Friday, 30 September 2016

ተቀምጠው የሰቀሉት


የኢራቅ ኩርዶች እንዲህ ይተርካሉ፤
አንዲት የልዑል ልጅ ነበረች፡፡ አንድ የምታፈቅረው ልጅም ነበረ፡፡ ታድያ ከአንድ የቤተ መንግሥቱ ጠባቂ ጋር ትመካከርና ይህንን ፍቅረኛዋን ክፍሏ ድረስ ታስገባው ነበር፡፡ የቤተ መንግሥቱ ጥበቃ የተወሰነ ገንዘብና ልብስ ትሰጠው ስለነበር በደስታ ምሥጢሩን ይደብቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ ልዕልቲቱና ፍቅረኛዋ አፕል ቆርጠው እየተጫወቱ ይበሉ ነበር፡፡ ሁለቱም አፋቸውን ከፍተው የአፕሉን ቁራጭ አንዳቸው ወደሌላቸው አፍ ወርውሮ የማስገባት ጨዋታ ነበር የሚጫወቱት፡፡ 
እየተሳሳቁ የአፕል ቁራጭ ወደየአፎቻቸው ሲወረውሩ ልዕልቲቱ የወረወረችው የአፕል ቁራጭ ድንገት የፍቅረኛዋ ጉሮሮ ውስጥ ተቀረቀረ፡፡ ውኃ ብትሰጠው፣ ማጅራቱን ብትመታው ሊወርድለት አልቻለም፡፡ ኡኡ ብላ እንዳትጮህ ልጁ ማነው? እንዴትስ መጣ ? ለሚለው ጥያቄ የምትመልሰው የላትም፡፡ በዚህ መካከል ልጁ ትንፋሽ አጥሮት ሞተ፡፡

የልጁ የመውጫ ሰዓት ሲደርስ የጥበቃ ሠራተኛው መጣ፡፡ እንደቀድሞው ግን ልጁን ደብቆ ሊያስወጣው አይችልም፡፡ አሁን ያለው ሬሳው ነው፡፡ ‹እባክህን የምትችለውን ሁሉ አድርገህ ይህንን ሬሳ አውጣልኝ፤ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ አደርግልሃለው› አለቺው፡፡ የጥበቃ ሠራተኛውም ‹ምንም ችግር የለውም፤ የምፈልገው ግን ገንዘብ ወይም ልብስ አይደለም› አላት፡፡ እርሷም ‹ምንም ችግር የለም፡፡ ብቻ በቶሎ አውጣልኝ› ብላ ለመነችው፡፡ የጥበቃ ሠራተኛው ሬሳውን ቆሻሻ አስመስሎ ደብቆ  አወጣው፡፡ እርሷም እፎይ አለች፡፡
የጥበቃ ሠራተኛው ተመልሶ መጣና ቃል በገባችው መሠረት የሚፈልገውን ነገር እንድታደርግለት ጠየቃት፡፡ ‹ምን?› አለች ልዕልቲቱ፡፡ ‹ካንቺ ጋር መተኛት ነው የምፈልገው› አላት፡፡ ፀሐይ እንደበዛባት ቅል ክው አለች፡፡ ተናደደች፡፡ ‹ምን ደፋር ነህ ከልዕልት ጋር ለመተኛት የምታስብ፤ አሁን ከዚህ ጥፋ› አለቺው፡፡ እሺ ብሎ ወጣና የፍቅረኛዋን አስከሬን ይዞላት መጣ፡፡ ይኼኔ የምታደርገው ግራ ገባት፡፡ ያላት አማራጭ የሰውዬውን ፈቃድ ማሟላት ብቻ ሆነ፡፡ ተሸነፈች፡፡ በአንድ ቀንም ሦስት ነገሮችን አጣች፡፡ ፍቅረኛዋን፣ ክብሯንና የወደፊት ተስፋዋን፡፡ ፍቅረኛዋን በሞት፤ ክብሯንም በአገልጋይዋ እግር ሥር በመውደቅ፤ የወደፊቱንም ተስፋዋን ድንግልናዋን በማጣት፡፡ 
በዚህ ብቻ አላበቃችም፡፡ ያ የጥበቃ ሠራተኛ እየመጣ ‹አጋልጥሻለሁ› ይላታል፡፡ ያን ቀን ሬሳውን ይዞ የመጣበትን ጆንያም ያሳያታል፡፡ እርሷም ትፈራለች፡፡ በፍርሃትም የማትፈልገው ሰው እግር ሥር ትወድቃለች፡፡ ከእርሱም ጋር ትተኛለች፡፡ ይህ ግን ሊያዛልቃት አልቻለም፡፡ ባርነት ሰለቻት፡፡ ችግሮችን ለመጋፈጥ ካልፈለግህ ችግሮችን እያነገሥካቸው ትሄዳለህ› ይላሉ ኩርዶች፡፡ ችግርን ካታለልከው መልሶ ይይዝሃል፤ ከተጋፈጥከው ግን ጥሎህ ይሸሻል የሚል አባባልም አላቸው፡፡ 
ልዕልቲቱ አሁንም ችግሩን መፍታት ሳይሆን ማምለጥ ፈለገች፡፡ አንድ ሌሊት የጥበቃ ሠራተኛው ተደብቆ ወደእርሷ ሲመጣ ለአባቷ የምታዘጋጀውን የልዑሉን ወይን አሰናድታ ጠበቀቺው፡፡ በደስታ እየደጋገመ ጠጣ፡፡ ከእርሷም ጋር ከተኛ በኋላ እንደ ተሸነፈ ቦክሰኛ በድካም ተዘረረ፡፡ አርሷም እየጎተተች ወስዳ በልዑሉ መኝታ በር ላይ አጋደመችው፡፡ ሊነጋጋ ሲል ጠባቂዎቹ አዩት፡፡ ጠጋ ብለው ሲያሸቱት አፉ የወይን ጠጅ ይሸታል፡፡ የወይን ጠጁ ሽታ የልዑሉ ወይን መሆኑን ይመሰክራል፡፡ የልዑሉን ወይን ሰርቆ ጠጥቷል ብለው በአደባባይ ሰቅለው ገደሉት፡፡ ነገሩም በዚህ የተቋጨ መሰለ፡፡ ነገር ግን የዕብድ ቀን አይመሽም፡፡ ኩርዶች እንዲህ ይላሉ፡፡ የምትሠራው በር ምንጊዜም ልትሄድበት የምትችል መሆኑን አረጋግጥ፡፡ ለአንድ ጊዜ መውጫ ብለህ በሩን ከሠራኸው ከበሩ በኋላ ወዴት እንደምትሄድ ግራ ይገባሃል፡፡ በሩን ከነ መንገዱ አስበው፡፡ መንገዱን ከነ መዳረሻው፤ መዳረሻውንም ከነመቆያው፤ መቆያውን ከነ መክረሚያው፡፡ 
የጥበቃው ሠራተኛ በአደባባይ ሲሰቀል፤ የወይኑ ጣዕም አፉ ላይ ቀርቶ ስለነበር እየደጋገመ ከንፈሩን ይልስ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ የጠጣው የወይን ጠጅ ጣዕም ነው ተብሎ ተወራ፡፡ ይህንን ወሬ የሰማ የሌላ ልዑል ልጅም ይህንን ወይን ያዘጋጀቺውን የልዑሉን ልጅ ለማግባት ፈለገ፡፡ እናም ወደ ልዕልቲቱ አባት ሽማግሌዎች ላከ፡፡
ይህ ዜና ለአባቷ የምሥራች ለልዕልቲቱ ግን መርዶ ነበር፡፡ ድንግልናዋን አጥታለች፡፡ በኩርድ ደግሞ ድንግል ያልሆነቺውን ልጅ እንኳን ልዑላን ተራዎቹ ሰዎች አያገቡም፡፡ እስካሁን ችግሩን ከመጋፈጥ እየሸሸች፣ ነገር ግን አንዱን ችግር በሌላ ችግር እያለፈች መጥታለች፡፡ አሁን የመጋፈጫው ሰዓት ደረሰ፡፡ ችግርን በመፍትሔ መፍታትና ችግርን በሌላ ችግር ማለፍ ይለያያሉ፡፡ ችግርን በችግር ካለፍከፈው ጊዜ እየገዛህ ነው፡፡ ችግርን በመፍትሔ ካለፍከው ደግሞ ልብ እየገዛህ ነው፡፡ ይላሉ ኩርዶች፡፡ 
የልዕልቲቱ አባት ጋብቻውን መቀበሉን ስትሰማ እንደተለመደው ልዕልቲቱ አንድ ዘዴ ቀየሰች፡፡ አንዱን ታማኝ አገልጋይዋን ጠራችውና አንድ እፍኝ ወርቅ ሰጥታ እንዲህ ስትል አዘዘችው ‹በመላዋ ኢራቅ ዙር፡፡ በመልክም፣ በቁመትም፣ በጠባይም እኔን የምትመስል ልጅ ፈልገህ ለደንገጡርነት አምጣልኝ›፡፡ ሰውዬውም ለወራት ያህል ከቦታ ወደ ቦታ ዞረ፡፡ በመጨረሻም አንዲት ልጅ አገኘ፡፡ ልዕልቲቱ ስታያት ቁርጥ እርሷን ትመስላለች፡፡ እንዲህ አለቻት ልጅቱን፡፡ አሁን አንቺ ልዕልት ሆነሻል አሉ፡፡ የልዑሉንም ልጅ ታገቢያለሽ፡፡ የጫጉላውንም ጊዜ አብረሽው ታሳልፊያለሽ፡፡ እኔም ያንቺ ደንገጡር ሆኜ አንቺንና ልዑሉን ለጊዜው እታዘዛለሁ፡፡ ልክ የጫጉላው ጊዜ እንዳለፈ ግን ትቀይሪኛለሽ፡፤ እንቺ ወደ ደንገጡርነትሽ እኔም ወደ እመቤትነቴ እመለሳለሁ፡፡ ለዚህ ውለታሽም ለጥሎሽ የሚመጣውን ሀብት ሁሉ ትወስጃለሽ› አለቻት፡፡ ልጂቱም በደስታ ተፍነከነከች፡፡ 
የሠርጉ ቀን ደረሰ፡፡ ደንገጡሯዋ የሙሽራ ልብስ ለበሰች፡፡ እመቤቲቱ ደግሞ የአገልጋይ ልብስ ለበሰች፡፡ ማንም ሊለያቸው የቻለ የለም፡፡ ልዑሉ መጣ፡፡ ሙሽራዋን ይዞ ሄደ፡፡ አገልጋይዋም ተከትላ ሄደች፡፡ በልዑሉ ቤት የነበረው ድግስ ሲያልቅ ልዑሉና ሙሽራዋ ወደ ጫጉላ ቤት ገቡ፡፡ አገልጋይዋም ከውጭ ቀረች፡፡ ታስበዋለች፡፡ ይህ ዕድል የእርሷ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን አይደለም፡፡ አሁን እርሷ ነበረች እዚያ ውስጥ መሆን የነበረባት፤ ግን ችግርን ለማለፍ ብላ በፈጠረችው ችግር ምክንያት ውጭ ቆማለች፡፡ እዚህ ደረጃ ሳትደርስ ነገሮችን አስተካክላ በክብር ልትወጣ ትችል የነበረባቸውን ዕድሎች ታስታውሳለች፡፡ ዕድሎች ሁሉ አምልጠዋታል፡፡ ችግሮችን በሌላ ችግር በመተካት ዕድሎችን አምክናቸዋለች፡፡ ስለዚህም ክብሯን ለሌላዋ አሳልፋ ሰጠቻት፡፡ ሕዝቡ ጫጉላ ቤት ያለቺው እርሷ መስላቸዋለች፡፡ ግን አይደለችም፡፡ የተመረጠችው እርሷ፣ ወደ ሠገነት የወጣችው ሌላዋ፡፡ የተዳረችው እርሷ፣ ያገባችው ሌላዋ፡፡
የጫጉላዎቹ ቀናት አለፉ፡፡ ልጂቱ ግን ወደ አገልጋይነቷ ልትመለስ አልቻለችም፡፡ አንድ ቀን መታጠቢያ ቤት ውስጥ እመቤትና ደንገጡር ተገናኙ፡፡ ደንገጡሯም ‹አሁን በቃሽ ወደቦታሽ ተመለሽ፡፡ ለውለታሽ ያዘጋጀሁትን ስጦታሽን ውሰጅ; አለቻት፡፡ እመቤቲቱም ‹የዋሕ ነሽ፡፡ ላየው የማልችለውን አሳየሺኝ፤ ላገኘው የማልችለውን ሰጠሽኝ፤ ልደርስበት የማልችለው ቦታ አደረሽኝ፡፡ ያኔ እሺ ስልሽ ይህንን ሁሉ አላውቅም ነበር፡፡ አልጋው እንዲህ የሚመች መሆኑን አልቀመስኩም ነበር፡፡ ክብሩ እንዲህ የሚያጓጓ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ ምቾቱ እንዲህ ልብ የሚለሰልብ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ ላንቺ ከደንገጡርነት ወደ እመቤትነት መምጣት ቀላል ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ከእመቤትነት ወደ ደንገጡርነት መውረድ ከባድ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ነገር ከቀመስኩ በኋላ ትተውልኛለች ብለሽ ማሰብሽ ሞኝነትሽ ነው፡፡ አልጋ አንዲህ በቀላሉ የሚተው አይደለም፡፡ ሀብቱ ሁሉ የእኔ መሆኑን እያየሁ ያንቺ ስጦታ የሚያጓጓኝ ይመስልሻል› አለቻት፡፡ 
›እነሆ› ይላሉ ኩርዶች፡፡ እነሆ በዚህ የተነሣ አገልጋይቱ እመቤት፣ እመቤቲቱም አገልጋይ ሆነው ኖሩ፡፡ ተቀምጣ የሰቀለቺውን ቆማ ማውረድ አቅቷት፡፡ 
ኤድመንተን፣ ካናዳ

No comments:

Post a Comment