Thursday, 5 July 2018

የሃይማኖት አባቶች ተጣልተው ፖለቲከኞች ታረቁ እያሏቸው ነው

ምላጩ አብጦ ውኃው አንቆ

‹ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል፣ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡታል› ይላል የሀገሬ ሰው፡፡ የኢትዮጵያም አንዱ ችግሯ ይኼ ነው፡፡ የምላጭ ማበጥና የውኃ ማነቅ፡፡ የተጣሉትን አስታራቂ፣ የተለያዩትን አንድ አድራጊ መሆን የነበረባቸው የሃይማኖት አባቶች ተጣልተው ፖለቲከኞች ታረቁ እያሏቸው ነው፡፡ ለፍትሕ ዘብ ቆመው፣ ደኻ አንዳይበደል ፍርድ እንዳይጓደል ማድረግ የነበረባቸው የዳኝነት አካላት ዜጎች እንዲበደሉ፣ የፍርድ ሚዛን እንዲያዘነብል፣ ግፈኞች በሕግ ስም የፈለጉትን እንዲያደርጉ መሣሪያ ሆነዋል፡፡ ዜጎችን በሕግ ጥላ ሥር ለማረም የተዘጋጁ ማረሚያ ቤቶች የሰዎች ‹ቄራ› ሆነዋል፡፡ የዜጎችን ችግር ለመፍታት የተቋቋሙ የ‹ኢሚግሬሽን› ቢሮዎች የዜጎች ማኘኪያ› ሆነዋል፡፡ 

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ከአውሮፓና ከእስያ የመጡ ስደተኞችን እየተቀበለ ከዜጋውም በላይ ክብርና ፍቅር ሲሰጥ የኖረ ማኅበረሰብ የገዛ ወገኑን ‹ውጣልኝ፣ ሂድልኝ፣ አልይህ፣ አልስማህ› ይላል፡፡ ከሺ ዓመታት በላይ የነጻነት ታሪክ የሚቆጥር ሕዝብ አሁንም ‹ነጻ አውጭ ድርጅት› ይመሠርታል፡፡ የእርሱን ሰንደቅ ዓላማ የነጻነት ዓርማ አድርጎ ለጥቁር ሕዝብ የሰጠ ሕዝብ እንደገና በሰንደቅ ዓላማ ላይ ይከራከራል፡፡ አፍሪካ ተከፋፍላ መነጋገርና መገናኘት ባቃታት ጊዜ ምዕራብና ምሥራቅ ዞሮ የአፍሪካን አንድነት ያመጣ ሕዝብ እርሱ ራሱ ተከፋፍሎ መከራውን ያያል፡፡ እነ እገሌ ‹እኛ ታግለን ባመጣነው ለውጥ እኛው መጠቀም አለብን› አሉ እያለ ሲያማርር የኖረ ወገን እርሱ ታግሎ ሌላ ለውጥ ያመጣ ሲመስለው፣ እርሱም በተራው ‹እኛ ታግለን ባመጣነው ለውጥ ሌላ ተጠቀመበት› እያለ ያላዝናል፡፡ አስገራሚ ነው መቼም፡፡
ውኃ አንቆ ምላጭ አብጦ መከራችን እናያለን፡፡

Daniel Kibert

Tuesday, 3 July 2018

ጊዜ ጠባቂ ቦንብ

Daniel Kibert

አንድን ሕዝብ ወይም ማኅበረሰብ በተመለከተ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚደረጉ አሉታዊ የገጽታ ግንባታዎች ውጤታቸው ከሚታሰበውም የከፋ ነው፡፡ በዓለም ላይ አደጋ ላይ የወደቁ ማኅበረሰቦችን ታሪክ ስንመለከት ከሁለት ወገን የመጡ አካላት የቆሰቆሱት እሳት ያስከተለውን ረመጥ እናይባቸዋለን፡፡ አንደኛው እነርሱን ከሚወደው ወገን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከሚጠላቸው ወገን ነው፡፡

የተጠቂው ወገን ነኝ የሚለው አካል ያልተሰጠውን ውክልና እየወሰደ የሚፈጽማቸው ተግባራትና የሚያቀርባቸው ሐሳቦች በተቃራኒ ሆነው ነገሩን ለሚቆሰቁሱት ቢላዋ ያቀብላል፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ልዩ ተጠቃሚዎች ሚሊዮኖችን ወክለው ለመታየት ይጥራሉ፡፡ እፍኝ የማይሞሉ አቀንቃኞች የማኅበረሰቡ አፈ ጉባኤ አድርገው ራሳቸውን እየሾሙ የሚናገሯቸው ንግግሮች የዚያ ማኅበረሰብ አቋም መስለው እንዲታዩ ይተጋሉ፡፡

በአንድ ማኅበረሰብ ስም ጥቅም የሚያገኙ አካላት በየዘመናቱ ይፈጠራሉ፡፡ በክርስትናና በእስልምና ስም በተፈጸሙ ወረራዎች፣ ዝርፊያዎች፣ ቅኝ ግዛቶች፣ ጦርነቶችና ጭቆናዎች ተጠቃሚዎቹ አማንያኑ አይደሉም፡፡ ተጠቃሚዎቹ በእምነቱና በአማንያኑ ስም የሚነግዱት አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት እምነቱንም ሆነ አማንያኑን የሚፈልጓቸው ለሁለት ነገር ነው፡፡ ለምክንያትነትና ለከለላነት፡፡ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው ግለሰባዊ ስግብግብነትና የሥልጣን ጥመኝነት ላስከተለው ክፉ ተግባር የተቀደሰው ሃይማኖት ምክንያት እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዘራፊዎቹና ገዳዮቹ እንዳይነኩ እምነቱን ለሽፋንነት ይፈልጉታል፡፡ እነርሱን መንካት እምነቱን መንካት ተደርጎ እንዲወሰድ፡፡ በዘር ከለላ ተከልለው የሚበዘብዙና የሚጨቁኑ ሰዎችም ይሄው ነው መንገዳቸው፡፡  

በአንድ ማኅበረሰብ ስም የሚነግዱት አካላት በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚፈጥሩት የተበላሸ ሥዕልም አለ፡፡ የእነርሱ መጠቀምና ክብር፣ ሥልጣን ማግኘትና መግዛት የማኅበረሰቡ ተደርጎ እንዲወሰድ ያደርጉታል፡፡ በተለይ ደግሞ ግልጽነትና ጠያቂነት ባልዳበረበት ማኅበረሰብ ውስጥ እገሌ እና እገሊት፣ ይሄና ያ፣ እንዲህና እንዲያ ሁሉንም የሚገልጡ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለጅምላ ፍረጃ ያጋልጣል፡፡ አበበ ተጠቀመ ማለት አበበ የተገኘበት ማኅበረሰብም ተጠቀመ ማለት ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡ አበበም እንደዚያ እንዲሆንለት ይፈልጋል፡፡

 ከዚህ ባሻገር ደግሞ ዐውቀውና ሳያውቁት ሌላውን ማኅበረሰብ የማጥላላት፣ የማናናቅና የመፈረጅ ዘመቻ የሚያደርጉም አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግለሰብን ከማኅበረሰብ መለየት ያቃታቸው ናቸው፡፡ አንድ በሬ ከወጋቸው በሬዎችን ሁሉ የሚጠሉና ሊያርዱ የሚነሡ ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ምንጊዜም የሚጠቀሰው በአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰው ነው፡፡ ምንም እንኳን ክርስቶስን የተቃወሙት፣ ያስፈረዱበትና የሰቀሉት ከአይሁድ ወገን የተገኙ ባለ ሥልጣናትና ጥቅመኞች ቢሆኑም፣ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያትና ክርስቲያኖችም ከአይሁድ ወገን የተገኙ ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ በየዘመናቱ የተገለጠው ግን ስለ ሰቃዮቹ አይሁድ እንጂ ስለ ክርስቲያኖቹ አይሁድ አልነበረም፡፡ በጅምላ ‹አይሁድ ይህንን አደረጉ› እየተባለ የተነገረው ነገር ከ40 ሚሊዮን በላይ አይሁድ ያለቁበትን ጥፋት በየዘመናቱ አምጥቷል፡፡

በዘመነ ክርስቶስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አይሁድ እንደነበሩ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ይናገራል፡፡ ከእነዚህ መካከል ግን በክርስቶስ መከራና ሞት የተሳተፉት ከአምስት ሺ አይበልጡም፡፡ መከራው ግን ለሁሉም ተረፈ፡፡

በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ በየቀልዶቻችንና በየዘፈኖቻችን የምናስተላልፈው አንድን ወገን የማስጠላትና የማክፋፋት ዘመቻ ማጣፊያው የሚያጥር ነው፡፡ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ የሚቀመጡት እነርሱ ናቸው፡፡ ልጆቻችን ስለዚያኛው ማኅበረሰብ የሚኖራቸውን አመለካከት የሚቀርጹት በነዚህ ጽሑፎች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነው፡፡ በሀገራችን አንድን ማኅበረሰብ የሚያጥላሉ ዘፈኖች ቦታ እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡፡ አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያጠቁ የፕሮፓጋንዳ ቃላት ተፈጥረዋል፤ አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያሸማቅቁ መግለጫዎች በባለሥልጣናት ደረጃ ተሰጥተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሌሎቹ ጋር እየተደመሩ የተጠቂነት ስሜት የሚሰማው፣ራሱን ወደመከላከል የሚገባ፣ሕልውናው አደጋ ላይ መድረሱን ያመነ ማኅበረሰብ ፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ያለው ማኅበረሰብ ሲፈጠር ደግሞ ከድልድይ ይልቅ ግንብ እየገነባ ከሌላው ጋር መራራቅንና መከለልን ይመርጣል፡፡

በአውሮፓ ከ16ኛው መክዘ በኋላ ለተስፋፋው የፀረ ሴማዊነት ስሜት የታላቁ ጸሐፌ ተውኔት የሼክስፒር ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር አስተዋጽዖ ማድረጉ ይነገራል፡፡ የቬነሱ ነጋዴ ዋና ገጸ ባሕርይ ሻይሎክ የተባለ ገብጋባ ይሁዲ ነው፡፡ ሻይሎክ የዕብራይስጥ ስም አይደለም፡፡ ነገር ግን ‹ሳላን› ከተሰኘውና የሴም የልጅ ልጅ፣ የዔቦር አባት ከሆነው ሰው ስም የተቀዳ መሆኑ ይታመናል፡፡ የሻይሎክ ገብጋባነትና ጭካኔ ለከት የለውም፡፡ ከእርሱ ገንዘብ የተበደረው ክርስቲያኑ አንቶኒዮ መክፈል ቢያቅተው መያዣው ከአንቶኒዮ ሰውነት የሚቆረጥ አንድ ሙዳ ሥጋ ነው፡፡ አንቶኒዮ ብድሩን መክፈል አቃተው፡፡ ሻይሎክም ሙዳ ሥጋውን ከአንቶኒዮ ሰውነት ቆርጦ ለመውሰድ ተነሣ፡፡

ሼክስፒር ይህንን ድራማ የጻፈበት የኤልሳቤጥ ዘመን(Elizabethan Era – 1558-1605) የሚባለው ጊዜ እንግሊዞች በፀረ ሴማዊነት የተለከፉበት ዘመን ነበር፡፡ ከ1290 ጀምረው ከእንግሊዝ የተባረሩት አይሁድ ወደ እንግሊዝ ለመግባት አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ የድራማው መቼት በሆነው ቬነስ ደግሞ አይሁድ ይጠላሉ፤ ለጥቃት የሚያጋልጥ የተለየ የመለያ ልብስ እንዲለብሱ ይገደዳሉ፡፡ በሼክስፒር ዘመን የነበሩ ድርሰቶች፣ ቀልዶች፣ ሥዕሎችና ድራማዎች አይሁድን ገብጋቦች፣ ክፉዎችና አጭበርባሪዎች አድርገው የሚስሉ ነበሩ፡፡ የሼክስፒርን ድርሰቶች ያጠኑ ሊቃውንትም ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር ‹የቬነሱ ይሁዲ› እየተባለ ይጠራ እንደነበር ይገልጣሉ፡፡ ይህም ክሪስቶፈር ማርሎዊ ከደረሰው ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ጋር ያመሳስለዋል፡፡ በ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ውስጥ የሚገኘው ይሁዲው ባራባስ እንደ ሻይሎክ ክፉ ነው፡፡ የቬነሱ ነጋዴ የሚያልቀው ሻይሎክ ወደ ክርስትና ሲመለስ ነው፡፡

ይህ በሼክስፒር ድርስት ውስጥ የተሳለው ይሁዲ ገጸ ባሕርይ አይሁድ ቀድሞ ከተሳሉበት ገጽታ ጋር ተደምሮ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታዩበትን መነጽር አበላሸው፡፡ ስለ እነርሱ ክፉ መናገር፣ መጻፍና መቀለድ የተፈቀደ መሰለ፡፡ ለእነርሱ የሚከራከርም ጠፋ፡፡ በኋላ ዘመን በአይሁድ ላይ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ያመጡት እነዚህን የመሰሉ ድርሰቶች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነበሩ፡፡ 

ዛሬም እኛ ኢትዮጵያውያን ከሁለቱም ወገን ልንርቅ ይገባናል፡፡ የሌላችሁን የማኅበረሰብ ውክልና ለሥልጣናችሁ፣ ጥቅማችሁና ለክብራችሁ ስትሉ የምታቀነቅኑ ተቆጠቡ፡፡ ማንም አልወከላችሁም፡፡ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤትም ይህንን አያረጋግጥላችሁም፡፡ ሕዝቡ ያላለውን በሕዝብ ስም አትናገሩ፡፡ እናንተ ስትጠግቡ ሕዝቡ እንደጠገበ አታስመስሉት፤ እናንተ ሲያማችሁም ሕዝቡ እንደታመመ አታስቃስቱት፡፡ እናንተ ስትራቡ ሕዝብ የተራበ አድርጋችሁ አትሳሉት፤ ዕዳችሁን ብቻችሁን ውሰዱ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ስለ አንድ ሕዝብ በጅምላ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች፣ ቀልዶች፣ ጽሑፎች፣ ዘፈኖች፣ ግለሰቦችን ጠቅመው ሕዝብን ይጎዳሉ፡፡ ይበልጥ ደግሞ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ ተቀርጸው እንደ ጊዜ ጠባቂ ቦንብ ይቀመጣሉ፡፡ ለሕዝብ ሲባል ግለሰቦችን መተው እንጂ ለግለሰቦች ሲባል ሕዝብን ማጥፋት ሕጋዊም ሞራላዊም አይደለም፡፡ 

Wednesday, 6 June 2018

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንበሮች | በዲ/ን ዳንኤል ክብረት ስለ ዶ/ር አብይ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጠዋት ወደ ቢሯቸው ማልደው ሲገቡ የእንግዳ መቀበያ ክፍሉ ወንበሮች ተሰልፈው ጠበቋቸው፡፡ ነገሩ እንግዳ ሆነባቸው፡፡ የዚህን ቤተ መንግሥት ባሕል ገና አልለመዱትም፡፡ የተለመዱ ችግሮችን ባልተለመደ መንገድ እፈታለሁ ብለው ለተነሡት ጠቅላይ ሚኒስትር ነገሩ ከተለመደውም የወጣ መሰላቸው፡

‹ምንድን ነው?› አሉ ሳቅ ይዟቸው፡፡

‹አሰናብቱን› አለ ደንዳሳ ትከሻ ያለው የቆዳ ወንበር፡፡በታሪኩ ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ እንግዶችን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡
‹ለምን? የት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ
‹በቃ እኛንም ጡረታ ያውጡና› አለ ሌላ እምቡር እምቡር የሚል ወንበር፤
የባለሥልጣን መቀመጫ መሆኑን የሥላሴን ዙፋን ከተሸከሙት ኪሩቤል በላይ ይኮራበታል፡፡
‹እንትናኮ እኔ ላይ ነው የሚቀመጠው› እያለ መጎረር ይወዳል፡፡
‹ምን ሆናችሁ› አሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጃቸውን አገጫቸው ላይ አድርገው፡፡
‹እኛ ከመጀመሪያው ስንገዛ ለዚህ ዓይነት ነገር መሆኑን የነገረን የለም፡፡ አሁን እየተሠራ ያለው ከለመድነው ውጭ ነው፡፡ ከተገዛንበት ዓላማ ውጭ ነው፡፡ የመርሕ መደባለቅ እያየን ነው› አለ ባለ ደንዳሳ ትከሻው ወንበር፡፡
‹ለምን ዓላማ ነበር የተገዛችሁት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልሰሙት የቤተ መንግሥት ምሥጢር መኖሩን እየጠረጠሩ፡፡
‹እኛኮ እዚህ ቦታ ብዙ ጊዜ ኖረናል› አለቺ አንዲት ቆንጠር ቆንጠር የምትል ድፉጭፉጭ ወንበር፡፡
‹እዚህ ስንኖር እነማን ይታሠሩ፣ ይባረሩ፣ አገር ጥለው ይጥፉ፤ ምን ዓይነት አሣሪና ጨምዳጅ ሕግ ይውጣ፣ እነማን ይመቱ፣ እነማን ይገለሉ፣ እነማን ይታገዱ፣ እነማን ይወገዱ፣ እነማን ይውደሙ፣ እነማን ይጋደሙ የሚል ነገር ነው ስንሰማ የኖርነው፡፡ እኛ የተገዛነው ይሄን የመሰለ ምክር ሊመከርብን ነው፡፡ እኛ እዚህ ቢሮ ስንኖር የተቀመጡብን ሰዎች በጣም የተከበሩ ናቸው፡፡ እዚህ እኛ ላይ በተመከረ ምክር ስንት አገር ተተራምሷል፤ ስንቱ ታሥሯል፣ ስንቱ ተገድሏል፤ ስንቱ ቀምሷል፣ ስንቱ ነፍዟል፡፡ አሁን የምንሰማው ነገር ግን የሚያዛልቀን አይደለም› አለቺ መሬቱን በስፒል እግሯ እየፈተገች፡፡

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን እርስዎ የሚናገሩት ቋንቋ እኛን ሊገባን አልቻለም፤ ለዚህ ቢሮ አዲስ ቋንቋ ነው፡፡ ለኛም ለወንበሮቹ አዲስ ልሳን ነው፡፡ስናየው በልሳን እየተናገሩ ይመስለናል› አለ፤ ሁለት ሰው እንዲይዝ ሆኖ የተሠራው አጭሬ ወንበር፡፡ ‹እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ፡፡ የማወራው አማርኛ ነው፤ ትግርኛ ነው፤ ኦሮምኛ ነው፤ እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ ወደ ውስጠኛው ቢሮ መግባቱን ተዉትና በሩ ላይ ቆሙ፡፡ የጽ/ቤት ኃላፊያቸውና አጃቢዎቻቸው በአግራሞት የሚሆነውን ሁሉ ይከታተላሉ፡፡

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ባለ ደንደሱ ትከሻ፡፡ ‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ይሄ የምናውቀው ቋንቋ አይደለም፡፡ በእርስዎ ደረጃ ሰምተንም አናውቅም፡፡ ምናልባት ዶክተር ሲባሉ ሰምተናልና ከውጭ ተምረውት ያመጡት ይመስለናል፡፡ እዚህ ሀገር እዚህ ቢሮ በዚህ ቋንቋ ሲወራ ሰምተን አናውቅም፡፡ ጭራሽ ማሠር እንጂ መፍታት የሚባል በዚህ ቢሮ መዝገበ ቃላት ውስጥ የለም፡፡ ውጡ እንጂ ግቡ የሚል ቃል አዲስ ነው ያመጡብን፡፡ ተለያዩ መባል ሲገባው ታረቁ፣ ተስማሙ፣ አንድ ሁኑ የሚባል መጋኛ እየመጣብን ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ ካሉ ለምን እስከዛሬ እዚህ ቢሮ ውስጥ አልሰማናቸውም?› ባለ ደንደሱ ትከሻ የአንገት መደገፊያውን በኀዘን ነቀነቀው፡፡

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫነት የተዘጋጀው ወንበር፡፡
‹ጭራሽ አሁን ስንሰማማ በሽብር የተከሰሰን ሰው፣ ሞት የተፈረደበትን ሰው መፍታት ሳያንስዎት እዚህ ጠርተው እጁን ሊጨብጡት፤ እኛ ላይ አስቀምጠው ሊያናግሩት ነው አሉ? ይኼንን ከምናይ ምነው ድሮ ተቀዳደን በወደቅን ወይም በሐራጅ በተሸጥን? እና ይሄ ሰውዬ መጥቶ የት ሊቀመጥ ነው? ከኛ ማናችንም ብንሆን እንዲቀመጥብን አንፈቅድም፡፡ ለእርስዎም ለስምዎ ጥሩ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርኮ እቆርጣለሁ፣ እፈልጣለሁ፣ አሥራለሁ፣ እቀፈድዳለሁ፣ ሲል ነው የሚያምርበት፡፡
‹እና እንዋጋለን፣ እንሸፍታለን፣ መንግሥት እንገለብጣለን፣ ሲሉ የኖሩት ሁሉ ብረታቸውን እያስቀመጡ እየመጡ ሊቀመጡብን ነው? ትናንትና እኛ ላይ ቁጭ ባሉት ባለ ሥልጣናት አሸባሪ፣ አደናባሪ፣ አቀናባሪ፣ ሲባሉ እንዳልነበር ዛሬ ዘመን ተቀየረ ብለው መጥተው ሊቀመጡብን?› ሞት ይሻለናል› አለ ሁለት ሰው የሚይዘው አጭሬ ወንበር፡፡
‹ክብራችን ተነክቷል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለቺ ድፉጭፉጯ ወንበር፡፡ ‹ጭራሽኮ አሁንማ ቤተ መንግሥቱን ሰው መጎብኘት አለበት እያሉ ነው፡፡ ታድያ በኛና በሰፊው ወንበር መካከል ምን ልዩነት አለው? የቤተ መንግሥት ወንበር በመሆንና የቤት ወንበር በመሆን መካከል ምን ልዩነት ሊኖር ነው?
መከበራችን፣ መታፈራችን፣ መፈራታችን፣ ሊቀርኮ ነው፡፡
ተራውን ሕዝብ ሁሉ ቤተ መንግሥት ጠርተው መጋበዝዎት ሳያንስ ጭራሽ የቤተ መንግሥቱን ቆሌ ገፍፈው ሊያስጎበኙት? እና የየሠፈሩን ሰዎች እዚህ ግቢ ውስጥ በመስኮት ልናያቸው? ሞተናላ!› ‹ሲደበደብ ከኖረ ቆዳ የተሠራ ከበሮ ዜማው ሁሉ በለው በለው ይመስለዋል› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ ‹አባቶቻችን ድንበር ሲያስከብሩ ኖሩ፤ እርስዎ ግን ድንበሩን ሁሉ ናዱት› አለ ዝም ብሎ ሲመለከት የነበረ በአገልግሎት ብዛት አርጅቶ አናቱ የተላጠ ወንበር› ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውስጥ የሚሰሙትን የስልክ ጥሪ የጽ/ቤት ኃላፊያቸው እንዲያነሣ አዝዘው ማዳመጥ ቀጠሉ፡፡
‹የቱን ድንበር ነው የናድኩት?› አሉት ፈገግ ብለው በትዕግሥት ቆመው፡፡
‹በተቃዋሚና በደጋፊ፣ በገዥና በተገዥ፣ በውጭና በውስጥ መካከል የጸናውን ድንበር ናዱትኮ፡፡ እግዜር ያሳይዎና ኢቲቪና ኢሳት አንድ ዓይነት ዜና እንዲያቀርቡ አደረጓቸውኮ፡፡ አሁን ጭራሽ ውጭ ሊሄዱ ነው አሉ፡፡ ዕንቁላል መወርወሩ ቀርቶ የዕንቁላል ሳንዱች ሊቀርብልዎት ነው አሉ? ከዚህ በላይ ድንበር መናድ የት አለ?› የተላጠ አናቱን አነቃነቀ፡፡ 

‹እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያሰናብቱን፤ አመለካከታችንን ከምንለውጥ ጾታችንን ብንለውጥ ይሻለናል፡፡ ዐርባ ዓመት ያልሰማነውን ቋንቋ ከምንሰማ – ጡረታ ወጥታችኋል የሚለውን ብንሰማ ይሻለናል፡፡ አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌው አቁማዳ ማስቀመጥ አቁማዳውንም መቅደድ ወይኑንም ማፍሰስ ነው፡፡› ባለ ደንደሱ ትከሻ ወንበር ወደ ውጭ ሲወጣ ሌሎችም ተከትለውት ወጡ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ብዕሮችና ወረቀቶች ግን ጤና አልተሰማቸውም፡፡‹እነዚህ ወንበሮች እውን በጤናቸው ነው ቢሮውን ለቅቀው የወጡት? ወይስ በበር ወጥተው በመስኮት ሊመለሱ ነው?› አለ አንዱ እስክርቢቶ፡፡‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል› አለና ሌላኛው እስክርቢቶ መለሰለት፡፡