ይህንን የተናገሩት ከሰባት እስከ 32 ዓመት ድረስ ሕይወታቸውን በግብረ ሰዶማዊነት ያሳለፉት ግብረ ሰዶማውያንና ግብረ ሰዶማውያት (ወንዶችና ሴቶች)፣ ‹‹ዝምታው ይሰበር ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ዶክሜንተሪ ፊልም (ቪሲዲ) ውስጥ ባካሄዱት ቃለ መጠይቅ ላይ ነው፡፡
በቸርችል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ የ666 አሠራር›› የሚል ታካይ ርእስ ባለውና ለምረቃ በበቃው በዚሁ ፊልም ውስጥ ይህንኑ ቃለ መጠይቅ ካካሄዱት ከእነዚህ ግብረ ሰዶማውያን ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው ሕጋዊና መደበኛ ሚስት አግብተው፣ ትዳር መስርተውና ልጆች ወልደው በሽምግልና ዕድሜያቸው ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ አዛውንቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‹‹አባባ መሽቷል እባክዎን ወደ ቤትዎ ሂዱ›› እያሉ ወጣት ግብረ ሰዶማውያን ይቀልዱባቸዋል፡፡ ይሳለቁባቸዋል፡፡ እነዚህም አዛውንቶች ታዋቂነታቸው በ‹‹ዜጎች›› ዘንድ ብቻ ስለሆነና በአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚታወቁት ባለትዳርና የልጆች አባት ስለሆኑ ከማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳይገለሉና ተከብረው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡