Wednesday, 4 April 2018

የዐቢይ ንግግር ሰባት አዕማድ



የሀገሬ ሰው ‹ካልተናገረ አይታይ ብልሃቱ፣ ካልታረደ ዓይታይ ስባቱ› ይላል፡፡ ንግግር የሰው ልጅ ከተሰጡት የላቁ ጸጋዎች አንዱ ነው፡፡ ንግግር ሰዎችን ሊያግባባቸው፣ ወደ አንድነትና ኅብረት ሊያመጣቸው፣ ሊያከራክራቸውና ሊያወያያቸው ኃይል አለው፡፡ ከመሪዎች ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ ኃይል ያለው ንግግር ነው፡፡ ኃይል ያለው ንግግር በሚመርጣቸው ቃላት፣ በሚጠቀምበት ድምፀት፣ በሚያቀርባቸው አገላለጦች፣ በሚሰጣቸው ምሳሌዎች፣ በሚቀርብበት ተፋሰስ፣ በሚዋቀርበት አሰካክና በምጣኔው ይታወቃል፡፡ ሊደመጥ፣ ሊነበብ የሚችል፣ በሐሳቡ ባንስማማም በአቀራረቡ የሚማርከን፣ በዝርዝሩ ባንግባባም ሐሳቡ ግን የሚገባን፤ ባንወደውም የምናደንቀው ንግግር ከመሪዎች ይጠበቃል፡፡ ዐፄ ምኒልክ ለዐድዋ ጦርነት ሕዝቡን ለመጥራት ያወጁት ዐዋጅ ከዐዋጅነቱ ይልቅ የመሪ ጥሪ የሆነ ቃል አለው፡፡ በውስጡ ንጉሡንና ሕዝቡን የሚያቀራርብ፣ የሀገሪቱን ችግር የሚገልጥ፣ ከሕዝቡ የሚፈልጉትን የሚያሳይ፣ ሀገር ስትጠራው እምቢ ብሎ የቀረ የሚገጥመውን ዕጣ ፈንታ የሚያመላክት ቃል ነው፡፡ መላዋን ኢትዮጵያ ለአንድ ዓላማ ያሰለፈና ውጤቱን በዐድዋ ተራሮች ላይ ያሳየ ቃል ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ሀገር ምጥ ላይ በምትሆንበት ጊዜ የመሪዎች ንግግር ወይ ፈዋሽ ወይ አባባሽ ይሆናል፡፡ ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል እንዲሉ፡፡ አነጋገሩ የሚያግባባ፣ የሚጠራና የሚያቀራርብ ከሆነ ሕዝብን ለመፍትሔ የማሰለፍ ኃይል ይኖረዋል፡፡ ንግግሩ ብቻ ሳይሆን ንግግሩ የተዋቀረበት መዓዝን የመሪውን ጉዞ ካርታውን እንድናይ ያደርገናል፡፡

የዶክተር ዐቢይ አሕመድ ንግግር በንግግሩ ይዘት፣ ንግግሩ በተቀናበረባቸው ቃላት፣ ቃላቱ በተሰናሠሉበት አወቃቀር፣ ሐሳቡ በተገለጠባቸው ምሳሌዎች፣ ማሳያዎች፣ ጥቅሶች፤ ትኩረትና አጽንዖት በተሰጣቸው የሐሳብ ዘውጎች፣ ብርታቱና ድክመቱ ሊተነተንና የመሪዎች ንግግር ምን መሆን እንዳለበት መማማሪያ ሊሆን ይገባዋል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ንግግሩ የተዋቀረባቸውን ሰባት አዕማድ ለዛሬ ላንሳ፡፡
የዶክተር ዐቢይ የበዓለ ሲመት ንግግር በሰባት አዕማድ የተዋቀረ ነው፡፡ እነርሱም ክብር፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ አንድነት፣ ይቅርታ፣ ሰውነትና ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያዊነት ናቸው፡፡

1.  ክብር፡- ዶክተር ዐቢይ ንግግራቸውን የጀመሩት ከእርሳቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትንና በፈቃዳቸው ሥልጣን ‹ያሸጋገሩትን› አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በማመስገን ነው፡፡ በዚህ ንግግራቸው ግን ክብርና ምስጋና የሰጡት ለእርሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ሰባት አካላትም ክብርና ምስጋና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ሀ. ሽግግሩን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ሚና ለተጫወቱ፣
ለ. ኢትዮጵያን ለሚያኮራት ታሪካችን፣
ሐ. ለኢትዮጵያውያን የማይበጠስ አንድነት፣
መ. ለኢትዮጵያ ታላቅነት በየዘመናቱ መሥዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን፣
ሠ. በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣
ረ. ለተፎካካሪ ፓርቲዎች፣
ሰ. አሁን ለመጣው ለውጥ ዋጋ ለከፈሉ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ክብር በንግግራቸው ውስጥ  ሰጥተዋቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከታሪክ መዝገብ የተፋቀ ይመስል ከመንግሥታዊ ዲስኩሮች ስሙ ጠፍቶ ለኖረው የካራማራ ድል ተገቢውን ክብር ሰጥተውታል፡፡

ኢትዮጵያውያንን የገለጡበት መንገድም ለዜጎች ያላቸውን ክብር የሚያሳይ ነበር ‹ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምናፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ አድልኦ ለመላው ዜጎች ይደርስ ዘንድአጥብቀው ይመኛሉ… ይደክማሉ። በሀገር ውስጥና በውጪ ሆነው ስለ ሀገርአንድነትና ሰላም… ስለፍትህና እኩልነትእንዲሁም ስለብልጽግና ይጮሃሉይሞግታሉ… ይሟገታሉ።› ነው ያሏቸው፡፡ የዜጎቻቸውን ትግልና ጥረት ክብር ሰጥተውታል፡፡ አሸባሪዎች፣ ነውጠኞች፣ አደገኛ ቦዘኔዎች፣ አላሏቸውም፡፡ ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ፤ የእኩል ተጠቃሚነት፤ በነጻ ተዘዋውሮ የመኖርና የመሥራት፤ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ገለልተኝነት፤ ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፤ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብትጥያቄና ትግል ክብርና ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡ 
 
2. ፍቅር፡- አንድነታችን ፈተና ገጥሞታል፤ ፍቅራችንን የሚያቀዘቅዙ ነገሮች እየተከሠቱ ነው፣ መጠላላቱና መከፋፋቱ በየአቅጣጫው ዕየታየ ነው በምንልበት ወቅት ፍቅርን የሚሰብክ የመሪ መልእክት ኃይል አለው፡፡ የዶክትር ዐቢይ ንግግር ይህንን የተረዳና ማሻሪያ ለመስጠት የተዘጋጀ ነበር፡፡ በሕዝቡ መካከል ከፍቅር ይልቅ ቅሬታ፣ ከወዳጅነት ይልቅ ጠላትነት፣ የሚያጭሩ ቃላትን ላለመጠቀም ጥንቃቄ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ከደርግ ዘመን ፓርላማ ወዲህ ‹ፀር› ከፓርላማ የተባረረበት የመሪ ንግግር ነበር፡፡ ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ፣ ጸረ ልማት፣ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ፀረ … የሚለውን እንደ ሃሌሉያ አዘውትሮ ሲሰማ ዐርባ ዓመት ላለፈው ፓርላማ እንግዳ ነገር ነው፡፡ ጠባብነት፣ ነፍጠኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሽብርተኝነት፣ የመሳሰሉት የሰለቹ ቃላት ባመሳተፋቸው አዝነው የዋሉበት ንግግር ነበረ፡፡

የዶክተር ዐቢይ ንግግር በ8 ገጽ፣ በ2776 ቃላት፣ በ12533 ምዕራፍ አልባ ቅንጣቶች(Characters without space)፣ በ15230 ባለ ምዕራፍ ቅንጣቶች(Characters with space)፣ በ79 ዐንቀጾችና በ259 መሥመሮች የተዋቀረ ነው፡፡ በዚህ ንግግር ውስጥ በዋናነት የተንጸባረቀው መግለጫ ‹እኛ› የሚለው ራስን ከሕዝብ ጋር የሚያስተሣሥርና ፍቅርን ሊገልጥ የሚችለው አንጓ ነው፡፡ ይህን ለመግለጥ በቃላት ላይ - ችን የሚል ድኅረ ቅጥያ ተጠቅመዋል፡፡ ኢትዮጵያችን፣ ሕዝባችን፣ ሀገራችን፣ ወገናችን፣ ችግሮቻችን፣ ስኬቶቻችን የሚሉ መግለጫዎች አሉ፡፡ በጽሑፉ ውስጥ ይህንን መንገድ ከ86 ጊዜ በላይ ተጠቅመውበታል፡፡ ከዚህ መካከል ከ18 ጊዜ በላይ ‹ሀገራችን› የሚለው መግለጫ ይገኝበታል፡፡

3. አንድነት፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ ከማራራቅ ይልቅ የሚያቀራርብ፣ ከመገፋፋት ይልቅ የሚያስተሣሥር፣ ከማግለል ይልቅ የሚያካትት፣ ከመነጣጠል ይልቅ የሚያስተባብር ነበር፡፡ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ ከመነሻቸው ይልቅ መድረሻቸው ላይ ነው ያተኮሩት፡፡ ራስ ካሣ እንዳሉት ‹ፀሐይን ለብቻዬ ልሙቅ አይባልም›፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአንድ ወገን አይደሉም፡፡ የጥንቶቹም የዛሬዎቹም፣ የደጋፊዎቹም የተፎካካሪዎቹም፣ የክርስቲያኖቹም፣ የሙስሊሞቹም፣ የሌሎቹም፤ የመረጧቸውም ያልመረጧቸውም፣ የሀገር ቤት ነዋሪዎቹም የዳያስጶራዎቹም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አሳይተውበታል፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የትናንቱም የዛሬውም፣ የነገውም ጠቅላይ ሚኒስትር ነውና የቀደሙትን ከዛሬዎቹ ጋር አስተሣሥረው ጠርተዋቸዋል፡፡ በታሪካችን ውስጥ ማሳያ የሚሆኑትን ኩነቶች አንሥተው የእገሌ ጎሳ መሬት ነው ሳይሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በየዘመናቱ የከፈሉትን መሥዋዕትነትና በመሥዋዕትነት ቦታቸው የዚያው ቦታ አፈር ሆነው መቅረታቸውን ገልጠዋል፡፡ ‹በአንድ ሀገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት እርግማንአይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርሕ ላይ ተመስርተንመግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሀሳብ ፍጭትውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመርእንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም… አገር ይገነባል። የኔሀሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብንያፈርሳል። ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊአንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝኃነታችንን በኅብረብሔራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት።› የሚለው መዓዝናዊ የአንድነት መግለጫቸው ነው፡፡

ይህ ለውጥ እንዲመጣ በየመሥመራቸው የታገሉትን የጠሩበት መንገድ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ እየተባሉ ሲጠሩ የኖሩትን ኃይሎች ‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች› ብለው የገለጡበት አካሄድ፡፡ ዳያስጶራውን ማኅበረሰብ ያቀረቡበት መንገድ የንግግሩ አንኳር ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ በተለያየ ጊዜ፣መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኞች፤ በቅጡ ሳይቦርቁሕይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስየተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች› እና ‹ሰላም ለማስከበርና ሕገመንግሥታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ሕይወታቸውን  የፀጥታ ኃይሎች› ጎን ለጎን የተመሰገኑበት መንገድ አስደናቂ ነው፡፡ መንግሥት ለአንጋቹ እንጂ ለሟቹ የማይወግንበትን አካሄድ ያረመም ነው፡፡

4. ይቅርታ፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከተዋቀረባቸው አዕማድ አንዱ ይቅርታ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች ገልጠውታል፡፡ በተለይም ስድስቱ ዋና ዋና ዘውጎች ይጠቀሳሉ፡-

፩. ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸውበርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን። ከስህተቶቻችን ተምረን ወደፊትበመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች ሀገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይነው።›፣‹የሁሉም ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እናፖለቲካዊ ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር ክፍተቶች ነበሩ።› የሚለው ስሕተትን የሚያምነው፤

. ‹ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው!› የሚለው ወቅቱን ከስሕተት አንጻር የገመገመው፡፡

፫.  ‹በተለያየ ጊዜ፣ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኛች፤በቅጡ ሳይቦርቁ ሕይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታእጠይቃለሁ› የሚለው ለተፈጠረው ችግር ይፋዊ ይቅርታ የሚጠይቀው፣

.‹በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንናትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውንምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍእንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ› የሚለውና ከሌላውም ወገን ይቅርታን የሚጠይቀው ንግግር ይቅርታውን በየደረጃው የጠየቀ ነው፡፡

.  ‹መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው!› ሲሉም ይሄንኑ አጽንተውታል፡፡ ይህም እንዲሳካ

፮.‹በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንናትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውንምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍእንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

5. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፡- ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ናት? እነዚህን 12 መግለጫዎቻቸውን እንመልከት፡-

 ሀ. ኢትዮጵያ ማኅጸነ ለምለም ናት
ለ. ትላንት፣ አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራ ማራአጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርናበአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን።
ሐ. እኛ ዕድለኞች ነን። ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንንእናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ዝብ ነን።
.ኅብረታችን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል። ጠላቶቻችንንአንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይለሌሎች ሕዝቦችም የነጻነት ትግል አርአያ ሆኗል።
ሠ. ማንነታችንን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖየተገመደ፣የተዋደደ እና የተዋሐደ ነው!
.የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖርኢትዮጵያ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።
. ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!
ሸ. ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነትይበልጣል።
ቀ. እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም !በ. ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉምድምጽ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትየመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን።
. ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን  ቸ. እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያንተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያንከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባልም ለዚህ ነው። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ከዜግነት በላይ ሐሳብ፣ ፍልስፍናና ሀገራዊ መርሕ አድርጎ ያቀረበ ነው፡፡
ይህንንም በአንድ አንኳር ‹ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታበጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካምአጋጣሚቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው።› ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ‹ኢትዮጵያዊነት› የሚለውን ሉዓላዊ ሐሳብ በክብር ገልጠውታል፡፡

 6. ሰውነት፡- ማንኛውም መሪ፣ መሪ ከመሆኑ በፊት ሰው ነው፡፡ አብዮታዊ ነን የሚሉ መሪዎች ሰውነትን ይተውትና ተቋማዊነትን ቦታ ይሰጡታል፡፤ ከሰው የተወለዱ፣ ሰው ያሳደጋቸውና የሰው ፍሬዎች መሆናቸው ይረሱታል፡፡ መነሻቸውን ከሰው ሳይሆን ከድርጅት ያደርጉታል፡፡ የዶክተር ዐቢይ ንግግር አንዱ ዓምድ ለሰውነት የሰጠው ቦታ ነው፡፡ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዳያስጶራዎች፣ መሥዋዕትነት የከፈሉ ዜጎች የተነሡበት መንገድ ለሰውነታቸው ቅርብ በሆኑ ቃላት ነው፡፡ እንደ ቡድን የሚያይ ሳይሆን ለግለሰብነታቸው ዋጋ የሚሰጥ ነው፡፡ ዳያስጶራዎች በምንም ዓይነት የፖለቲካ መሥመር ውስጥ ቢሆኑም ‹ሁላችሁምበታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነትባሕሪ የኢትዮጵያና የዕሴቶቿ እንደ ራሴዎች ናችሁ።› የሚለው ገለጻ ግን የማይመለከተው የለም፡፡ ‹አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሀገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙትስለሀገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም።› ሲል ቁጭታቸውን ይቆጫል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ‹እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ› ለማየት ጥረዋል፡፡ ከድርጅቶቹ ይልቅ ሰዎቹን ‹ወንድም፣ ዜጋ› እያሉ በሰውነት ጠርተዋቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩም እናታቸውን፣ ባለቤታቸውንና የትግል አጋሮቻቸውን ያመሰገኑበት መንገድ ሰውዬው ሰው ናቸው እንድንል የሚያደርግ ነው፡፡ እናታቸውን ከኢትዮጵያውያን እናቶች አንዷ አድርገው፣ ባለቤታቸውን ሚና ከኢትዮጵያውያን ሚስቶች ጋር አስተሣሥረው የገለጡበት መንገድ ‹ሰውነት› የታየበት ነው፡፡ ሰው ከሆኑ ደግሞ እንደሰው ይሠራሉ፣ እንደሰውም ይሳሳታሉ፡፡

7. ተስፋ፡- ሰባተኛው የንግግሩ ዓምድ ተስፋ ነው፡፡ ምን ሊሠሩ አስበዋል? ምን እንጠብቅ? ሊሠሩ ያሰቡትን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አካላት የሚፈልጉትንም ገልጠውበታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ ቃል መግባትንና ጥሪን የተመለከቱ 19 ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-
       i.   ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ እድልነው፤ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት  ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል።

ii.  በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነጻነትና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የሕግየበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን 
ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉያለውን ክፍተት እንሞላለን።

iii.  ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባትእንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። 
የበኩላችንንም እንወጣለን።

iv.  ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆንለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ 
እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ

v.   አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ፣ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትን እናየተደራጀ ሙስናን፣ መላው ሕዝባችንን 
በሚያሳትፍ እርምጃ ለመመከትሌት ተቀን እንተጋለን።

vi.   በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን እና ከቴክኒክ እና ሙያኮሌጆች የሚወጡት ተማሪዎቻችን 
ከሚገበዩት ዕውቀት የሚነጻጸርከሂሎት እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥራት ይደረጋል።

vii.  የሁለተኛውን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሁሉት ዓመት ተኩልአፈጻጸም በመገምገም አስፈላጊ 
የሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ለማስቀጠል እንታገለን

viii.  ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ፣ ተስፋ የምታስቆርጥ አገርእንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ 
እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ።በሚቀጥሉት ጊዜያት ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆንወጣት 
ባለሀብቶች በብዛት እንዲፈጠሩ እንሠራለን። ለዚህ እንቅፋትናመሰናክል ለሚሆኑ አመላካከቶችና የተንዛዙ 
አድሏዊ የሆኑ አሠራሮችተወግደው ፍትኃዊ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዲኖረንመንግሥት ምቹ ሁኔ
ይፈጥራል።

ix.   መንግሥታችን ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍጥነት እና የትግበራ ስኬት በላቀመልኩ ለሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነትይሠራል።

x.   ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና ሀብት የማፍራትመብታቸው መከበር አለበት። 
በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነድርጊት እንዲያበቃና ዳግም እንዳይፈጠር መሥራት ይኖርብናል።

xi. በቀሪው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዓመታት ቀሪየልማት መርሐ ግብሮቻችንን በፈጠነ ጊዜ ለማሳካት ጥረት ይደረጋል።

xii.   ከመደበኛው የሥራ ሰዓታችን በሚሻገር ጊዜ፣ ከፍ ባለ ፍጥነትና ተነሳሽነትበመሥራት በቅርብ ዓመታት 
ውስጥ በተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትየደረሰብንን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ለማካካስ አገራዊ ንቅናቄ
እንድናደርግ ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

xiii.   ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሀገራችሁ መመለስናሀገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተንእንቀበላችኋለን።

xiv.   በውጭ ሀገራት ኑሯችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩበሀገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ
 እንድትሆኑና ሀገራችንን በሙሉምመልክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋጽኦ መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ 
ማድረጉን ይቀጥላል።

xv.   ከጎናችን የቆማችሁ የልማት አጋሮቻችን የሀገራችን ጥብቅ ወዳጆችእንደሆናችሁ እንገነዘባለን። የሀገራችንን ልማት እና ሰላም ለማረጋገጥበምናደርገው ጥረት እንደ ወትሮ ሁሉ ከጎናችን እንደምትቆሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።

xvi.   ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምርበዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፡፡

xvii.   በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገለግሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ
 የሚጥሉ፤ ብሔራዊጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆአስተዋይነትና ሀገራዊ 
ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርሕ የተሻለ የፖለቲካባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን
አስተላልፋለሁ፡፡

xviii.   ሁላችንም የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንረባረብሀገራችንን ከድህነትአዘቅት ውስጥ ለማውጣት እንትጋዘረኝነትና መከፋፈልን ከሀገራችንእናጥፋየተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!

xix.   ከግድቡ መጠናቀቅ ባሻገር የሀገራችንን ብልጽግና እስከምናረጋግጥበትከፍታ ድረስ እንድንዘልቅ ጥሪዬን 
አቀርባለሁ፡፡

ከእነዚህ መካከል 11ዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም መንግሥትን የሚመለከቱ ሲሆኑ 8ቱ ደግሞ ጥሪ  ተደረገላቸውን አካላት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ይህም የችግሩ ዋና መነሻ የመንግሥት አካሄድ ነውና የመፍትሔው ዋና ቁልፍም በመንግሥት እጅ መሆኑን ያሳያል፡፡

 የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃልና ጥሪ 19 ርእሰ ጉዳዮችን የተመለከተ ነው፡፡

፩. የሥልጣን ሽግግሩን አጠቃቀም
፪. የዴሞክራሲ ጥያቄ
፫. የፍትሕ ጥያቄ
፬. የኤርትራን መንግሥት የተመለከተ
፭. ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት
፮. ሙስና
፯. የትምህርት ጥራት
፰. የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ
፱. የኢኮኖሚ ፖሊሲው ማሻሻያ
፲. ለወጣቱ ምቹ የምትሆን ሀገር
፲፩. የሴቶች ተጠቃሚነት
፲፪. ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና የመሥራት መብት
፲፫. በተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሣራ የተቸገረውን ሕዝብ መካስ
፲፬. የተፈጠረውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሣራ የሚያካክስ ሥራ መሥራት
፲፭. ዳያስጶራ
፲፮. የልማት አጋሮች
፲፯. ተፎካካሪ ፓርቲዎች
፲፰. ዘረኝነትና መከፋፈል
፲፱. የሕዳሴው ግድብ ናቸው፡፡

እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ አድርጎ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኝነት፣ ቁርጥ ያለ ዕቅድ፣ አካታች የሆነ አካሄድ፣ ሳይዘናጉ መፍጠንና ከአንኳር የሕዝብ አካላት ጋር መወያየትን ይጠይቃል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ተጉዞ የተለየ ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ ‹ቃል ይቀድሞ ለነገር› ነውና ይህ ቃል የነገው ተግባር መግቢያ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ እንደታየው ሕዝብ ዕድል ይሰጣል፡፡ ሕዝቡ የሰጠውን ዕድል የማይጠቀሙ መሪዎች ሲገጥሙት ግን በአሳቻ ሰዓት እንደተመካከረ ሰው ‹ሆ› ብሎ ይነሣል፡፡ ዝምታውን እንደ መሸነፍና ፍርሃት የሚቆጥሩ መሪዎች ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ የሀገራችን ሊቃውንት ሁለት ዓይነት መብራት አለ ይላሉ፡፡ አንዱ ፏ ብሎ የሚበራና መንገዱን ወገግ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ከሩቁ ሆኖ መድረሻን የሚጠቁም መብራት ነው፡፡ የመጀመሪያው ከተገኘ መንገዱን ያለ ዕንቅፋት ለመሄድ፣ በቶሎም ለመድረስ ይመቻል፡፡ እርሱ ካልተገኘ ደግሞ ማዶ ተሰቅሎ መድረሻውን የሚጠቁመው መብራት መኖር አለበት፡፡ መንገዱን ወገግ አድርጎ ባያሳይም መድረሻውን ያመለክታል፡፡ የሚጓዘው ሰው እየወደቀም እየተነሣም ይሄዳል፤ መድረሻውን ያውቀዋልና፡፡ በሩቁ ስለሚያየው አይስተውም፡፡ ተስፋ አይቆርጥም፣ እንደሚደርስ ርግጠኛ ነውና፡፡ ድቅድቅ ጨለማ ግን እንኳን ለሀገር ለግለሰብም አስቸጋሪ ነው፡፡ የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ይህ የሕዝብ ድጋፍና ፍቅር እንደ በረዶ ከመቀዝቀዙ በፊት ቢችል መንገዱን ያብራ፣ ባይችል መድረሻውን ያሳይ፡፡ ካልሆነ ግን ምናልባት ሌሎቹ ቀደምቶቹ ያገኙትን ዕድል ላያገኘው ይችል ይሆናል፡፡ ሰው የሚጠየቀው በተሰጠው መጠን ነውና፡፡ አሁን ተግባሩን እንጠብቃለን፡፡ ችግሮቹን ሁሉ እንዲፈቱ ሳይሆን መፍታት እንዲጀምሩ፤ ስሕተቶቹን ሁሉ እንዲያርሙ ሳይሆን ማረም እንዲጀምሩ፤ መንገዱን በሙሉ እንዲሠሩ ሳይሆን መሥራት እንዲጀምሩ፡፡

ወቅቱ የትንሣኤ ዋዜማ ነውና እባክዎን ሥራዎትን መፈታት የሚገባቸውን የፖለቲካ እሥረኞች (በተለይም ደግሞ ይህንን የእርስዎን ንግግር ከእሥር ቤት ውጭ እንዲሰሙ ከተፈቱ በኋላ፣ እሥር ቤት ተመልሰው የሰሙትን እነ እስክንድር ነጋን) ና መነኮሳቱን በመፍታት ይጀምሩ፡፡ የእርስዎም የሕዝቡም ፋሲካ ደርብ ፋሲካ እንዲሆን፡፡ 
ይቅናዎት፡፡

Tuesday, 3 April 2018

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሙሉ ንግግር







የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ክቡራትና ክቡራን!

ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንግስት አስተዳደር ስርዓቷ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በምታከናውንበት በዚህ ታሪካዊ ቀን በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርቤ ይህንን ንግግር ለማድረግ ስለበቃሁ የተሰማኝን ልዩ ክብር ለመግለጽ እውዳለሁ።
ከሁሉ አስቀድሜ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአገራችን ለተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመፍትሄ አካል ለመሆን፤ የሀገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ በአዲስ አመራር ሊጠበቅ ይችላል ብለው በማሰብ፣ ለአህጉራችን ምሳሌ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ላሸጋገሩት ለክቡር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከፍ ያለ አክብሮቴን እገልጻለሁ። በተመሳሳይ የመንግስታዊ ስልጣን ሽግግሩ ያለ እንከን እንዲከናወን ልዩ ሚና ሲጫዋቱ ለቆዩት ሁሉ በመላው ህዝባችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ዕለቱ ለሀገራችን ታሪካዊ ቀን ነው!

በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር እድሎችን አግኝተን ብዙዋቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል። አሁንም፣ ይህ የስልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ እድል ነው፤ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል።

ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ እድልኦ ለመላው ዜጎች ይደረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ… ይደክማሉ። በሀገር ውስጥና በውጪ ሆነው ስለ ሀገር አድነትና ሰላም… ስለፍትህና እኩልነት…እንዲሁም ስለብልጽግና ይጮሃሉ…ይሞግታሉ… ይሟታሉ።

ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት አበይት እውነታዎችን የሚመላክት ነው። ክስተቱ፣ በአንድ በኩል በሀገራችን ዘላቂ፤ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ የህገ-መንግሥትታዊ ስርዓት መሰረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በህዝብ ፍላጎት፤ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑ ያመለክታል።

ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው!

መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ ሀገራችንን ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት በሁሉም መስክ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ህገ-መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብቷል። ዓለም በአንድ በኩል በጥሞና፣ በአግራሞትና በጉጉት በሌላ በኩል ደግሞ በስጋት እየተመለከተው ያለ ሀገራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን። ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን። ከስህተቶቻችን ተምረን ወደ ደፊት በመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች ሀገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይ ነው። ዋናው ቁም ነገር፤ አገራችንን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገሩ እና አንድነቷን ጠብቃ የምትቆይበትን ሁኔታ በቀጣይነት እያረጋገጡ መሄዱ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታ በጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው። ትላንት፣ አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራ ማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን። እኛ እድለኞች ነን። ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ህዝብ ነን። ህብረታችን ለዓ ለም ምሳሌ መሆን ይችላል። ጠላቶቻችንን አንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ ለሌሎች ህዝቦችም የነጻነት ትግል አርአያ ሆኗል። ማንነታችንን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳትነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣የተዋደደ እና የተዋሀደ ነው!

አማራው በካራ-ማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራ-ማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉል፣ ወላይታ፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሀዲያው እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል።

አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሀገር እንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ስጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።

ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!

በአንድ ሀገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሀሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ።ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም… አገር ይገነባል። የኔ ሀሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳለ። ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝሃነታችንን በህብረ-ብሔራዊነት ያደመደቀ መሆን አለበት።

እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም !

ዲሞክራሲ ለኛ ባዕድ ሃሳብ አይደለም። በዓለም ውስጥ በብዙ ማሕበረሰቦችና ሀገራት ዲሞክራሲ በማይታወቅበት ዘመን በገዳ ሥርዓታችን ተዳድረን ለዓለም ተምሳሌት ሆነን፣ ኖረናል። አሁንም ዲሞክራሲን ማስፈን ከየትኛውም ሀገር በላይ ለኛ የሕልውና ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን። ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም። ነጻነት ከመንግስት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንሱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ። ነጻነትን በዚህ መልኩ ተረድቶ እውቅና የሰጠውን ህገ-መንግሥታችንን በአግባቡ መተግበር፣ የሰባዓዊ እና ዲሞክራዊ መብቶች በተለይም ሃሳብን የመግለጽ፣ የመሰባሰብና የመደራጀት መብቶች በሕገ-መንግሥታችን መሰረት ሊከበር ይገባል። የዜጎች በሀገራቸው የአስተዳደር መዋቅር በዲሞክራሲያዊ አግባብ በየደረጃው የመሳተፍ መብትም ሙሉ በሙሉ እውን መሆን አለበት። ሁላችንም መገንዘብ ያለብን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መደማመጥን ይጠይቃል። ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፣ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው።

መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነው። ምክንያቱም ገዥ መርሃችን የህዝብ ሉዓላዊነት ነውና። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ፣ የመጀመሪያው የመጨረሻውም መርህ፣ በመደማመጥ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን።ዲሞክራሲ ሲገነባ መንግሥት የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማክበር አለበት። ዲሞክራሲን ከዜጎች ሰላማዊ እንቅስቀቃሴና ከመንግስት መሪነት፣ ደጋፊነትና ሆደ ሰፊነት ውጭ ማዳበር አይቻልም። በመሆኑም መንግሥት የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓገል በጽናት ይሰራል።

በተመሳሳይ ዜጎች ሀሳባቸውን ሲገልጹ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆን ይገባዋል። የራስን ዲሞክራሲያዊ መብት እየጠየቁ የሌለውን መብት መጋፋት እርስ በእርሱ ይጣረሳል፤ ዲሞክራሲያንም ያቀጭጫል። መንግስት ህግን ማክበር አለበት፤ ማስከበርም ግዴታ ነው፤ ታጋሽነትም ኃላፊነቱ ነው። የመንግስት ታጋሽነት ሲጓደልም ዲሞክራሲ ይጎዳል። በሁለቱም አካሄድ የምንናፍድቀው ዲሞክራሲ ሊመጣ አይችልም።

በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የህግ የበላይነት መስፈን ይገባዋል። የህግ የበላለይነትን ለማስፈን በምናደርገው ደትግል መርሳት የሌለብን ቁም ነገር ሕዝባችን የሚፈልገው የሕግ መኖርን ብቻ ሳይህን የፍትህ መረጋገጥንም ጭምር ነው።

የሕዝብ ፍላጎት ከፍትህ የተፋታ ደረቅ ሕግ ሳይሆን፣ በፍትህ የተቃኘ፣ ለፈትህ የቆመ የሕግ ስርዓትን ነው። የሕዝብ ፍላጎት የሕግ አስከባሪ ተቃማት ገለልተኛና ለፍትህ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ቀናኢ እንዲሆኑ ነው። ሕግ ሁላችንንም እኩል የሚዳኝ መሆን አለበት። እንዲህ ሲሆን ሕግ በተፈሮ ያለንን ሰብዓዊ ክብራችንን ያስጠብቅልናል። ይህን እውነታ በመረዳት በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነጻነትና ፍትህ እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እንሞላለን።

ለሰላም መሰረቱ ፍትህ ነው። ሰላም የግጭት አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም በመግባባት ላይ የተመሰረተ ጽኑ አንድነታችን ነው፣ ሰላም- መተማመናችን ነው። ሰላም-በሁላችንም ፈቃድ ዛሬም የቀጠለ የአብሮነት ጉዞችን ነው። ሰላም አለመግባባትና ተቀርኖዎችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት የሚያስችል መንገድና ግባችን ነው።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ክቡራትና ክቡራን

ያለንበት ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ በቀውስ ውስጥ ያለበት፣ ብዙ የየራሳቸው ፍላጎትና ዓላማ ያላቸው ኃይሎች የሚራኮቱበት፣ ውስብስብ መጠላለፍ በቀጠናው ያለበት ወቅት ነው። በዚያው ልክ ደግሞ በደም፤ በባህል፣ በቋንቋ እና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ያለንበት አካባቢ ነው የውጭ ግንኙነታችንን በተመለከተ ሀገራችን የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት፣ የአፍሪካ ህብረት መስራችና መቀመጫ፣ የቀድምት ዓለምአቀፍ ተቋማት መስራችና በአለም አቀፍ፤ በአህጉር አቀፍ እንዲሁም ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህና ገንቢ ሚና የምትጫወት ሀገር ናት። ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተውን ፖሊሲያችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።

ከአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ወንድሞቻችን ጋር በአጠቃላይ፤ እና ከጎረቤቶቻችን ጋር በተለይ በችግርም በተድላም አብረን እንቆማለን። ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለአመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለት ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለለጽኩ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስዱ በዚሁ አጋጣማ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ የተከበራችሁ የም/ቤት አባላት ክቡራትና ክቡራን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሙስና አንዱ ነው። ሙስናን ጸረ-ሙስና ተቋም በመመስረት ብቻ መከላከል እንደማይቻል ተረድተን፤ ሁላችንም፣ ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሰርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ። ትናንት የተፈጠረን ሃብት ከሌላው በመቀማት ሂሳብ ለማወራረድ የሚተጋ አገርና ሕዝብ ወደፊት ለመራመድ አይችልም። ገበታው ሰፊ በሆነበት፣ ሁሉም ሰርቶ መበልጸግ በሚችልበት ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ የሚያስገድድ ይቅቅርና የሚያሳስብ ምንም ምክንያት ይለም። ይልቁንም ወቅቱ የፈጠረልንን ልዩ አጋጣሚና ሀገራዊ አቅማችንን አቀናጅተን የእጥረትና እጦት አስተሳሰብን በማስቀረት ለጋራ ብልጽግና እንትጋ። ታዋቂው የህንድ የነጻነት ንቅናቄ መሪ ማህተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንደተነገረው፣ አገር ለሁሉም የሚሆን በቂ ሀብት አላት፤ ሁሉም እንደልቡ የሚዘርፈው ሀብት ግን ሊኖራት አይችልም። አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ፣ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትን እና የተደራጀ ሙስናን፣ መላው ህዝባችንን በሚያሳትፍ እርምጃ ለመመከት ሌት ተቀን እንተጋለን።

ክቡራትን ክቡራን

ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ባስመዘገባችው ፈጣን እድገት የተነሳ በድህነት ቅነሳ፣ በመሰረተ-ልማት ግንባታ፣ በሰው ሀይል ልማት እና በመሳሰሉት ያገኘናቸው ስኬቶች ለሁሉም የሚሰታዩ ናቸው። ከዚህ አኳያ መንግሥት የዋጋ ንረት እና የውጪ ምንዛሬ ዋጋን ለማረጋጋ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ፣ ለኢኮኖሚ የሚቀርበውን የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነትን ለማስፋት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን እንዲሁም ቁጠባን እና ኢንቨስትመንት ለማበረታታት፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የሕዝቡን የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም አስከፊ ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የፖሊሲ እና የትግበራ አርምጃዎችን ወስዷል።በአንፃሩ፣ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት የኢኮኖሚ እድገቱን እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቱን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ተከስተዋል። ከእነዚህም ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የውጪ ንግድ በምንፈልገው መጠን አለማደጉ፣ ይሄን ተከትሎ የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ የውጪ እዳ ጫና እና የሀገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ናቸው።

በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረየታች ቢሆኑም ዘርፉን በተገቢው ሁኔታ በቴክኖሎጂ መደገፍ ባለመቻሉ እንደ ሀገር ማግኘት የሚገባንን የኢኮኖሚ ትሩፋት ሳናገኝ ቆይተናል። እንደ ደትልቅ ሀገር እና ሕዝብ ከምናስበው የስኬት ጫፍ ላይ መድረስ የምንችለውና ችግሮቻችንን የምንፈታበትን ዋና ቁልፍ የምናገኘው በትምህርት እና በትምህርት ብቻ እንደሆነ በማመን መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም በተለይ የትምህርትን ጥራት ከማስጠበቅ አንጻር እጅግ ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊታችን እንዳሉ በውል በመገንዘብ በርካታ ስራዎች ይሰራሉ።

የትምህርት መስፋፋት ይበል የሚያስኝ የመንግስታችን ስኬት ቢሆንም ይህ የትምህርት ሽፋን እድገት በጥራት እስካልተደገፈ ድረስ ልፋት ጥረታችን ሁሉ የምንተጋለትን ውጤት ሊያመጣልን አይችልም። በመሆኑም ከመጀመርያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉትን የአውደደቀት አለሞቻችንን በጥራት ላይ አትኩረው እንዲሰሩ መንግሥት በፍጹም ቁርጠኝነት ይረባረባል። በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቻችን እና ከቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች የሚያወጡት ተማሪዎቻችን ከሚገበዩት እውቀት የሚነጻጸር ከህሎት እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥራት ይደረጋል። እነዚህንና ሌሎቹንም ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የሁለሰደተኛውን የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን የሁሉት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በመገምገም አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ለማስቀጠል እንታገለን።

ውድ የሀገራችን ወጣቶች

ኢትዮጵያ የናንተ ነች፣ መጭውም ዘመን ከሁሉ በላይ የእናንተ ነው አሁንም አገሪቷን በመገንባት ግንባር ቀደም ሆናችሁ መሳተፍ ይኖርባችሀል። የወጣቱ ጥያቄ የኢኮኖሚ የእኩል ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲና የፈትህ ነው ብለን እናምናለን። የሁሉም ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ማሕበራዊ ፍትህ እና ፖሊቲካዊ ተሳትፎ ከማሳደግ አጻር ክፍተቶች ነበሩ።

አገራችን፣ ጥሩ የሚባል ኢኮኖሚያዊ እድገትን እያስመዘገበች እንደሆነ ቢታወቅም እድገቱ በቅርፅና በይዘት ተለዋዋጭ የሆነውን የወጣቱን ትውልድ ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ የሚያረካ አልነበረም። ይህም፣ ህዝባችንን ለብሶት እንደደረገው እንገነዘባለን። ያለውጣቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት አገር የትም ልትደርስ እንደማትችልም እንረዳለን።

ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ፣ ተስፋ የምታስቆርጥ አገር እንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ። በሚቀጥሉት ጊዜያት ለወጨጣቱ የሥራ እድል መፍጠር ብቻቀ ሳይሆን ወጣት ባለሀብቶች በብዛት እንዲፈጠሩ እንሰራለን። ለዚህ እንቅፋትና መስናክል ለሚሆኑ አመላካከቶችና የተንዛዙ አድሏዊ የሆኑ አሰራሮችን አስወግደው ፍትሃዊ የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት እንዲኖረን መንግሥት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። መርሳት የሌለብምን ሀቅ ግን ለራሱም ሆነ ለሀገሩ በሥራውና በጥራቱ ሀብት የሚፈጥረው ወጣቱ እራሱ መሆኑን ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ሴቶች

በብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያን ገንብታችሁ፣ ታሪክ ሰርታችሁ፣ ትውልድ ቀርጻችሁ ዛሬ ላይ ደርሰናል። በትግላችሁም የተሻለች ሃገር እንድትኖረን ብዙ መስዋዕትነት ከፍላችኋል። ትግላችሁ የፍትህ ትግል ነው፣ ትግላችሁ ክቡር ትግል ነው፣ ትግላችሁ ትግላችን ነው። መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና በሃገራችን ሁለንተናዊ የእድገት ግስጋሴ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኝ ቢሆንም አሁንም ከሰራነው ይልቅ ያልሰራናቸው ስራዎች እጅግ እንደሚበዙ እናምናለን። በመሆኑም በቀጣይ የሃገራችን ሴቶች ተፈጥሮ እና ኑሮ የሰጧችሁን በረከቶች ተጠቅማችሁ ለሃገራችን እድገት እና ብልጽግና እንዲሁም ለፖለቲካችንም ስምረት አዎንታዊ ሚና እንደምትጫወቱ ተስፋዬ የላቀ ነው።

አገራዊ ማንነታችን ያለ እናንተ ያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ምንም ነው። አገሪቷን የገነቡ፣ ያገለገሉ፣ ያቆሙ ሴቶችን እውቅና በመንፈግ ሀገራዊ ትንሳኤን ማረጋገጥ አይቻልም። መንግስታችን ለሴቶች መብትና እኩልነት የሚቆመው፣ ለሴቶቻችን ውለታ ለመዋል ሳይሆን ለሁላችንም ብለን ነው። ግማሽ አካሉን የረሳን ሀገር ሙሉ የሀገር ስዕል ይኖረው ዘንድ ከቶ እንደማይችልና ወደፊትም እንደማይራመድ መንግስት በውል ይገነዘባል። በመሆኑም መንግስታችን ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍጥነት እና የትግበራ ስኬት በላቀ መልኩ ለሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ይሰራል።

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ጥሪ የተደረገላቸሁ እንግዶች ክቡራትና ክቡራን

ችግሮቻችን በርካታ እና ፋታ የማይሰጡ ናቸው። የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል አለመኖር፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ የተደራጀ የሙስና እና ብልሹ አሰራር መስፋፋት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ተደማምረው ሰፊና ውስብስብ ፈተና ደቅነውብናል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወገኖቻችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለመፈናቀል፣ ለህይወት እና ንብረት መጥፋት ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል። ዜጎች በሃገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና ሃብት የማፍራት መብታቸው መከበር አለበት። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲያበቃና ዳግም እንዳይፈጠር መሥራት ይኖርብናል።ችግሮቻችንን፣ ተለያይተን ቀርቶ ተባብረን እና ተዋደንም ለመፍታት ዓመታት ያስፈልጉናል። በመሆኑም የባከነውን ግዜ በማካካስ ወደፊት መጓዝ እንችል ዘንድ በአዲስ መንፈስ መረባረብ ይጠበቅብናል።

ሁሉም ችግሮቻችን በአንዲት ጀንበር ሊፈቱ አይችሉም። ነገር ግን የጀመርነውን የተሻለች ሀገር የመገንባት ሂደት ማፋጠን እንችላለን። የተሻለች አገር መገንባት የሚያስችል ጠንካራ ተነሳሽነት አለ። ጠንካራ አገር ለመገንባት ሁላችንም ሀላፊነት አለብን። እንደ ተለያየ አገር ዜጋ በባእድነት እና ባይታወርነት ሳይሆን፣ ሁላችንም እንደ ባለቤቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ ይጠበቅብናል። ይህ ሲሆን ስንወድቅም፣ ስንነሳም በጋራ ይሆናል። በቀሪው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዓመታት ቀሪ የልማት መርሀ-ግብሮቻችንን በፈጠነ ጊዜ ለማሳካት ጥረት ይደረጋል። ከመደበኛው የሥራ ሰዓታችን በሚሻገር ጊዜ፣ ከፍ ባለ ፍጥነትና ተነሳሽነት በመሥራት በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የደረሰብንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ለማካካስ አገራዊ ንቅናቄ እንድናደርግ ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ የተከበራችሁ የም/ቤት አባላት ክቡራትና ክቡራን

በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለስራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው። ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነት ባህሪ የኢትዮጵያና የዕሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ።

አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሃገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለሃገራችሁ ቁጭት ሳይሰማቹ አይቀርም። ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ። እንደገሀር ያለንን ሃብት አሟጠን ለመጠቀም የምናደርገው ጥረት በቂ ሳይሆን ሲቀር መቆጨታችሁ አይቀርም። መቆጨትም አለባችሁ። ይሄንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ ሀገር አለችንና እውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሃገራችሁ መመለስና ሃገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን። በውጭ ሃገራት ኑሯችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩ በሃገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑና ሃገራችንን በሙሉም መልክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋጽኦ መንግስት ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።

ውድ የልማት አጋሮቻችን

እስካዛሬ ባደረግነው የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ከጎናችን የቆማችሁ የልማት አጋሮቻችን የአገራችን ጥብቅ ወዳጆች እንደሆናችሁ እንገነዘባለን። የአገራችንን ልማት እና ሰላም ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት እንደ ወትሮ ሁሉ ከጎናችን እንደምትቆሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው!

ሀገራችን ፍትህ፣ ነጻነትና ሰላም የሰፈኑባት፣ ዜጎችዋ በሰብዓዊነት የሚተሳሰቡት፣ በእህት/ወንድማማችነት የተሳሰሩባት እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ህልማችን እውን የሚሆነው ከእንቅልፋችን ነቅተን ስንሰራ ነው፡፡ መመኘታችን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መሥራት፣ መትጋት፣ መታገል ይጠበቅብናል፡፡ በመጀመሪያ ሥራችን ልናደርገው የሚገባንና ትግላችን ማተኮር ያለበት ራሳችን ላይ ነው፡፡

አመለካከቻችንን ከጥላቻ፣ ከቂም በቀል ስሜትና ከዘረኝነት ማጽዳት ይገባናል፡፡ በብሔር፣ በጾታ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኃይማኖት… ወዘተ ያሉንን ልዩነቶች እንደ በረከትነታቸው በፍቅር በማስተናገድ ከልዩነቶቹ የሚነሳ አለመግባባት ቢኖር እንኳ ከፍትህ እንጂ ከበደል ጋር ባለመተባበር ሞራላዊ እይታዎቻችንን ልናስተካክል ይገባል፡፡ ፍትህ ዋናው መርሃችን ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርና ክብር የሞራል መልህቃችን ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሰርተን የማናገባድደው፣ ሁሌም ልፋት፣ ትግል የሚጠይቅ የእድሜ ዘመን ሁሉ የቤት ሥራ ነው፡፡

ሀገራችን በአሁሉ ወቅት ለደረሰችበት ምእራፍ በርካታ ትውልዶች መስዋእት ሆነዋል፡፡ አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን እውን እንዲሆንም አእላፎች ተሰውተዋል፡፡

ታዳጊውን ዴሞክራሲያችንን ለማዳበር ግን ተጨማሪ የህይወትም ሆነ የአካል መስዋእትነት አያስፈልገንም፡፡ ባለፉት ዓመታት እንደመንግሥትም እንደ ዜጎችም ከዴሞክራሲ ባህላችን አለመዳበር ጋር ተያይዞ በታዩብን እጥረቶች በዜጎቻችን ህይወት እና በግልም በጋራም ንብረቶቻችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሳል፡፡ ይህንን ሁላችንም ማስቀረት እንችልና ይገባንም ነበር፡፡

በተለያየ ጊዜ፣ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኛች፤ በቅጡ ሳይቦርቁ ህይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለስነልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ እንዲሁም ሰላም ለማስከበርና ህገመንግሥታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ህይወታቸውን ላጡ የፀጥታ ኃይሎች አባላት ለከፈሉት መስዋእትነት ያለኝን አድናቆትና አክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ህዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ክቡራን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፡-

ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግስት በኩል ጽኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ ስለሰላምና ፍትህ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

የሀገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ በሁሉም ደረጃ የምትገኙ የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ በገጠርም ሆነም በከተማ የምትገኙ የተለያየ ሞያ ባለቤቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ ዋቄፈታዎች እንዲሁም ሌሎች ኃይማኖቶችን የምትከተሉ ወገኖች፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምእራብ የምትገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ሁላችንም የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንረባረብ! አገራችንን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት እንትጋ! ዘረኝነትና መከፋፈልን ከአገራችን እናጥፋ! የተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!

የዛሬው እለት በአኩሪ ኢትዮጵያዊ ወኔ የተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሰባተኛ ዓመት ነው፡፡ በዚህ ግድብ ግንባታ የታየው አንድነት እና መሰባሰብ የሀገራችንን ችግሮች በሙሉ መቅረፍ እና መሻገር እንደምንችል ያረጋገጠልን በመሆኑ ይህንኑ መንፈስ ይዘን ከግድቡ መጠናቀቅ ባሻገር የሀገራችንን ብልጽግና እስከምናረጋግጥበት ከፍታ ድረስ እንድንዘልቅ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በመጨረሻም በዚህ ወቅት ሀገሬን እና ህዝቤን ለማገልገል ይህንን ከባድ ኃላፊነት ስቀበል አመሰግናቸው ዘንድ የሚገቡኝን አካሎች እንዳመሰግን ትፈቅዱልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ፤

በመጀመሪያ ለዚህ ኃላፊነት የመረጡኝና እምነት የጣሉብኝ ድርጅቴ ኢህአዴግን እና የአገሬን ህዝብ በተለየ አክብሮት እና ፍቅር አመሰግናለሁ፡፡ ሁለተኛ የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ እንዲህ ከፊታችሁ እንደምቆም የምታውቅ እና ይህንን ሩቅ ጥልቅ እና ረቂቅ ራእይ በውስጤ የተከለች፣ ያሳደገች እና ለፍሬ ያበቃች አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት እንዳመሰግን በትህትና እጠይቃለሁ….. ይህች ሴት እምዬ ናት፤ እናቴ ከሌሎቹ ቅን የዋህ እና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን እንደ አንዶቹ የምትቆጠር ናትና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ሳይሆን አለማዊ እውቀትም የላትም፡፡ በእናቴ ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋ እና ምሥጋና እንደመስጠት በመቁጠር ዛሬ በህይወት ካጠገቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ ከዐፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በብዙ ክብር ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶቼ በልጆቻቸው የነገ ራእይ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ ነገ ለሚያጥዱት መልካም ፍሬ ዛሬ ላይ የሚዘሩት ዘር ዋና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለሚከፍሉት መስዋእትነት ያለኝን በምንም የማይተካ አድናቆት ምስጋና እና ክብር በብዙ ልባዊ ፍቅር ሳቀርብ በቀጣይም ልጆቻችን የዚህች ሀገር ህዳሴ እንዲረጋገጥ ዋና ተዋንያን መሆን እንዲችሉ እናታዊ አይተኬ ሚናችሁን እንድትወጡ አደራ በማለትም ጭምር ነው፡፡

ሦስተኛ የሚስቶች ስኬት ሁለት-ሦስት ነው፡፡ ሁለት ሲሆን፣ አንዱ የራሳቸው ሌላው የባላቸው፡፡ ሦስት ሲሆን ደግሞ የልጆቻቸውም ይጨመርበታል፡፡ አንዳንዴ ድል ስኬታቸው ከዚህም ይሻገራል፡፡ የእናቴን ራእይ ተረክባ በብዙው የደገፈችኝና የእናቴ ምትክ የሆነችልኝ ውዷ ባለቤቴ ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ከነዚህ ሚስቶች ተርታ ትመደባለችና እጅግ አድርጌ ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም ከትግል ጓዶቼ እና በዝለት ብርታት፤ በድካም ጊዜ ኃይል ከሆኑኝ የቅርብ-የሩቅ ወዳጆቼ ውጪ ዛሬ እኔ ከፊታችሁ መቆም ባልቻልኩ ነበር፤ ለሁላችሁም ከልብ የመነጨ ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡

“ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
አመሰግናለሁ!!

Saturday, 31 March 2018

“ይህንን ሁሉ የምታደርጉት ሀገራችሁን ስለምትወዱ ከሆነ ሀገራችሁን ባትወድዱ ኖሮስ ከዚህ የከፋ ምንታደርጉ ነበር?”

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት



ሰውዬው የውጭ ሀገር ዜጋ ቢሆኑም ዐሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አስተምረዋል፡፡ ሚስተር ዣክ ይባላሉ፡፡
ሻሂ እየጠጡ ኢትዮጵያዊውን ጓደኛቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ ሁለት ጊዜ ፉት እንዳሉት ጓደኛቸው ከች አለ፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የተጠለፈበት ቆብ አድርጓል፡፡ በለመዱት የኢትዮጵያውያን ባህል መሠረት ከመቀመጫቸው ተነሥተው ተቀበሉት፡፡
ወንበር ስቦ እንደ ተቀመጠ ያጠለቀውን ቆብ ጠረጲዛው ላይ አኖረው፡፡
ሚስተር ዣክ የተቀመጠውን በኢትዮጵያ ባንዴራ የተጠለፈ ቆብ አየት አደረጉና «እናንተ ኢትዮጵያውያን ለምንድን ነው በባንዴራችሁ ማጌጥ የምትወዱት?» አሉና ኢትዮጵያዊውን እንግዳቸውን ጠየቁት፡፡
«እኛ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን እንወዳለን፡፡ በሀገራችን ለመጣ ርኅራኄ የለንም፡ ይህ የሀገር ፍቅር በደማችን ውስጥ አራተኛ ሴል ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ለዚህ ነው» አላቸው፡፡
«ቆይ ግን ሀገራችንን እንወዳለን ስትሉ ምን ማለት ነው? ወንዙ እና ተራራው ነው? ሜዳው እና ጫካው ነው? ምኑ ነው ሀገር?»
ኢትዮጵያዊው ትኩር ብሎ እያያቸው «ሁለመናው ነው፡፡ ሰው፣ እንስሳው፣ ሜዳው፣ተራራው፣ ጫካው፣ ወንዙ፣ ሁሉም» አለና መለሰላቸው፡፡
«እኔ ግን አይመስለኝም» አሉት ሚስተር ዣክ፡፡
«እንዴት?» ተገርሞ ጠየቃቸው፡፡
«እናንተ ለሀገራችሁ የድመት ፍቅር ይመስለኛል ያላችሁ»
«የድመት ፍቅር ምን ዓይነት ነው» እንግዳው ተገርሞ እንደገና ጠየቀ፡፡
«ቤት ያከራዩኝ ሰውዬ ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ፡፡ ድመት ልጆቿን የምትበላው ስለምትወዳቸው ነው፡፡ ፍቅሯን የምትገልጠው ልጆቿን በመብላት እና ለዘላለም ሆዷ ውስጥ በማድረግ ነው አሉኝ»
«እና»
«እናማ እናንተም ለሀገራችሁ ያላችሁን ፍቅር የምትገልጡት ሀገራችሁን በመብላት ይመስለኛል»
«ያንን ያህል እንደርሳለን ብለው ነው» አንገቱን ወዘወዘ እንግዳው፡፡
«ኧረ እንዲያውም ሳይብስ አይቀርም፡፡ አሁን ለምሳሌ እናንተ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ገዥዎች ለመገዛታችሁ ስትኮሩበት አያለሁ፡፡ ልክ ነው ለጀግኖች አባቶቻችሁ ምስጋና ይግባቸውና ለዚህ የታሪክ ዕድል አብቅተዋችኋል፡፡
የሦስት ሺ ዘመን የነጻነት ታሪክ አለን እያላችሁ በኛ በአፍሪካውያን ላይ ትኮሩብናላችሁ እንጂ በሦስት ሺ ዘመን ምን ሊሠራበት እንደሚችል አላሳያችሁንም፡፡
ነጻነትን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል አሳያችሁን እንጂ በነጻነት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል አርአያ ልትሆኑን አልቻ ላችሁም፡፡
እርስ በርስ ስትዋጉ፣ አንዳችሁ የሠራችሁትን ሌላችሁ ስታጠፉ፣ መቶ ዓመት የለፋቸሁበትን በአንድ ቀን ደምስሳችሁ እንደገና ስትጀምሩ ነው የኖራችሁት፡፡ እስቲ ተመልከቱት የሦስት ሺ ዘመን ታሪክ አለን ነውኮ የምትሉት፡፡
ታድያ ሦስት ሺ ዘመን ተጉዛችሁ እዚህ መድረስ ብቻ ነው የቻላችሁት? አቆጣጠራችሁ ግን በምንድን ነው? አንድ ዓመትስ በእናንተ ዘንድ ስንት ቀን ነው?
«ለመሆኑ ሀገራችሁን ስለምትወዱ ነው እርስ በርስ ስትዋጉ የኖራችሁት? ሀገራችሁን ስለምትወዱ ነው የቀደመውን እያፈረሳችሁ እንደ አዲስ የምትጀምሩት? ወንዙን ሰው ሲነካባችሁ ዘራፍ ብላችሁ ትነሣላችሁ፤ እናንተ ግን ወንዙን አትጠቀሙበትም፡፡
መሬቱን ሰው ሊቆርስ ሲመጣ አራስ ነብር ሆናችሁ ትነሣላችሁ፤ እናንተ ግን መሬቱን አታለሙትም፡፡ ቅርሳችሁን ሰው ሊዘርፍ ሲመጣ የቻለ ይዘምታል ያልቻለ ያቅራራል፤ እናን ተም ግን ቅርሱን አትጠብቁትም፡፡
አሁን ይሄ ምቀኝነት ነው ወይስ ሀገር መውደድ ነው?»
ኢትዮጵያዊው እንግዳ ያልጠበቀው ነገር ስለመጣበት ትክዝ እንደማለት አለና «በርግጥ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ዋልጌዎች የሚሠሩት ሥራ ግን መላውን ሕዝብ መወከል የለበትም» አላቸው፡፡
«ልክ ነህ» አሉ ሚስተር ዣክ «ልክ ነህ ጥቂቶች ሁሉንም አይወክሉም፡፡ የማየው ነገር ግን ይህንን አባባልህን እንዳልቀበለው ያስገድደኛል፡፡
ተመልከት ቅቤው ውስጥ ሙዝ እየጨመረ የሚሸጠውኮ የራሳችሁ ሰው ነው፡፡ ለውጭ ሀገር አይደለም የሚሸጠው ለገዛ ጎረቤቱ ነው፡፡
ሂድ እስኪ በየሱቁ ስንት ጊዜው ያለፈበት የታሸገ ምግብ ይሸጣልኮ፡፡ ገዥው የሌላ ሀገር ሰው አይደለም፡፡ የራሳችሁ ወገን ነው፡፡ ያደረ ኬክ፣ ያደረ ምግብ፣ የተበላሸ ሥጋ የምትሸጡትኮ ለጠላት ሀገር አይደለም ለራሳችሁ ሰው ነው፡፡
አሁን እነዚህ ሰዎች ሀገራችንን እንወድዳለን ብለው ግሥላ ሲሆኑ ባይ ይገርመኛል፡፡ ወገናቸውን እየገደሉ ምኑን ነው የሚወድዱት እላለሁ፡፡
አሥር ብር የገዛችሁትን ዕቃ አንዳች እሴት ሳትጨምሩበት በገዛ ወገናችሁ ላይ መቶ ብር አትርፋችሁ ያለ ርኅራኄ እየሸጣችሁ ሀገራችሁን ትወድዳላችሁ ማለት ነው?» «መሬቱን ብቻ ነው እንዴ ሀገር የሚሉት?
በአንድ መንደር ውስጥ የሚገኝ መሸታ ቤት መንደርተኛውን እየበጠበጠ ስላስቸገረ የቀበሌ ጥበቃዎች መጡና ድምጽ ቀንሱ አሏቸው፡፡
እነርሱም እሺ አሉና የሚገርም ዘፈን ከፈቱ አሉ፡፡»
«ምን የሚል?»
«እኛም አንተኛ ሰውም አናስተኛ የሚል»
«ሆሆይ! ይህቺን አገር አገላብጠው ነውኮ የሚያውቋት» አለ እንግዳው ተደንቆ፡፡
«ሂድና ሠራተኛውን እየው፡፡ ሌላ ትርፍ ሀገር ያለው፣ በቅኝ ገዥዎች ተገድዶ የሚሠራ ነውኮ የሚመስለው፡፡
አንዳንዱ ዘግይቶ ይገባል፣ አንዲት ነገር ሳይሠራ ለሻሂ ይወጣል፤ እጁን ወደ ኋላ አጣምሮ እየተዝናና ቢሮ ይመለሳል፣ አንዲት ነገር ሳይሠራ ለምሳ ይወጣል፡፡
አንድ ነገር ከጠየቅከው «ነገ፣ ነገ» ነው የሚለው፡: ነገ መቼ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ግንባታዎቻችሁ ለጠላት ሀገር የሚሠሩ እንጂ እንወድዳታለን ለምትሏት ሀገር የሚሠሩ አይመስሉም፡፡
የሚጀመሩበትን እንጂ ግንባታው የሚያልቅበትን ጊዜ ማንም አያውቅም፡፡ ተሠርቶ ሳይመረቅ ይፈራርሳል፡፡ ከሚሠራበት ገንዘብ የሚበላው ይበልጣል፡፡
ሠራተኛው ምድጃ ከብቦም ተረት ያወራል፣ አካፋ ተደግፎም ሥራ ላይ ተረት ያወራል፡፡ «ለመሆኑ እነዚያ የዚህ ሁሉ ግንባታ ሠሪዎቹ፣ አሠሪዎቹ፣ ተቆጣጣሪዎቹ አሁን አንተ እንደምትለኝ ሀገራቸውን ይወዳሉ ማለት ነው?
የትኛዋን ሀገር ነው የሚወድዱት? ወይስ እኛ የማናውቃት ሌላ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለቻችሁ? ቻይናዎቹ ያሉትን ሰምተሃል?»
«ምን አሉ?»
«መንገድ ሲሠሩ፣ እነርሱ ቀን ቀን የሠሩትን እና የሰበሰቡትን የአካባቢው ሰው ሌሊት ሌሊት አፍርሶ እና አግዞ እየወሰደ አስቸገራቸው፡፡
በኋላ እንደ እኔው ሀገራችሁን ትወዳላችሁ ሲባል ሰምተው ስለነበር «ቆይ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሌላ ሀገር አላቸው እንዴ? ከሀገራቸው ሰርቀው የት ነው የሚወስዱት?» አሉ ይባላል» «አሁን አሁንኮ ትውልዱ ጉዳዩን እያስተዋለ እየተለወጠ ነው፡፡
ምናልባት ቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር ሊኖር ይችላል» አለ ኢትዮጵያዊው እንግዳ፡፡
«የለም የለም እንዲያውም ብሷል፡፡ አዲሱ ትውልድ የምትለው የሚገኘውኮ እኔ በማስተምርበት ኮሌጅ ነው፡፡ አየሁትኮ፡፡
ቤተ መጻሕፍት ገብቶ በድኻ ሀገር በጀት የታተመ መጽሐፍ የሚሰርቅ፣ የሚቀዳድድ፣ እላዩ ላይ ትርኪ ምርኪ ነገር የሚጽፍ ይህ ነው ሀገር ወዳዱ ትውልድ?
ከእርሱ ቀጥሎ እዚህ ትምህርት ቤት የሚማረው የራሱ ወንድም እና እኅት መሆኑን እንኳን የሚረሳው ነው ሀገር ወዳዱ? ከዕውቀት ክርክር ይልቅ በጎጠኛነት ተቧድኖ መደባደብ የሚቀናው ነው ሀገር ወዳዱ ትውልድ?
ነገሩ ምን ያድርግ የሚያስተምሩትም ቢሆኑኮ የሀገራቸውን ሰው የሚያስተምሩ፣ እንወዳታለን ለሚሏት ሀገር ትውልድ ሊያፈሩ የሚያስተምሩ አይመስሉም፡፡
የዛሬ ሃያ ዓመት ባዘጋጁት ማስታወሻ እያስተማሩት፣ ከቤተ መጻሕፍት አውጥተው ቢሮአቸው የደበቁትን መጽሐፍ ማጣቀሻ እየሰጡ ጥናት እያዘዙት ምን ያድርግ፡፡
በገጠሩ ሴት ልጅ በልጅነቷ ተጫውታ ሳትጨርስ ትዳርና በልጅነቷ ትወልዳለች፡፡ እርሷም ልጅ፣ የወለደችውም ልጅ ይሆንባትና አብረው እየተጫወቱ ያድጋሉ፡፡ አሁንም ኮሌጃችሁን እንደዚያው አደረጋችሁትኮ፡፡
«አሁን በየሕክምና ቦታው የሚሠራው የድሮው ትውልድ ነው ልትለኝ ነው? ለመሆኑ እርሱ ሀገር ወዳድ ነው?
ጊዜ ባለፈበት መድኃኒት ወገኑን የሚያክመው፣ በመንግሥት በጀት የተገዛ መድኃኒት አውጥቶ የሚሸጠው፣ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሌለ ምርመራ እያዘዘ ድኻው ተማርሮ ከሕክምና ይልቅ ወደ ዳማ ከሴ እንዲጓዝ ያደረገው ሀገሩን ስለሚወድድ ነው? «እስቲ የመኪና ምርመራ እንዴት እንደሚደረግ ተመልከት፡፡
መኪናው ሳይታይ በስልክ እኮ ነው የሚመረመረው፡፡ ለመሆኑ መርማሪው ሰውዬ ይሄ መኪና እርሱን፣ ቤተሰቡን፣ ዘመዶቹን እንደማይገጭ ርግጠኛ ነው?
ሀገሩን ስለሚወድ ነው ሕዝብ እንዲያልቅ ፈቅዶ የተበላሸ መኪና ጤነኛ ነው ብሎ የሚፈርመው? «በአንድ ወቅት አዲስ አበባ መንገዶቿን ሰየመች ተብሎ በየቦታው ተለጠፈ፡፡
ሦስት ወር አልሞላውም ሲወድቅ እና ሲጠፋ፡፡ ማን ዘረፈው? ሀገር ወዳዱ፡፡ ተካዮቹስ ቢሆኑ ለምን ዘወር ብለው አላዩትም? ሀገር ወዳድ ስለሆኑ፡፡
«እኔ ሀገር የመውደድን ጉዳይ አሁን እርስዎ ባሰቡበት መንገድ አስቤው አላውቅም፡፡ ብቻ እኛ የሀገራችን ጉ
ዳይ ሲነሣ ደመ ቁጡዎች፣ አትንኩን ባዮች እና ኮስታሮች መሆናችንን አውቃለሁ፡፡» አለ ኢትዮጵያዊው እንግዳ፡፡
«ልክ ነህ ይህንንማ ዓለም በሙሉ ይመሰክርላችኋልኮ፡፡ ይህች ሀገርኮ ዝም ብላ እንዲሁ በነጻነት አልኖረችም፡፡ አንዳች ልዩ ነገርማ አላችሁኮ፡፡ ሀገራቸውን ባይወድዱ ኖሮ አባቶቻችሁ ደማቸውን ባልገበሩ ነበር፡፡
አጥንታቸውን ከስክሰው ድንበር ባላጠሩ ነበር፡፡ ዘመናዊ መሣርያ የታጠቁትን በባህላዊ መሣርያ ባላሸነፉ ነበር፡፡
ግን ሀገር መውደድ ይሄ ብቻ ነወይ) ሌላ አይንካን እኛ ግን እንደፈለግን እንጫረስ፣ ሌላ አይዝረፈን እኛ ግን እንዘራረፍ፣ ሌላ አይጨቁነን እኛ ግን እንጨቋቆን፣ ቅኝ ገዥ መጥቶ ቀንበር የሆነ ሕግ አያውጣብን እኛ ግን እርስ በርሳችን ቀንበር እንጫጫን፣ ጠላት ወርሮ መብታችንን አይንካ፣
እኛ ግን መብታችንን እርስ በርስ እንገፋፈፍ ነው የምትሉት) ይሄኮ ነው ያልገባኝ ነገር፡፡ ሀገር ማለትኮ መልክዐ ምድሩ ብቻ አይደለም፤ ይሄ ባለጉዳይ ሆኖ ቢሮህ የመጣው፣ታምሞ ሊታከም አንተጋ የመጣው፣ሊማር አንተ ጋ የመጣው፣ሊገዛ ሱቅህ ጋ የቆመው፣ በሞያህ እያገለገልከው ያለኸው፣በመኪናህ ላይ የተሳፈረው፣ እርሱኮ ነው ሀገር» አሉ ሚስተር ዣክ፡፡
«እንዴ ሚስተር ዣክ በዐሥረኛው ዓመት ሀገራችን መረረዎት መሰለኝ፡፡ እርስዎም እንደኛው ደመ ቁጡ ሊሆኑ ነው ማለት ነው፤ባለፈው ታምመው ተኝተው እያለ የኢትዮጵያዊ ደም ነበር እንዴ የተደረገልዎ» አለ ኢትዮጵያዊው ነገሩን ወደ ቀልድ ወስዶ ሀሳብ ለማስቀየር፡፡
«አየህ ይህች ሀገር ይበልጥ ስታውቃት ይበልጥ የምታሳዝን፣ ይበልጥ የምታስቆጭ፣ ይበልጥ የምታንገበግብ ናት፡፡
ቆይ ግን ህንን ሁሉ የምታደርጉት ሀገራችሁን ስለምትወዱ ከሆነ ሀገራችሁን ባትወድዱ ኖሮስ ከዚህ የከፋ ምንታደርጉ ነበር? አንድ እዚህ ሀገር የሰማሁት ቀልድ ነገር አለ፡፡
አንድ ባል ሚስቱን ይደበድባታል፡፡ እርሷም ቤቷን ትታ ትወጣለች፡፡
በኋላ ሽማግሌ ገብቶ ታረቁ ይላቸዋል፡፡ ባልም እኔኮ ስለምወዳት ነው የመታኋት፣ የፍቅር ነው ይላል፡፡ ሚስቲቱም ስትወደኝ ከሆነ እንዲህ የምትመታኝ ስትጠላኝ ምን ልታደርግ ነው? አለችው አሉ፡፡
አሁንም እናንተ በሀገራችሁ ላይ ራሳችሁ ይህንን ሁሉ ግፍ የምትፈጽሙት ሀገር ወዳድ ስለሆናችሁ ከሆነ ብትጠሏት ኖሮ ምን ልታደርጉ ነበር?