን ኬር በተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት የሚረዱ 150 ተማሪዎችን አላካተተም፡፡
በሌሎች የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ቢኖርም እንደ ብርሃንህ ዛሬ ግን የተባባሰባቸው አይደሉም፡፡ ከብርሃንህ ዛሬ በጥቂት መቶ ሜትሮች የሚርቀው ምሥራቅ ድል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤትነት ቢቋቋምም፣ ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ መንግሥት ትምህርት ቤትነት ተቀይሯል፡፡ በትምህርት ቤቱ 937 ሕፃናት በተያዘው የትምህርት ዘመን ለመማር ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን 72 ተማሪዎች (7.6 በመቶ) ብቻ በፕሮግራሙ እንደሚካተቱ የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ወ/ሮ ፅዮን ጌታቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ፅዮን ጉዳዩን ለማስተባበር የተቋቋመው ኮሚቴ ሊቀመንበርም ናቸው፡፡
በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ያለው ችግር በአማካይ ቢሰላ እንኳን ወደ 36,000 ሕፃናት ተማሪዎች በምግብ ችግር ምክንያት በአዲስ አበባ ብቻ ከትምህርት ውጪ ይሆናሉ፡፡ አዲስ የሚጀመረው ፕሮግራምም ለመቅረፍ ያቀደው የእነዚህን ተማሪዎች ችግር ነው፡፡
የሕፃናት የትምህርት መብትና የምግብ ፕሮግራም
የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነቶች ቻርተር ለሕፃናት ነፃና አስገዳጅ ትምህርት ስለማቅረብ ይደነግጋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2002 ኢትዮጵያ ያፀደቀችው ይኼው ቻርተር በአንቀጽ 11 ላይ የስምምነቱ አካል የሆኑ አገሮች ይኼንን መብት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሚባሉ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ ያሳስባል፡፡
ኢትዮጵያ የቻርተሩን አፈጻጸም አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርቡ ሪፖርት ያቀረበች ሲሆን፣ ስምምነቱ ግን የመጀመሪያው ሪፖርት ከቀረበ በኋላ በየሦስት ዓመቱ ጊዜውን የጠበቀ መደበኛ ሪፖርት እንዲቀርብ ይጠይቃል፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ ሪፖርት የመጀመሪያና የሦስት ዙር ውዝፍ ሪፖርቶችን ያካተተ ነው፡፡ በቻርተሩ የተቋቋመው የሕፃናት መብት ኤክስፐርቶች ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ጋር መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ውይይት አድርጎ ነበር፡፡
በዕለቱ የልዑካን ቡድን በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ የተመራ ሲሆን በቡድኑ ውስጥ የጤና፣ የትምህርትና የፍትሕ ሚኒስቴር ተወካዮችን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ባለሙያዎች ተካተው ነበር፡፡ በዚህ መልኩ የተደራጀ ልዑክ ማስተናገድ አዲስ የሆነባቸው ኤክስፐርቶቹ ለኢትዮጵያ ጥረት የምሥጋና ቃላትን ቸረው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ባለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተረዳች ባለፉት አሥር ዓመታት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ሞት በመቀነስ፣ የትምህርት ቅበላን በማሳደግ፣ የሕፃናት ምዝገባን በማድረግ፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ መድልኦዎችን በማጥፋት፣ ጎጂ ልማዶችን በመቀነስ ላመጣችው ከፍተኛ ውጤትም ተሞግሳለች፡፡
‹‹በአፍሪካ የሚገኙ አንዳንድ አገሮች ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡና የተፈጥሮ ሀብትም እያገኙ ነው፡፡ የሕፃናት መብት ኤክስፐርቶች ኮሚቴም ‹ይህን ዕድል ለሕፃናት ምቹ የሆነች አፍሪካን ለመፍጠር ምን ያህል እየተጠቀማችሁበት ነው?› ሲል ይጠይቃል በማለት የገለጹት የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች የኤክስፐርቶች ኮሚቴ ሰብሳብ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቢንያም ዳዊት መዝሙር ናቸው፡፡
የተመድ የሕፃናት መብት የኤክስፐርቶች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢም የሆኑት ዶ/ር ቢንያም፣ ኢትዮጵያ የቻርተሩን አፈጻጸም ሪፖርት ስታደርግ አገሪቱ ያለችበት ልዩ ሁኔታ ከግንዛቤ እንዲገባ መጠየቋን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ልዩ ሁኔታዎችም አገሪቱ ውስጥ 45 ሚሊዮን ሕፃናት መገኘታቸው፣ ስምምነቱ ሲፀድቅ አገሪቱ በዚህ መብት አፈጻጸም ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷና ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመዘገቡት አበረታች ስኬቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሪፖርት የሕፃናት የምግብ ፕሮግራምን ከትምህርት ቅበላና ከትምህርት ጥራት ጋረ አገናኝቶ ያቀርበዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል የምግብ ፕሮግራሙ የተማሪዎችን የቅበላ አቅም በ25 በመቶ ጨምሯል፤›› ሲልም ያትታል፡፡
ዶ/ር ቢንያምም፣ ‹‹ሕፃናት በባዶ ሆድ ትምህርት ትርጉም ባለው መንገድ እንዲማሩ መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመላው አፍሪካ የምግብ ፕሮግራሞችን በትምህርት ቤቶች ማካሄድ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎችን ቁጥር በመጨመር፣ አቋርጠው እንዳይወጡ በመከላከልና የትምህርት ውጤታቸውን በማሻሻል ለውጥ ማምጣቱንም ዶ/ር ቢንያም ያስረዳሉ፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመንግሥት ዕርዳታ ካላገኙ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዕርዳታ ላይ መንጠልጠላቸው ግድ ይሆናል፡፡ ከብርሃንህ ዛሬ ትምህርት ቤት በተቃራኒ ምሥራቅ ድል ትምህርት ቤት ችግረኛ ብሎ የለያቸውን 72 ተማሪዎች የሚረዳ የውጭ አካል የለውም፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍ መምህራኑና ተባባሪ ሠራተኞች ራሳቸው በማዋጣት የተማሪዎቹን ችግር ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
‹‹ከደመወዛችን አሥር በመቶውን ለማዋጣት እየተወያየን ነው፤›› በማለት ወ/ሮ ፅዮን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ይህ መዋጮ ተማሪዎቹን በትምህርት ገበታቸው እንዲቆዩ ለማድረግ በቂ ስለመሆኑ ወ/ሮ ፅዮን እርግጠኛ አይደሉም፡፡