Wednesday, 6 November 2019

የኢትዮጵያ ልጅ መሆን ደግሞ የምር ከባድ ነው


በዕውቀቱ ስዩም

መኖር ቀላል አይደለም! የኢትዮጵያ ልጅ መሆን ደግሞ የምር ከባድ ነው፤ የምር! አገር ቤት የሚኖርው አብዛኛ ው ሰው ስራ የለውም! ቁርስ ካገኘ ምሳን ሸውዶት ያልፋል ፤ቤት የለውም፤ ከሁሉ በላይ ሰላም የለውም፤አገሩ ካሁን አሁን በላየ ላይ ፈረሰ እያለ በስጋት ይኖራል

አገሩ ውስጥ ያለው ሃብት ጥቂት ነው፤ ጥቂቱንም ሃያላን ይቀራመቱታል፤ ባገር ውስጥ ያለውን ሀብት በዶሮ ወጥ ብንመስለው ፤ መንግስት “ፈረሰኛውን “ ይበላል፤ ዋናው ሽፍታ መንግስትን አስቦክቶ “ ቅልጥም “ ይደርሰዋል ፤ ለህዝቡ “ ክንፍ “ ይወረውሩለታል ፤ የግዜሩ ወኪል ነኝ እሚለው ሰውየ ደግሞ ፤ ህዝቡ የደረሰውን ክንፍ “ ባርኬ ልመልስልህ” በሚል ሰበብ ወስዶ ይበላበታል! ህዝብ ሲያጉረመርም “ አይዞህ! የሚራቡ ብጡአን ናቸው ይጠግባሉና! በማያልፈው አለም ቅልጥምና ፈረሰኛ እየዘነበልህ ትኖራለህ “ ብሎ ያፅናናዋል! 

የህዝቡ የኑሮ ድርሻ ዶሮ ማርባት ነው ፤ ከዚያ የተረፈውን እድሜውን “ቅልጥሙ” እሚገባው ለሽፍታው ነው ወይስ ለመንግስት የሚል አጀንዳ ፈጥሮ እየተከራከረ፤ አልፎ አልፎ እየተደባደበ ኖሮ ይሞታል! 

ውጭ እሚኖረው ያገር ሰው ስራ አለው፤ ንብረቱ በባንክ፤ ደህንነቱ በፖሊስ ይጠበቅለታል ! ህይወቱ ስራ ነው! እረፍት የለውም፤ በስልኩ ደወል ተቀስቅሶ ለስራ ይሰማራል ! አውቶብስ ውስጥ እየተኛ ፌርማታ አልፎ ይወርዳል፡፡
እየፈጋ ለወንድሙ ይልካል፤ወንድምየው በተላከለት ገንዘብ ይጠብስበታል፤ዲቃላ ይወልድበታል፤ ከዛ ዲይስፖራው፤ ለወንድሙየው ቢራ፤ ለልጅየው ደግሞ ወተት በመግዛት ይጠመዳል ! አላማው ከለታት አንድ ቀን አገር ቤት ገብቶ፤ የሆነ ቢዝነስ ከፍቶ፤ የጦቢያን ፀሃይ እየሞቀ ፅድት ብሎ ለመኖር ነው! ከዚያ አንድ ቀን ገላውን ሲታጠብ ሳሙና አድጦት ባፍጢሙ ተድፍቶ ይገላገላል ! ፅድት ብሎ መኖር ባይሳካለትም ፅድት ብሎ ይሞታል፤ 

አንዳንድ ሰዎች ከድህነት ስለመውጣት እንደቀላል ሲሰብኩ ያስገርመኛል! በድሃነት መውጣት በጣም ከባድ ነው፤ የድሃነት ቅርንጫፉና ስሩ ረጅምና ጥልፍልፍ ነው፤ “ሞ ሰፈር” እሚባል የሴተኛ አዳሪዎች ሰፈር ነበር ፤ በዛ የምትኖር እንዲት ሴትዮ ያካባቢውን ወንዶች ስታስደስት ኖረችና ሞተች ፤ከመሞቱዋ በፊት እድሜ ልኩዋን የለፋችበትን አምስት ሺህ ብር ለብቸኛ ልጁዋ አወረሰችው ፤ ከሰልስቱ በሁዋላ፤ ጎረምሳ ልጅ ከናቱ የወረሰውን ገንዘብ ይዞ እዛው ሴተኛ አዳሪዎች ጋር መጨፈር ጀመረ፤ ይሄንን ያስተዋሉት የሰፈር ሽማግሌ ልጁን ጠርተው “ አንተ ልጅ ይሄ ገንዘብ በእ*ስ መጥቶ በእ*ስ እንዳይሄድ ባግባቡ ያዘው” ብለው መከሩት ይባላል፤ “ ምን እናርግ ተቸገርን “ አለ መንግስቱ ሃይለማርያም! ድህነት ወደ መነሻው እየጎተተን ተቸገርን! 

በዛ ላይ የጉልቤዎች እብሪት፤ ለህዝብ ስቃይ ያላቸው ደንታቢስነት ይዘገንናል ፡፤ተስፋ ለማስቆረጥ አይደለም፤ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ከመተጋገዝ ከመተዛዘን ሌላ ተስፋ የለንም ፤ አንዱ ሌላው ህይወት፤ ቅመም እንጂ ህመም ለመጨመር ባይሞክር ትልቅ ነገር ነው!