የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል። ያልታደለች ሀገር… ዕንቁ ኢንጅነሯን አጣች፡፡ የገዳዮች ማንነትና ከገዳዮች ጀርባ ማን እንዳለ ባይረጋገጥም…. በሰው እጅ እንደተገደሉ ግን ታውቋል፡፡ የሸሚዝ ኮሌታቸው ተቀዶ በግራ ጆሯቸው እየደሙ እንዳዩአቸው እማኞች ተናግረዋል። ከሕሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ብዙ ምሥጢር ስለያዘ ግድያው ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ኢንጅነሩ ሁሌም ለገብርኤል በዓል… በዓልይ ንግሥ ሲሆን ግቢ ገብርኤል ያስቀድሳሉ። እኔም ሁለት ጊዜ በዓይኔ አይቻቸዋለሁ። ዛሬም የተገደሉት ወደ ገብርኤል ንግሥ እየሄዱ ሳለ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ለንግሥ እንደማይቀሩ ይታወቃልና።
ትጉሁ ሰው፣ ጠቢቡ መሐንዲስ፣ ትሁቱ ክርስቲያን ኢንጅነር ስመኘው ሞቱ ሲባል ሰማይ ምድሩ ነው የዞረብኝ። በአካል ከ4 ጊዜ በላይ አግኝቻቸዋለሁ። ፈገግታ የማይለያቸው ትሁት ሰው ናቸው። እና ሞቱ? እኔ አላምንም። እንባየን ማቆም አልቻልሁም።
የበረሃው ትጉህ ሰው ሞቱ። “የሕዳሴው ግድብ እንዳለቀ ብሞት አይቆጨኝም” ይሉ የነበሩት ተስፈኛ መሐል ላይ ቀሩ። “ይህ ግድብ የቀደሙ አባቶቻችን ድል ማስታወሻ ነው። አድዋ ላይ ሞተው የቀሩህ ጀግኖች ሕይወት ማስታወሻ ነው። እነርሱ የሞቱት ልጆቻቸው ይህን መሰል ታሪክ እንድንሰራ ነው። ይህ እንደ አድዋ ሕዝቡን በአንድነት ያዘመተ ታሪክ ነው።” እያሉ ሕዝቡን ያጽናኑ የነበሩት ባለ ብሩህ አእምሮውና ትሁት ሰብዕናን የተላበሱት ጀግና በጨካኞች ሞቱ። ምን አይነት አረመኔነት ይሆን? እንዴት ያለ ጭካኔ የተላበሰ ሰወ በላ በእኝህ ዕንቁ ሰው ላይ ሞት ፈረደ??? ያማል። የምር ያማል።
No comments:
Post a Comment