"የቆሠለውን የአገሪቱን ነፍስ እያከማችሁ የተፈረካከሰውን የኢትዮጵያዊነት ክብርና ማንነት ፈልጋችሁ ከወደቀበት አንሡት። የዚህን ምስኪን ሕዝብ ፍርሃቱንና ድንጋጤውን አርግቡለት ። ጥላቻና አለመተማመን፣ ጭካኔና ስግብግብነት፣ የበሽታ ምልክቶች ናቸው እንጂ የጤነኛ ሰው የሠለጠነ ኅብረተሰብ ባሕርያት አይደሉም።
አለመደማመጥ፣ ልዩነትን መፍራት፣ በኩራት ተወጥሮ በበታችነት ስሜት መሠቃየት፣ ሌላውን ጥሎ ትልቅ ለመሆን መሞከር ሁሉ የተሸነፈ ማንነት፣ የዘቀጠና የተቀጠቀጠ ስብዕና መገለጫዎች ናቸው።" "ትልቅነትን ከውስጣችን፣ ታላቅነትንም በመካከላችን ፈልገን ልናገኝ ያስፈልጋል።
አፍሪቃን ሊመራና የጥቁር ሕዝብ አዕርያ ሊሆን የሚችል ሕዝብ በጦር መሣሪያ ጥንካሬ ወይም ባለፈ ታሪክ ላይ የሙጢኝ በማለት አይፈጠርም። በኅብረተሰብ የጅምላ ጫጫታ ውስጥ የጠፋውን ግለሰባዊ የስብዕና ማንነትና ድምፅ ፈልጋችሁ አግኙት። ስታገኙት ደግሞ በራስ ወዳድነትና ስግብግብነት፣ በተጠላለፈ ግለ ፍቅር ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር በመናናቅና በመናቆር እንዳይጠፋ፣ የአንድነቱን ገመድ የኅብረ-ማንነት መለያ ሀገራዊ ነፍሱን አስጨብጡት። ሥልጣኔ የሚፈጠረው በግለሰብ ነፃነትና በማኅበረሰባዊ ኃላፊነት መካከል ባለው ሚዛን ላይ ነው። ግለሰብን እየገደሉ ሀገር ሀገር ማለት ቀልድ ነው። ሀገራዊ ኃላፊነትና ማንነትን እንደ ኳስ እየለጉ ነፃነትና መብት እያሉ ማላዘንም ትርጉም የለውም።"
"የኢትዮጵያንና የልጆቿን ፈውስና ዕድገት፣ ብልፅግናዋንና ከፍታዋን በሰው ሕይወት ክቡርነትና ዕኩልነት ላይ መስርቱት። ሰው መሆን በራሱ እጅግ የከበረ ምስጢርና ድንቅ የጥበብ መደምደሚያ ነው። ሰውነት ከፆታና ከዕድሜ በላይ ነው፣ ከብሔርና ቋንቋ ይርቃል፣ ከቁሳዊ ሀብትና ሐይማኖታዊ ቀኖናም ይገዝፋል። የሁላችንም ስራ ይህንን በየልቦናውና በየቤቱ እንደገና መፍጠር ነው።"
……"ሌላ ሰው" በዶ/ር ምህረት ደበበ ገጸ-16…