Wednesday, 19 December 2018

አሜሪካዊው ቢሊየነር ስቲቭ ጆብስ፣ በህይወቱ መጨረሻ ሰዓት ላይ ያስተላለፈው መልዕክት።


[ስቲቭ ጆብስ በ56 አመቱ ያረፈ አሜሪካዊ ቢሊየነር ሲሆን፣ ህይወቱ ያለፈው በካንሰር በሽታ ነው።]

"በንግዱ አለም ውስጥ የመጨረሻ ከፍታ ጫፍ የሚባለው ቦታ ደርሻለሁ፣ ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ሀብት ደስታን ማግኘት አልቻልኩም። በልፋቴ ካከማቸሁት ሃብት ያገኘሁት ደስታ እዚህ ግባ የማይባል ነው። አሁን፣ በህይወቴ የመጨረሻው ሰዓት አካባቢ፣ አልጋ ላይ ሆኜ ያሳለፍኩትን ነገር ሁሉ ወደኋላ ሳስበው፣ እኮራበት የነበረው ሀብቴና ዝናዬ ከንቱ እና ትርጉም አልባ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ አንድን ሰው መኪና እንዲነዳልህ ወይም ሰርቶ ገንዘብ እንዲያስገባልህ ልትቀጥረው ትችላለህ፣ እየተሰቃየህበት ያለውን ህመም እንዲሸከምልህ ግን ልትቀጥረው አትችልም፡፡


ምድራዊ የሆኑ ቁሳቁሶች ሁሉ ሊጠፉ፣ ዳግም ሊገኙም ይችላሉ፥ አንድ ጊዜ ካመለጠ ደግመህ ልታገኘው የማትችለው አንድ ነገር ግን አለ… እርሱም ህይወትህ ነው! አንድ ሰው የቀዶ ጥገና ወደሚደረግለት ክፍል ሲገባ አንብቦ ያልጨረሰው አንድ መጽሃፍ ትዝ ቢለው የመጽሐፉ ርዕስ "ጤናማ ህይወት የመኖር ሚስጥር" የሚል ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ በየትኛውም የህይወት ከፍታ ላይ ብንሆን የህይወታችን መጋረጃ የሚዘጋበትን ቅጽበት ፊት ለፊት የምንጋፈጥበት አንድ ቀን መምጣቱ አይቀርም፡፡


ለቤተሰብህ፣ ለትዳር አጋርህ እና ለጓደኞችህ የፍቅርን ውርስ አስቀምጥላቸው፡፡ ራስህን ተንከባከብ፣ ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት ይኑርህ። እያደግን ስንሄድና የህይወት ትርጉሙ ሲገባን፣ ውድ ሰዓትም አሰርን ርካሽ ሰዓት፣ ሁለቱም የሚነግሩን ጊዜ እኩል መሆኑ ይገባናል፡፡ በኪሳችን ውድ ቦርሳም ያዝን ርካሽ ቦርሳ፣ በውስጡ የሚኖረውን የገንዘብ መጠን አይቀይረውም፡፡

የአንድ ሚሊየን ብር መኪናም ነዳን የሶስት መቶ ሺህ ብር መኪና፣ የመንገዱ ርዝመት አይቀየርም፣ አቅጣጫውም ያው አንድ ነው፥ የምንደርሰውም ያው እዚያው ቦታ ነው፡፡ ውድ መጠጥም ጠጣን ርካሽ መጠጥ፣ ስካሩና አድሮ የሚያመጣው ራስ ምታት ለውጥ የለውም፡፡ ሰፊ ግቢ ውስጥ ኖርንም ጠባብ ቤት፣ ብቸኝነቱ ያው እኩል ነው፡፡ የውስጥ ደስታ በቁሳቁስ እንደማይገኝ ያን ጊዜ ይገባሃል። አውሮፕላን ላይ የክብር ቦታም ተቀመጥክ ወይም ተራ ቦታ፣ አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ እኩል ቁልቁል ትወርዳለህ።


እውነተኛው ደስታ የሚገኘው ከቤተሰብህ፣ ከጓደኞችህ፣ ከዘመዶችህ ጋር በሚኖርህ ውብ ጊዜዓት ብቻ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር በምታሳልፈው ጊዜ፣ በምትጫወተው ጨዋታ፣ በምትዘምረው መዝሙር፣ በምትስቀው ሳቅ እውነተኛ ደስታን ታገኛለህ፡፡ ሊካዱ የማይችሉ የህይወት እውነታዎች ግን አሉ ልጆችህ ሀብታም እንዲሆኑ አታስተምራቸው፥ ይልቅ እንዴት ደስተኛ መሆን እንደሚችሉ አስተምራቸው፡፡ ሲያድጉ የነገሮች ዋጋ ሳይሆን ጥቅማቸው ይገባቸዋል፡፡ ምግብህን እንደ መድሃኒት ውሰድ ካልሆነ መድሃኒት እንደምግብ ትወስዳልህ፡፡ የሚወድህ ሰው በቀላሉ አይለይህም፣ ከአንተ ለመለየት 99 ምክንያት ቢኖረው እንኳ መለየት በማይችልባት አንዲት ነገር ላይ ፀንቶ ይቆማል፡፡
"ሰው ሆኖ በመፈጠር"ና "ሰው በመሆን" መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፥ ይህ የሚገባቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ስትወለድ ውድ ነበርክ፣ ስትሞትም ውድ ትሆናለህ፣ በመካከል ያለውን ማስተካከል ያንተ ፋንታ ነው፡፡ በፍጥነት ለመሄድ ከፈለክ ብቻህን ሂድ፣ ሩቅ ለመድረስ ከፈለግህ ግን ከሌሎች ጋር አብረህ ተጓዝ፡፡

በዓለም ላይ ያሉ ስድስቱ ፈዋሽ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው…
★የፀሃይ ብርሃን
★እረፍት
★ስፖርት
★ጥሩ ምግብ
★በራስ መተማመን እና
★ጓደኛ
እነዚህን አጥብቀህ ያዝ፥ ደስተኛ ህይወትን አጣጥም!