Saturday, 11 April 2020

መሪነት የሚገለጠው በአገልጋይነት ነው


መሪነት የሚገለጠው በአገልጋይነት ነው። ከአጠገብህ ቆሜ ለማገልገል ያገኘሁት እድል ክብሬ ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣
የሰጠኸንን አንድ ሺህ ኪሎግራም የምግብ ዱቄት ለኮሮና ፈተና መቋቋሚያ በመላው ከተማችን ባሰናዳናቸው የምግብ ባንኮች አስቀምጠን ለደሃው እንደርስበታለን። ድጋፍህ ፈተናውን ለማለፍ በእጅጉ ይረዳናል። እናመሰግናለን።








Wednesday, 8 April 2020

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐውጇል፡፡

ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን

እየተመለከታችሁትና እየታዘባችሁት እንደሆነው ዓለም በአስቸጋሪ የፈተና ምእራፍ እያለፈች ነው፡፡ ዓለም ይሄንን መሰል ነገር ሲገጥማት ከመቶ ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ነገር ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሮና (ኮቪድ -19) የዓለም ሁለንተናዊ ችግር ሆኖ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ደረጃ በደረጃ የመፍትሔ ርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ፣ የሕክምና ተቋማት እንዲዘጋጁ፣ የመከላከያና የሕክምና መሣሪያዎች ከውጭ እንዲገቡ፣ የማቆያ ሥፍራዎች እንዲዘጋጁ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፤ አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች በቤት እንዲወሰኑ፣ ብዙ ሕዝብ ሊሰበሰብባቸው የሚችሉ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎታቸውን ሕዝብ ሊሰበሰብ በማይችልበት መንገድ እንዲከውኑ፣ በአብዛኛው ሥፍራዎች የሕዝብ ትራንስፖርት እንዲቋረጥ፣ ለአስቸጋሪ ጊዜ የሚሆን ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡

መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ የሚከተለው ስትራቴጂ በመከላከል ላይ ያተኮረ ነው፡፡
1. ኅብረተሰቡን አስተባብሮ በባለሞያዎች ምክር መሠረት ለመከላከል መቻል
2. ከመከላከል ያለፈ ነገር ሲመጣ ለማከም የሚያስችሉ ዐቅሞችን ማዳበር፡፡
3. የከፋው ነገር ከመጣም አስቀድሞ በመዘጋጀት እንደየ አስፈላጊነቱ ተገቢ ውሳኔዎችን እያሳለፉ መሄድ፡፡ 

እስካሁንም በዚህ መንገድ ነው የተጓዝነው፡፡
አሁን ያሉን መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቫይረሱ የተያዙ ወገኖች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው፡፡ ይሄም በመሆኑ ሁላችንም ያለንን ዐቅም ሁሉ አስተባብረን ወገኖቻችንን ከዚህ ወረርሽኝ ለመከላከልና የታመሙትንም ለማዳን ማዋል አለብን፡፡ ያለንበት ጊዜ ሕዝብና ሀገርን ለማዳን ሲባል አስቸጋሪ የተባሉ ውሳኔዎችን መወሰን ያለብን ጊዜ ነው፡፡ ይህም ውሳኔ፣ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንደ ተቋምና እንደ መንግሥት የሚወሰኑ ናቸው፡፡ 

ይህ ውሳኔ በዛሬው ትውልድ ላይ ብቻ የምንወስነው ውሳኔ አይደለም፡፡ በልጅ ልጆቻችን ላይ ጭምር የምንወስነው ነው፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ላይ የምንወስነው ብቻ አይደለም፤ በነገዋና በከነገ ወዲያዋ ኢትዮጵያ ላይ ጭምር የምንወስነው ውሳኔ ነው፡፡ የኛ የመሪዎቹ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ውሳኔ በታሪክ የሚመዘገብ ነው፡፡ 

ይሄንን አስቸጋሪ ጊዜ ልናልፈው የምንችለው በአካል ተራርቀን በመንፈስ ግን አንድ ሆነን ከቆምን ብቻ ነው፡፡ የያንዳንዳችን ሀብት የሁላችን፣ የእያንዳንዳችንም ችግር የሁላችን መሆን አለበት፡፡ አንዱ በልቶ ሌላው ተርቦ፣ አንዱ ሠርቶ ሌላው ሥራ አጥቶ፣ አንዱ መኖሪያ አግኝቶ ሌላው ውጭ አድሮ፣ አንዱ አትርፎ ሌላው ከሥሮ ይሄንን ችግር ለማለፍ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ይህ ችግር የመጣው በህልውናችን ላይ በመሆኑ፡፡ ይህ ችግር የተጋረጠው ሰው ሆኖ በመኖርና ባለመኖር ላይ በመሆኑ፡፡

መንግሥት ችግሩን በደረሰበት ልክ ለመቋቋም ተዘጋጅቷል፡፡ የምንወስዳቸው ውሳኔዎች ክብደት እንደ ችግሩ ክብደት የሚወሰን ነው፡፡ ታሪክ እዚህ አድርሶናል፡፡ ሀገርና ትውልድ በእጃችን ላይ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በምንሠራው ሥራ ወይ እንመሰገናለን ወይ እንወቀሳለን፡፡ ከምንም በላይ ግን በጊዜውና በዐቅማችን ማድረግ ያለብንን ካላደረግን የበለጠ እንወቀሳለን፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት ነው፡፡ ከተረፍን አብረን ነው፡፡ ከከሠርንም አብረን ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ እየተባባሰ በመምጣጡ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐውጇል፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱ ዐንቀጽ 93 መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ ይሄንን መሳይ ዐዋጅ ብዙ ሀገሮች ካወጁ ሰንብተዋል፡፡ እኛ እስክንዘጋጅና ሁኔታው የግድ እስኪለን ጠብቀናል፡፡ ጊዜው ሲጠይቅ ግን ዐውጀናል፡፡ ሀገርን ለማዳንና ትውልድን ለመታደግ ከዚህ በላይ ልንወስን እንደምችልም መታወቅ አለበት፡፡ ዜጎቻችንም ከዚህ በላይ ግዴታቸውን ለመወጣት ወገባቸውን አጥብቀው መጠበቅ አለባቸው፡፡ 

በዚህ ወቅት ሁላችሁም ችግሩን ለመቋቋም ከሚሠሩት አካላት ጋር አብራችሁ እንድትቆሙ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ችግሩን ለማባባስ የሚሠሩ ካሉ ግን፣ በሕጉ መሠረት የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን፡፡ 

ወገኖቼ፤

ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን መረዳዳቱና መደጋጋፉ ነው፡፡ ድኾችን እንርዳ፡፡ በአካባቢያችን ላሉት ዐቅመ ደካሞች እንድረስላቸው፡፡ የቤት ተከራዮቻችንን ዕዳ እንካፈላቸው፡፡ ከቻልን አናስከፍላቸው፤ ካልቻልን ቅናሽ እናድርግላቸው፡፡ ያም ካልሆነ ይህ ጊዜ እስኪያልፍ እንታገሣቸው፡፡ በዚህ ወቅት ተከራዮችን ከቤት ማስወጣት ፈጣሪም፣ ታሪክም ሕግም ይቅር የማይሉት ወንጀል ነው፡፡ ማናችን አልፈን ማናችን እንደምንተርፍ ለማናውቅበት ጊዜ ከመተባበር የተሻለ መሻገሪያ የለንም፡፡ የግል ባለሀብቶች የሠራተኞቻቸው ሕይወት እንዲያስጨንቃቸው አደራ እላለሁ፡፡ መንግሥት የኢኮኖሚ ችግሮቻችንን ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እየወሰነ አብሯችሁ እንደሚሆን በዚህ አጋጣሚ እገልጥላችኋለሁ፡፡ 

ለሌሎች ወገኖቻቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ቤታቸውን፣ ሆቴላቸውን፣ አዳራሾቻቸውን፣ የእምነት ተቋሞቻቸውን፣ መኪኖቻቸውን፣ ገንዘባቸውንና እህላቸውን የሰጡ ዜጎቻችንን ስናይ ይሄንን አስቸጋሪ ወቅት ከፈጣሪ ጋር ሆነን ልናልፈው እንደምንችል ርግጠኞች እንሆናለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከወገኖቻቸው መከራ ለማትረፍ የሚሽቀዳደሙ፣ ከመከራ እንኳን የማይማሩ ሰዎችን ስናይ መንገዱ ከባድ እንዳይሆንብን እንሠጋለን፡፡ በጎ አድራጊዎችን የምናመሰግነውን ያህል መንገዳችን

የሕክምና ባለሞያዎቻችንን በሚቻለው ሁሉ እንርዳ፡፡ ያለ እነርሱ ግንባር ቀደምነት ትግሉን ልናሸንፍ አንችልም፡፡ የሕክምና ባለሞያዎችን ማክበር፣ ማመስገንና በጉዟቸው ሁሉ መተባበር ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ ለሕክምና ባለሞያዎች ተገቢውን ሁሉ አለማድረግ እጅን በእጅ እንደመቁረጥ ነው፡፡ ከእነርሱ በተጨማሪ የመከላከያ አባላት፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሚዲያ ባለሞያዎች፣ የመገናኛ መሥመሮቻችን ላይ 24 ሰዓት የሚያገለግሉ ዜጎች፣ እኛ ቤት እንድንውል እነርሱ ውጭ የሚውሉ ሠራተኞች ተገቢው ምስጋናና ድጋፍ ከቤተሰባቸውም፣ ከማኅበረሰባቸውም ያስፈልጋቸዋል፡፡

በዚሁ አጋጣሚ አርሶ አደሮቻችን የበልግ ወቅት እንዳያልፍብን ራሳቸውን ከቫይረሱ እየተጠነቀቁ በምርት ሥራ ላይ ጠንክረው እንዲሳተፉ አደራ እላቸዋለሁ፡፡ ከቫይረሱ ባልተናነሰ የእርሻ ምርት መቀነስና የእርሻ ምርት አለመኖር ሀገራችንንና ሕዝቧን ይጎዳል፡፡ እናንተ ሀገር መጋቢዎች ስለሆናችሁ፣ እየተጠነቀቃችሁ ካለፈው የተሻለ ምርት ለማምረት ትጉ፡፡ መንግሥትም አስፈላጊውን ሁሉ ሞያዊና ድጋፍ ያደርግላችኋል፡፡

የኢንዱስትሪ ምርቶቻችንም ፈጽመው መቆም የለባቸውም፡፡ ለሠራተኞቻችን ሕይወት እየተጠነቀቅን፣ በወረርሽኙ ምክንያት የሚያጋጥመንን ተግዳሮት ሁሉ እየተቋቋምን በፋብሪካ ምርቶች ላይ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ፡፡ በተለይም ከውጭ የምናመጣቸውን ምርቶች ለመተካት ለሚደረገው ጥረት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግላችሁ እገልጥላችኋለሁ፡፡ በተለይ ግን በምርት ዝውውር ጊዜ ከፍተኛ የሆነውን የመጨረሻ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለአፍታም ቢሆን እንዳትዘነጉት ይሁን፡፡ 

ይህ ጊዜ ያልፋል፡፡ ሀገራችን ከዚህ የሚስተካከሉና ከዚህም የሚብሱ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡ ዓለማችን በየዘመናቱ የከፉ ተግዳሮቶችን አልፋ ነው እዚህ ዘመን የደረሰችው፡፡ የሚሰጡንን መመሪያዎች በሚገባ እናክብር፣ የጤና ባለሞያዎች የሚሉንን ለሕይወታችን ስንል እንስማ፡፡ በኮሮና አይቀለድም፡፡ ጉዳዩ ከመኖርና ካለመኖር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ 

ይሄንን ፈተና ለማለፍ ባለ ሦስት መዓዘን ትብብር ያስፈልገናል፡፡ ወደ ጎን እኛ እርስ በርሳችን፡፡ እያንዳንዳችን ደግሞ ከፈጣሪያችን ጋር፡፡ እኔ ከሌላው ወገኔ ጋር፣ ሌላው ወገኔ ከእኔ ጋር፣ እኔና ሌላው ወገኔ ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት መሥመር መቼም መቋረጥ የለበትም፡፡ 

በርትተንና ተረባርበን የሚጠበቅብንን እናድርግ፣ ጸንተንና በተሰበረ ልብ ሆነን ወደ ፈጣሪ እንለምን፡፡ ፈጣሪ ከእኛ ጋር ነው፡፡ መከራውን ያቀልልናል፤ ፈተናውን ያሳልፈናል፤ ማዕበሉን ያሻግረናል ብለን እናምናለን፡፡ የሃይማኖት አባቶች ያዘዙንን ጥንቃቄ እየፈጸምን ያዘዙንንም ጸሎት ተግተን እንጸልይ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
መጋቢት 30/ 2012 ዓ.ም