Saturday, 14 May 2016

የስኳር ፕሮጀክቶች እንዳልተሳኩና አገሪቱን ለእዳ እንደዳረጉ በይፋ ተነገረ

2   ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ፤ 40 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ውስጥ እዳ

የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች፤ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ተጠያቂ አድርገዋል - ክፍያ ወስዶ የፋብሪካ ግንባታዎችን በእንጥልጥል አስቀርቷል በማለት፡፡ 
ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ፤ የስኳር ኮርፖሬሽንን ኃላፊዎች ለከሰምና ለተንዳሆ ግድቦች መጓተት የፌደራል የውሃ ስራዎች ድርጅትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ 

አዲስ አድማስ፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የስኳር ፕሮጀክቶች እንደማይሳኩ ተጨባጭ መረጃዎችንና ትንታኔዎችን በማቅረብ በተደጋጋሚ ዘግቧል፡፡ 

“ውሎ አድሮ ወደ ቀውስ ማምራቱ አይቀርም”…አዲስ አድማስ 2003 ዓ.ም
“የስኳር ፋብሪካዎችን እቅድ ማሳካት ፈጽሞ አይቻልም” 2005 ዓ.ም
“መንግስት …10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች መገንባት ይችላል ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ፣ ‹ተአምር› የማየት ረሃብ ይዟችኋል”…2006 ዓ.ም 

የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች ሰሞኑን ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፤ የመንግስት ነባር የስኳር ፋብሪካዎች ውጤታማ አለመሆናቸውን ገልፀው፤ አዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች ክፉኛ ተዝረክርከው የብዙ ቢሊዮን ብር ኪሳራ እያስከተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ የሀብት ብክነት፣ ህሊናን የሚያቆስል የአገር ጉዳት እንደሆነ ሃላፊዎቹ ጠቅሰው፤ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ እንደተጠራቀመ ገልፀዋል፡፡ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ሀብት በፈሰሰባቸው ፕሮጀክቶች፤ በየአመቱ ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር በማምረትና አብዛኛውንም ኤክስፖርት በማድረግ እዳው ከመመለስ አልፎ አትራፊ እንደሚሆን ታስቦ ነበር። አልተሳካም እንጂ። ጉዳቱ በዚህ አያበቃም ፕሮጀክቶቹ ከመዝረክረካቸው የተነሳም፤ እቅዱ መቼ እንደሚሳካ እንደማይታወቅ የኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎቹ ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን አስገራሚ ሪፖርት ያዳመጡ የፓርላማ አባላት፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቶች ኦዲት እንዲደረጉ ወስነዋል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም የፕሮጀክቶቹ ኪሳራ በይፋ በተገለፀ ማግስት፣ ጉዳዩ የአገር ዋና መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ነገር ግን፣ የፕሮጀክቶቹ የውድቀት መረጃዎች ተገቢ ትኩረት ሳያገኙ በመቆየታቸው እንጂ፤ የፕሮጀክቶቹ ቀውስ አሁን ድንገት የተፈጠረ አይደለም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አድማስ የቀረቡ ተከታታይ ዘገባዎችን መመልከት ይቻላል፡፡  

በቅድሚያ፤ የስኳር ፕሮጀክቶችና እቅዶችን በጥቅሉ ለመቃኘት፤ ከአንድ የአዲስ አድማስ ዘገባ፤ ጥቂት የመጀመሪያ አንቀጾችን ላስነብባችሁ.... መንግስት ቢዝነስ፣ ውስጥ ገብቶ አገሪቱን ልማት በልማት ሲያደርጋት ለማየት የሚፈልጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ደግሞም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ቃል የሚገባ መንግስት አያጡም።  ቢያንስ ቢያንስ በምኞት ደረጃ የልብ የሚያደርስ እቅድ  በሽ በሽ ነው። ልማታዊ መንግስት፣ እቅዶች ያንሱታል ተብሎ አይታማም። የስኳርን ምርት በብዙ እጥፍ ለማሳደግ የወጡ እቅዶችን ብቻ ብናይ እንኳ፣ ያስጎመጃሉ።

…በ1997 የወጣው የአምስት አመት እቅድ፤ የአገሪቱን የስኳር ምርት በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድግ ይገልፃል። በወቅቱ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል የነበረው አመታዊ የስኳር ምርት፤  በ2002 ዓ.ም ወደ 15 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ የያኔው እቅድ ያብራራል። ያጓጓል አይደል?  ነገር ግን መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፣ እቅዶች አይሳኩም። የመንግስት ጉድለት፣ የፓርቲ ድክመት ወይም የባለስልጣናት ስንፍና አይደለም ችግሩ። በቃ፤ የትም አገር፣ የትኛውም ፓርቲ ስልጣን ቢይዝ፣ ማናቸውም ባለስልጣን ቢሾም አልያም አንዱ ተሽሮ በሌላው ቢተካ፣ ለውጥ የለውም። የመንግስት ቢዝነስ ውሎ አድሮ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ይበዛል፤ እቅዶቹ ሃብት እያባከኑ ይጓተታሉ፤ ምኞት ብቻ ሆነው ይቀራሉ።

በእርግጥ የስኳር ምርት በአምስት እጥፍ ለማሳደግ የወጣው እቅድ፣ ምኞት ብቻ ሆኖ እንደማይቀር፣ በ1998 ዓ.ም የወጣው የመንግስት ሪፖርት ያበስራል። በፊንጫ፣ በወንጂና በመተሃራ የስኳር ፋብሪካዎች ላይ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ይጠቅሳል፤ በተንዳሆም አዲስ የስኳር ፕሮጀክት እየተፋጠነ እንደሆነ ያወሳል። (የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባሳተመው አመታዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ገፅ 79-81 ይመልከቱ - PASDEP Annual progress report 2005-2006)።
በወንጂ… አሮጌው ፋብሪካ በአዲስ ተተክቶ፤ አመታዊ ምርቱን ከሰባት መቶ ሺ ኩንታል ወደ 2.8 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ሪፖርቱ ይገልፃል።

በፊንጫ፤ 800ሺ ኩንታል አመታዊ ምርቱን ወደ 2.7 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ መታቀዱን ይዘረዝራል። በመተሃራም እንዲሁ፣ የከሰም ግድብ ሲጠናቀቅ 12 በላይ ሄክታር በማልማት፤  የፋብሪካውን አቅም 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 3.75 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ሪፖርቱ ያወሳል። አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር በማምረት 1999 .  ስራ እንዲጀምር በታሰበው አዲሱ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ 2002 . አመታዊ ምርቱ 6 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ሪፖርቱ ይጠቁማል።
በድምር 15 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑ ነው።
ያስጎመጃል?

እነዚህ በ1997 ዓ.ም የታወጁ እቅዶች አልተሳኩም። የስኳር ምርት ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ፈቅ ማለት አልቻለም፡፡
እናም በ2002 ዓ.ም የወጣው የአምስት አመት እድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ፤  ተጨማሪ የስኳር ፕሮጀክቶችን በማካተት አዲስ እቅድ አቀረበ። የበለስ፤ የወልቃይትና የኩራዝ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ይዞ የወጣው አዲስ እቅድ፤ አስር የስኳር ፋብሪካዎች እንደሚገነቡ ይገልፃል፡፡

በ2007 ዓ.ም የስኳር ምርት ከ22 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ይሆናል ተብሎም ተበሰረ በያኔው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ፡፡ 
የ1997 እቅዶች እንዳልተላኩ የዘገባው አዲስ አድማስ፤ አዲሱን እቅድ በተመለከተ ያኔውኑ ትንታኔ እንዳቀረበ ይታወሳል፡፡ 
የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በታወጀበት ወቅት በ2003 ዓ.ም፣  በአዲስ አድማስ የወጣው ጽሑፍ፤ እቅዱ አሳሳቢ መሆኑን ለማስረዳት የስኳር ፕሮጀክቶችን በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡ እንዲህ ይላል 

“ባለፉት ጥቂት አመታት፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻና ቁጥጥር እየሰፋ መጥቷል። በጣም አሳሳቢው ነገር ደግሞ፤ ይበልጥ እየሰፋ እንዲሄድ መታቀዱ ነው።  በርካታ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች በመንግስት ባለቤትነት እንዲቋቋሙ ታቅዷል። ፋብሪካዎቹ የሚገነቡትም በመንግስት ድርጅት ነው (በብረታ ብረት ኮርፖሬሽን)” በማለት አሳሳቢነቱን ይገልፃል፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻ እየተስፋፉ ሲሄድ፣ የሙስናና የብክነት አደጋ እንደሚበራከት ጽሑፍ ጠቅሶ፣ በየትኛውም አገር ውጤቱ ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻ ሲሰፋ፣ ውሎ አድሮ ወደቀውስ ማምራቱ አይቀርም በማለትም ያስጠነቅቃል፡፡ 
ውሎ ይደር እንጂ የስኳር ፕሮጀክቶቹ፤ ቀውስ እንደሚያስከትሉና ኪሳራቸው እንደሚበዛ የተዘገበው፤ በየዘመኑና በየአገሩ የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ ውድቀቶችን በማገናዘብ ብቻ አይደለም፡፡ በተጨባጭ የአገራችን የስኳር ፕሮጀክቶችን የወደፊት አዝማሚያ በግልጽ የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎች በዝርዝር ተዘግበዋል - በአዲስ አድማስ፡፡ 

በ2004 ዓ.ም መግቢያ ላይ የወጣውን ዘገባ ተመልከቱ፤ ለስኳር እርሻ ታስበው የተጀመሩ የከሰምና የተንዳሆ ግድቦች ላይ ያተኮረው ይሄው ዘገባ፤ የግድቦቹ ግንባታ እየተጓተተ የበርካታ ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደተደራረበበት ለበርካታ አመታት መዝለቁን ይዘረዝራል፡፡ ጥቂት አንቀፆችን ላስነብባችሁ፡፡ … ለግድቦቹ ግንባታ በ1999 ዓ.ም ተጨማሪ በጀት እንደተመደበ የሚገልፀው የገንዘብ ሚኒስትር ሰነድ፣ በዚያው አመት ግንባዎቹ እንደሚጠናቀቁ ይገልፃል፡፡ 

“በ1999 በጀት አመት፣ የሁለቱንም ግድቦች ቀሪ ስራ በማጠናቀቅ ውሃ እንዲይዙ ማድረግና በከሰም 5ሺ ሄክታር፣ በተንዳሆ 10ሺ ሄክታር የመስኖ መሬት ዝግጅትን የማጠናቀቅ ስራዎች ታቅደዋል” ይላል ሰነዱ (ገፅ 162)።
(ግን፣ የግድቦቹ ግንባታ በዚያው ዓመት አልተጠናቀቀም፡፡ በቀጣዩ አመት እንደገና ተጨማሪ ገንዘብ የሚመድብ የበጀት ሰነድ ፀደቀ)
“በ2000 በጀት አመት የሁለቱንም ግድቦች ቀሪ ስራ በማጠናቀቅ ውሃ እንዲይዙ ማድረግና በከሰም 3ሺ ሄክታር፣ በተንዳሆ 10ሺ ሄክታር የመስኖ መሬት ዝግጅትን የማጠናቀቅ ስራዎች ታቅደዋል” ይላል ሰነዱ። በከሰም ለመስኖ እርሻ የሚዘጋጀው መሬት ወደ ሶስት ሺ ዝቅ እንዲል ከመደረጉ ውጭ፤ የ2000 ዓ.ም እቅድ ከቀዳሚው የ1999አ.ም እቅድ የተለየ ነገር የለውም። ፅሁፉ ራሱ “ኮፒ - ፔስት” የተደረገ ይመስላል። 

ነገር ግን አሁንም እንደታቀደው አልተሳካም። የ2001ን የበጀት ሰነድ ገፅ 196 መመልከት ትችላላችሁ። በዚሁ አመት ለውሃ ሚኒስቴር ከተያዘው፤ 1.7 ቢ ብር የልማት በጀት ውስጥ፤ 471 ሚ. ብር ለከሰምና ለተንዳሆ  የሚውል ሆኗል፡፡ የቀዳሚዎቹ ሁለት አመታት የግድብ ግንባታ እቅዶች ሳይሳኩ በመቅረታቸው፤ እንደገና በርካታ መቶ ሚሊዮን ብር አስፈልጓቸዋል። ለምን? ያንኑን ስራ ለማከናወን።  

“በ2001 በጀት አመት የሁለቱንም ግድቦች ቀሪ ስራ በማጠናቀቅ ውሃ እንዲይዙ ማድረግና በከሰም 3ሺ ሄክታር፣ በተንዳሆ 10ሺ ሄክታር የመስኖ መሬት ዝግጅትን የማጠናቀቅ ስራዎች ታቅደዋል” ይላል የ2001 የበጀት ሰነድ፤ 
የግድቦቹ ስራ፤ “ዘንድሮ ይጠናቀቃል” እየተባለ ስንቴ እየታቀደ፤ ስንቴስ ተጨማሪ  ገንዘብ እየተመደበ፣ እዚያው ባለበት እየረገጠ ይቀጥላል? 
አሁንም ስራው እንደታቀደለት የሚሳካ ሆኖ አልተገኘም። ምን ይሄ ብቻ?  እንደገና ከቀድሞው የበለጠ ተጨማሪ በጀት አስፈልጎታል። ለእነዚያው የከሰምና የተንዳሆ ግድቦች ተጨማሪ  690 ሚ. ብር ገደማ እንደተመደበላቸው የሚገልፀው የ2002 የበጀት ሰነድ እንዲህ ይላል። 

“በ2002 በጀት አመት፣ የሁለቱንም ግድቦች ቀሪ ስራ በማጠናቀቅ ውሃ እንዲይዙ ማድረግና በከሰም 3ሺ ሄክታር፣ በተንዳሆ 10ሺ ሄክታር የመስኖ መሬት ዝግጅትን የማጠናቀቅ ስራዎች ታቅደዋል”… 
ይሄ ነገር መጨረሻው የት ይሆን? የሚል ጥያቄ ቢፈጠርባችሁ አይገርምም። ግን፤ ከዓመት በኋላ በ2003ም “ዘንድሮ ይጠናቀቃሉ” በሚል ለእነዚያኞቹ ግድቦች እንደገና በጀት ተመድቧል 680 ሚ. ብር፡፡ ምን ዋጋ አለው? ይሄኛው እቅድም አልተሳካም። እናም በ2004 እንዲጠናቀቅ እቅድ ተይዞ፣ በጀት ተመድቦለታል። ለእነዚሁ የከሰምና የተንዳሆ የግድብና የመስኖ ስራዎች  1.3ቢሊዮን ብር ተጨመረላቸው፡፡  ግድቦቹ 1999 . ይጠናቀቃሉ ከተባለ ወዲህ፤ 4.1 ቢሊዮን ብር ገደማ ተጨማሪ ገንዘብ  የተመደበ ቢሆንም፤ እቅዶቹ ሳይሳኩና ለአመታት እየተንከባለሉ ብዙ ሃብት ባክኗል፡፡

ይሄ ሁሉ በ2004 ዓ.ም በአዲስ አድማስ የታተመው ጽሑፍ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር፤ የግድቦቹ ግንባታ፣ አስር ዓመት ቢደፍናቸውም፤ እስከዛሬ ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁ፡፡ በመንግስታዊ የውሃ ስራዎች ድርጅት ነው ግንባታዎቹ የሚካሄዱት፡፡ የድርጅቱን ዝርክርክነትና የሃብት ብክነት በትንሹ ለመረዳት ከፈለጋችሁ፣ የግንባታ መኪኖች አጠቃቀሙን ማየት ትችላላችሁ፡፡ ብዙ መኪኖች አሉት፡፡ ግን፤ መኪኖቹ አንዳች እክል ሲገጥማቸው፣ መለዋወጫ እቃ ለመግዛትና ለመጠገን፣ ብዙ ወራትን መጠበቅ የግድ ነው፡፡ እናም በመቶ የሚቆጠሩ መኪኖች ያለ አገልግሎት ይቆማሉ፡፡ ግን ችግር የለውም፡፡ መኪኖችን ይከራያል፡፡ ለመኪና ኪራይ የሚያወጣው ገንዘብ፤ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ በየቀኑ አንድ ገልባጭ መኪና ለመግዛት የሚያስችል ነው በማለት ብዙ የአገር ሃብት እንደባከነ የፌደራል ዋና ኣዲተር ገልጿል፡፡ 

በአጭሩ፤ የግድብና የመስኖ ግንባታ የሚካሄደው በመንግስት ድርጅት በመሆኑ ለዓመታት ተጓተተ፤ ብዙ ቢሊዮን ብር ባከነ፡፡ አዳዲሶቹ የፋብሪካ ግንባዎችም፤ ለመንግስት ድርጅት ተሰጥተዋል - ለብረታ ብረት ኮርፖሬሽን፡፡ ታዲያ፤ የፋብሪካዎቹ ግንባታ መጓተቱና እንደገና ብዙ ቢሊዮን ብር መባከኑ እንዴት ይገርማል? 
በ2004 ዓ.ም በአዲስ አድማስ የታተመው ትንታኔ እንዲህ ይላል፡፡

“በሌሎች አገሮችም ሆነ በአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ በተደጋጋሚ እንደታየው፤ መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፤ ስራዎች እጅግ እንደሚጓተቱና የገንዘብ ብክነት እጅግ እንደሚበዛ በጣም ግልፅ ነው። ግን መፍትሄውም ግልፅ ነው፡፡  መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ይበልጥ እንዲገባ ማድረግ አይደለም መፍትሄው። ቢዝነስ ውስጥ እንዳይገባ፤ እስካሁን ከገባባቸው ቢዝነሶችም ቀስ በቀስ እንዲወጣ ማድረግ፤ ከዚሁም ጋር የግል ቢዝነስ እንዲስፋፋ መንገዱን ነፃ ማድረግ ከቻልን እንደሌሎቹ አገራት የማንበለፅግበት ምክንያት አይኖርም።”ይላል ጽሑፉ፡፡

2005 ዓ.ም መግቢያ ላይ፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው አዲስ ካቢኔ ባቋቋሙበት ወቅት የወጣ ሌላ ጽሑፍ  ላይም፤ ተመሳሳይ ሃሳብ እናገኛለን፡፡ እንዲህ ይላል፡፡ “ከሁለት አመት በፊት በታወጀው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት፣ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በየቦታው እንደተጀመሩና እየተገነቡ እንደሆነ ይታወቃል። የህዳሴ ግድብ፣ የመንገድ፣ የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ግንባታ፣ የስኳር እርሻዎች ዝግጅት፣ የጤና ጣቢያዎች ግንባታ፣ የተለያዩ ፋብሪካዎች ዲዛይን ... ወዘተ። እነዚህን ስራዎች በሙሉ፣ በእቅድ ሰነዱ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ሰርቶ ማጠናቀቅ ከባድ ነው። ግን ደግሞ ጨርሶ ሊጠናቀቁ የማይችሉ እቅዶችም አሉ ... ለምሳሌ 10 የስኳር ፋብሪካዎችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የወጣውን እቅድ ማሳካት ፈፅሞ አይቻልም።…ጭራሽ ከ8 አመት በፊት የተጀመረው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡

እቅዶቹ የማይሳኩት በእሳቸው ድክመት ምክንያት ባይሆንም፤ የወቀሳ ሸክም ይጠብቃቸዋል። ግን መፍትሄ ሊያበጁለት ይችላሉ። ከወዲሁ በግልፅ ለዜጎች መረጃ መስጠትና ለግል ኢንቨስተሮች ማስተላለፍ…” ይላል ከሦስት ዓመት በፊት የታተመው ጽሑፍ፡፡በእርግጥ የስኳር ፕሮጀክቶችን ለግል ኢንቨስተሮች መሸጥ ትክክለኛ መፍትሔ ነው፡፡ የድሮዎቹ የስኳር ፋብሪካዎች ከሦስት አመት ባልበለጠ ጊዜ ተገንብተው ማምረት የጀመሩት፣ በግል ኢንቨሰተሮች መሪነት እንደሆነ ማስታወስ ይቻላል፡፡ 


ነገር ግን፤ መንግስት፣ ፕሮጀክቶቹን ለግል ኢንቨስተር ለማስተላለፈ ፈቃደኛ ቢሆንስ? ምስጋና የሚጎርፍለት አይመስለኝም፡፡ ተቃራኒው፤ “50ሺ ሄክታር መቶ ሺ ሄክታር መሬት ለባለሃብቶች ተቸበቸበ፤ የአገር መሬት ተወረረ” የሚል ተቃውሞ ከዳር ዳር መራገቡ ይቀራል? አብዛኛው የአገራችን ሰው (ማለትም ህዝቡ) የኢንቨስትመንት ወዳጅ አይደለም፡፡ እና ምን ተሻለ? ፕሮጀክቶቹ በመንግስት እጅ ውስጥ ከቀጠሉ፤ የሃብት ብክነትና ኪሳራ እየገዘፈ መሄዱ አይቀርም፡፡ ለኢንቨስተሮች ከተሸጡም፤ ተቃውሞ መራገቡ አይቀርም፡፡ አጣብቂኝ ነው፡፡ “መፍትሔ የሌላቸው የስኳር ፕሮጀክቶች” በሚል ርዕስ የወጣው ዘገባ ትዝ አለኝ፡፡ 

1 comment: