Friday, 9 August 2013

የእስክንድር ነጋ ባለቤት የሰርካለም ፋሲል የመጨረሻ ቃል – “የልጄ አዕምሮ እንዳይጎዳ ከሃገር መውጣትን መርጫለሁ”

ሀምሌ16/2005 .. በጣም መጥፎና ጥሩ ስሜት የማይፈጥር ቀን ነበር፡፡ ቤተሰብን፣ ወዳጅ ዘመድን በተለይ የሚወዷትን ሃገር ጥሎ መውጣት ምንኛ ይከብዳል? ከሀገርስ በላይ ምን አለ? አፈር ፈጭቼ ካቦካሁባት፣ ተወልጄ ካደግኩባት፣ ክፉ ደጉን ካየሁባት አገሬ የመውጣቴ የመጨረሻ ቀን መቃረቡን ሳስብ በሕይወቴ አጋጥሞኝ የማያውቅ የመደበት ስሜት ውስጥ ነው የተዘፈቅኩት፡፡ ከቤተሰብ፣ ከጐረቤት፣ ከወዳጅ ዘመድ የመለያየት መቃረቢያው ክፉኛ ያሳምማል፡፡ ከምንም በላይ በሀገር መኖር ክብር መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ከሚወዷት ሃገር ተገፍቶ እና ተገፍትሮ መውጣት ከመርግ የከበደ መሆኑን አሁን መጨረሻው ላይ የግዴን አወቅኩት፡፡ በቅርብ የሚያውቁኝሰርካለም ከምትንሰፈሰፍላት ውድ ሀገሯ ወጥታ ለመኖር እንዴት ጨከነች?” እንደሚሉ እገምታለሁ፡፡ ሀገሬን እጅግ እወዳታለሁናእንደወጣሁ እቀራለሁየሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም፡፡ ደሕንነቴ አደጋ ውስጥ ሲወድቅ፣ ውክቢያና እንግልቱ ሲከፋብኝ ግን ለራሴ ብቻ ሳይሆን በአባቱ እስራት ለሚንገላታው ልጄ ስል ይሕን መወሰኔ ግድ ሆነብኝ፡፡ ቤተሰብ ያለው ሰው የሚሰማው የተለየ ስሜት ይኖራል፡፡ ለኔ ሕይወት የራሷ የሆነች ስም ካላወጣችለት በቀር ከመደበኛው የተለየች ሆናብኛለች ማለት እደፍራለሁ፡፡ ሁሌም በውክቢያና እስር፣ በማጠስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ሥር ሆኖ መኖር በእጅጉ ያስመርራል፡፡ የኔ ሕይወት ይሄ ነው፡፡ ባለቤቴ እስክንድር ነጋ ለእስር ከተዳረገ ዓመቱን ሊደፍን ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ ነው የቀረው፡፡ በእስር ቤት የተወለደው ልጃችን ናፍቆት እስክንድር ነጋ የአባቱ ናፍቆት እያሰቃየው፣ እንደ እኩዮቹ ከመፈንጠዝና ከመቦረቅ ርቆ በትካዜ ውስጥ መኖሩ በእጅጉ ሲያሰቃየኝ ቆየ፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህ እየተሰቃየና እየተጎዳ መኖር አይኖርበትም፡፡ በእስር ያጣው ውድ አባቱን በየሳምንቱ እያየው ከሚሰቃይ ከሃገር ርቆአንድ ቀን እንገናኛለንየሚል ተስፋ ውስጥ ቢገባ የተሻለ ሊሆንለት እንደሚችልም አምኛለሁ፡፡ ማንም ወላጅ ይሕን ስሜቴን ይረዳኛል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ልጃችን ናፍቆት ዕድሜው ከሚችለው በላይ መከራ በመቀበል ከማናችንም በላይ ተጐድቷል፡፡ በትምሕርት ቤት ከአቻ ጓደኞቹ ጋር መጫወት ትቶ ብቻውን አቀርቅሮ መሬት ሲጭር ይውላል፡፡አባቴ መቼ ነው የሚመጣው?” ከሚለው የመናፈቅ ጥያቄው ጋር እየታገለ ትምሕርቱን መከታተል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ሞራሉ እየወደቀ ሲሄድ ያየሁ መሰለኝ፡፡ የወለድኩት ቃሊቲ ወሕኒ ቤት ስለሆነ እንደ እናት ተገቢውን እንክብካቤ እንኳን አላደረግኩለትም፡፡ ከሰው ተነጥዬ የምችለውን ላደርግለት የሞከርኩ ቢሆንም አንድ ሕፃን ሊደረግለት ከሚገባው በትንሹ እንኳን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ልጄ ባህሪው በእጅጉ ተለወጠ፤ ከሰው ጋር መግባባት ተቸገረ፤ ዝምታንና ለብቻው መገለልን ምርጫው አደረገ፡፡ ሰው ይፈራል፤ ከእኔ ከእናቱና ከወንድሜ ጋር ብቻ የሚግባባው ናፍቆት ከሌላ ሰው ጋር መግባባት አልሆንለት አለ፡፡ እኛ ተጐድተንበስነ ልቦና የተጐዳ ልጅ መፍጠር አይኖርብንም፡፡ እኔና ልጄ ከእስር ስንፈታ፣ አባቱ ተመልሶ ወሕኒ ከወረደ በኋላ ደግሞ የልጃችን የባህሪ ለውጥ እየከፋ ሄደ፡፡ እስቲ ለሰከንዶች ብቻ እንደ አንዲት እናት ሆናችሁ አስቡት፡፡ ማንም የወለደው ልጅ ሲጐዳበት ማየት አይፈልግም፡፡ ዘጠኝ ወር አርግዤው 1998 .. በእስር ቤት የወለድኩት ናፍቆት እስክንድር ነጋ ላለፉት ሠባት ዓመታት የገፋው የሰቆቃ ኑሮ እንዲበቃው መፈለጌ ነው ወደማልፈልገው ስደት እንዳመራ ያስገደደኝ፡፡ የውክቢያ ዘመኑ ያኔም ዛሬም ፈፅሞ አልተቀየረም፡፡ ባለቤቴ እስክንድር ያለ ፍትሕ መታሰሩ፣ እኔና ናፍቆት የምንመራው የሰቆቃ ሕይወት የብዙሃን ግፉአን ኢትዮጵያውያን ሕይወት ግልባጭ ነው፡፡ በጠመንጃ ታጅቤ ፖሊስ ሆስፒታል የወለድኩት፣ የሕፃንነት ጊዜው የቃሊቲ እስር ቤት በር ተዘግቶበት ያሳለፈው የምወደው ልጄ አዕምሮው እንዳይጎዳ ለጊዜው ከስደት የተሻለ አማራጭ አላገኘሁም፡፡

ጉዞ ወደ አሜሪካ የጉዞዬ ዓላማ ኑሮን በአሜሪካ ማድረግ አይደለም፡፡ የአሜሪካን የተንደላቀቀ ኑሮ ብንፈልግ ኖሮ እኔም ሆንኩ ዛሬ እስር ላይ የሚገኘው ባለቤቴ እስክንድር ነጋ ልጃችንን ይዘን ቀድመን ከሀገር በወጣን ነበር፡፡ እስክንድር ለዓመታት አሜሪካ ኖሮ በሃገሩ ሃሳብን የመግለጽ መብትኤክሰርሳይስለማድረግ ነው የመጣው፤ እኔም ብሆን አሜሪካ ደርሼ የተመለስኩት ሃገሬን ስለምወድ እንጂ ሌላ ጥቅም ስላለ ነው፡፡ ሁለታችንም ከሃገር የመውጣት ሃሳቡ አልነበረንም፤ ዛሬ የእኔው ግድ ሆነ፡፡ የልጃችን የአእምሮና ስነ ልቦና ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ናፍቆት እስክንድር ነጋ ከሰኞ እስከ አርብ በትምሕርት ቤት ሲናውዝ ቆይቶ፣ የቅዳሜና እሁድ የዕረፍት ቀኑን እንደ እኩዮቹ መዝናኛ ቦታ ሣይሆን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ነው የሚያሣልፈው፡፡ ናፍቆት ለአባቱ ያለው ፍቅር የተለየ ነው፡፡ እስክንድር ዳግም ሲታሰር ልጃችን ናፍቆትን ከትምህርት ቤት እያመጣ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች እስክንድርን ሲይዙት፣ ልጃችን ናፍቆትአባቴን ልቀቁትእያለ ያለቅስ ነበር፡፡ ይህንን ክስተት እስኪ ለአፍታ መለስ ብላችሁ አስቡት፡፡ እስክንድር ነጋ በሃገሩ የሚኖር ሕጋዊ ሰው፣ ቋሚ አድራሻ ያለውና ፖሊስም ሆነ የደሕንነት ባልደረቦች በፈለጉበት ጊዜ ጠርተው ሊያስሩት እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡ ልጁን ከትምህርት ቤት ሲያወጣ ጠብቀው በጠመንጃ ከበው፣ እየደነፉ የያዙት እሱንም ሆነ ልጃችንን ለማሳቀቅ እንደሆነ ማንም ሰው ይረዳዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በወቅቱ እስክንድርን የያዙት ሰዎች የልጅ አባት ይሆኑ ይሆናል፡፡ እነርሱ በእስክንድርና በናፍቆት ላይ ያደረሱት ሽብርና ማሸማቀቅ በራሳቸውና በልጆቻቸው ቢፈፀም ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ለመገመት ለምን እንደተቸገሩ አይገባኝም፡፡ እናምምነዋ! ሰርካለም ከሀገር ወጣችብላችሁ ለጠየቃችሁ ምላሼ ይድረሳችሁ፡፡ ወደአሜሪካ የጉብኝት እድሉን ከቅርብ ወዳጃችን ነው ያገኘነው፡፡ ልጄ የተወሰነ ቢሆን ቦታ መቀየር የራሱ የሆነ እገዛ ይኖረዋል ድምዳሜ ላይ በመድረሴ ግብዣውን ተቀበልኩት፡፡ የስማችን መጠሪያ፣ ሃገር ተረካቢው ልጃችን በኛ ዳፋ ሞራሉ ደቆ ሲጐዳ ከማየት እንዲያገግም ስል ይኸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተጉዣለሁ፡፡ (-ሐበሻ ድረገጽን ሁሌም ያንብቡ)

እስክንድርን ጥሎ መሄድ ባለቤቴ እስክንድር ነጋ እስር ላይ ነው፡፡ የቃሊቲን አታካችና አሰልቺ ጉዞ ተቋቁሞማን ስንቅ ያቀብለዋል?” የሚለው ጥያቄ ውሳኔዬን እንድቀለብስ ሞግቶኝ ነበር፡፡ እሱን ጥሎ መሄድ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለእኔ፣ ላንተ፣ ላንቺ መብት አይደል የታሰረው? እና ለእኔ ሲል ታስሮ እሱን ጥሎ መሄድ እንዴት እደፍራለሁ፡፡ እስክንድር የልጃችንን ጉዳት በመረዳቱ ከሃገር ርቀ ቢቆይ የተሻለ ነገር እንደሚየገኝ ሲያግባባኝ ዓመት አልፎታል፡፡ እስካሁን ሳልቀበለው ቆይቻለሁ፡፡ አሁን ግን እስክንድርም አመረረ፡፡ልጃችን ሲጎዳ እምቢኝ ከሃገር አልወጣም ያልሽኝ አንቺ ከእኔ የተሻለ አንፃራዊ ነፃነት ስላለሽ (ስላልታሰርሽ) ነውየሚለውን ግፊት አጠነከረው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜየት በተደጋጋሚ ወዳጆቻችን የእረፍት ቪዛ ሲልኩልን አሻፈረኝ ብዬ ሳቃጥለው የነበረውን ዕድል ማክተሙን ተረዳሁት፡፡ እስክንድርእኔ የታሰርኩበት አላማ አለኝ፤ በዚህች ሀገር ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን አሁንም ትግሌ ይቀጥላል፤ በእስር ቤት የተወለደው ልጄ ግን አዕምሮው ከዚህ በላይ መጐዳት አይኖርበትም፡፡ እና በአፋጣኝ እረፍት እንዲያደርግ ብለሽ ውጡነው ያለኝ፡፡ በሣምንት አራት ቀን የምጠይቀው ባለቤቴን መራቅ ቢከብደኝም በአንድ ነገር ግን ገዘተኝ፡፡እስክንድር ቢታሰርም አይሟሟም፤ እኔ ስለፍትህ፣ ነፃነትና ዴሞክራሲ የምናገር እንጂ አሸባሪ አይደለሁም፤ ልጄ ደግሞ በኔ እስር የአባቱን ፍቅር አጥቶ መጨነቅና አእምሮው መጐዳት የለበትም፤ ሲያድግ ጥሩ አእምሮ ኖሮት ሀገሩን እንዲያገለግል ውሳኔዬ ነውየሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ የጉዞ ውሳኔ ላይ አድርሶኛል፡፡ እናም የእሱን ቃል ማክበር ስላለብኝ ይህን አደረኩ፡፡ ውድ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼና እህቶቼ እኛ ማለትም ባለቤቴና እኔ ወደ አሜሪካ የምንሄድበት እድል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ተፈጥሮልን ነበር፡፡ ግን ለምን ሀገራችንን ለቀን አንሄዳለን ብለን ነው የወሰን ነው፡፡ የኔም ሆነ ባለቤቴ አቋም ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለይ ባለቤቴ እስክንድር ነጋ ስለዴሞክራሲ ከሀገር ወጥቶ መታገል በሚለው ነገር ላይ ፈፅሞ እምነት የለውም፡፡ ሰላማዊ ትግል በሀገር ውስጥ ማድረግ ነው የሚል እምነት አለው፡፡ ከዛ በመነሣት ነው ብዙ የቆየ ነው፡፡ አሁን ግን የልጃችን አእምሮ እየተጐዳ በመምጣቱ መቼም ወላድ ….ኢትዮጵያዊ ይመስክር የልጅን ነገር የወለደ ያውቀዋልና ለዛም ስንል የተወሰነ እረፍት ቢያገኝ ብለን ወደ አሜሪካ ይዤው ለመሄድ ተገደድኩ፡፡ ይህ ህፃን በእስር ላይ ተወልዶ የቤተሰብ ፍቅር ያልጠገበ ባይተዋር ልጅ ሆነብን፡፡ በሁሉም መጐዳት የለብንም ልጃችን በእኛ ስህተት ሣይሆን እኛ በምናደርገው ትግል ሁሌም መታሰራችን የፈጠረበት የቤተሰብ እንክብካቤ ማነስ ተጐዳ፡፡ አያት ወይም አጐት እንደ ወላጅ ሆኖ ለማሣደግ ይቸገራል፡፡ ለሀገራችን ስንታገል የልጃችን ጭንቅላት ጐዳት እስክንድርንም እኔንም ለውሣኔ አበቃን፡፡ እስክንድር ብቻውን አይደለም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቃሊቲዞን 2″ እየሄድ ይጠይቀዋል፡፡

ያለፉት ስድስት አመታት 1998 .. ታስረን ከእስር ከተፈታን በኋላ ምናልባትም የስድስት አመታት ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ ለእስክንድር የከበደ ጊዜ ነበር፡፡ የጋዜጣ ፈቃድ አውጥቶ በሞያው ለመንቀሣቀስ ቢፈልግም ፈቃድ የማግኘት እድል ግን ፈፅሞ ማግኘት አልቻለም፡፡ ከዛ በኋላ በፖለቲካዊ ትንታኔዎች ዙሪያ መንቀሣቀስ ጀመረ፡፡ እስክንድር እንደሌሎች ከሀገር እንደወጡ ፖለቲከኞች ውጭ ሆኖ ድምፁን ማሰማት ይችላል፡፡ ግን የእሱ አላማ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ በሀገር ውስጥ መንቀሣቀስ ጀመረ፡፡ ነገር ግን በጠላትነት አስፈርጆት ሁሌም በክትትል ሕይወት ውስጥ እንዲኖር አደረገው፡፡ እስክንድር ሁሌምበመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ክትትል ስር የወደቀ ነበርቤታችን ይጠበቃል፣ እሱም ነፃ ሆኖ መንቀሣቀስ አልቻለም፡፡ እሱን ለመጠየቅ የመጣ፣ ከእሱ ጋር የቆመና የተነጋገር ችግር ይገጥመዋል፡፡ የሰቆቃ ዘመን ነበር ያሣለፈው፡፡ በመጨረሻም ታሰረ፡፡ ዳግም መታሰር ይከብዳል፡፡ እስክንድር ባለፉት 20 አመታት ወይም በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶየፕሬሱ ፋና ወጊ ነውግን በእስር እጁን እስከመሰበር ደርሷል፡፡ ከአሜሪካ ሀገር ድረስ መጥቶ በዚህች ሀገር ላይ ስለዴሞክራሲ ነፃነትና መብት የሚናገር ማነው እናም እነዚህ ያለፉት ስድስት አመታት እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ የሆኑ ጊዜያት ነበሩ፡፡

የወጣትነት ዘመን እኔ የወጣትነት ዘመን ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔና እስክንድር ስንገናኝ 21 አመት ወጣት ነበርኩ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ የመዋከብና በዚህ ሕይወት ዙሪያ የመረጋጋት ሕይወት ሣይኖረን ቆይተናል፡፡ ወጣትነት ብዙ ነገር ማለት ነው፡፡ፈፅሞ አላውቀውምከእድሜ እኩዮቼ ጋር ሆኖ መዝናናት በእኔ እድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት ልታደርግ የሚገባውን ነገር ፈፅሞ አድርጌ አላውቅም፡፡ በእኛ ስር ሦስት ጋዜጦች ነበሩ፡፡ ምኒልክ፣ አስኳልና ሳተናው፡፡ ሦስቱም በሣምንቱ ውስጥ ይወጣሉ፡፡ እነዚህን ማዘጋጀት መምራት ምን ጊዜ ይሰጣል፡፡ ለዛውም የፖለቲካ ጋዜጣ ማዘጋጀት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በዚህ በሦስት ጋዜጣ ስር ደግሞ ምን ያህል ሠራተኞች አሉ፡፡ እናም ወጣትነቴን አላውቀውም፡፡ወጣትነት ምንም እንደሆነ ስለወጣትነት የተፃፈውን መፅሐፍ ከማንበብ ባለፈ ይህ ነው የሚባል የወጣትነት ትዝታ ፈፅሞ የለኝም፡፡በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ ነው ወጣትነቴን ያሣለፍኩት፡፡ አልፏል ብዙም አልቆጭበትም፡፡ ከዚህ በኋላ ወጣት የሚባል ደረጃ ላይ አይደለሁም፡፡ ባለፉት ጊዜያትም የምቆጭ አይደለሁም፡፡ ስለዴሞክራሲ ስሰራ በመኖሬ ደግሞ እኮራለሁ፡፡

የእስክንድር ዳግም እስር ምን ፈጠረ; የእስክንድር ዳግም መታሰር ቤተሰባችን እንዲበተን አድርጓል፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ በሕይወቱ ሊያደርጋቸው ከሚገባቸው ነገሮች መካከል በትዳር ተጥምሮ ወልዶ መኖር ነው፡፡ ይህ ግን ለእኛ የተፈቀደ አይደለም፡፡ እስክንድር ከጥሩ ቤተሰብ የወጣ ጥሩ አቅም ያለው ነው፡፡ የእሱ ቤተሰብ ምንጭ ጥሩ ነጋዴ ሆነን ተንደላቀን እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የእሱ ቤተሰብ ንብረት ፈፅሞ በሚገርም መልኩ ሽብርተኛ በሚል ተወረሰ፡፡ በመጨረሻም ይኸው ዳኛ ቤተሰብ በተነ፡፡ እስክንድር 18 አመት ተፈረደበት፡፡እኔም ለልጄ ጭንቅላት ስል ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ወዳጅ ዘመድ በፈጠረው እድል ተጠቅሜ ወደ አሜሪካ አመራሁ፡፡ ይገርማችኋል እኛ ሰላማዊ ነን ልጃችን አፍ ፈቶ መናገር ከቻል በኋላ አብረን ለመኖር መታገዳችን ምን ያህል ያስቆጫል፡፡ እስክንድር በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ፍትህ የእውነት ካልሰፈነ በቀር በአደባባይ ቢሰቀልና ቢሰቃይ ቦታ የለውም፡፡ ግን ልጃችን ለምን ይሰቃይ የሚል እምነት አለው፡፡ ማንም ቢሆነ የልጁን ስቃይ ማየት አይወድምና፡፡

የሀገር ነገር ይህንን ስል እንባዬ ምን ያህል በአይኔ ላይ እየወረደ እንደጠረኩት አውቃለሁ፡፡ ያለቀስኩበት ዘመን አልፏል፡፡ …. ሀገሬን እወዳለሁ፡፡ ግን መልካም አስተዳደርን እመኛለሁ፡፡ ከሀገሬ አልርቅም ወደ ሀገሬም እመለሣለሁ፡፡ እኔና ባለቤቴ ለልጃችን ስንል እንጂ የደረሰብን በርካታ ስቃዮች የጐዳን አይደለም፡፡ እናም ሁሌም ቢሆን ኢትዮጵያን እወዳለሁ፡፡ ከሀገሬ መራቅ የምፈልግ አይደለሁም፡፡ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፡፡ እስክንድር ነጋ ሀገሩን የሚወድ አሜሪካ መኖር እየቻለ ስለሀገሩ ሲል ቃሊቲ /ማረሚያ ቤት/ መኖሪያው የሆነ ሰው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment