Thursday, 9 August 2018

ባንዲራ የማስረዘም ፉክክር

ሰሞኑን የማያቸው ሁለት ነገሮች ግርርርርም ይሉኛል
ባንዲራ የማስረዘም ፉክክር ይገርመኛል
አንዳንዱ ባንዲራ ከመርዘሙ የተነሳ ፤ተሸንሽኖ፤ ሱሪና ቀሚስ ሆኖ ቢሰፋ አንድ የገጠር መንደር አመት ያለብሳል፤

የጦቢያ ፖለቲካ የተራቀቀ አይደለም፤ ለብር እና ለክብር የሚደረግ ትግል ነው፤ ከላይ ያሉት ጮሌዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ፤ በተራበ ሰው ስም፤ በተፈናቀለ ሰው ስም፤ነፃነት በጠማው ሰው ስም ፤ በግዜር ስም፤ በናት ሀገር ስም፤ በናት ጎሳ ስም፤ ሀብት ፤ ስልጣንና ዝና ይሰበስባሉ፤
ከታች ያለው ጎበዝ የኔ ባንዲራ ቁመት ካንተ ባንዲራ ቁመት ይበልጣል፤ በሚል ሀሳብ ተጠምዶ ድርሻውን ሳይጠይቅ፤ ክሬም እድሜውን ያባክናል ፤ አንድ ቀን ባንኖ ሲነቃ በጁ ምንም የለም፤ ሰው መሆን አይቀርምና ላመፅ ያቆበቁባል፤ ይህን ጊዜ ተጠባባቂው ጮሌ ከሰገነቱ ወርዶ ለጭፍራነት ይመለምለዋል፤የምድር ወገብ የሚያክል ባንዲራ ያሸክምና በግሩ ፈንጅ ያስጠርገዋል፤
ካርታ በመሳል ሰመመን ጦዘው የሚውሉ አሉላችሁ ደግሞ፤ ድሮ አገር ለመያዝ ያማረው ብዙ ድካም ነበረበት፤ ፈረስ መግዛት ፤ጭፍራ ማደራጀት፤ ግብር ማብላት፤ መድማት መራብ መጠማት እንቅልፍህን እና ህይወትህን መሰዋት ይጠበቅበት ነበር፤ አሁን አገር ማቅናት አልጋ ላይ ተንበልብሎ ላፕታፕ ላይ ካርታ ከመሳል አያልፍም፤ እያንዳንዱ ጎራ የሚስለው ካርታ አንድ የሚያስቅ ተመሳሳይነት አለው፤ ወደ አጎራባች ባህር ወይም ክልል ዘልቆ የሚገባ ሾጠጥ ያለ ነገር አለው፤ያ ሾጣጣ ነገር ያባት አገር ብልት ይሆን? ለማንኛውም ካርታ ስንስል ፤ ጊዜው፤ የመነጋገር፤ የማሽኮርመም፤በፍቅር የመማረክ እንጂ አስገድዶ መድፈር እንዳልሆነ እናስብ፤
የለማ ቡድን የፍቅር የትህትናንና የታታሪነትን ዋጋ ለማሳየት የሚያደርገው ሙከራ የሚደነቅ ነው፤ ግን ሌላው ተምሳሌትነቱን ካልተከተለው በቀር፤ ለውጥ አይታሰብም፤ አሁን አሁን፤ ተምሳሌትነት አጠገብ ቆሞ ፎቶ መነሳት እንጂ ተምሳሌትነትን መከተል ብዙ አይታይም፤
እዚህ ላይ የቀበጢቱ ታሪክ ትዝ አለኝ፤
አንዲት ከመዘነጥና ሞባይሉዋን እንደ ልጅ ራስ ከመደባበስ ውጭ፤ ስራ በደረሰበት የማትደርስ ቀበጥ ልጅ ነበረች፤ታላቅ ወንድሙዋ እና እናቱዋ የልጂት ባህርይ አሳሰባቸው፤ እስቲ ስራ እንድትለምድ አንድ ነገር እናድርግ ተባባሉ፤ለምን አርአያ ሆነን አናሳያትም? ያኔ ህሊናዋ ወቅሱዋት መስራት ትጀምራለች ብለው እቅድ ነደፉ፤
አንድ ማለዳ ላይ፤ ቀበጢት መስታወት ፊት ቆማ ፤ፊትዋን በፓውደር ስትጠበጥብ ፤ እናት አጠገቡዋ ያለውን ወለል መጥረግ ጀመሩ፤ ልጅ እየሮጠ ደረሰና “ እማየ እኔ እያለሁማ በደካማ ጉልበትሽማ አትጠርጊም” ብሎ መጥረጊያውን ለመቀማት ይታገል ጀመር፤እናት በበኩላቸው “እኔ እናትህ ክንዴን ሳልንተራስማ አንተ አትጠርግም” ብለው መጥረጊያውን ሰንገው ያዙ፤በዚህ አይነት ሲፋለሙ ቀበጢቱ ፊትዋን ከመስታውቱ ሳትነቅል እንዲህ ስትል ተሰማች፤
“ሽሽሽሽሽሽስ ! እየረበሻችሁኝ ነው ተራ በተራ ጥረጉ!”

Bewketu Seyoum

No comments:

Post a Comment