Saturday, 21 November 2015

የኢትዮጵያ ችግር፣ ከቢቢሲ ዘገባም ይብሳል!

ታዲያ፤ በእንዲህ አይነት ድህነት መሃል፣ መንግስት፣ “በእህል ምግብ ራሳችንን ችለናል” ብሎ ሲያውጅ፣ አይገርምም? ባለፉት አስር ዓመታት፣ ፈጣን እድገት ታይቷል፣ ብሎ መናገር፣ አንድ ነገር ነው። ከድህነት እንደተላቀቅንና የምግብ እጥረት እንደተቃለለ አድርጎ መናገር ደግሞ፣ ሌላ ነገር ነው። የኢትዮጵያ ድህነት፣ ከብዙዎቹ ድሃ የአፍሪካ አገራትም እንደሚብስ ይረሳዋል መሰለኝ።


በኢትዮጵያ የረሃብ አደጋ ላይ ያተኮረው የቢቢሲ ዘገባ፣ ይሄውና ብዙዎችን እያወዛገበ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል። 

የጋዜጠኛውን ዘገባ፣ በአድናቆት የሚያሞግሱ በርካታ ሰዎች፣ ‘መንግስት፣ የረሃብ አደጋውን ችላ ብሏል፤ መረጃም ደብቋል’ በማለት መራራ ትችት አውርደውበታል። 

መንግስት በበኩሉ፣ በቢቢሲ ዘገባ ተቆጥቶ፣ በየአቅጣጫው ሲያስተባብል ሰንብቷል። በአንድ የዜና ዘገባ፣ እንዲህ ግራ ቀኙ በውዝግብ መተራመሱ አይግረማችሁ። እንዲያውም፣ በዘገባው መሃል በገባች አንዲት አጭር ዓረፍተነገር ነው፣ አገር ምድሩ የተናወጠው። 

“በአንድ አካባቢ፣ በየእለቱ ሁለት ህፃናት እንደሚሞቱ ዩኤን ይገልፃል” ብሏል የቢቢሲው ጋዜጠኛ። “The UN says that in one area, two babies were dying every day”... በ13 ቃላት የተነገረች አጭር አረፍተነገር ናት። ግን የተራራ ያህል፣ ከፍተኛ ድንጋጤ፣ ቁጣ፣ እና ውዝግብን ፈጥራለች። 

በጣም አስደንጋጩ ነገር... ምን መሰላችሁ? ያቺ፣ አስደንጋጯ ዓረፍተነገር፣ ከእለት ተእለት፣ ከዓመት ዓመት፣ የአገራችን የዘወትር ሕይወት ናት።

 • የኢትዮጵያ ድህነት፣ የሕፃናት ሞት... ከባድ ድርቅ ባያጋጥም እንኳ፣ ‘ደህና’ በሚባለው ዓመትም፣ ብዙ ሕፃናት የሚሞቱባት፣ እጅግ ድሃ አገር ናት - ኢትዮጵያ። በየቀኑ፣ ከ500 በላይ ሕፃናት እንደሚሞቱ ታውቃላችሁ? በዓለም ወይም በአፍሪካ ማለቴ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ! ብዙዎቻችን ይህንን አናውቅም። ለምን? የአገራችንን የድህነት መጠን፣ በደንብ አንገነዘበውም። አምና 190ሺ ህፃናት ሞተዋል - እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት። እንዲሁ ልናስበው ስለማንፈልግ እንጂ፣ ይሄ ሚስጥር አይደለም። የዩኤን፣ የዩኤስኤአይዲ፣ የአለም ባንክ ሪፖርቶች ላይ በየዓመቱ የሚመዘገብ፣ ቁጥር ነው። ካቻምና ወደ ሁለት መቶ ሺ ገደማ፣ ህፃናት ሞተዋል። ዘንድሮም፣ እንደዚሁ...

በመላ አገሪቱ፣ በየወረዳው፣ በየቀኑ... ከ500 የሚበልጡ ሕፃናት ይሞታሉ። ለምን? ከቅርባችን የምናገኘው ትልቁ የሞት መንስኤ፣ ድህነት ነው። በርካታ ህፃናት፣ ተርበው ባይሞቱም እንኳ፣ በምግብ እጥረት ይዳከማሉ። ከመቶ ሕፃናት መካከል፣ አርባ ያህሉ በምግብ እጥረት የተጎዱ ናቸው። አስር በመቶ ያህሉ ደግሞ፣ ሰውነታቸው እጅጉን ይመነምናል። በሽታ የመቋቋም አቅማቸው ይዳከማል። እናም፣ ለወባ ወይም ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሲጋለጡ፤ ብዙዎቹ ይሞታሉ። ማለትም... በየእለቱ 500 ህፃናት!

 የአገራችን ድህነት፣ የዚህን ያህል የከፋ ነው። ...ከሦስት ሰዎች አንዱ፣ ከሦስት ሕፃናት አንዱ፣ በምግብ እጥረት የሚቸገረው፣ ሁልጊዜ ነው። መደበኛ የዘወትር ሕይወት! (ድርቅ በሌለበት ዓመትም ጭምር... ወይም፣ “በእህል ምግብ፣ ራሳችንን ችለናል” በተባለበት ዓመትም ጭምር)። ታዲያ፤ በእንዲህ አይነት ድህነት መሃል፣ መንግስት፣ “በእህል ምግብ ራሳችንን ችለናል” ብሎ ሲያውጅ፣ አይገርምም? 

ባለፉት አስር ዓመታት፣ ፈጣን እድገት ታይቷል፣ ብሎ መናገር፣ አንድ ነገር ነው። ከድህነት እንደተላቀቅንና የምግብ እጥረት እንደተቃለለ አድርጎ መናገር ደግሞ፣ ሌላ ነገር ነው። የኢትዮጵያ ድህነት፣ ከብዙዎቹ ድሃ የአፍሪካ አገራትም እንደሚብስ ይረሳዋል መሰለኝ። 

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአገሪቱ ድህነትና ረሃብ፣ የመንግስት ችግር ብቻ የሚመስላቸውም ሞልተዋል - የአገሪቱን የድህነት መጠን በትክክል ባይገነዘቡት ነው። ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት፣ ‘ከዓለም አንደኛ’ በተባለ ፍጥነት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢያድግ ብላችሁ አስቡ። ድንቅ ነው። ግን፣ “ከድህነት ለመላቀቅ የሚረዳ፣ ጅምር ጉዞ”... ከመሆን አያልፍም። ያኔም፣ ከአብዛኞቹ ድሃ የአፍሪካ አገራት በታች፣ ከመሆን አያድነንም። 

• ስለየትኛው አገር ነው የምናወራው? አንድ ሁለት መረጃዎችን ልድገምላችሁ።... በአመት አንዴ፣ ስጋ ለመብላት የሚቸገር ሕዝብ ያለባት፣ በጣም ድሃ አገር ውስጥ ነን ያለነው። 

ከ15 ሚሊዮን ቤተሰቦች መካከል፤12 ሚሊዮን ቤተሰቦች፣ በአመት አንዴ፣ ቢያንስ ቢያንስ ለዓመት በዓል፣ በግ ወይም ፍየል ለማረድ አቅም የላቸውም። እሱስ ይቅር። 6 ሚሊዮን የገበሬ ቤተሰቦች፣ የእርሻ በሬ የላቸውም።

 እዚህች አገር ውስጥ፣... “የከብቶች እበትና ትንፋሽ፤ ለአለም ሙቀት መጨመር አደጋ ስለሆነ፤ እርምጃ መውሰድ አለብን” ተብሎ ሲነገር ይታያችሁ። በስህተት ያመለጠ፣ ተራ ንግግር እንዳይመስላችሁ! ለዚያውም፤ በአመታዊ የፓርላማ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነው፤ ይሄ የተነገረው። የመንግስትና የኢህአዴግ ጥፋት ከመሰላችሁም ተሳስታችኋል። ብዙዎቹ ምሁራንና ብዙዎቹ ፓርቲዎች የሚስማሙበትና የሚደግፉት ጉዳይ ነው። 

“የአካባቢ ጥበቃ” እና “የአለም ሙቀት መጨመር”፣ “አረንጓዴ ልማት” ... እየተባለ፣ ሌትተቀን በየሚዲያው የጋዜጠኛ፣ የምሁር፣ የፖለቲከኛና የባለስልጣን፣ የገዢና የተቃዋሚ ፓርቲ ተመሳሳይ ዲስኩር የምንሰማው ለምን ሆነና! የከብቶች ትንፋሽና እበት ያስጨንቃቸዋል - በአመት አንዴ ስጋ ለመብላት የሚቸገር ሕዝብ በሞላበት ድሃ አገር ውስጥ ሆነው። 

ከአስር የገበሬ ቤተሰብ መካከል አራቱ፣ የእርሻ በሬ የላቸውም... እንዲህ፣ ድህነት ክፉኛ በደቆሳት አገር ውስጥ ሆነን፤ “የከብቶች እበት፣ ለአለም ሙቀት አደገኛ ነው... ወይም አደገኛ ሊሆን ይችላል” ... ብለን እንጨነቅ? ይህም ብቻ አይደለም። 

የኢትዮጵያ ገበሬዎች፣ በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ አጠቃቀም፣ እጅጉን ወደ ኋላ ቀርተው እንደቆዩ ይታወቃል። ያው፣ በድህነትስ ወደ ኋላ ቀርተን የለ! 

ታዲያ፣ በዚህችው አገር፣ ምርጥ ዘርንና ማዳበሪያን በማጥላላት፣ የተቃውሞ ዘመቻ ሲካሄድ ማየት ነበረብን? ‘ምርጥ ዘርን መጠቀም፣ ነባር የዘር ዓይነቶችን ማግለል ነው’ የሚል ተቃውሞ፤ እንደ ቁምነገር ተቆጥሮ ሲስተጋባ አይገርምም? ለዚያውም፣ በመንግስታዊ ተቋም... ለዚያውም በምሁራን... ለዚያውም፣ መዓት ሕዝብ በተራበበት ዓመት፡፡ ስለየትኛው አገር ነው የሚያወሩት? ሌላስ? 

26ሺ የገጠር ቤተሰቦች፣ “በፀሐይ ኃይል፣ ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ መሳሪያ” ተገጥሞላቸዋል የሚል ሪፖርት አለላችሁ። ወጪውን ደግሞ ልንገራችሁ፤ 270 ሚሊዮን ብር! 

መሳሪያው የተገጠመው፤ ለገጠር ጤና ጣቢያ፣ ለትምህርት ቤትና ለመሳሰሉት ቢሆን እሺ። ለምን? ቀን ላይ፣ ለስራ ነው፣ ኤሌክትሪክ የሚፈልጉት። ቀን ላይ፣ ብዙውን ጊዜ፣ ፀሐይ ይኖራል። በመኖሪያ ቤት ወይም ጎጆ ውስጥ ግን፣ በአብዛኛው፣ ማታ ማታ ነው ኤሌክትሪክ የሚያስፈልገን። ግን፣ ማታ ፀሃይ የለም። እና፣ ይሄ ሁሉ ብር የሚባክነው፣ ለምንድነው? 

“ምናልባት፣ ቀን ላይ ምግብ ለማብሰል ይጠቀሙበት ይሆናል” እንበል? ዋናውን የኤሌክትሪክ መስመር፤ ወደ ሁሉም የገጠር ቤተሰብ ማድረስ አይቻልም። ስለዚህ፣ ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም፣ የፀሃይ ሃይል መሳሪያ ይገጠምላቸው? በአገሪቱ ድህነት ላይ፣ ተጨማሪ ሸክም ቢሆንም... እሺ ይሁን። ግን፣ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ፣ ለኮንዶምኒዬም ቤቶችም፣ ‘በፀሐይ ሃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ መሳሪያ’ ይገጠምላቸዋል የሚል መግለጫ በቅርቡ ሰምተናል። እንዴት ነው ነገሩ? ኤሌክትሪክ የሚቸግረን፣ በማታ ነው። ማታ ደግሞ፣ ፀሐይ የለም። ይሄ ግልፅ አይደለም? ደግሞምኮ፣ ኮንዶምኒዬም ቤቶቹ፣ እንደማንኛውም የከተማ ቤት፣ መደበኛው የኤሌክትሪክ መስመር ይዘረጋላቸዋል። የፀሐይ ሃይል መሳሪያው፣... ተጨማሪ ነው። ተጨማሪ ጥቅም የለውም። ተጨማሪ ወጪ ብቻ! መሳሪያውን ለመግጠም፣ በገጠር፣ ለአንድ ቤተሰብ፣ ከ10ሺ ብር በላይ ወጪ ያስከትላል። 

ፍሪጅ፣ ኤሌክትሪክ ምጣድ፣ ካውያና ወዘተ በበዛበት ከተማማ፣ ለአንድ መኖሪያ ቤት፣ የ10ሺ ብር መሳሪያ አይበቃውም። ምንም ተጨማሪ ጥቅም ለማያስገኝ ነገር፣ እንዲህ በከንቱ፣ የድሃ አገር ሃብት ለማባከን መቻኮል ምንድነው? በደፈናው፣ “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “ታዳሽ ሃይል”፣ “አረንጓዴ ልማት” ለሚሉ ቃላት ነው፤ ያን ሁሉ ሃብት በከንቱ የምንገብረው። እና ደግሞ፤ ዞር ብለን፣ ስለ ኢትዮጵያውያን ረሃብ፣ ተቆርቋሪ ሆነን እናወራለን። እንዴ... ካሁን በፊት፣ በነፋስ ተርባይን ሳቢያ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የድሃ አገር ሃብት ባክኗል። እስካሁን ከተተከሉት ተርባይኖች ይልቅ፣ በ5 ቢሊዮን ብር የተገነባ ግድብ ይሻላል። ብዙ የኤሌክትሪክ መጠን ያመነጫል። ለነፋስ ተርባይኖቹ የወጣው ወጪ ግን፣ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ቀላል ብክነት አይደለም። የአስር ቢሊዮን ብር ብክነት? ዘንድሮ በድርቅ ለተጠቁ ሰዎች የሚያስፈልግ እህል፣ አሟልቶ ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ነው። 

አሁን ደግሞ፣ “የፀሐይ ሃይል” እየተባለ... ሃብት ይባክናል። አላዋቂነትና ቀልድ አልበዛም? አገሪቱ፤ በኤሌክትሪክ ሃይልና በብልፅግና የተንበሸበሸች ብትሆን ኖሮ፣... ብክነቱን ስንመለከት፣ ... “ጥጋብ ነው” ብለን ባጣጣልነው ነበር። ኢትዮጵያ ግን፣ ከሃብታም አገራት ጋር ሳይሆን፣ ከድሃ የአፍሪካ አገራት ጋር ስትነፃፀር እንኳ፣ በድህነትና በኤሌክትሪክ እጦት፣ ወደኋላ የቀረች ጨለማ አገር ናት። በእርግጥ፣ ሌሎች ድሃ የአፍሪካ አገራትም... ያው ጨለማ ናቸው። ግን፣ ከእነሱ ጋር ሲነፃፀር፣ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ፍጆታ፣ ግማሽ ያህል እንኳ አይደርስም። እና እዚህች አገር ውስጥ ነው፤ የነፋስ ተርባይን እና የፀሃይ ሃይል እየተባለ፣ ሃብት የሚባክነው። 

ይሄ ሁሉ ሃብት የሚባክነው ደግሞ፤ “አረንጓዴ ልማት”፣ “የአለም የሙቀት መጠን”፣ “የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት”፣ “የአካባቢ ጥበቃ”... በሚሉ ዝባዝንኬ መፈክሮች ነው! “ካርቦንዳይኦክሳይድ”? ኢትዮጵያ ጨርሶ የሌለችበትን! መች ነዳጅ ለመጠቀም በቃንና! 

“የአለምን ሙቀት እንዲጨምር ያደርጋል” የሚባለው ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ከሞላ ጎደል፣ ከነዳጅ ፍጆታ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ፣ እጅግ ድሃ ከመሆኗ የተነሳ፣ የነዳጅ ፍጆታዋ፣ ከአለም እጅግ... እጅግ ዝቅተኛ ነው። ከቁጥር የሚገባ አይደለም። 

ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የ150 ሰዎች የነዳጅ ፍጆታ፣ በበለፀጉት አገራት፣ የአንድ ሰው ፍጆታ ነው። የበለፀጉትን አገራት እንተዋቸው። አጠገባችን ያሉት ድሃ የአፍሪካ አገራት እንኳ፣ የነዳጅ ፍጆታቸው ከኢትዮጵያ በአስር እጥፍ ይበልጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በፍፁም በፍፁም፣ ስለ ‘ኮርባንዳይኦክሳይድ’ መወራት አልነበረበትም። 

ግን፣ ዋና ወሬ አድርገነዋል። ምን ማውራት ብቻ! በዚሁ ዝባዝንኬ መፈክር ሰበብ፣ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ሃብት እንዲባክን ይወስናሉ። የት አገር ያሉ እየመሰላቸው ይሆን? ግን፣ ብዙዎቻችን፣ ብክነቱን እንፈቅዳለን፤ እንደግፋለን፤ እናጨበጭባለን። 

 ያው፣ መንግስትን አምርረው የሚተቹ ብዙ ፖለቲከኞችና ዜጎችም፣ አገሪቱን በወጉ አያውቋትም። በአንዱ ፓርቲ ምትክ፣ ሌላ ፓርቲ ስልጣን ላይ ቢወጣ፣ አንዱ ባለስልጣን ተሽሮ፣ በቦታው ሌላ ቢሾም... በአንዳች ተዓምር፣ በማግስቱ፣ የኢትዮጵያ ድህነትና ችጋር፣ ብን ብሎ የሚጠፋ ይመስላቸዋል። ወይም... በአመት፣ ቢበዛ ደግሞ በሁለት ዓመት፣ ዘገየ ከተባለ ደግሞ በአምስት ዓመት፣... ብልፅግና እንዲፈጠር ይመኛሉ። የአገሪቱን የድህነት አይነትና መጠን በወጉ አልተገነዘቡትም። 

አንዳንዶቹ ደግሞ፣ ...የሆነች ያህል ገንዘብ ብናዋጣና ብንለግስ፣ የአገሬው ችግር ሁሉ መፍትሄ የሚያገኝ ይመስላቸዋል። በቃ፤ ያኔ... የተቸገረ አዛውንት ሁሉ በምቾት ይኖራል።... የታመመ ሁሉ፣ ያሻውን ያህል ይታከማል።... ምግብና መጠለያ ያጣ ሰውም፣ ከችጋር ነፃ ይሆናል... ብለው ያልማሉ - በመዋጮና በምፅዋት። እውነታው ግን፣ የአገሪቱን እንቁላሎች ሁሉ፣ ለህዝቡ እናካፍል ብለን ብናዋጣና ብንለግስ፣ አዳሜ... በዓመት ከአንድ እንቁላል በላይ አይደርሰውም። የሌለንን እንቁላል ከየት አምጥተን እንለግሳለን? ሌላውም ችግር ተመሳሳይ ነው። ለልገሳ የሚሆን ብዙ ሃብት የለም። አገሬው ድሃ ነው። ይህንን ከፍተኛ ድህነት፣... 

እውነታውን ከምር ብንገነዘብ ኖሮ፣ በቢቢሲው ዘገባ፣ ቅንጣት የምንወዛገብበት ምክንያት አይኖርም ነበር። ይልቅ፣ መፍትሄ ለመፈለግና ለማበጀት እንተጋ ነበር።እውነታውን ሳንገነዘብ፣ ወይም ለመገንዘብ ፈቃደኛ ሳንሆን የምንቀጥል ከሆነ ግን፤ መፍትሄውን የማሰብና የማግኘት ተስፋ አይኖረንም። ወይ፣ በዝባዝንኬ ሰበቦች፣ ሃብትን እናባክናለን። አልያም፣ ፓርቲና ባለስልጣን በማፈራረቅ ብቻ፣ ተዓምረኛ ለውጥ የምናመጣ መስሎን፣ ያለፋታ እየተናቆርን፣ በአዙሪት ጉዞ ሕይወታችንን እናባክናለን። በሌላ አነጋገር፤ የቢቢሲ ጋዜጠኛ፣ ችግራችንን እስኪነግረን ድረስ እየጠበቅንና መወዛገቢያ እያደረግን፤ እኛው እንባክናለን።

No comments:

Post a Comment