ከዕለታት በአንዱ ቀን በአንዲት ሀገር በሚገኝ አንድ መካነ ትምህርት (ዩኒቨርሲቲ) ውስጥ በሥነ-ልቦና (ሳይኮሎጂ) የትምህርት ዘርፍ በአንደኛው ክፍለ ጊዜ የሚያስተምሩ አንድ መምህር ለተማሪዎቻቸው ይህንን ጥያቄ አነሱ፡- ‹‹ሰዎች ለምን ይሳደባሉ?›› የሚለውን፡፡ ተማሪዎችም የመሰላቸውንና በአዕምሯቸው ለስድብ ምክንያት ይሆናል ብለው ያሰቡትን/የገመቱትን ሁሉ መናገር ጀመሩ፡፡
አንደኛው ተማሪ፡- ‹‹በእኔ ግምት ሰዎች ሰዎችን የሚሳደቡት ስለሚበሳጩና ተሰዳቢዎችንም ለማበሳጨት ሲሉ ነው፡፡››
መምህሩ፡- ‹‹ሰዎች በሰዎች ለምን ይበሳጫሉ? ሰዎችንስ ለማበሳጨት ለምን ይፈልጋሉ?››
ተማሪው፡- ‹‹ምን አልባት ስለሚጠሏቸው ይሆናል፡፡››
መምህሩ፡- ‹‹ሰው ሰውን ለምን ይጠላዋል? … ተማሪው ግራ ተጋብቶ ዝም አለ፡፡
ሁለተኛው ተማሪ፡- ‹‹እኔ ደግሞ ሰዎች ሰዎችን የሚሳደቡበት ዋናው ምክንያት ከሀሳባቸው በመነሳት ማለትም የሚናገሩት ንግግር ስለሚያናድዳቸው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሚያስቡት ሀሳብና የሚናገሩት ንግግር በጣም ያናድዳል፡፡ እነዚያ አናዳጅ ሰዎች ካልተሰደቡ ሊስተካከሉ አይችሉም፡፡››
መምህሩ፡- ‹‹በሰዎች ሀሳብ መናደድ ስትል… የሰዎችን የአዕምሮ ሀሳብ ማወቅ ይቻላልን? ያልተነገሩ/ያልተገለጹ ሀሳቦች ሊያናድዱ የሚችሉበት መንገድ ሊኖር ይችላል? የሰዎች ንግግርስ ለምን ያናድደናል? መልካም ያልሆኑ ንግግሮች ቢኖሩስ በስድብ ነው ማስተካከል የምንችለው?›› … ይህኛው ተማሪም መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ሦስተኛው ተማሪ፡- ‹‹በእኔ በኩል… ሰዎች ሰዎችን የሚሳደቡት እንዲሁ በአዕምሮ ከሚፈጠር ጥላቻ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ አለ አይደል… አንዳንድ ሰዎች እንዲሁ ይደብራሉ… በቃ የሆነ ስደባቸው ስደባቸው የሚልህ ስሜት ይመጣብሃል፡፡ ያኔ ትሳደባለህ፡፡››
መምህሩ፡- ‹‹በመሠረቱ ሰውን እንዲሁ መጥላት ትክክል ነው ትላለህ? ‹ሰው ዝም ብሎ ይደብራል› ያልኸው ንግግርህ ራሱ ይደብራል፡፡ ከእነርሱ በኩል ምንም ቃል ሳይወጣ ሀሳባቸውን ሳታውቅ እንዴት ስታያቸው ብቻ ስደባቸው ስደባቸው ሊልህ ይችላል?››
መምህሩ ከዚህ በላይ ለተማሪዎች የመገመት ዕድል መስጠት አልፈለገም፡፡ በሦስተኛው ተማሪ ግምት ቢናደድም ራሱን አረጋግቶ ገለጻ ማድረጉን ቀጠለ፡፡
‹‹ተማሪዎች… አንድ ማስተዋል ያለባችሁ መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ ይኸውም የስድብ መነሻው የተሳዳቢው ልብ/አዕምሮ እንጅ ተሰዳቢው አለመሆኑን ነው፡፡ ሰዎችን የምንሰድባቸው በአዕምሯችን ለእነርሱ ከሰጠነው ሥዕል በመነሳት እንጅ እነርሱ በትክክል ለመሰደብ የሚያበቃ ችግር ስላለባቸው አይደለም፡፡ ሰዎች በምንም መልኩ ስህተት ቢሠሩ እንኳን በመሳደብ ከስህተታቸው ልናርማቸው አንችልም፡፡ እንዲያውም ለበለጠ ጥፋት ነው የምናዘጋጃቸው፡፡ ለመሰደብ ብሎ ክፉ ነገር የሚሠራ ሰውም አይኖርም፡፡ ስህተቱን ሊፈጽመው የሚችለው ባለማስተዋል/ባለማወቅ ነው፡፡ ያንን ስህተት ልናስተካክለው የምንችለው ደግሞ በማስተማር ብቻ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ትክክል አይደሉም በሎ ማመን በራሱ ስህተት ነው፡፡ ስህተት ናቸው ብለን ያመነው ከእኛ ምልከታ አንጻር እንጅ ነገሩ በትክክል ስህተት ሆኖ ላይሆን ይችላል፡፡ በመሠረቱ ‹ፍጹም ስህተት የሆነም ፍጹም ትክክል የሆነም ሀሳብ የለም›፡፡ ሁሉም ነገር አንጻራዊ ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ ለነገሮች ያላቸው ምልከታና ግንዛቤ ይለያያል፡፡ ‹የግድ እንደኔ ካልተመለከትኸው ስህተት ነህ› ማለት ጤነኛ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ በተለይም ለስድብ መሮጥ የአለማወቅን ጥግ ነው የሚያሳየው፡፡ ነገሩን በተሳሳተ መንገድ የተረዳነው እኛው ተሳዳቢዎች ብንሆንስ? የእኛን ትክክለኛነት እንዴት አረጋገጥን? የእነርሱን ስህተትነትስ? ስህተትነታቸውን ብናረጋጥስ መሳደባችን የእነርሱ ችግር ሊሆን ይችላልን? በፍጹም፡፡ ስድብ የተሳዳቢው እንጅ የተሰዳቢው ችግር አይደለም፡፡
ከእያንዳንዱ ስድብ ጀርባ የተሳዳቢው ድክመት አለ፡፡ ተሳዳቢው የመሳደቡ ምሥጢር የተሳደበበት ነገር ለራሱ ሰላም ስለነሳው ወይም ስላበሳጨው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በነገሮች ሁሉ ሰላም የሚያጣና የሚበሳጭ ከሆነ በራስ የመተማመን ችግር እንዳለበት በግልጽ ያሳያል፡፡ የሌሎች ሀሳብ የሚረብሸው ሰው ሀሳብን በሀሳብ ማሸነፍ የማይችል ደካማ ሲሆን ነው፡፡ ባጭሩ ‹መሳደብ ተሸናፊነትን እንጅ አሸናፊነትን አያሳይም›፡፡ የሚያሸንፍ ሁሉ በአሸናፊነቱ ደስ ይለዋል እንጅ አይናደድም አይሳደብምም፡፡
ሰዎች እንዲሁ የሚደብሩንና የምንጠላቸው ከሆነ ደግሞ በውስጣችን ያለው ፍቅር እንደተሟጠጠና ልባችን በጥላቻ መንፈስ እንደተሞላ ያሳያል፡፡ እንዴት ሰው ዝም ብሎ ይደብራል ይባልል? እንኳን ሰው ምንም ነገር የሚያስጠላን ከሆነ ችግሩ ያለው ከእኛው ጋር ነው፡፡ ‹ጥላቻ የሚመነጨው ከውስጣችን እንጅ ከውጭ አይደለምና›፡፡ እኛ የጠላንበት ምክንያት የአዕምሯችን ስሌት እንጅ የነገሮች ሐቂቃ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ልቡ ከፍቅር ሲራቆት የሆነ ያልሆነውን ምክንያት እየፈጠረ ነገሮችን መጥላት ይጀምራል፡፡ ምክንያት ፈልጎ መውደድ እንጅ ምክንያት ፈልጎ መጥላት ለሰው ልጅ የሚጠቅም ባሕርይ አይደለም፡፡ ከሁሉም ሰው ዘንድ መልካም ነገር አለ፡፡ ነገር ግን የእኛ እይታ በጥላቻ ከተሸፈነ ያንን መልካም ነገር ልናገኘው አንችልም፡፡
በሌላ በኩል መሳደብ ትዕግሥት የሌላቸውና ነገሮችን የማመዛዘን አቅምን ያላዳበሩ ሰዎች ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ለበጎም ሆነ ለመጥፎ ነገሮች ምላሽ ከመስጠት በፊት በትዕግሥት አመዛዝኖ ማየት መልካም ነው፡፡ አዕምሯዊ ሆነን የመፈጠራችን ምሥጢርም እንድናመዛዛን ነው፡፡ የሰው ልጅ በስሜት ብቻ ይነዳ ዘንድ መልካም አይደለምና፡፡
ሰበብ እየፈለጉ ከአንደበታቸው ስድብን ብቻ የሚያወጡ ሰዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ካልተሳደቡ ሰላም የማይሰማቸው አይነቶች ናቸው፡፡ ይህ የሥነ-ልቦና (ሳይኮሎጂ) ችግር ነው፡፡ መታከም ያለበት በሽታም ነው፡፡ ጤነኛ ሰው ለመሳደብ አይፈጥንም፤ በመሳደብም አይኖርም፡፡ ሰዎች ካልተሳደቡ የሚያማቸው ከሆነ በሽታው የመሳደብ ልምዳቸው ነው፡፡ ከስድብ ሱሳቸው እስካልተላቀቁ ድረስም በሽተኛ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ተሳዳቢነት በምንም መስፈርት ጤነኝነትሊሆን አይችልም፡፡ ልንታከመው የሚገባ ትልቅ በሽታ እንጅ፡፡››
ተማሪዎች በጸጥታ ውስጥ ናቸው፡፡ መምህሩ ዝም ሲል ሁሉም ጭንቅላታቸውን በአዎንታ ነቀነቁ፡፡ በፊታቸው ላይ የሚታየው የመገረም ስሜትም በግልጽ ይነበብ ነበር፡፡ ውስጣቸው በአንዳች የጥበብ እሳት ሲቃጠል የእሳቱ ነበልባልም ልባቸውን ሲገርፈው ብርሃኑ በፊታቸው ላይ ተንፀባርቆ ይታይ ነበር፡፡ ማንኛቸውም እንደዚህ አስበውት አያውቁም ነበርና በአዲስ እይታ ውስጥ ለአዳዲስ ሀሳቦች መብረር የጀመረው አዕምሯቸው የሰሙትን ከማድነቅ ሌላ አማራጭ አልነበረውም፡፡ በስሜት የምትለፈልፍ ምላሳቸውም በልባቸው የመገረም ልጓም ተገትታ ዝምምም አለች፡፡
‹‹ግልጽ ያልሆነና እንዲብራራላችሁ የምትፈልጉት ሀሳብ ካለ አንሱና እንነጋገር፡፡ ተጨማሪ ማብራሪያ ያለውም አይከለከልም…›› አሉ መምህሩ በጸጥታ ውስጥ ከተቀመጡት ተማሪዎቻቸው ፊት ለፊት እንደቆሙ፡፡ አሁንም ዝምታ ሰፈነ፡፡ ሁሉም ከዚህ ክፍለ ጊዜ በፊት ስለ ስድብ የነበረውን ግምትና ግንዛቤ ከመምህሩ ገለጻ ጋር እያነጻጸረ በመገረም ላይ ነው፡፡
በመጨረሻም አንድ በዕድሜ ሸምገል ያሉ ተማሪ (በዕድሜ ለአንቱታ የደረሱ) እጃቸውን አነሱና ተፈቅዶላቸው ተናገሩ፡፡ ‹‹… መምህራችን ያሉት ሁሉ እውነታ ያለውና ልንማርበትም ልናስተምርበትም የሚገባ ታላቅ ቁምነገር ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ያልተተቀሰ የስድብ ዐቢይ ምክንያትም አለ፡፡ ይኸውም የክፉ መናፍስት ድር ነው፡፡ ሰዎች ተሳዳቢ የሚሆኑት ከክፉ መንፈስ የተነሳም ሊሆን ይችላል፡፡ ክፉ መንፈስ በሰዎች ላይ እያደረ ተሳዳቢ ያደርጋቸዋል፡፡ መሳደባቸውን እንደ ጽድቅ የሚቆጥሩና ብልግናቸውን እንደ ጀብዶ የሚያወሩ ሰዎች የመብዛታቸው ምስጢርም ከራሳቸው የሥነ-ልቦና ድክመት በተጨማሪ የክፉ መናፍስት ተሸካሚ መሆናቸውም ጭምር መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በቅዱሱ መጽሐፍ በዮሐንስ ራእይ በምዕራፍ 13 ላይ የተጻፈውን ማንበብም ለተናገርሁት ማስረጃ ነው፡፡ ‹… አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? … ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጥቶታልና…› ይላል ቃሉ፡፡ እንግዲህ በቅዱስ መጽሐፍ አምናለሁ ለቃሉም እገዛለሁ የሚል ሰው አፉ እንዳመጣለት የሚሳደብ ከሆነ ለአውሬው የነፃ ፈቃድ አግልግሎት እየሰጠ ነው ማለት ነው፡፡ አውሬው ስድብን ብቻ ሳይሆን ታላቅ ነገርንም እንደሚናገር እናስተውል፡፡ ታላቅ ነገርን የሚናገሩ ሁሉ ቢሳደቡም አይግረመን፡፡ አንዳች ክፉ መንፈስ ካልለከፈው በቀር ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር አፉን ለስድብ አይከፍትም፡፡ መሳደብ በሁሉም ዘንድ የተነቀፈና ከሰውነት ተራ የሚያስወጣ ነውረኛ ተግባር ነውና ሁላችንም ከመሳደብ እንታረም፡፡››
መምህሩም ተማሪዎችም በሌላ የመገረም ስሜት ዝም አሉ፡፡ ክፍለ ጊዜውም አበቃ፡፡ መምህሩም ለተማሪዎች የቤት ሥራ ሰጥተዋቸው ወጡ፡፡ የቤት ሥራውም እንዲህ የሚል ነው፡-
‹‹ሰዎች ምንም ይሁኑ ምን በፍጹም መሳደብ እንደሌለብን የሚያስገነዝቡ ቢያንስ 5 ምክንያቶችን ከሥነ-ልቦናም ሆነ ከሌላ አስተምህሮ አንጻር ጽፋችሁ ኑ፡፡››
Source Diretube