-የንብረት አስተዳደር ችግር አሳሳቢ ሆኗል
በመንግሥት መሥርያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ያለሥራ ተከማችተው የሚገኙ ንብረቶች አገሪቱ በየዓመቱ በዕርዳታና በብድር ከምታገኘው ገንዘብ እንደማይተናነስ፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥናት አመለከተ፡፡
ኮሚሽኑ የመንግሥት መሥርያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች የንብረት አስተዳደር ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ያለው ተጋላጭነት ላይ ያዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ድርሻ ውስጥ እስከ 14 በመቶ የሚደርሱት የተለያዩ አገራዊ ተግባራትን ለማከናወን በግብዓትነት የሚያገለግሉ ቋሚና አላቂ ንብረቶች ናቸው፡፡ የመንግሥት ተቋማት ከሚመደብላቸው በጀት ውስጥ ከ60 አስከ 70 በመቶ የሚሆነው ለዕቃና ለአገልግሎት ግዥ ተግባር የሚውል ቢሆንም፣ ከፍተኛ በጀት የፈሰሰበት የመንግሥት ንብረት ከብክነት፣ ከብልሽትና ከስርቆት ለመከላከል የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
በጥናቱ ላይ ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ የተገኙት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንደተናገሩት፣ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚታየው የንብረት አስተዳደር የሙስና ተጋላጭነትና ብልሹ አሠራር አሳሳቢ ሆኗል፡፡
በየተቋማቱ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ግዥ በከፍተኛ ወጪ እንደሚፈጸም፣ የተገዙ ንብረቶች ከአያያዝ ጉድለት ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ ለብክነትና ለግለሰቦች የግል ጥቅም ማግኛ መዋላቸውንም አቶ ወዶ አስረድተዋል፡፡
በመንግሥት ተቋማት በሚታየው የንብረት አስተዳደር ለሙስና ተጋላጭነትና ብልሹ አሠራር ላይ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተወያዩት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ፣ ‹‹ከምንም በላይ የራሳችሁን ጓዳ መፈተሽ አለባችሁ፡፡ ችግሩ የጋራና አሳሳቢ ነው፡፡ ሆኖም መቅረፍ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን ወክለው የተገኙት ወይዘሮ ሣራ ብሩ፣ በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚታየው የንብረት አስተዳደር ችግር ሁልጊዜም የሚነገር ሆኖም በተነገረው ልክ ባለመሠራቱ ችግሩን መፍታት አለመቻሉን አስገንዝበዋል፡፡ በንብረት አስተዳደር ላይ ለሚታየው ብልሹ አሠራር ከታችኛው ሠራተኛ እስከ ኃላፊው ድረስ ተጠያቂ አለማድረግም ችግሩን አስፋፍቶታል ብለዋል፡፡
የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትና ንብረት ያላግባብ እየባከነ በመሆኑ ምክንያት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በልማት ድርጅቶች የንብረት አስተዳደር ላይ በኮሚሽኑ የተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኮሚሽኑ የሚቀርቡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የተሠሩ የአሠራር ሥርዓት ጥናቶችና የምርመራ ሥራ ውጤቶች በንብረት አስተዳደር ላይ የአሠራር ክፍተቶች እንዳሉና በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የአገር ሀብት ብክነት መኖሩን አመላክተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ላይ ያከናወናቸውን የአሠራር ሥርዓት ጥናቶችና በተጨማሪነት ያካሄዳቸውን የዳሰሳ ጥናቶች መሠረት በማድረግ ባዘጋጀው ዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ አብዛኞቹ የተቋማት ኃላፊዎች ንብረቶች እንዲገዙ ከማድረግ በዘለለ የተገዙትን ንብረቶች በአግባቡ ተቆጣጥሮ የመረከብ፣ መዝግቦና ጠብቆ የመያዝ፣ ለተገቢው ሥራ በአግባቡ የመጠቀምና የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲያበቃ ለማስወገድ ተገቢውን ክትትልና ትኩረት እንደማይሰጡ ታይቷል፡፡
በተቋማቱ ንብረቶች ተገዝተው ሲገቡ ጠንካራና ወጥነት ያለው የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር፣ ንብረቶች ለብልሽት፣ ለብክነት፣ ለቁጥጥር በማያመችና ለስርቆት በተጋለጠ ሁኔታ የሚያዙ መሆናቸው፣ ወጪ የተደረጉ ንብረቶች ለተጠየቁበት ተግባር መዋላቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል አሠራር አለመኖር፣ ወጥነት ያለውና የተደራጀ የቋሚ ንብረቶች የቁጥር አሰጣጥ፣ መዝግቦ የመያዝና የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖሩንም ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ለተቋማቱ ሥራ የማያገለግሉ ንብረቶች ለረዥም ጊዜ ሥራ ላይ ሳይውሉ አከማችቶ መያዝ፣ የዕቃ ገቢ፣ ወጪ መጠየቂያና ወጪ ማድረጊያ ሰነዶች በአግባቡ አለመጠቀም፣ አገልግሎት የማይሰጡ አሮጌ ንብረቶች በሰነድ ተመዝግበው የሚያዙበትና በየጊዜው የሚወገድበት አሠራር አለመኖር፣ የንብረት ማሰባሰብና መልሶ የመጠቀም መመርያ አለመኖር፣ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ቋሚ ንብረቶች በሰነድ መዝግቦ አለመያዝና በኃላፊነት ተረክቦ የሚያስተዳድር አካል አለመኖር፣ በተገቢ ሙያተኛ አለማሠራትና የውስጥ የቁጥጥር ሥርዓት ጠንካራ አለመሆን በተቋማቱ የታዩ ዋና ችግሮች መሆናቸው ተዘርዝሯል፡፡
No comments:
Post a Comment