ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
ሰውዬው የውጭ ሀገር ዜጋ ቢሆኑም ዐሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አስተምረዋል፡፡ ሚስተር ዣክ ይባላሉ፡፡
ሻሂ እየጠጡ ኢትዮጵያዊውን ጓደኛቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ ሁለት ጊዜ ፉት እንዳሉት ጓደኛቸው ከች አለ፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የተጠለፈበት ቆብ አድርጓል፡፡ በለመዱት የኢትዮጵያውያን ባህል መሠረት ከመቀመጫቸው ተነሥተው ተቀበሉት፡፡
ወንበር ስቦ እንደ ተቀመጠ ያጠለቀውን ቆብ ጠረጲዛው ላይ አኖረው፡፡
ሚስተር ዣክ የተቀመጠውን በኢትዮጵያ ባንዴራ የተጠለፈ ቆብ አየት አደረጉና «እናንተ ኢትዮጵያውያን ለምንድን ነው በባንዴራችሁ ማጌጥ የምትወዱት?» አሉና ኢትዮጵያዊውን እንግዳቸውን ጠየቁት፡፡
«እኛ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን እንወዳለን፡፡ በሀገራችን ለመጣ ርኅራኄ የለንም፡ ይህ የሀገር ፍቅር በደማችን ውስጥ አራተኛ ሴል ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ለዚህ ነው» አላቸው፡፡
«ቆይ ግን ሀገራችንን እንወዳለን ስትሉ ምን ማለት ነው? ወንዙ እና ተራራው ነው? ሜዳው እና ጫካው ነው? ምኑ ነው ሀገር?»
ኢትዮጵያዊው ትኩር ብሎ እያያቸው «ሁለመናው ነው፡፡ ሰው፣ እንስሳው፣ ሜዳው፣ተራራው፣ ጫካው፣ ወንዙ፣ ሁሉም» አለና መለሰላቸው፡፡
«እኔ ግን አይመስለኝም» አሉት ሚስተር ዣክ፡፡
«እንዴት?» ተገርሞ ጠየቃቸው፡፡
«እናንተ ለሀገራችሁ የድመት ፍቅር ይመስለኛል ያላችሁ»
«የድመት ፍቅር ምን ዓይነት ነው» እንግዳው ተገርሞ እንደገና ጠየቀ፡፡
«ቤት ያከራዩኝ ሰውዬ ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ፡፡ ድመት ልጆቿን የምትበላው ስለምትወዳቸው ነው፡፡ ፍቅሯን የምትገልጠው ልጆቿን በመብላት እና ለዘላለም ሆዷ ውስጥ በማድረግ ነው አሉኝ»
«እና»
«እናማ እናንተም ለሀገራችሁ ያላችሁን ፍቅር የምትገልጡት ሀገራችሁን በመብላት ይመስለኛል»
«ያንን ያህል እንደርሳለን ብለው ነው» አንገቱን ወዘወዘ እንግዳው፡፡
«ኧረ እንዲያውም ሳይብስ አይቀርም፡፡ አሁን ለምሳሌ እናንተ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ገዥዎች ለመገዛታችሁ ስትኮሩበት አያለሁ፡፡ ልክ ነው ለጀግኖች አባቶቻችሁ ምስጋና ይግባቸውና ለዚህ የታሪክ ዕድል አብቅተዋችኋል፡፡
የሦስት ሺ ዘመን የነጻነት ታሪክ አለን እያላችሁ በኛ በአፍሪካውያን ላይ ትኮሩብናላችሁ እንጂ በሦስት ሺ ዘመን ምን ሊሠራበት እንደሚችል አላሳያችሁንም፡፡
ነጻነትን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል አሳያችሁን እንጂ በነጻነት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል አርአያ ልትሆኑን አልቻ ላችሁም፡፡
እርስ በርስ ስትዋጉ፣ አንዳችሁ የሠራችሁትን ሌላችሁ ስታጠፉ፣ መቶ ዓመት የለፋቸሁበትን በአንድ ቀን ደምስሳችሁ እንደገና ስትጀምሩ ነው የኖራችሁት፡፡ እስቲ ተመልከቱት የሦስት ሺ ዘመን ታሪክ አለን ነውኮ የምትሉት፡፡
ታድያ ሦስት ሺ ዘመን ተጉዛችሁ እዚህ መድረስ ብቻ ነው የቻላችሁት? አቆጣጠራችሁ ግን በምንድን ነው? አንድ ዓመትስ በእናንተ ዘንድ ስንት ቀን ነው?
«ለመሆኑ ሀገራችሁን ስለምትወዱ ነው እርስ በርስ ስትዋጉ የኖራችሁት? ሀገራችሁን ስለምትወዱ ነው የቀደመውን እያፈረሳችሁ እንደ አዲስ የምትጀምሩት? ወንዙን ሰው ሲነካባችሁ ዘራፍ ብላችሁ ትነሣላችሁ፤ እናንተ ግን ወንዙን አትጠቀሙበትም፡፡
መሬቱን ሰው ሊቆርስ ሲመጣ አራስ ነብር ሆናችሁ ትነሣላችሁ፤ እናንተ ግን መሬቱን አታለሙትም፡፡ ቅርሳችሁን ሰው ሊዘርፍ ሲመጣ የቻለ ይዘምታል ያልቻለ ያቅራራል፤ እናን ተም ግን ቅርሱን አትጠብቁትም፡፡
አሁን ይሄ ምቀኝነት ነው ወይስ ሀገር መውደድ ነው?»
ኢትዮጵያዊው እንግዳ ያልጠበቀው ነገር ስለመጣበት ትክዝ እንደማለት አለና «በርግጥ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ዋልጌዎች የሚሠሩት ሥራ ግን መላውን ሕዝብ መወከል የለበትም» አላቸው፡፡
«ልክ ነህ» አሉ ሚስተር ዣክ «ልክ ነህ ጥቂቶች ሁሉንም አይወክሉም፡፡ የማየው ነገር ግን ይህንን አባባልህን እንዳልቀበለው ያስገድደኛል፡፡
ተመልከት ቅቤው ውስጥ ሙዝ እየጨመረ የሚሸጠውኮ የራሳችሁ ሰው ነው፡፡ ለውጭ ሀገር አይደለም የሚሸጠው ለገዛ ጎረቤቱ ነው፡፡
ሂድ እስኪ በየሱቁ ስንት ጊዜው ያለፈበት የታሸገ ምግብ ይሸጣልኮ፡፡ ገዥው የሌላ ሀገር ሰው አይደለም፡፡ የራሳችሁ ወገን ነው፡፡ ያደረ ኬክ፣ ያደረ ምግብ፣ የተበላሸ ሥጋ የምትሸጡትኮ ለጠላት ሀገር አይደለም ለራሳችሁ ሰው ነው፡፡
አሁን እነዚህ ሰዎች ሀገራችንን እንወድዳለን ብለው ግሥላ ሲሆኑ ባይ ይገርመኛል፡፡ ወገናቸውን እየገደሉ ምኑን ነው የሚወድዱት እላለሁ፡፡
አሥር ብር የገዛችሁትን ዕቃ አንዳች እሴት ሳትጨምሩበት በገዛ ወገናችሁ ላይ መቶ ብር አትርፋችሁ ያለ ርኅራኄ እየሸጣችሁ ሀገራችሁን ትወድዳላችሁ ማለት ነው?» «መሬቱን ብቻ ነው እንዴ ሀገር የሚሉት?
በአንድ መንደር ውስጥ የሚገኝ መሸታ ቤት መንደርተኛውን እየበጠበጠ ስላስቸገረ የቀበሌ ጥበቃዎች መጡና ድምጽ ቀንሱ አሏቸው፡፡
እነርሱም እሺ አሉና የሚገርም ዘፈን ከፈቱ አሉ፡፡»
«ምን የሚል?»
«እኛም አንተኛ ሰውም አናስተኛ የሚል»
«ሆሆይ! ይህቺን አገር አገላብጠው ነውኮ የሚያውቋት» አለ እንግዳው ተደንቆ፡፡
«ሂድና ሠራተኛውን እየው፡፡ ሌላ ትርፍ ሀገር ያለው፣ በቅኝ ገዥዎች ተገድዶ የሚሠራ ነውኮ የሚመስለው፡፡
አንዳንዱ ዘግይቶ ይገባል፣ አንዲት ነገር ሳይሠራ ለሻሂ ይወጣል፤ እጁን ወደ ኋላ አጣምሮ እየተዝናና ቢሮ ይመለሳል፣ አንዲት ነገር ሳይሠራ ለምሳ ይወጣል፡፡
አንድ ነገር ከጠየቅከው «ነገ፣ ነገ» ነው የሚለው፡: ነገ መቼ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ግንባታዎቻችሁ ለጠላት ሀገር የሚሠሩ እንጂ እንወድዳታለን ለምትሏት ሀገር የሚሠሩ አይመስሉም፡፡
የሚጀመሩበትን እንጂ ግንባታው የሚያልቅበትን ጊዜ ማንም አያውቅም፡፡ ተሠርቶ ሳይመረቅ ይፈራርሳል፡፡ ከሚሠራበት ገንዘብ የሚበላው ይበልጣል፡፡
ሠራተኛው ምድጃ ከብቦም ተረት ያወራል፣ አካፋ ተደግፎም ሥራ ላይ ተረት ያወራል፡፡ «ለመሆኑ እነዚያ የዚህ ሁሉ ግንባታ ሠሪዎቹ፣ አሠሪዎቹ፣ ተቆጣጣሪዎቹ አሁን አንተ እንደምትለኝ ሀገራቸውን ይወዳሉ ማለት ነው?
የትኛዋን ሀገር ነው የሚወድዱት? ወይስ እኛ የማናውቃት ሌላ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለቻችሁ? ቻይናዎቹ ያሉትን ሰምተሃል?»
«ምን አሉ?»
«መንገድ ሲሠሩ፣ እነርሱ ቀን ቀን የሠሩትን እና የሰበሰቡትን የአካባቢው ሰው ሌሊት ሌሊት አፍርሶ እና አግዞ እየወሰደ አስቸገራቸው፡፡
በኋላ እንደ እኔው ሀገራችሁን ትወዳላችሁ ሲባል ሰምተው ስለነበር «ቆይ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሌላ ሀገር አላቸው እንዴ? ከሀገራቸው ሰርቀው የት ነው የሚወስዱት?» አሉ ይባላል» «አሁን አሁንኮ ትውልዱ ጉዳዩን እያስተዋለ እየተለወጠ ነው፡፡
ምናልባት ቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር ሊኖር ይችላል» አለ ኢትዮጵያዊው እንግዳ፡፡
«የለም የለም እንዲያውም ብሷል፡፡ አዲሱ ትውልድ የምትለው የሚገኘውኮ እኔ በማስተምርበት ኮሌጅ ነው፡፡ አየሁትኮ፡፡
ቤተ መጻሕፍት ገብቶ በድኻ ሀገር በጀት የታተመ መጽሐፍ የሚሰርቅ፣ የሚቀዳድድ፣ እላዩ ላይ ትርኪ ምርኪ ነገር የሚጽፍ ይህ ነው ሀገር ወዳዱ ትውልድ?
ከእርሱ ቀጥሎ እዚህ ትምህርት ቤት የሚማረው የራሱ ወንድም እና እኅት መሆኑን እንኳን የሚረሳው ነው ሀገር ወዳዱ? ከዕውቀት ክርክር ይልቅ በጎጠኛነት ተቧድኖ መደባደብ የሚቀናው ነው ሀገር ወዳዱ ትውልድ?
ነገሩ ምን ያድርግ የሚያስተምሩትም ቢሆኑኮ የሀገራቸውን ሰው የሚያስተምሩ፣ እንወዳታለን ለሚሏት ሀገር ትውልድ ሊያፈሩ የሚያስተምሩ አይመስሉም፡፡
የዛሬ ሃያ ዓመት ባዘጋጁት ማስታወሻ እያስተማሩት፣ ከቤተ መጻሕፍት አውጥተው ቢሮአቸው የደበቁትን መጽሐፍ ማጣቀሻ እየሰጡ ጥናት እያዘዙት ምን ያድርግ፡፡
በገጠሩ ሴት ልጅ በልጅነቷ ተጫውታ ሳትጨርስ ትዳርና በልጅነቷ ትወልዳለች፡፡ እርሷም ልጅ፣ የወለደችውም ልጅ ይሆንባትና አብረው እየተጫወቱ ያድጋሉ፡፡ አሁንም ኮሌጃችሁን እንደዚያው አደረጋችሁትኮ፡፡
«አሁን በየሕክምና ቦታው የሚሠራው የድሮው ትውልድ ነው ልትለኝ ነው? ለመሆኑ እርሱ ሀገር ወዳድ ነው?
ጊዜ ባለፈበት መድኃኒት ወገኑን የሚያክመው፣ በመንግሥት በጀት የተገዛ መድኃኒት አውጥቶ የሚሸጠው፣ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሌለ ምርመራ እያዘዘ ድኻው ተማርሮ ከሕክምና ይልቅ ወደ ዳማ ከሴ እንዲጓዝ ያደረገው ሀገሩን ስለሚወድድ ነው? «እስቲ የመኪና ምርመራ እንዴት እንደሚደረግ ተመልከት፡፡
መኪናው ሳይታይ በስልክ እኮ ነው የሚመረመረው፡፡ ለመሆኑ መርማሪው ሰውዬ ይሄ መኪና እርሱን፣ ቤተሰቡን፣ ዘመዶቹን እንደማይገጭ ርግጠኛ ነው?
ሀገሩን ስለሚወድ ነው ሕዝብ እንዲያልቅ ፈቅዶ የተበላሸ መኪና ጤነኛ ነው ብሎ የሚፈርመው? «በአንድ ወቅት አዲስ አበባ መንገዶቿን ሰየመች ተብሎ በየቦታው ተለጠፈ፡፡
ሦስት ወር አልሞላውም ሲወድቅ እና ሲጠፋ፡፡ ማን ዘረፈው? ሀገር ወዳዱ፡፡ ተካዮቹስ ቢሆኑ ለምን ዘወር ብለው አላዩትም? ሀገር ወዳድ ስለሆኑ፡፡
«እኔ ሀገር የመውደድን ጉዳይ አሁን እርስዎ ባሰቡበት መንገድ አስቤው አላውቅም፡፡ ብቻ እኛ የሀገራችን ጉ
ዳይ ሲነሣ ደመ ቁጡዎች፣ አትንኩን ባዮች እና ኮስታሮች መሆናችንን አውቃለሁ፡፡» አለ ኢትዮጵያዊው እንግዳ፡፡
«ልክ ነህ ይህንንማ ዓለም በሙሉ ይመሰክርላችኋልኮ፡፡ ይህች ሀገርኮ ዝም ብላ እንዲሁ በነጻነት አልኖረችም፡፡ አንዳች ልዩ ነገርማ አላችሁኮ፡፡ ሀገራቸውን ባይወድዱ ኖሮ አባቶቻችሁ ደማቸውን ባልገበሩ ነበር፡፡
አጥንታቸውን ከስክሰው ድንበር ባላጠሩ ነበር፡፡ ዘመናዊ መሣርያ የታጠቁትን በባህላዊ መሣርያ ባላሸነፉ ነበር፡፡
ግን ሀገር መውደድ ይሄ ብቻ ነወይ) ሌላ አይንካን እኛ ግን እንደፈለግን እንጫረስ፣ ሌላ አይዝረፈን እኛ ግን እንዘራረፍ፣ ሌላ አይጨቁነን እኛ ግን እንጨቋቆን፣ ቅኝ ገዥ መጥቶ ቀንበር የሆነ ሕግ አያውጣብን እኛ ግን እርስ በርሳችን ቀንበር እንጫጫን፣ ጠላት ወርሮ መብታችንን አይንካ፣
እኛ ግን መብታችንን እርስ በርስ እንገፋፈፍ ነው የምትሉት) ይሄኮ ነው ያልገባኝ ነገር፡፡ ሀገር ማለትኮ መልክዐ ምድሩ ብቻ አይደለም፤ ይሄ ባለጉዳይ ሆኖ ቢሮህ የመጣው፣ታምሞ ሊታከም አንተጋ የመጣው፣ሊማር አንተ ጋ የመጣው፣ሊገዛ ሱቅህ ጋ የቆመው፣ በሞያህ እያገለገልከው ያለኸው፣በመኪናህ ላይ የተሳፈረው፣ እርሱኮ ነው ሀገር» አሉ ሚስተር ዣክ፡፡
«እንዴ ሚስተር ዣክ በዐሥረኛው ዓመት ሀገራችን መረረዎት መሰለኝ፡፡ እርስዎም እንደኛው ደመ ቁጡ ሊሆኑ ነው ማለት ነው፤ባለፈው ታምመው ተኝተው እያለ የኢትዮጵያዊ ደም ነበር እንዴ የተደረገልዎ» አለ ኢትዮጵያዊው ነገሩን ወደ ቀልድ ወስዶ ሀሳብ ለማስቀየር፡፡
«አየህ ይህች ሀገር ይበልጥ ስታውቃት ይበልጥ የምታሳዝን፣ ይበልጥ የምታስቆጭ፣ ይበልጥ የምታንገበግብ ናት፡፡
ቆይ ግን ህንን ሁሉ የምታደርጉት ሀገራችሁን ስለምትወዱ ከሆነ ሀገራችሁን ባትወድዱ ኖሮስ ከዚህ የከፋ ምንታደርጉ ነበር? አንድ እዚህ ሀገር የሰማሁት ቀልድ ነገር አለ፡፡
አንድ ባል ሚስቱን ይደበድባታል፡፡ እርሷም ቤቷን ትታ ትወጣለች፡፡
በኋላ ሽማግሌ ገብቶ ታረቁ ይላቸዋል፡፡ ባልም እኔኮ ስለምወዳት ነው የመታኋት፣ የፍቅር ነው ይላል፡፡ ሚስቲቱም ስትወደኝ ከሆነ እንዲህ የምትመታኝ ስትጠላኝ ምን ልታደርግ ነው? አለችው አሉ፡፡
አሁንም እናንተ በሀገራችሁ ላይ ራሳችሁ ይህንን ሁሉ ግፍ የምትፈጽሙት ሀገር ወዳድ ስለሆናችሁ ከሆነ ብትጠሏት ኖሮ ምን ልታደርጉ ነበር?