የአዉሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ልዑካን የኢትዮጵያን እስር ቤቶች እንዳይጎበኙ ተከለከሉ። አሶሲየትድ ፕረስ ከአዲስ አበባ እንደዘገበዉ ልዑካኑ ቀደም ሲል እስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችንና የፖለቲከ ኞችን ለመጎብኘት ፈቃድ አግኝተዉ ነበር። በጀርመናዊቱ የምክር ቤቱ እንደራሴ በባርብራ ሎህቢለር የተመራዉ የኅብረቱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ልዑካን ቡድን በሶስት ቀን ቆይታዉ ከኢትዮጵያና ከአፍሪቃ ኅብረት ባለስጣናት ጋ ተነጋግሯል። ከኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የምክር ቤት አፈ ጉባኤ፤ እና የኢትዮጵያ የሰብዓቂ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች ጋ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብት ይዞታ አስመልክቶ ተወያይቷል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የቡድኑ መሪ ባርብራ ሎህቢለር ኢትዮጵያ ዉስጥ መሻሻሎች መኖራቸዉ እንደማይካድ በመጠቆም ይጎድላል ያሉትን እንዲህ ገልጸዋል፤
«በመጀመሪያ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብትን ለምሳሌ የመማር መብትና የመሳሰሉትን ማረጋገጣቸዉን አድንቀናል፤ ሆኖም በመልዕክታችን የጸረ ሽብር ህጉን የጸጥታ ስጋት ያልሆኑና ትችት የሚሰነዝሩ ወገኖችን ወደወህኒ ለማዉረድ አትጠቀሙበት፤ በተጨማሪም ትርጉም ያለዉ ስራ እንዳይሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚያግደዉን ህግ እንዲያሻሽሉ ወይም እንዲያነሱ፤ ከዚህ ሌላ በሰላማዊ መንገድ ስለተቃወሙ ወይም መንግስትን በአንድም በሌላ መልኩ ስለተቃወሙ ብቻ የታሰሩትን እንዲፈቱ ጠይቀናል።»
ልዑካኑ እስረኞችን እንዲጎበኙ ከተፈቀደላቸዉ በኋላ የተከለከሉበት ምክንያት በዉል አልተገለፀም። ቀደም ሲል ከአፍሪቃ ኅብረት የፖለቲካ ኮሚሽነርና የጸጥታ ጉዳይ ባለስልጣናት ጋ በመገናኘትም በአካባቢዉ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ እንዲሁም የሁለቱ አህጉር ኅብረቶች ትብብርን አስመልክተዉ መወያየታቸዉ ተገልጿል።
No comments:
Post a Comment