Tuesday, 31 July 2018

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም

Image result for fekadu teklemariam

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ህልፈተ ህይወቱን ሰማን፡፡ በበርካታ የኪነጥበብ ስራዎቹ የምናውቀው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በወሎ ሲሪንቃ ቅድስት አርሴማ ፀበል ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ አመሻሽ ለይ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡

Monday, 30 July 2018

በእውቀቱ ስዩም

ባገራችን ባሁኑ ጊዜ ብዙ ተከታይ ያለው ሃይማኖት ብሄርተኝነት ይባላል፡፡የብሄርተኝነት ምእመን ከሆንክ የነፍስ አባት ይኖርሀል፣በጭፍን የምትቀበለው ቀኖና ይኖርሀል፣ነገ የምትገባባት የተስፋ ምድር ይኖርሀል፣ከሁሉ በላይ ደግሞ ብርቱ ችግርህን የምትደፈድፍበት የመስዋእት በግ ይኖርሀል፡፡

ሃይማኖቶች ምእመናንን ብቻ ሳይሆን መናፍቃንንም ያፈራሉ፡፡ብሄርተኞች በስሜት የሚነድደውን ምእመን ብቻ ሳይሆን የኔ ቢጤውን መነፍቅም እንደሚያፈሩ አንርሳ፡፡በነገራችን ላይ ሃይማኖትን መካድ ማለት ሃይማኖት የሚያነሳቸውን አብይ ጥያቄዎች መካድ ማለት አይደለም፡፡እንዲሁም፣ ብሄርተኝነትን መካድ ማለት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ህልውና መካድ ማለት አይደለም፡፡በዚህ ጉዳይ ፣መናፍቅ መሆን ማለት፣ የብሄርተኛ ነቢያት ሰለ ጭቆና ስለ ነጻነት ብሎም ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀርቡትን አጉል እምነት መጠራጠር ማለት ነው፡፡

ከኢትዮጵያዊነት እንጀምር

ከዘመናችን የብሔርተኝነት ነቢያት አንዱ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ከእንቁ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ላይ ስለኢትዮጵያዊነት የሚከተለውን ይላል፡፡
‹‹…ኢትዮጵያን የመሠረታት የሶሰትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡በአማራው፣በኦሮሞው፣በትግሬው ግብግብ ውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡በዚህ የተነሳ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭት እና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡…የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት የምንለው የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው››
ጃዋር የኢትዮጵያን መሠረት የሦስት ብሄረሰቦች የስልጣን ግብግብ አድርጎ ወስኖታል፡፡ በመጀመርያ፣ ሌሎች ብሄረሰቦች በግብግቡ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አድርጎ ማቅረቡ አንድ ጉድለት ነው፡፡ ግን ዋናው ቁምነገር ይሄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የግጭት ውጤት ብቻ እንደሆነች አድርጎ ማቅረቡ ነው ትልቁ ስሕተት፡፡ ሲጀምር፣ የግብግብ ታሪክ መሠረት ይንዳል እንጂ መሠረት አይገነባም፡፡ እንደኔ ግምት፣የኢትዮጵያ መሠረት የሆነው ብሄረሰቦች ለጋራ ሕልውና ሲሉ የሚያደርጉት የመደጋገፍ ታሪክ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ፣ ታሪክ ከላሾች፣የብሄሮችን የ‹‹ግብግብ››ታሪክ ሞቅ አድርገው፣አኳሽተው ሲጽፉ፣የብሄሮች መደጋገፍ ታሪክን ግን ቸል ይሉታል፡፡ አለያም እጅግ በቀዘቀዘ ስሜት፣ በጥቂት መስመሮች ብቻ ጨረፍ አድርገው ያልፉታል፡፡ለነገሩ፣ከፋፋይነትን ብቸኛ ያስተዳደር ፈሊጥ አድርጎ የሚቆጥር ሰው በታሪክ ገጾች ውስጥ መመልከት የሚፈልገው ክፍፍልን ብቻ ነው፡፡ታሪክ ግን ብዙ በጎ የትብብር ገጠመኞችን መዝግቧል፡፡ለምሳሌ ጀግናው አጼ ዮሐንስ አራተኛ በበዛሬይቱ ኤርትራ የግብጽን ወራሪ ጦር ድል የነሡት የትግራይ ጀግኖችን ብቻ አሠልፈው አልነበረም፡፡ በዚህ ጦርነት ከግብጽ ጎን ሆኖ፣የተዋጋው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይ እንደመሠከረው ወልቃይቶች፣ጥልጣል የተባሉ የአፋር ንኡስ ክፍሎች፣የወረኢሉ ኦሮሞዎች ለንጉሰነገስቱ ድጋፍ ለማድረግ ተሸቀዳድመዋል፡፡በራስ ወሌ የሚመሩ የአማራ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡የጎንደር ቀሳውስት ለጦርነቱ ድጋፍ ለማድረግ አድዋ ገብተዋል፡፡ የጎጃሙ ራስ አዳል የደርሼልሀለሁ አለኝታቸውን አሳይተዋል፡፡ የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ሳይቀር በመቶ የሚቆጠሩ በቅሎዎችንና ማበረታቻ ልከዋል፡፡ ዝርዝሩን ማንበብ ለሚፈልግ Muslim Egypt Christian Abyssinia የተባለውን የዚህ ደራሲ ማስታወሻ ገጽ 291-292 ያንብብ፡፡ መጽሐፉን በኢንተርኔት ቤተ-መጻህፍት ውስጥ በብላሽ ማግኘት ይቻላል፡፡

ከተለያየ መአዘን የመጡ እኒህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ቃላት ይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደ አረቄ ይወጣል፡፡ ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹‹የአማራ ባህል ››ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለው አይመስለኝም፡፡

ጃዋር‹‹አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭትና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች›› በማለት ሳይወሰን ‹‹የኢትዮጵያ አገራዊ መለያ ማንነት የምንለው አማራ ብሄራዊ ማንነት ነው›› ሲል ይጨምራል፡፡ ጎበዝ ኧረ በህግ አምላክ!!! የኢትዮጵያ ባህልኮ ካንድ አለት የተጠረበ ሕንጻ አይደለም፡፡ ከብዙ የመዋጮ ጡቦች የተገነባ ነው፡፡ ጃዋር እያንዳንዱን ጡብ ቀርቦ ቢመረምረው እዚህ የደረሰበት እርግጠኝነት ውስጥ የሚደርስ አይመስለኝም፡፡

እስቲ ከደቃቅ ምሳሌ እንጀምር፡፡ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡና ስነ-ስራታችን ነው፡፡ አንዲት ጠይም ፣ባለሹርባ ሴት፣ያበሻ ቀሚስ ለብሳ ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስል በየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ይህ ችክ ያለ ምስል በስነ-ስእል ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ቢዮንሴና ጆን ኬሪ አገራችንን በጎበኙበት ሰአት የቡና ስነስርአት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡና ስርአታችንን እንደ ኢትዮጵየዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው፡፡ ለዋለልኝ መኮንን እና ለጃዋር መሀመድ ይህ የአማራ ባህል መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ እይታ ይመስላል፡፡ ጉዱ ዝርዝሩ ላይ ነው፡፡ የሴትዮዋ ሹርባ ከሐማሴን ወይም ከተንቤን ሴቶች ልማድ ጋር ስምም ነው፡፡ ያበሻ ቀሚሱን የሽሮሜዳ ጋሞ የሸመነው ሊሆን ይችላል፡፡ ጀበናው የጂማ ሙስሊም ኦሮሞዎች ያስተዋወቁት ነው፡፡ አቦል ቶና በረካ አረብኛ ወይም የተወላገደ አረብኛ የተገኙ ቃላት ናቸው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ትንሳኤ በአል በሉባንጃ የሚታጀብ ቡና የማያፈላ ክርስትያን ኢትዮጵያዊ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ከጥቂት መቶ አመታት በፊት ግን ቡና የእስላም ልማድ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ የቡና ትርኢት የሙስሊም አበው በኢትዮጵያ ባህል ላይ የጨመሩት በጎ መዋጮ እድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ጊዜ በተባለው አናጢ ከብዙ ጡቦች የተገነባች ናት የምንለው ለዚህ ነው፡፡

ጃዋር አማራው የራሱን ባህል በኦሮሞው ላይ እንደጫነ ሲያምን ተገላቢጦሹ ያለው አይታየውም፡፡ ኦሮሞ በረጅም ዘመን፣በሠፊ ምድር፣ ሰፍሮ የመኖሩን ያክል በጎረቤቶቹና በወደረኞቹ ላይ የባህል ተጽእኖ አላሳደረም ማለት ብርቱ ባህል የለውም ከማለት አይለይም፡፡ ባገራችን ዋና ዋናዎቹ የባህል ቀራጺዎች ጦርነትና ሐይማኖት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፣ጀግኖችን እና ነገስታትን አባ በዝብዝ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኘው አባ ነጋ ወዘተ እያሉ መሰየም ገናና ኢትዮጵያዊ ባህል መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ብዙዎቻችን የማናውቀው ይህንን ባህል ያስተዋወቁት ለግማሽ ምእተአመት ያክል ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ቼ በለው በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እንዲህ በማለት ያረጋግጣሉ- ‹‹ነገስታቱ በ‹‹አባ›› ወይም የእገሌ ባለቤት በሚል ቅጽል ስም መጥራት የጀመሩት የኦሮሞዎችን ወይም የወረሸሆችን ልምድ በመከተል ነው ከ1838 ዓም ወዲህ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ወትሮ ግን በተለይም 1474-1713 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ቅብዓ መንግሥቱ በሚደረግላቸው ሰአት ይወጣላችው የነበረው የግርማ ስም ወይም ስመ መንግስት ‹‹ሰገድ›› የሚል ኃይለቃል በመጨመር እንደነበር ቀጥሎ ያለው ያረጋግጣል፡፡ ወናገድ ሰገድ፣ አጽናፍ ሰገድ፣ አድማስ ሰገድ፣ መለክ ሰገድ፣አድያም ሰገድ ሉል ሰገድ››በማለት ይዘረዝራሉ፡፡
ከጥቅሱ ሦስት ፍሬ ነገሮችን መረዳት ይቻላል፡፡

1- ይህ ባህል ባንድ የዘመን ምዕራፍ ላይ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የመነጨ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡

2- ባህሉ ብርቱ ተጽእኖ ከመፍጠሩ የተነሳ አማራና ትግራይ ነገስታት ለረጅም ዘመን ይጠቀሙበት የነበረውን የስያሜ ዘይቤ ሽሯል፡፡

3- አማራው ታሪክ ጸሀፊ ለባህሉ አስተዋዋቂዎች የባለቤትነት እውቅና ሰጥተዋል፡፡

በሃይማኖት ረገድም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚገጥመን፡፡ ለምሳሌ አቴቴ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድ ሲተረጉሙ ‹‹ዛር፣በሴት ስም የምትጠራ፣ ውቃቤ ፣ አማሮች ከኦሮሞዎች የወረሷት ጨሌ የሚያጠልቁላት አቴቴ ጊንቢ ሐራ አቴቴ ዱላ እያሉ እንቀት የሚቀቅሉላት አምልኮ ባእድ፣ትርጓሜ ጠባቂ ማለት ነው››ይላሉ፡፡

‹‹አምልኮ ባእድ ››የሚለውን አሉታዊ ሐረግ፣የክርስትያን አድልኦ ያለበት ፍርድ አድርገን እንለፈው፡፡ ዋናው ፍሬ ነገር፣ የአሮሞው ባህል በአማራው ባህል ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ማወቃችን ነው፡፡ ይህም አንዱ ብሄረሰብ ሁልጊዜ ጫኝ ፣ ሌላው ብሄረሰብ ሁልጊዜ ተሸካሚ እንደነበረ አድርገው ሊነግሩን የሚፈልጉትን ሰዎች ያስተባብላል፡፡ በሁለቱ ግዙፍ ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ግኑኝነት የእኩዮች ልውውጥ ነው፡፡ የባህሎች ውርርስ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ የማንኩሳ ዘመዶቼ የሚያስደነግጥ ነገር ሲገጥማቸው ‹‹አቲቲን ወሰድከው›› ይላሉ፡፡ ቀልቤን ገፈፍከው ለማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ባህላዊ ተጽእኖ በወለጋ ድንበር ላይ ቆሟል ያለው ማነው?

ስለጉዲፈቻ ባህል ብዙ ሰዉ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ በጦርነት ወቅት ምርኮኞችን ባርያ ማድረግ ወይም መግደል በብዙ ማህበረሰቦች የተለመደ ነው፡፡ በኦሮሞ አበዋዊ ባህል ውስጥ ግን ምርኮኞች በልጅነት ይታቀፋሉ፡፡ ከሌላ ብሄረሰብ ቢመጡም የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚያገኘውን መብት ሳይነፈጋቸው ያድጋሉ፡፡ ይህንን ልማድ በአማራው ማህበረሰብ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በጎጃሙ ንጎስ ተክለይማኖትና በወለጋ መሳፍንት መሀል በተደረገው ጦርነት የተማረከው ብላቴና ነገሮ ዋቅጅራን እንደልጅ አሳድገውታል፡፡ ክርስትና አስነስተው ተክለኢየሱስ አሰኝተውታል፡፡ ራሱ በጻፈው ማስታወሻ ‹‹በጠጅና በስጋ አደግሁ›› በማለት የመሳፍንት ልጆች ያገኙት የነበረውን ምቾት ሳይነፈገው ማደጉን ይመሰክራል፡፡ ነገሮ ፣ ከማእረግ ወደ ማእረግ እየወጣ የንጉሱ ጸሐፌ ትዝዛዝ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ተመሳሳይ መልኩ በሸዋ ምርኮኛው ቆሴ ዲነግዴ በቤተመንግስት እየተቀማጠለ አድጎ ሐብተጊዎርጊስ በሚል ስመ ክርስትና የኢትዮጵያ የጦር ምኒስትር እስከመሆን ደርሷል፡፡ ሰዎችን በልዩ ቋንቋቸው ምክንያት ባይተዋር ማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህል አልነበረም፡፡ እኩዋን ባህላችን አማርኛችን እንኳ የጉራማይሌነታችን ምስክር ነው፡፡ አሁን ኦሮምኛ ያልተነካካ አማርኛ ማግኘት ይቻላል?፡፡ እሰቲ ለናሙና ያክል ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› ከተባለው የዮሐንስ አድማሱ ምርጥ የአማርኛ ግጥም ውስጥ ጥቂት መስመሮች ልቆንጥር፡፡

1) ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ
2) ሜዳና ተራራ በመሐል ሸለቆ ጨፌውና መስኩ በኒህ ተደብቆ
3) ሐቀኛ ጠፍቶበት በዋለበት መልቲ ጌጥ ነው ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ
4) ብልጭ ብሎ ጠፋ ተወርዋሪ ኮከብ የሐሳብ አንጋፋ በመረጥኳቸው መስመሮች ውስጥ የሚገኙት ‹‹ይፋ፣ ጨፌ፣ መልቲ፣ ሎቲ፣ አንጋፋ፣›› የተባሉት ቃላት ኦሮሚኛ ናቸው፡፡ ካንድ የአማርኛ ግጥም ይህን ያህል ኦሮሚኛ ከተገኘ በሙሉ መዝገበ ቃላት ውስጥ ምን ያህል ሊገኝ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህን ያክል ነው የተዋሀድነው፡፡

የኢትዮጵያ ባህል የተውጣጣ ባህል እንጂ ጃዋር እንደሚለው የአማራ ባህል ብቻ አለመሆኑን በመጠኑም ቢሆን ያሳየሁ ይመስለኛል፡፡ ጃዋርን እዚህ ላይ ላሰናብትና ለማጠናቀቂያ የምትሆን አንዲት አንቀጽ ልጨምር፡፡
ባህልን ማክበር ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በስሜት ሚነድደው የብሄርብሄረሰብ ፖለቲካችን፣ ዜጎች ለባህል ያላቸውን ፍቅር ወደ ጭፍን አምልኮአዊ ፍቅር እያዘቀጠው ነው፡፡

ባባቶቻችንና በእኛ መካከል የባህል ፋይዳ ልዩነት ያለ ይመስለኛል፡፡ አባቶች ባህላቸውን ያገኙት በኑሮ ጣጣ አስገዳጅነት ነው፡፡ ለምሳሌ የኔ አያት ቁምጣ ሱሪ የሚታጠቀው ከሌሎች ብሄረሰቦች ለየት ብሎ ለመታየት አይመሰለኝም፡፡ በቂ አቡጀዲ ስላላገኘ ነው፡፡ ወይም ለስራ እንዲያመቸው ባጭር መታጠቁ ይሆናል፡፡ እኔ ግን የብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ቁምጣ ለብሼ ራሴን በማስጎብኘት እንድኮራ ይጠበቅብኛል፡፡ ጉድ እኮ ነው!!! ጋቢ በጥንት ጊዜ የሙቀት ምንጭ ነበር፡፡ ዘንድሮ የኩራት ምንጭ ሊሆን ይቃጣዋል፡፡

የዛሬዎቹ ባህል አምላኪዎች ባህል ሲያስቡ ለውጥን ይረሳሉ፡፡ ባንድ ወቅት የሚያኮራው ያንድ ብሄረሰብ ባህል በሌላው ወቅት ይናቃል፡፡ ባንድ ወቅት የሚያስሸልመው በሌላ ጊዜ ያስቀጣል፡፡ ከጥቂት መቶ አመት በፊት ዝሆን መግደል በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የሚያጎናጽፍ ተግባር ነበር፡፡ ዝሆን የገደለ ልዩ አምባር ክንዱ ላይ ያጠልቃል፡፡ እስኪ ዛሬ ያባቶቼን ባህል ለማክበር ነው ብለህ ፓርክ ውስጥ አርፎ የተኛውን ዝሆን ግደል፡፡ በአምባር ምትክ ካቴና ይጠልቅልሀል፡፡

የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት የተባለውን የተደጋገመ ግን ያልታሰበበት ቃል ከዚህ አንጻር ቃኙት፡፡ ሲጀምር ፣ዛፍ እንኳ ቅርፊቱን በሚቀያይርበት ዓለም፣ብሄር ብሄረሰቦች በየጊዜው አልባሳታቸውን አይቀያይሩም ወይ?፡፡ የብሄረሰቡ አልባስ ሲባል በየትኛው ዘመን የሚለበሰው ነው? የእንዳለጌታ ከበደ እናት ሲነግሩን፣ ዛሬ በጉራጌ ዘፈን ላይ በቲቪ የምናየው የሴቶች ሻማ ቀሚስ በደርግ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ሸማ ነው፡፡ ከሸማው በፊት ደግሞ የቆዳ ቀሚስ ይለበስ ነበር፡፡

ሌላው፣ አንድ ማህበረሰብ አልባሳት በየማእረጉ ልዩ ልዩ ልብሶች ይኖሩታል፡፡ ወታደሩ ያባ ገዳውን ልብስ የሚለብስ አይመስለኝም፡፡ ባሮች ከጌቶች ልብስ ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንዲለብሱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ በፊውዳል ማህበረሰብ ከላይ አስከታች መልበስ መከናነብ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ ይህንን በሸዋና በትግራይ ብቻ ሳይሆን በቅድመ ምኒልክ ከፋ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ባንጻሩ፣ባሮች በከፊል ተራቁተው መታየት አለባቸው፡፡ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አለባበስ በበሄረሰብ ላይ ሳይሆን በመደብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ የብሄር አልባሳት የሚባለው እንደ ማንኛውም ሾላ በድፍን ሐሳብ በጥርጣሬ መታየት አለበት፡፡

ትውልዱ የባህል ፈጣሪ መሆን ሲገባው፣የባህል ሙዚየም ሆኖ ተተክሏል፡፡አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ባንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ካባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ፣ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል››

ማሳረጊያ

ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ያቆያት የነገስታቱ ጉልበት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያ የተሸመነችበትን ውስብስብ ክር ማየት ያልታደሉ ናቸው፡፡ዛሬ ኢትዮጵያን በታትነን ክልላችንን እናድናለን ብለው ባደባባይ ሳያፍሩ የሚናገሩ ሰዎችን የምናይበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ ማእበል ከበረታባት እንደ ታይታኒክ ትሰጥም ይሆናል፡፡ግን መርከቢቱ ስትሰጥም የመርከቢቱ ሳሎን ብቻውን አይንሳፈፍም፡፡የመርከቢቱ ጓዳ ብቻውን አይተርፍም፡፡ኢትዮጵያ ስትከስም ብሄሮች ተነጥለው ይለመልማሉ ማለት ተፈጥሮ አመሏን እንደ ግትቻ የትም ጥላለች ማለት ነው፡፡

Thursday, 26 July 2018

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል።

Image result for simegnew bekele

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል። ያልታደለች ሀገር… ዕንቁ ኢንጅነሯን አጣች፡፡ የገዳዮች ማንነትና ከገዳዮች ጀርባ ማን እንዳለ ባይረጋገጥም…. በሰው እጅ እንደተገደሉ ግን ታውቋል፡፡ የሸሚዝ ኮሌታቸው ተቀዶ በግራ ጆሯቸው እየደሙ እንዳዩአቸው እማኞች ተናግረዋል። ከሕሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ብዙ ምሥጢር ስለያዘ ግድያው ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

ኢንጅነሩ ሁሌም ለገብርኤል በዓል… በዓልይ ንግሥ ሲሆን ግቢ ገብርኤል ያስቀድሳሉ። እኔም ሁለት ጊዜ በዓይኔ አይቻቸዋለሁ። ዛሬም የተገደሉት ወደ ገብርኤል ንግሥ እየሄዱ ሳለ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ለንግሥ እንደማይቀሩ ይታወቃልና።
ትጉሁ ሰው፣ ጠቢቡ መሐንዲስ፣ ትሁቱ ክርስቲያን ኢንጅነር ስመኘው ሞቱ ሲባል ሰማይ ምድሩ ነው የዞረብኝ። በአካል ከ4 ጊዜ በላይ አግኝቻቸዋለሁ። ፈገግታ የማይለያቸው ትሁት ሰው ናቸው። እና ሞቱ? እኔ አላምንም። እንባየን ማቆም አልቻልሁም።
የበረሃው ትጉህ ሰው ሞቱ። “የሕዳሴው ግድብ እንዳለቀ ብሞት አይቆጨኝም” ይሉ የነበሩት ተስፈኛ መሐል ላይ ቀሩ። “ይህ ግድብ የቀደሙ አባቶቻችን ድል ማስታወሻ ነው። አድዋ ላይ ሞተው የቀሩህ ጀግኖች ሕይወት ማስታወሻ ነው። እነርሱ የሞቱት ልጆቻቸው ይህን መሰል ታሪክ እንድንሰራ ነው። ይህ እንደ አድዋ ሕዝቡን በአንድነት ያዘመተ ታሪክ ነው።” እያሉ ሕዝቡን ያጽናኑ የነበሩት ባለ ብሩህ አእምሮውና ትሁት ሰብዕናን የተላበሱት ጀግና በጨካኞች ሞቱ። ምን አይነት አረመኔነት ይሆን? እንዴት ያለ ጭካኔ የተላበሰ ሰወ በላ በእኝህ ዕንቁ ሰው ላይ ሞት ፈረደ??? ያማል። የምር ያማል።

Tuesday, 24 July 2018

የዶ/ር አብይ የ'መደመር' ሃሳብ ምንድን ነው? | ዶ/ር ምህረት ደበበ እና ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ


ABIY AHMED AMAZING PREACH | ከቤተ-መንግሥት የሰበከው አስገራሚ ወንጌል


የበቅሎዋ ጥያቄ

ንዲት ግልገል በቅሎ እናቷን እንዲህ ብላ ጠየቀቻት፡፡
‹‹እማዬ እኔ ግን ማነኝ››
እናቷም ገረማትና ‹አንቺማ በቅሎ ነሽ፤ ግን ለምን ጠየቅሽኝ››
ግልገሏም ጥቂት ጊዜ ዝም ብላ ከቆየች በኋላ፤ ‹‹መጀመሪያ ግን አህያ

ነበርኩ ወይስ ፈረስ›› አለቻት፡፡ እናቲቱምአንገቷን ነቅንቃ ‹‹እንስሳ ነሽ ልጄ፤ እንስሳ፡፡ ፈረስም አህያም እንስሳ ነው፡፡ ስንፈጠር እንስሳ ነበርን፡፡ የቤት የዱር፣ የሸክም የግልቢያ፣ የእርሻ የሜዳ፣ የንጉሥ የባሪያ የሚለው በኋላ የመጣ ነው፡፡ አዳምኮ ሲፈጠር ቤት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የቤት እንስሳ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ሁላችንም ይህቺን ምድር እንደልባችን እንጠቀምባት ነበር፡፡ ነገር የመጣው በኋላ ነው፡፡ ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው ይህንን አሁን ያለንበትን ሁኔታ የፈጠረው፡፡››

‹‹ጓደኛዬ የአንቺ አያቶች ጨቁነውናል አለኝ፡፡››
‹‹እንዴት አድርገው ነው የጨቆኑት፤ ለመሆኑስ የአንቺ አያቶች ስንት ናቸው?

እርሱ የተነገረውን ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ያልተነገረውስ?  ከታሪካችንኮ በጣም ጥቂቱ ነው የተጻፈው፤ ከተጻፈውም በጣም ጥቂቱ ነው የተነገረው፡፡ ባልተጻፈው ታሪካችን ውስጥ ማን ምን እንደነበረ ማን ያውቃል?

ለምሳሌ በሀገረ እሥራኤል አህዮች እጅግ የሚወደዱ የቤት እንስሳት ነበሩ፡፡ ነገሥታቱም፣ ካህናቱም፣ ነብያቱም ዘመኑ ዘመነ ሰላም ሲሆን በአህያ ነው ይሄዱ የነበሩት፡፡ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በአህያ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ወደ ግብጽ የተሰደደችው በአህያ ነው፡፡ በጥንታውያን ግብጾች ዘንድ አህያ የመኳንንትና የነገሥታት ሀብት ማሳያ ነበር፡፡ የናርማር ወይም የሖር – አሃመቃብር እንደሆነ በሚታመነው ቦታ ላይ በተደረገ ቁፋሮ አህዮች ከነገሥታቱ ጋር በክብር ተቀብረው ተገኝተዋል፡፡ በዚያ ጊዜ አህዮች የቤተ መንግሥቱን ምግብ እየተመገቡ፣ በቤተ መንግሥቱም እየተሸለሙ ኖረዋል፡፡  በሌላው ዘመን ደግሞ ይህንን ፈረሶቹ ወስደውታል፡፡››

‹‹ወደኋላ ተመልሰሽ ሁሉን እንስሳት ብታያቸው ታሪካቸው እንደዚሁ ነው ልጄ፡፡ በዘርሽ አትጨቁኝም፤ በዘርሽም አትጨቆኝም፡፡ የጭቆና መሠረቱ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ አቤልን የገደለውኮ ቃየል ነው፡፡ የአንድ ማኅፀን ልጆች ናቸውኮ፡፡ ቃየል አቤልን የገደለው ለጥቅም ሲል ነው፡፡ እስኪ የሰዎችን ታሪክ እይው አፍሪካውያንኮ በራሳቸው በአፍሪካውያን ይጨቆኑ ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ሰው መሰሎቹን ይሰበስብና ሌሎቹን የሀገሩን ልጆች ይጨቁናል፡፡ መጀመሪያ የገዛ ወገኖቻቸውን ለዐረቦች በባርነት ሲሸጡ የነበሩት የሀገራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አፍሪካውያን በባርነት ተሽጠው አሜሪካ ሲሄዱ ደግሞ ነጮቹ ጥቁሮቹን መጨቆን ጀመሩ፡፡ አየርላንዳውያን በእንግሊዞች መከራቸውን አይተዋል፡፡ ዓረቦች በዓረቦች ተሰቃይተዋል፡፡ አየሽ ቤተ መንግሥቱ ላይ ስትቀመጭ ሌላውን ለማግለል ሳጥን ትከፍቻለሽ፤ ከዚያ ሁሉንም በየሳጥኑ ታስቀምጭዋለሽ፡፡
የእምነት፣ የዘር፣ የመልክ፣ የአካባቢ፣ የቋንቋ ሳጥኖችን ከፍተው ሁሉንም እዚያ ስላስቀመጧቸው ተቀማጮቹ ሳጥኑን እንዳለ ተቀበሉት፡፡ ማንነታቸውም አደረጉትና ሳጥኑን ለማስቀረት ከመታገል ይልቅ ራሳቸውን ብቻ ከሳጥኑ ለማውጣት ይታገሉ ነበር፡፡ በሳጥኑ ዛሬ አህዮች ይገቡበታል፤ ነገ ፈረሶች፣ ከነገ ወዲያ ግመሎች፣ ከዚያም በጎች፣ ከዚያም ፍየሎች እየገቡበት ይቀጥላል፡፡ እኛም ዛሬ ያለሳጥን መኖር ከማንችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ እኔን ሲያገኙኝ እንስሳ መሆኔን አይደለም የሚያዩት፤ የትኛው እንስሳ? ይላሉ፡፡ – ፈረስ፡፡ በዚህ አያቆሙም፡፡ ከዚያ ደግሞ የትኛው ፈረስ? የዱር ወይስ የቤት? ይቀጥላል፡፡ -የቤት፡፡ ለጭነት ወይስ ለግልቢያ? መቋጫ የለውም ልጄ፡፡ በትልቁ ሳጥን ውስጥ ራሳችን የሠራናቸው ትንንሽ ሳጥኖችም አሉ፡፡ በእነዚያም ውስጥ ሌሎች ትንንሽ ሳጥኖች አሉ፡፡››
‹‹ ለአንድ የገጠር ጉዞ በእኔ ላይ ይሄድ የነበረ አንድ ሰው ሲናገረው የሰማሁትን ታሪክ ልንገርሽ፡፡ ሰውዬው የከባድ መኪና ሾፌር ነበረ፡፡ ድሮ አሰብ እየተመላለሰ ዕቃ ይጭን ነበር፤ አንድ ጊዜ ወደ አሰብ ሲሄድ በረሃው ላይ መኪናው ይበላሽበታል፡፡ ከዚያም እዚያው ማደር ስለነበረበት ለምግቡ የሚሆን ፍየል ከአካባቢው የአፋር ሰው ይገዛል፡፡ አፋሩ ሰውዬው ፍየሏን መሸጥ ብቻ ሳይሆን አርዶ፣ ጠብሶ ያቀርብለታል፡፡ ሾፌሩ ምግቡን እየበላ የሸጠለትን የአፋር ሰው ‹‹እንግዲህ ትቼህ መብላቴ ነው፤ እንብላ እንዳልልህ የክርስቲያን ሥጋ አትበላም ብዬ ነው›› ይለዋል፡፡ አፋሩ ሰውዬ ይገርመውና ‹‹እኔው አዋልጄ፣ እኔው አሳድጌ፣ እኔው አርጄ፣ እኔው ጠብሼ ያመጣኋትን ፍየል ምንጊዜ ክርስቲያን አደረግካት?›› አለኝ ብሎ ሲያወራ ሰማሁት፡፡ አየሽ ሌላን ማግለል ስትፈልጊ የሆነ ነገር ትፈጥሪያለሽ፡፡ ማቅረብም ስትፈልጊ እንደዚያው፡፡› ‹‹ብዙ ዓይነት ነጻ አውጭዎች አሉ፡፡ እኔ አሁን የፈረስ ነጻ አውጭ ውስጥ ልግባ ወይስ የአህያ? ወይስ የበቅሎ?›› አለቻት ግልገሏ፡፡ ‹‹የእንስሳት ነጻ አውጭ ካለ እዚያ ግቢ፡፡ አንቺ እንስሳ ነሽ፡፡ የቀረው ከመኖር የመጣ ስም ነው፡፡  እንስሳት ሁሉ ነጻ ሳይሆኑ በቅሎ ተለይታ ነጻ ልትሆን አትችልም፡፡ አንድን አካባቢ ብቻውን ንጹሕ ማድረግ አትችይም፡፡ ምክንቱም ዝንቧ ከወዲያኛው ማዶ ትመጣለችና፡፡ ከእኛም ወገኖችኮ ሜዳ በመኖራቸው የተነሣ ‹የሜዳፈረስ›› ተብለው የቀሩ አሉ፡፡ እኛ ከሰው ተጠግተን ‹የቤት ፈረስ›› ለመሆን ቻልን፡፡ ‹‹የቤት አህዮች›› አሉ፡፡ ‹‹የሜዳ አህዮች››ም አሉ፡፡  የስም ጉዳይ ነው፡፡ የአኗኗር ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ መንግሥት ከነገሥታት ጋር የሚኖር አንበሳ ነበርኮ፡፡  የነገሥታቱ ዙፋን እንዲያውም የአንበሳ ቅርጽ ነበረው፡፡ በዚያው ዘመን ግን ንጉሡ ጫካ ወጥተው ሌላ አንበሳ ገድለው እየተዘፈነላቸው ይመጣሉ፡፡ ጀርባሽን ለመጋለብ ምቹ ካደረግሽው ምንጊዜም የተሻለ ተወዳጅ ትሆኛለሽ፡፡
እንግሊዞች ‹‹Better to ride on ass that carries me, than on a horse that throws me –
የምትገለብጠኝን ፈረስ ከምጋልብ፣የምትሸከመኝን አህያ ብጋልብ ይመረጣል›› ይላሉ፡፡ ቤት የቀረው ውሻ ዱር ከቀረው ውሻ ጋር በመለያየታቸው ዛሬ አንዱ አንዱን እንደ ጠላት ያባርረዋል፡፡ ሰው ብልጥ ነው፡፡ አንዱን ወደ ራሱ አቅርቦ ውሻ አደረገውና ‹‹ቦቢ›› እያለ በማቆላመጥ ነጻ የወጣ አስመሰለው፤ ሌላውን ደግሞ ቀበሮ፣ ተኩላ ብሎ ጫካ ተወውና እርሱን መግደል ጀግንነት እንዲሆን አደረገው፡፡ አሁን ውሾቹ የሠለጠኑና ነጻ የወጡ መስሏቸው ተኩላና ቀበሮ ሲያብርሩ ይኖራሉ፡፡ አየሽ ጉዳዩ የዘር አይደለም፡፡ በዘር ከሰው ተኩላ ለውሻ ይቀርበዋል፣ ቀበሮ ይዛመደዋል፡፡  ጉዳዩ የጥቅም ጉዳይ ነው፤ የመደብ ጉዳይ ነው፡፡ ከቀበሮውና ከተኩላው መካከል ደግሞ የተወሰነውን ይወስዱና ፓርክ ውስጥ አስገብተው ያለፈለት ያስመስሉታል፡፡ እርሱም ማግኘት የሚገባውን ሳይሆን ራሱን ከጫካው ኑሮ ጋር ስለሚያነጻጽር ‹ተመስገን› እያለ ይኖራል፡፡››
‹‹ነጻነት የፍጡር ሀብት ነው፡፡ ለእነ እገሌ ተብሎ የሚቆረስ አይደለም፡፡ ጨቋኙም ተጨቋኙም ነጻ ካልወጣ ሙሉ ነጻነት አይገኝም፡፡ ጨቋኝነት ከአስተሳሰብ ባርነት የሚመጣ ነው፡፡ ከአመለካከት ድህነት የሚከሰት ነው፡፡ ሙሉ ነጻነትን ለማግኘት እርሱን ነጻ ማውጣት አለብሽ፡፡ ካልሆነ ግን ጉዞው አንዱን ጨቋኝ በሌላ ጨቋኝ መተካት ነው የሚሆነው፡፡

( ኤነር ደብረ መንከራት ቅዱስ አማኑኤል ገዳም )

Wednesday, 11 July 2018

ለውጥን ባልተለወጠ ሰው እንደማካሄድ ያለ ከባድ ነገር የለም


ከገበሬዎች ጥበብ አንድ እናንሣ፡፡



ጉንዳን ቤቱን ሲወርረው አንድ ቁራጭ ሥጋ ያመጣሉ፡፡ መሐል ወለሉ ላይ ይጥሉታል፡፡ ዓላማ ሰንቆ በአንድ የጉንዳን ንጉሥ እየተመራ በሰልፍ የገባው የጉንዳን ሠራዊት ነገር ዓለሙን ሁሉ ትቶ እየተተራመሰ ወደ ቁራጩ ሥጋ ይሰበሰባል፡፡ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ሥጋው ላይ ይሠፍራል፡፡ ገበሬዎቹ ሁሉም ጉንዳን አንዱ በሌላው ላይ እየወጣ እስኪቆነስ ድረስ ይጠብቁትና ያንን ሥጋ አውጥተው ይጥሉታል፡፡
ከጉንዳን የተሻለ አእምሮ ሳይዙ ለውጥን ማራመድ በአጭር ለመቀጨት ራስን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ በዓላማ የታገልንበትን፣ የዘመትንበትንና የተሰለፍንበትን ዋና ነገር ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ቁራጭ ሥጋዎች ሲያስቱን እንደማየት አስቂኝም አሳዛኝም ክስተት የለም፡፡ የሆኑ ብልጦች ቁራጭ ነገር በመንገዳችን መካከል ይወረውሩልናል፡፡ እኛም ጅሎች መንገዳችንን እንተወዉና ወደተወረወረው ቁራጭ ሥጋ እንሯሯጣለን፡፡ እዚያ ላይ እንደ ጉድ እንሠፍራለን፡፡ ያን ጊዜ እኛን ከዓላማችን አውጥቶ መጣል ቀላል ይሆናል፡፡ መቼም ለውጥን ባልተለወጠ ሰው እንደማካሄድ ያለ ከባድ ነገር የለም፡፡ ቁርጥራጭ ሥጋዎችን ትተን ወደ ዓላማችን እንገሥግሥ፡፡ ሪከርድ ለመስበር እየሮጠ፣ መንገድ ላይ ለሚሳደብ ሰው መልስ የሚሰጥ አትሌት የለም፡፡ ወይ ጅል ወይ ቂል ካልሆነ በቀር፡፡



Daniel Kibert

Thursday, 5 July 2018

የሃይማኖት አባቶች ተጣልተው ፖለቲከኞች ታረቁ እያሏቸው ነው

ምላጩ አብጦ ውኃው አንቆ

‹ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል፣ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡታል› ይላል የሀገሬ ሰው፡፡ የኢትዮጵያም አንዱ ችግሯ ይኼ ነው፡፡ የምላጭ ማበጥና የውኃ ማነቅ፡፡ የተጣሉትን አስታራቂ፣ የተለያዩትን አንድ አድራጊ መሆን የነበረባቸው የሃይማኖት አባቶች ተጣልተው ፖለቲከኞች ታረቁ እያሏቸው ነው፡፡ ለፍትሕ ዘብ ቆመው፣ ደኻ አንዳይበደል ፍርድ እንዳይጓደል ማድረግ የነበረባቸው የዳኝነት አካላት ዜጎች እንዲበደሉ፣ የፍርድ ሚዛን እንዲያዘነብል፣ ግፈኞች በሕግ ስም የፈለጉትን እንዲያደርጉ መሣሪያ ሆነዋል፡፡ ዜጎችን በሕግ ጥላ ሥር ለማረም የተዘጋጁ ማረሚያ ቤቶች የሰዎች ‹ቄራ› ሆነዋል፡፡ የዜጎችን ችግር ለመፍታት የተቋቋሙ የ‹ኢሚግሬሽን› ቢሮዎች የዜጎች ማኘኪያ› ሆነዋል፡፡ 

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ከአውሮፓና ከእስያ የመጡ ስደተኞችን እየተቀበለ ከዜጋውም በላይ ክብርና ፍቅር ሲሰጥ የኖረ ማኅበረሰብ የገዛ ወገኑን ‹ውጣልኝ፣ ሂድልኝ፣ አልይህ፣ አልስማህ› ይላል፡፡ ከሺ ዓመታት በላይ የነጻነት ታሪክ የሚቆጥር ሕዝብ አሁንም ‹ነጻ አውጭ ድርጅት› ይመሠርታል፡፡ የእርሱን ሰንደቅ ዓላማ የነጻነት ዓርማ አድርጎ ለጥቁር ሕዝብ የሰጠ ሕዝብ እንደገና በሰንደቅ ዓላማ ላይ ይከራከራል፡፡ አፍሪካ ተከፋፍላ መነጋገርና መገናኘት ባቃታት ጊዜ ምዕራብና ምሥራቅ ዞሮ የአፍሪካን አንድነት ያመጣ ሕዝብ እርሱ ራሱ ተከፋፍሎ መከራውን ያያል፡፡ እነ እገሌ ‹እኛ ታግለን ባመጣነው ለውጥ እኛው መጠቀም አለብን› አሉ እያለ ሲያማርር የኖረ ወገን እርሱ ታግሎ ሌላ ለውጥ ያመጣ ሲመስለው፣ እርሱም በተራው ‹እኛ ታግለን ባመጣነው ለውጥ ሌላ ተጠቀመበት› እያለ ያላዝናል፡፡ አስገራሚ ነው መቼም፡፡
ውኃ አንቆ ምላጭ አብጦ መከራችን እናያለን፡፡

Daniel Kibert

Tuesday, 3 July 2018

ጊዜ ጠባቂ ቦንብ

Daniel Kibert

አንድን ሕዝብ ወይም ማኅበረሰብ በተመለከተ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚደረጉ አሉታዊ የገጽታ ግንባታዎች ውጤታቸው ከሚታሰበውም የከፋ ነው፡፡ በዓለም ላይ አደጋ ላይ የወደቁ ማኅበረሰቦችን ታሪክ ስንመለከት ከሁለት ወገን የመጡ አካላት የቆሰቆሱት እሳት ያስከተለውን ረመጥ እናይባቸዋለን፡፡ አንደኛው እነርሱን ከሚወደው ወገን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከሚጠላቸው ወገን ነው፡፡

የተጠቂው ወገን ነኝ የሚለው አካል ያልተሰጠውን ውክልና እየወሰደ የሚፈጽማቸው ተግባራትና የሚያቀርባቸው ሐሳቦች በተቃራኒ ሆነው ነገሩን ለሚቆሰቁሱት ቢላዋ ያቀብላል፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ልዩ ተጠቃሚዎች ሚሊዮኖችን ወክለው ለመታየት ይጥራሉ፡፡ እፍኝ የማይሞሉ አቀንቃኞች የማኅበረሰቡ አፈ ጉባኤ አድርገው ራሳቸውን እየሾሙ የሚናገሯቸው ንግግሮች የዚያ ማኅበረሰብ አቋም መስለው እንዲታዩ ይተጋሉ፡፡

በአንድ ማኅበረሰብ ስም ጥቅም የሚያገኙ አካላት በየዘመናቱ ይፈጠራሉ፡፡ በክርስትናና በእስልምና ስም በተፈጸሙ ወረራዎች፣ ዝርፊያዎች፣ ቅኝ ግዛቶች፣ ጦርነቶችና ጭቆናዎች ተጠቃሚዎቹ አማንያኑ አይደሉም፡፡ ተጠቃሚዎቹ በእምነቱና በአማንያኑ ስም የሚነግዱት አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት እምነቱንም ሆነ አማንያኑን የሚፈልጓቸው ለሁለት ነገር ነው፡፡ ለምክንያትነትና ለከለላነት፡፡ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው ግለሰባዊ ስግብግብነትና የሥልጣን ጥመኝነት ላስከተለው ክፉ ተግባር የተቀደሰው ሃይማኖት ምክንያት እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዘራፊዎቹና ገዳዮቹ እንዳይነኩ እምነቱን ለሽፋንነት ይፈልጉታል፡፡ እነርሱን መንካት እምነቱን መንካት ተደርጎ እንዲወሰድ፡፡ በዘር ከለላ ተከልለው የሚበዘብዙና የሚጨቁኑ ሰዎችም ይሄው ነው መንገዳቸው፡፡  

በአንድ ማኅበረሰብ ስም የሚነግዱት አካላት በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚፈጥሩት የተበላሸ ሥዕልም አለ፡፡ የእነርሱ መጠቀምና ክብር፣ ሥልጣን ማግኘትና መግዛት የማኅበረሰቡ ተደርጎ እንዲወሰድ ያደርጉታል፡፡ በተለይ ደግሞ ግልጽነትና ጠያቂነት ባልዳበረበት ማኅበረሰብ ውስጥ እገሌ እና እገሊት፣ ይሄና ያ፣ እንዲህና እንዲያ ሁሉንም የሚገልጡ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለጅምላ ፍረጃ ያጋልጣል፡፡ አበበ ተጠቀመ ማለት አበበ የተገኘበት ማኅበረሰብም ተጠቀመ ማለት ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡ አበበም እንደዚያ እንዲሆንለት ይፈልጋል፡፡

 ከዚህ ባሻገር ደግሞ ዐውቀውና ሳያውቁት ሌላውን ማኅበረሰብ የማጥላላት፣ የማናናቅና የመፈረጅ ዘመቻ የሚያደርጉም አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግለሰብን ከማኅበረሰብ መለየት ያቃታቸው ናቸው፡፡ አንድ በሬ ከወጋቸው በሬዎችን ሁሉ የሚጠሉና ሊያርዱ የሚነሡ ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ምንጊዜም የሚጠቀሰው በአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰው ነው፡፡ ምንም እንኳን ክርስቶስን የተቃወሙት፣ ያስፈረዱበትና የሰቀሉት ከአይሁድ ወገን የተገኙ ባለ ሥልጣናትና ጥቅመኞች ቢሆኑም፣ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያትና ክርስቲያኖችም ከአይሁድ ወገን የተገኙ ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ በየዘመናቱ የተገለጠው ግን ስለ ሰቃዮቹ አይሁድ እንጂ ስለ ክርስቲያኖቹ አይሁድ አልነበረም፡፡ በጅምላ ‹አይሁድ ይህንን አደረጉ› እየተባለ የተነገረው ነገር ከ40 ሚሊዮን በላይ አይሁድ ያለቁበትን ጥፋት በየዘመናቱ አምጥቷል፡፡

በዘመነ ክርስቶስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አይሁድ እንደነበሩ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ይናገራል፡፡ ከእነዚህ መካከል ግን በክርስቶስ መከራና ሞት የተሳተፉት ከአምስት ሺ አይበልጡም፡፡ መከራው ግን ለሁሉም ተረፈ፡፡

በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ በየቀልዶቻችንና በየዘፈኖቻችን የምናስተላልፈው አንድን ወገን የማስጠላትና የማክፋፋት ዘመቻ ማጣፊያው የሚያጥር ነው፡፡ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ የሚቀመጡት እነርሱ ናቸው፡፡ ልጆቻችን ስለዚያኛው ማኅበረሰብ የሚኖራቸውን አመለካከት የሚቀርጹት በነዚህ ጽሑፎች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነው፡፡ በሀገራችን አንድን ማኅበረሰብ የሚያጥላሉ ዘፈኖች ቦታ እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡፡ አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያጠቁ የፕሮፓጋንዳ ቃላት ተፈጥረዋል፤ አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያሸማቅቁ መግለጫዎች በባለሥልጣናት ደረጃ ተሰጥተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሌሎቹ ጋር እየተደመሩ የተጠቂነት ስሜት የሚሰማው፣ራሱን ወደመከላከል የሚገባ፣ሕልውናው አደጋ ላይ መድረሱን ያመነ ማኅበረሰብ ፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ያለው ማኅበረሰብ ሲፈጠር ደግሞ ከድልድይ ይልቅ ግንብ እየገነባ ከሌላው ጋር መራራቅንና መከለልን ይመርጣል፡፡

በአውሮፓ ከ16ኛው መክዘ በኋላ ለተስፋፋው የፀረ ሴማዊነት ስሜት የታላቁ ጸሐፌ ተውኔት የሼክስፒር ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር አስተዋጽዖ ማድረጉ ይነገራል፡፡ የቬነሱ ነጋዴ ዋና ገጸ ባሕርይ ሻይሎክ የተባለ ገብጋባ ይሁዲ ነው፡፡ ሻይሎክ የዕብራይስጥ ስም አይደለም፡፡ ነገር ግን ‹ሳላን› ከተሰኘውና የሴም የልጅ ልጅ፣ የዔቦር አባት ከሆነው ሰው ስም የተቀዳ መሆኑ ይታመናል፡፡ የሻይሎክ ገብጋባነትና ጭካኔ ለከት የለውም፡፡ ከእርሱ ገንዘብ የተበደረው ክርስቲያኑ አንቶኒዮ መክፈል ቢያቅተው መያዣው ከአንቶኒዮ ሰውነት የሚቆረጥ አንድ ሙዳ ሥጋ ነው፡፡ አንቶኒዮ ብድሩን መክፈል አቃተው፡፡ ሻይሎክም ሙዳ ሥጋውን ከአንቶኒዮ ሰውነት ቆርጦ ለመውሰድ ተነሣ፡፡

ሼክስፒር ይህንን ድራማ የጻፈበት የኤልሳቤጥ ዘመን(Elizabethan Era – 1558-1605) የሚባለው ጊዜ እንግሊዞች በፀረ ሴማዊነት የተለከፉበት ዘመን ነበር፡፡ ከ1290 ጀምረው ከእንግሊዝ የተባረሩት አይሁድ ወደ እንግሊዝ ለመግባት አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ የድራማው መቼት በሆነው ቬነስ ደግሞ አይሁድ ይጠላሉ፤ ለጥቃት የሚያጋልጥ የተለየ የመለያ ልብስ እንዲለብሱ ይገደዳሉ፡፡ በሼክስፒር ዘመን የነበሩ ድርሰቶች፣ ቀልዶች፣ ሥዕሎችና ድራማዎች አይሁድን ገብጋቦች፣ ክፉዎችና አጭበርባሪዎች አድርገው የሚስሉ ነበሩ፡፡ የሼክስፒርን ድርሰቶች ያጠኑ ሊቃውንትም ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር ‹የቬነሱ ይሁዲ› እየተባለ ይጠራ እንደነበር ይገልጣሉ፡፡ ይህም ክሪስቶፈር ማርሎዊ ከደረሰው ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ጋር ያመሳስለዋል፡፡ በ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ውስጥ የሚገኘው ይሁዲው ባራባስ እንደ ሻይሎክ ክፉ ነው፡፡ የቬነሱ ነጋዴ የሚያልቀው ሻይሎክ ወደ ክርስትና ሲመለስ ነው፡፡

ይህ በሼክስፒር ድርስት ውስጥ የተሳለው ይሁዲ ገጸ ባሕርይ አይሁድ ቀድሞ ከተሳሉበት ገጽታ ጋር ተደምሮ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታዩበትን መነጽር አበላሸው፡፡ ስለ እነርሱ ክፉ መናገር፣ መጻፍና መቀለድ የተፈቀደ መሰለ፡፡ ለእነርሱ የሚከራከርም ጠፋ፡፡ በኋላ ዘመን በአይሁድ ላይ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ያመጡት እነዚህን የመሰሉ ድርሰቶች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነበሩ፡፡ 

ዛሬም እኛ ኢትዮጵያውያን ከሁለቱም ወገን ልንርቅ ይገባናል፡፡ የሌላችሁን የማኅበረሰብ ውክልና ለሥልጣናችሁ፣ ጥቅማችሁና ለክብራችሁ ስትሉ የምታቀነቅኑ ተቆጠቡ፡፡ ማንም አልወከላችሁም፡፡ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤትም ይህንን አያረጋግጥላችሁም፡፡ ሕዝቡ ያላለውን በሕዝብ ስም አትናገሩ፡፡ እናንተ ስትጠግቡ ሕዝቡ እንደጠገበ አታስመስሉት፤ እናንተ ሲያማችሁም ሕዝቡ እንደታመመ አታስቃስቱት፡፡ እናንተ ስትራቡ ሕዝብ የተራበ አድርጋችሁ አትሳሉት፤ ዕዳችሁን ብቻችሁን ውሰዱ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ስለ አንድ ሕዝብ በጅምላ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች፣ ቀልዶች፣ ጽሑፎች፣ ዘፈኖች፣ ግለሰቦችን ጠቅመው ሕዝብን ይጎዳሉ፡፡ ይበልጥ ደግሞ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ ተቀርጸው እንደ ጊዜ ጠባቂ ቦንብ ይቀመጣሉ፡፡ ለሕዝብ ሲባል ግለሰቦችን መተው እንጂ ለግለሰቦች ሲባል ሕዝብን ማጥፋት ሕጋዊም ሞራላዊም አይደለም፡፡