ሀምሌ16/2005 ዓ.ም. በጣም መጥፎና ጥሩ ስሜት የማይፈጥር ቀን ነበር፡፡ ቤተሰብን፣ ወዳጅ ዘመድን በተለይ የሚወዷትን ሃገር ጥሎ መውጣት ምንኛ ይከብዳል? ከሀገርስ በላይ ምን አለ? አፈር ፈጭቼ ካቦካሁባት፣ ተወልጄ ካደግኩባት፣ ክፉ ደጉን ካየሁባት አገሬ የመውጣቴ የመጨረሻ ቀን መቃረቡን ሳስብ በሕይወቴ አጋጥሞኝ የማያውቅ የመደበት ስሜት ውስጥ ነው የተዘፈቅኩት፡፡ ከቤተሰብ፣ ከጐረቤት፣ ከወዳጅ ዘመድ የመለያየት መቃረቢያው ክፉኛ ያሳምማል፡፡ ከምንም በላይ በሀገር መኖር ክብር መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ከሚወዷት ሃገር ተገፍቶ እና ተገፍትሮ መውጣት ከመርግ የከበደ መሆኑን አሁን መጨረሻው ላይ የግዴን አወቅኩት፡፡ በቅርብ የሚያውቁኝ “ሰርካለም ከምትንሰፈሰፍላት ውድ ሀገሯ ወጥታ ለመኖር እንዴት ጨከነች?” እንደሚሉ እገምታለሁ፡፡ ሀገሬን እጅግ እወዳታለሁና “እንደወጣሁ እቀራለሁ” የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም፡፡ ደሕንነቴ አደጋ ውስጥ ሲወድቅ፣ ውክቢያና እንግልቱ ሲከፋብኝ ግን ለራሴ ብቻ ሳይሆን በአባቱ እስራት ለሚንገላታው ልጄ ስል ይሕን መወሰኔ ግድ ሆነብኝ፡፡ ቤተሰብ ያለው ሰው የሚሰማው የተለየ ስሜት ይኖራል፡፡ ለኔ ሕይወት የራሷ የሆነች ስም ካላወጣችለት በቀር ከመደበኛው የተለየች ሆናብኛለች ማለት እደፍራለሁ፡፡ ሁሌም በውክቢያና እስር፣ በማጠስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ሥር ሆኖ መኖር በእጅጉ ያስመርራል፡፡ የኔ ሕይወት ይሄ ነው፡፡ ባለቤቴ እስክንድር ነጋ ለእስር ከተዳረገ ዓመቱን ሊደፍን ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ ነው የቀረው፡፡ በእስር ቤት የተወለደው ልጃችን ናፍቆት እስክንድር ነጋ የአባቱ ናፍቆት እያሰቃየው፣ እንደ እኩዮቹ ከመፈንጠዝና ከመቦረቅ ርቆ በትካዜ ውስጥ መኖሩ በእጅጉ ሲያሰቃየኝ ቆየ፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህ እየተሰቃየና እየተጎዳ መኖር አይኖርበትም፡፡ በእስር ያጣው ውድ አባቱን በየሳምንቱ እያየው ከሚሰቃይ ከሃገር ርቆ “አንድ ቀን እንገናኛለን” የሚል ተስፋ ውስጥ ቢገባ የተሻለ ሊሆንለት እንደሚችልም አምኛለሁ፡፡ ማንም ወላጅ ይሕን ስሜቴን ይረዳኛል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ልጃችን ናፍቆት ዕድሜው ከሚችለው በላይ መከራ በመቀበል ከማናችንም በላይ ተጐድቷል፡፡ በትምሕርት ቤት ከአቻ ጓደኞቹ ጋር መጫወት ትቶ ብቻውን አቀርቅሮ መሬት ሲጭር ይውላል፡፡ “አባቴ መቼ ነው የሚመጣው?” ከሚለው የመናፈቅ ጥያቄው ጋር እየታገለ ትምሕርቱን መከታተል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ሞራሉ እየወደቀ ሲሄድ ያየሁ መሰለኝ፡፡ የወለድኩት ቃሊቲ ወሕኒ ቤት ስለሆነ እንደ እናት ተገቢውን እንክብካቤ እንኳን አላደረግኩለትም፡፡ ከሰው ተነጥዬ የምችለውን ላደርግለት የሞከርኩ ቢሆንም አንድ ሕፃን ሊደረግለት ከሚገባው በትንሹ እንኳን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ልጄ ባህሪው በእጅጉ ተለወጠ፤ ከሰው ጋር መግባባት ተቸገረ፤ ዝምታንና ለብቻው መገለልን ምርጫው አደረገ፡፡ ሰው ይፈራል፤ ከእኔ ከእናቱና ከወንድሜ ጋር ብቻ የሚግባባው ናፍቆት ከሌላ ሰው ጋር መግባባት አልሆንለት አለ፡፡ እኛ ተጐድተን… በስነ ልቦና የተጐዳ ልጅ መፍጠር አይኖርብንም፡፡ እኔና ልጄ ከእስር ስንፈታ፣ አባቱ ተመልሶ ወሕኒ ከወረደ በኋላ ደግሞ የልጃችን የባህሪ ለውጥ እየከፋ ሄደ፡፡ እስቲ ለሰከንዶች ብቻ እንደ አንዲት እናት ሆናችሁ አስቡት፡፡ ማንም የወለደው ልጅ ሲጐዳበት ማየት አይፈልግም፡፡ ዘጠኝ ወር አርግዤው በ1998 ዓ.ም. በእስር ቤት የወለድኩት ናፍቆት እስክንድር ነጋ ላለፉት ሠባት ዓመታት የገፋው የሰቆቃ ኑሮ እንዲበቃው መፈለጌ ነው ወደማልፈልገው ስደት እንዳመራ ያስገደደኝ፡፡ የውክቢያ ዘመኑ ያኔም ዛሬም ፈፅሞ አልተቀየረም፡፡ ባለቤቴ እስክንድር ያለ ፍትሕ መታሰሩ፣ እኔና ናፍቆት የምንመራው የሰቆቃ ሕይወት የብዙሃን ግፉአን ኢትዮጵያውያን ሕይወት ግልባጭ ነው፡፡ በጠመንጃ ታጅቤ ፖሊስ ሆስፒታል የወለድኩት፣ የሕፃንነት ጊዜው የቃሊቲ እስር ቤት በር ተዘግቶበት ያሳለፈው የምወደው ልጄ አዕምሮው እንዳይጎዳ ለጊዜው ከስደት የተሻለ አማራጭ አላገኘሁም፡፡