Tuesday, 26 July 2016

መንግስት ተዝረከረከ፤ ወገኛ ‹ህዝብ› በዛ፤ አገር በግጭት ተመሳቀለ፤ ‹የአፍሪካ መዲና› በቆሻሻ ሽታ ታወደ


ሰዎች፣ “የዘራነውን እያጨድን ነው”

   አዲስ አበባ ለወትሮም ከቆሻሻና ከመጥፎ ሽታ፣ ትንሽ እፎይታ የሚያስብል ትንሽ ፋታ ያገኘችበት ጊዜ የለም፡፡ የክረምት ዝናብ ሲመጣ፣ አገስ ገሰሱን ጠራርጎ የሚያፀዳ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ዝናብ ሲያባራ፣ በየጎዳናው የምታዩት ጎርፍ፣ ጥቁረቱ ያስፈራል፡፡ ሽታው ያጥወለውላል፡፡ በየመፀዳጃ ቤቱና በየቱቦው የተጠራቀመውን ቆሻሻ ጎልጉሎ፣ በየአደባባዩ ይዘረግፈዋል፡፡ 

የቆሻሻ ሽታ በከተማዋ የተባባሰው ግን፣ ባለፉት አምስት አመታት ነው፡፡ ድሮ ድሮ፣ በየቦታው ከሚከማቸው ቆሻሻ፣ ግማሽ ያህሉ በመኪና እየተጫነ ይወሰድ ነበር፡፡ ግማሹ ደግሞ፣ እዚያው እየበሰበሰ ከተማዋን በሚሰነፍጥ መጥፎ ሽታ ያውዳታል። ብዙ ሰው ይህንን የማማረር ልምድ ነበረው፡፡ መንግስትም፣ ቆሻሻውን ሙሉ ለሙሉ ለማንሳትና ለማፅዳት ቃል ከመግባት አይቦዝንም ነበር - “ሁሉም ሰው አካባቢውን ቢያፀዳ፣ ከተማዋ ትፀዳለች” የሚል ማምለጫ መፈክርንም እየተጠቀመ፡፡ 

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን፣ አዲስ ፈሊጥ መጥቷል - “ቆሻሻ ሀብት ነው”  የሚል ፈሊጥ። ይሄ ቀልድ አይደለም፡፡ የከተማዋ መስተዳድር፣ ይህንን ፈሊጥ በደማቁ እያተመ በየአካባቢው ሲለጥፍ አይተናል፡፡ ከዚህም ጋር፣ “ቆሻሻን መልሶ መጠቀም” የሚል ስብከት፣ የእለት ተእለት ድግምት ሆኗል። ከዚህ በኋላ ነው፤ በየሰፈሩ ቆሻሻ እያጠራቀሙ መከመር፣ እንደ ቁም ነገር መታየት የተጀመረው፡፡ በቃ፤ ፋታ የሌለው መጥፎ ሽታ፣ የከተማዋ የዘወትር ድባብ ሆነ፡፡ 

ቆሻሻው የሚነሳው፣ እንደ ተራራ ከተከመረ በኋላ ነዋ፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ደግሞ፤ ተከምሮ ተከምሮ እዚያው እየበሰበሰ ነው፡፡ ከከተማዋ ውጭ የሚገኘው ቆሻሻ መጣያ ድንገት ተዘግቷል፡፡ በቃ፣ ከዳር ዳር፣ ቀን ከሌት፣ ክፉኛ የምትሰነፍጥ ከተማ ሆናለች  አዲስ አበባ፡፡
በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ፈፅሞ ያልታየ ሰፊ የኮሌራ ወረርሽኝ በአዲስ አበባ መከሰቱ ምን ይገርማል?
ብዙ መመራመር አያስፈልግም፡፡ መንግስት በጣም ከመዝረክረኩ ተነሳ፣ ከተማዋ በቆሻሻ ተጥለቅልቃ፣ ውሎና አዳሯ ከመጥፎ ሽታ ጋር ሆኗል። ነገር ግን ብዙዎቻችንም፣ የዚህ ጥፋት ተካፋዮች መሆናችንን ማስተዋል አለብን፡፡ “ቆሻሻ ሀብት ነው” የሚለው ፈሊጥ፣ ውሎ አድሮ ከተማዋን ለቆሻሻ ክምር፣ ነዋሪዎቿን ለኮሌራ ወረርሽኝ እንደሚዳርግ ማወቅና መናገር ነበረብን፡፡ ግን፣ የተናገረ አለ? ይሄ ቀልድና ጨዋታ ይቅርብን ብሎ ምክር የለገሰ ሰውስ አለ? “ቆሻሻን መልሶ መጠቀም” በማለት፣ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና ባለስልጣናት ስብከታቸውን ለአመታት ሲያዘንቡብን፣ “ኧረ ለንፅህና ቅድሚያ እንስጥ” ብሎ የተከራከረ ሰው ካለ ንገሩኝ፡፡ 

“ግንኮ ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ይቻላል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ መልሶ መጠቀም ከተቻለ ደግሞ ቆሻሻ ሀብት ይሆናል” ብሎ ዛሬም የሚከራከር ይኖራል፡፡ ይሄ ዝርክርክ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከመነሻው አንድ ነገር፤ የማንጠቀምበትና የሚጎዳ ሲሆን ነው ቆሻሻ ተብሎ ከየቤቱ የሚወጣው፡፡ አለበለዚያማ አውጥተን ለምን እንጥለዋለን? ከጣልነውም፣ ተሻምቶ የሚወስድ አይጠፋም ነበር፡፡ በቃ፣ ቆሻሻ ነው፡፡ የንፅህና ጉድለት መጥፎ መሆኑንና ቆሻሻን ማፅዳት እንደሚያስፈልግስ አናውቅም? በአጭሩ፣ ቆሻሻን ማስወገድ ቀዳሚ ትኩረት መሆን ነበረበት - ስለ ቆሻሻ የምናስብ ከሆነ። ምናልባት፣ የተወሰነውን ቆሻሻ መልሶ መጠቀም የሚችል ሰው ካለ … ይቅናው፡፡ ዋናው ቁም ነገራችን ግን፣ ቆሻሻን ማስወገድና ማፅዳት መሆን ነበረበት፡፡  እንዲህ በእውነታ ላይ ተመስርተን በስርዓት ማሰብ ብንችል ኖሮ፣ “ቆሻሻ ሀብት ነው” በሚል ፈሊጥ አብረን ከመጨፈር ወይም በዝምታ ከማለፍ ይልቅ፣ መንግስት ወደ ህሊና እንዲመለስ መምከር እንችል ነበር፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው? በዝርክርክ አስተሳሰብ፣ “ቆሻሻ ሀብት ነው” የሚለውን ፈሊጥ እንደ ዋና የኑሮ መርህ የምንሰብክ፣ የምንቀበል አልያም በቸልታ የምናስተናግድ ከሆነ ግን፤ ተያይዘን የቆሻሻ ክምር ስር ተጨፍልቀን ለማደር እንደተስማማን ይቆጠራል፡፡ 

ዝርክርክ አስተሳሰብና ጭፍን ሃሳቦች፣ በተግባር መዘዝ እንደሚያስከትሉ ማወቅ አለብን፡፡ ጭፍን ሃሳቦችን እየሰበክን፣ እየተቀበልን ወይም በቸልታ እያስተናገድን የከረምን ሰዎች፤ ውሎ አድሮ መዘዙ ሲመዘምዘን፣ በቆሻሻ ሽታ እና በኮሌራ ስንወረር፣ … መንግስትን ለማማረርና ባለስልጣናትን ለመውቀስ እንሯሯለጣለን፡፡ ይሄ፣ … ወገኛ ግብዝነት ነው፡፡ 

ሌሎቹንም ችግሮች ተመልክቷቸው፡፡ ከ20 ዓመት በፊት፣ እነ ኢህአዴግ፣ ኦነግ፣ መአህድ እና የመሳሰሉ ፓርቲዎች ነበሩ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ፊታውራሪዎች፡፡ ዛሬ ግን፤ ብዙ ሰዎች ወደ ጭፈራው ተቀላቅለዋል፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ አብረናቸው ባንጨፍርም፣ በዝምታ ከማስተናገድ ያለፈ ቁም ነገር እየሰራን አይደለም፡፡ 

ታዲያ፣ በዘረኝነት የተቃኙና በብሄረሰብ የተቧደኑ ግጭቶች በየቦታው ሲቀጣጠሉ፣ ተጠያቂው ማን ነው?  አዎ፣ መንግስት ትክክለኛ ኃላፊነቱን ስላልተወጣ ጥፋተኛ ነው፡፡ በብሄረሰብ ተቧድነው ግጭት የሚቆሰቁሱ ሰዎችም፣ ዋና ጥፋተኞች ናቸው። ነገር ግን፣ ዘረኝነትን እንዲሁም የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካን፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያስተጋቡ ብዙ ሰዎችም፣ ጥፋተኞች ናቸው፡፡ በቸልታ ዝምታን የመረጥን ሰዎችም፣ ከጥፋት የፀዳን አይደለንም፡፡ 

እናም፤ ግጭት በተፈጠረ ቁጥር መንግስትንና ባለስልጣናትን ብቻ ማውገዝ፣ ቀሽም ግብዝነት እንዳይሆንብን፣ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካንና የዘረኝነት አስተሳሰብን ከስረ መሰረቱ መቃወም ይኖርብናል፡፡ በጅምላ የመፈረጅና የመናገር በሽታችንን ማስወገድ አለብን፡፡ እያንዳንዱን ሰው፣ በስራውና በባህርይው የምንመዝንበት ስልጡን አስተሳሰብ ይዘን ጥረት ካላደረግን፣ ወገኛ ሆነን እንቀራለን፡፡ 
 
ይህን ብቻ አይደለም፡፡
ኢንቨስትመንትንና ባለሀብትን በጭፍን በመጥላት በኩል፤ የ60ዎቹ ዓመተ ምህረት ሶሻሊስት ምሁራን፣ ኢህአፓንና ኢህአዴግን ጨምሮ በርካታ የአገራችን ፓርቲዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን፣ ስንቶቻችን ነን፣ የሀብት ፈጠራ ስኬታማነትን እንደ ጀግንነት የምንቆጥረው? በኢቲቪ የሚሰራጨው “ማያ” የተሰኘውን አሰልቺ ፕሮግራም ለአፍታ ተመልከቱ፡፡ የግል ሆስፒታሎችንና ክሊኒኮችን የሚያወግዝ ተከታታይ ፕሮግራም፤ ከዚያ ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶችን በዘመቻ ለመዝጋት የሚቀሰቅስ ፕሮግራም፤ በዚህ ሳምንት ደግሞ በደፈናው ባለ ሀብቶችን የሚያወግዝ ፕሮግራም … 

“ማያ” የሚያሰራጫቸው፣ እንዲህ ዓይነት ሃሳቦች ለአገራችን አዲስ አይደሉም፡፡ ከአገራችን ባህል ጋር የተሳሰሩ ነባር ሃሳቦች ናቸው፡፡ ከአገራችን ፓርቲዎችና ከፖለቲከኞች፣ ከጋዜጠኞችና ከምሁራን ዘወትር የምንሰማው ተደጋጋሚ ስብከት ምን ሆነና! በዚህ ስብከትም ነው፤ መንግስት በየጊዜው፣ በዋጋ ቁጥጥርና በአላስፈላጊ ገደቦች፣ የግል ኢንቨስትመንትን  የሚያዳክሙ ተግባራት የሚፈፀመው፡፡ በዚህ ስብከትም ነው፣ መንግስት በየመስኩ በቢዝነስ ስራ ላይ ለመሰማራት ከፍተኛ ሀብት የሚያባክነው፡፡ 
በአንድ በኩል፣ ሚኒባስ ታክሲዎች በኪራሳ ከገበያ እየወጡ የሚገኙት በአላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥር ሳቢያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ መንግስት ለአዲስ አበባ ካመጣቸው ባቡሮች መካከል ግማሾቹ በብልሽት ያለ አገልግሎት መቀመጣቸውን ተመልከቱ። ታዲያ፤ ‹‹በትራንስፖርት እጥረት ተንገላታን›› በማለት መንግስትን ተጠያቂ ብናደርግ ይገርማል? አይገርምም፡፡ ነገር ግን፤ የሃብት ፈጠራ ስኬታማነትን የማናከብር ከሆነ፤ በተቃራኒው መንግስት በቢዝነስ ስራ ላይ መሰማራቱን የምንደግፍ ከሆነ፤ እኛም የጥፋቱ ተካፋይ ነን፡፡ 
ሰዎች ራሳችንን ባናታልልና ባንሞኝ ይሻላል፡፡ የዘራነውን ነው እያጨድን ያለነው፡፡