Monday, 19 January 2015

ካፒቴን አምሳሉ ጓሉ


በበረራ መማረክ የጀመርኩት ልጆች ሳለን አባቴ፣ እኔና እህቶቼን ወደ አየር ማረፊያ እየወሰደ አውሮፕላን ሲያርፍና ሲነሳ ያሳየን በነበረበት ወቅት ነው፡፡ አባቴ አውሮፕላኑን የሚያሳየን የአብራሪነት ፍላጎት እንዲቀሰቀስብን አስቦ አይመስለኝም፡፡ በእኔ ልብ ውስጥ የአብራሪነት ፍላጎት ያደረገው ግን በዚያ ጊዜ ነበር፡፡ ግዙፎቹ አውሮፕላኖች ሰማዩን እየሰነጠቁ ሲከንፉ በደስታ ተጥለቅልቀን መመልከታችን፣ አባታችንን ሳይከነክነው እንደማይቀር አስባለሁ፡፡ አባታችን ሁላችንም እንደየፍላጎታችን እንድንጓዝ ከማበረታታት ችላ ያለበት ጊዜ ባይኖርም፤ ያ የየሳምንቱ የአየር ማረፊያው ጉብኝታችን፣ እንዴት የበኩር ልጁ የእድሜ ልክ ሕይወትና ሙያ ሊሆን እንደቻለ አሁንም ድረስ ይገርመዋል፡፡
የተወለድኩት በ1969 ዓ.ም ባህርዳር ከተማ ነበር፡፡ አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቼ፤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ ደህና ገቢ የነበራቸውን ወላጆቼን በአርአያነት እየተመለከትኩ ነው ያደግሁት፡፡ አባትና እናቴ በራሴ እንድተማመንና ህልሜን ለማሳካት እንድጣጣር ያበረታቱኝ ነበር፡፡ “ሴት በመሆንሽ ገደብሽ እዚህ ድረስ ነው” ብለውኝ አያውቁም፡፡
ያደግሁበት ማህበረሰብም፣ ለዛሬው ማንነቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የአካባቢያችን ሰው ሁሉ እንደራሱ ልጅ ነበር የሚያየኝ፡፡ የእለት ተዕለት እድገቴን ከመከታተልም ባሻገር በትምህርቴ በርትቼ እንድገፋ ያበረታቱኝ ነበር፡፡
አብራሪ የመሆን ፍላጎቴን ሁሉም ያውቁ ስለነበር የማያደንቀኝ አልነበረም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ፣ ሁለት ታንዛኒያውያን (አንድ ወንድና አንድ ሴት) የበረራ ሰልጣኞች እኛ ሰፈር ይኖሩ ነበር፡፡ እናም በዩኒፎርማቸው ተማርኬ ፈዝዤ እመለከታቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡
የሶስት ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ ቤተሰቦቼ ወደ አዲስ አበባ ስለመጡ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በአሳይ የህዝብ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተልኩ፡፡ በ1987 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ገብቼ፣ ሥነ-ህንፃ (አርኪቴክቸር) መማር ጀመርኩ፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን የልጅነት ህልሜን አልዘነጋሁትም ነበር፡፡ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመግቢያ ፈተናን ወስጄ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተፈታኞች በመጀመርያ ሙከራቸው ይወድቁ ነበር፡፡ እኔም ሳላልፍ ቀረሁ፡፡
በእርግጥ በመግቢያ ፈተናው መውደቄ ተስፋ አለመቁረጥንና የበለጠ መጣርን አስተምሮኛል፡፡ የሥነ - ህንፃ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ የመግቢያ ፈተናውን በድጋሚ ወሰድኩና አለፍኩ፡፡ ክፋቱ ግን አስቸጋሪ ሰዓት ላይ ሆነብኝ፡፡ የበረራ ሥልጠናው በሚጀመርበት በመጋቢት ወር 1992 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነበር፡፡
እናም ለዓመታት የለፋሁበትን ትምህርት ገደል እንደመክተት ሆነብኝ፡፡ የማታ ማታ ግን በሐምሌ 1992 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ሥልጠናውን እንድጀምር ተፈቀደልኝ፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደውን ሥልጠና አጠናቅቄ በአብራሪነት የተመረቅሁት በህዳር 1994 ዓ.ም ሲሆን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ተኩል በዘለቀው የሥራ ዘመኔም በረዳት አብራሪነት ለ4ሺ475 ሰዓታት አብርሬያለሁ፡፡
ከዚም ከተለያዩ ፈተናዎች፣ ምዘናዎችና ግምገማዎች በኋላ፣ እድገት ተሰጥቶኝ በዋና አብራሪነት (የካፒቴን) ሥልጠና ጀመርኩኝ፡፡ አስፈላጊውን የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና እንዳጠናቀቅሁም ከመጀመሪያ በረራዬ ከሰባት ዓመት ተኩል በኋላ በ2002 ዓ.ም ካፒቴን ሆንኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከአንድ ሺ በላይ ሰዓታት አብርሬአለሁ፡፡
ምንጭ፡ (“ተምሳሌት፡ ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” ከተሰኘው አዲስ መፅሃፍ ላይ የተቀነጨበ፤ 2007 ዓ.ም)

No comments:

Post a Comment