Sunday, 26 April 2015

ጌትነት እንየው የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሀዘን መግለጫ ስነ ስርዓት ላይ “እኛው ነን “ በሚል ርዕስ ያቀረበውን ግጥም ይመልከቱ



እኛው ነን
(በጌትነት እንየው)


እኛ ነን; እኛው ነን; እኛ የዛሬዎች
በአጭር የተቀጩ ሩቅ መንገደኞች
ሰላሳ ህልመኞች፣ ሰላሳ ተስፈኞች፣ ሰላሳ ወጣቶች
ሀገር እንደሌለው በሰው ሀገር ምድር ሲቀላ አንገታቸው
ወገን እንደ ሌለው ከሰው ሀገር ባህር ሲቀየጥ ደማቸው
በአገር ቁጭ ብለን ከአለም ጋራ እያየን
ከሬት የመረረ ከቋጥኝ የሚከብድ
ከቶን የሚያቃጥል ከብራቅ የሚያርድ
ሀገር ያህል መርዶ በሰንበት አመሻሽ በአገር የተሸከምን
በገዛ ሞታችን እዝን የተቀመጥን፡፡
ካሳለፍነው ህይወት ካለፈው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች፣
የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ
ከፋይም ተቀባይ እኛው ነን ባለእዶች፡፡


እኛው ነን….


ከቅጣትም ቅጣት ከመርገምትም መርገት፣
የገዛ አንገታችን በስለት ሲቀላ
የገዛ ደማችን ባህሩን ሲያቀላ
የራሳችንን ሞት ቆሞ መመልከቱ፣
ምን ያህል ነው ፍሙ ምን ያህል ይከብዳል ሰቆቃው እሳቱ?
ምን ያህል ነው ሸክሙ? ምን ያህል ይዘፍቃል? መከራው ክብደቱ
ምን ያህል ይጠልቃል? ምን ያህል ይሰማል? መጠቃት ስለቱ
ሀዘን ነው? ቁጣ ነው? ጸጸት ነው? ምንድነው መጠሪያው?
ምንድነው ስሜቱ?
እውን ይህን መአት ይኼን የእኛን መቅሰፍት
ቋንቋዎች በቃላት ችለው ይገልጹታል?
እውን ይህ ስቃይ፣ ይህንን ሰቆቃ፣ እናትና ሀገር ሸክሙን ይችሉታል?


እኛው ነን እኛው ነን…


ለዚህ ክፉ እጣችን ለዚህ መርገምታችን
ለአለም ለፈጣሪ አልፈታ ላለው እንቆቅልሻችን
መነሻም መድረሻም ጥያቄዎች እኛ መልሶችም እኛው ነን፡፡
እኛው ነን የገፋን፣ እኛው ነን የከፋን
እኛው ነን ያጠፋን ፣እኛው ነን ያጠፋን፡፡
ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን ተስኖን
ሰፊ አገር ይዘን በሀሳብ እየጠበብን
በፍቅር ተሳስቦ አብሮ መራመዱ አቀበት የሆነን
ቂም እየቆነጠርን፣ ቂም እየመነዘርን
በዛሬ መንጋጋ የትናንቱን ድርቆሽ የምናመነዥክ
በዛሬ ምድጃ የትናንቱን አመድ ታቅፈን የምንሞቅ
ባንድ ላይ ከመጓዝ በየፊና ሩጫ አረፋ ምንደፍቅ


እኛው ነን እኛው ነን….


ከእምነት የተፋታን ከፈጣሪ የራቅን፡፡
እኛው ተጋፊዎች፣ እኛው ተገፊዎች
እኛው አሳዳጆች፣ እኛው ተሳዳጆች
ካሳለፍነው ህይወት ካለፍነው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች
እኛው ነን እኛው ነን እኛ የዛሬዎች
የነገ፣ የታሪክ ያገር ባለእዳዎች፡፡


እኛው ነን….


በንፍገት በስስት በስግብግብ መዳፍ
ከድሆች ጉሮሮ ካፋቸው መንጭቀን
ሌሎችን ረግጠን ሌሎችን ጨፍልቀን
በሌሎች ጀርባ በሌሎች ጫንቃ ላይ ወደ ላይ መሳቡ ቅንጣት የማይጨንቀን
በማስመሰል ጥበብ በአድርባይ አንደበት በሸፍጥ የሰለጠን
ከብዙዎች ድርሻ ተሻምተን ተናጥቀን
ላንድ ለራሳችን በወርቅ ላይ አልማዝ በህንጻ ላይ ህንጻ
ስንቆልል ስንከምር የማይሰቀጥጠን፣
የመንፈስ ድውዮች የንዋይ ምርከኞች
የወንበር ሱሰኞች የሆድ አምላኪዎች
ከሰውነት ወርደን በነፍስ የኮሰመን የስጋ ብኩኖች
የራሳችን ሀጢያት የራሳችን ሲኦል እኛው ነን መርገምቶች


እኛው ነን!


በዚህ ሁሉ ግና …..
መቼም ቢሆን መቼ ሰው ይሞታል እንጂ ተስፋ አይሞትምና
በመንገድ የቀሩት ወጣቶቻችን
በአጭር የተቀጨው ሀሳብ ምኞታቸው
ተስፋ አለን ተስፋቸው፡፡
በአገራቸው አፈር በታናሾቻቸው
ነገ ውብ ይሆናል ለምልሞ ይጸድቃል በዛሬው ደማቸው
ዛሬ የመከነው ውጥን ርዕያቸው
በጊዜና በአገር ነገ እውን ይሆናል ይፈታል ህልማቸው
ይህ ነው መጽናኛችን ይህ ነው መዕናኛቸው፡፡

No comments:

Post a Comment