Wednesday, 19 September 2018

የድኅረ ወሊድ ጭንቀት (postnatal depression)

የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) እናቶች ከወለዱ በኋላ የሚያጋጥማቸው፣ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ሊዘልቅ የሚችል የጭንቀት ዓይነት ነው፡፡ ልጅ መውለድ የሚያስከትለውን አዲስ ሁኔታ፣ ጠባይ፣ የሰውነትና የስሜት ለውጥ ለማስተናገድ በሚደረገው እናታዊ ትግል ምክንያት በመጀመሪያዎቹ ቀናት የጠባይ ልውጠት(baby blues) ይከሠታል፡፡ ይህ ግን ለሁለትና ለሦስት ቀናት የሚቆይ ነው፡፡ ነገሩ ከእነዚህ ቀናት በላይ ከዘለቀ ወደ ጭንቀት ያድጋል፡፡ እርሱም የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) ይባላል፡፡ በዚህ ዓይነት ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ እናቶች ‹ሙዳቸው› ይጠፋል፤ የተሸናፊነት ስሜት ይሰማቸዋል፤ ተስፋ ቢስነት ይነግሥባቸዋል፤ ስለ ተወለደው ሕጻን አብዝተው ይጨነቃሉ፤ አንዳች የሆነ ነገር ልጃቸውን የሚነጥቃቸውና የሚገድልባቸው ወይም የሚያሳምምባቸው ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ፈልገው የሚያመጡት ጠባይ ሳይሆን ወሊድ የሚያመጣባቸው ክስተት ነው፡፡
የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ቁጣን ያስከትላል፣ ያነጫንጫቸዋል፣ ተናጋሪ አንዳንዴም ጯሂ ያደርጋቸዋል፡፡ እጅግ የሚገርመው ደግሞ የሚቆጡትም፣ የሚነጫነጩትም፣ የሚናገሩትም፣ የሚጮኹትም በሚወዱትና በሚቀርባቸው ሰው ላይ ነው፡፡ ይህም መውለድ ያመጣው የጠባይ ለውጥ እንጂ ውሳጣዊ የልቡና ለውጥ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የሚነጫነጩበትን፣ የሚቆጡበትንና የሚጮኹበትን ብቻ ለተመለከተ ሰው ትዳሩ የፈረሰ፣ ቤተሰቡ የታመሰ ሊመስለው ይችላል፡፡ ግን በውስጣቸው ፍቅር አለ፡፡ ለዚህም ነው በሚቀርቡትና በሚወዱት ሰው ላይ ብቻ የሚያደርጉት፡፡
በዚህ የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ውስጥ ያሉ እናቶች ከምንም ጊዜ በላይ ክብካቤ፣ ፍቅርና እገዛን ይፈልጋሉ፡፡ ከምንም ነገር በላይ የሚረዳቸው፣ የሚገነዘባቸው ሰው ይሻሉ፡፡ ባሎቻቸው፣ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውና ጠያቂዎቻቸው ሳይረዷቸው ከቀሩ ጭንታቸው ይበልጥ ይጨምራል፡፡ ይህ ችግር የቤተሰባቸውን መረዳትና እገዛ ካገኘ በቶሎ የሚጠፋ መሆኑን የሚያውቁ ብልሆች ጊዜውን በትዕግሥት፣ በአርምሞ፣ በመቻልና በማሳለፍ ይሻገሩታል፡፡ የማይረዱ ቤተሰቦች ግን መልሰው ይጮኹባቸዋል፤ ይቆጧቸዋል፤ ያኮርፏቸዋል፤ ይርቋቸዋል፤ ከዚህም አልፎ ይፈርዱባቸዋል፡፡ በተለይም ወንዶች በዚህ ይታማሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለውጥንና ተስፋን ወልዳ አሁን የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ላይ ናት፡፡ ስለዚህም በሕዝቡ ላይ ንጭንጭ፣ ተሥፋ መቁረጥ፣ ስሜታዊነትና ቁጣ ይታያል፡፡ ይህንን የሚገልጠው ደግሞ በሚያደንቀው፣ በሚወደውና በሚያከብረው ላይ ነው፡፡ ይህ ግን የሚያልፍ ጠባይ ነው፡፡ ልጁ እያደገ፣ እናቲቱም እየበረታች ስትሄድ ጭንቀቷ ወደ ደስታ፣ ንጭንጯም ወደ ሳቅና ጨዋታ ይቀየራል፡፡ ነገር ግን ይህን ወቅት በሚገባ የሚረዳ የቅርብ ቤተሰብ ያስፈልጋታል፡፡ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የሕዝብ መሪዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ሹማምንትና የሐሳብ መሪዎች ይህንን የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ጠባይ መረዳት፣ ለአንዲት ወላድ እናት ሊደረግ የሚገባውን ክብካቤ ማድረግ፣ በወሊድ ምክንያት የሚከሠቱ የጠባይ ለውጦችን ዐውቆ የተጠናና ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ሁሉም ተናዳጅ፣ ሁሉም፣ ተሥፋ ቆራጭ፣ ሁሉም ጯሂ፣ ሁሉም ተነጫናጭ፣ ሁሉም አፉ እንዳመጣለት ወርዋሪ፣ ሁሉም ልቡ ያጎሸውን ሁሉ ተናጋሪ ከሆነ የእናቲቱ ጭንቀት እየጨመረ፣ ጤንነቷ እየተቃወሰ፣ የልጁ ጤንነት እየተበላሸ፣ የቤተሰቡ ሰላም እየተናጋ፣ በመጨረሻም ለደስታና ለእልልታ የተወለደው ልጅ ለመከራና ለጭንቀት ይሆናል፡፡
እንረጋጋ፣ እናረጋጋ፤ ሀገር የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) ላይ ናት፡፡

No comments:

Post a Comment