Sunday, 9 June 2019

ለማኙና የኢትዮጵያ ህዝብ!

ለማኙና የኢትዮጵያ ህዝብ!
«ዘውድአለም ታደሠ»

ጠሚዶ አብይ  አህመድን ወደካርቱም ይዛው የሄደችው አውሮፕላን ላይ ቴክኒሺያን ሆኖ የሄደው ጓደኛዬ ነው። ትናንት «ከጠሚዶ አብይ  አህመድ ጋር ካርቱም ደርሼ መጣሁ» ሲለኝ «ኦህ ፎቶ ተነሳሃ አብረኸው?» አልኩት። «አዪዪ» አለኝ በሃዘኔታ። «ስንመለስ እነሳለሁ ብዬ አስቤ ነበር። ሲመለስ ግን ከሰባ በላይ በእስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ይዞ ስለመጣ ግፊያና ለቅሶ ነበር። አልተመቸኝም» አለኝ።
ጠሚዶ አብይ  አህመድን ልታግዘው ቢበዛንኳ አልፎ አልፎ ልትተቸው የምትችለው እንጂ በቋሚነት ደምስርህ እስኪገታተር እያማጥክ ምትቃወመው መሪ አይደለም። ጠሚዶ አብይ  አህመድ ተቃዋሚዎችን አጀንዳ ያሳጣ መሪ ነው። አሁን አሁንማ ሚቃወሙትን ሲያጡ ለምን ፎቶ ተነሳ? ሐገሪቱ ልትፈርስ ደርሳ ለምን ችግኝ ተከለ? ማለት ሁሉ ጀምረዋል 

አዳሜ ፍሬንድሺፕ ተጎልታ ተረከዟን እያስሞረደች፣ የብርጭቆ ወረቀት የመሰለ ቆዳዋን ለማለስለስ 5 ሺ ከፍላ ፌሻል እየተሰራች፣ «ሐገሪቷ ልትፈርስ ደርሳ ጠሚዶ አብይ  አህመድን ለምን ችግኝ ተከለ?» ብላ ትውረገረጋለች። ልክ ሐገሪቷ ልትፈርስ ነው ብላ ሁሉን እርግፍ አርጋ ፆም ፀሎት የያዘች እኮ ነው ምትመስለው አዳሜ! 
የምሬን እኮ ነው። ምድረ ፖለቲከኛ ሐገሪቱ ልትፈርስ ነው!! ይልህና በየሳምንቱ ግሮሰሪ እቁብ ሊጥል ሲመጣ ታገኘዋለህ። ብራዘር ሐገሪቱ ምትፈርስ ከሆነ እቁብ ምን ይሰራልሃል? ያለህን ይዘህ አትነካውም እንዴ? በምትፈርስ ሐገር ላይ በሶስት አመት ሚወጣ እቁብ ይገባል እንዴ? አዳሜ ሐገሪቱ ልትፈርስ ቋፍ ላይ ነች!! እያለ ልጅ ይፈለፍላል። ቆይ የምትፈርስ ሐገር ላይ ልጅ ይወለዳል እንዴ? የታባቱ ሊያሳድጋቸው ነው? ኦገኔ ... ሐገሪቱ ልትፈርስ ነው የሚለው ቁጪ በሉ ሁላ ሐገሩ ላይ የሃምሳ አመት ፕሮጀክት ቀርፆ ነው ሚንቀሳቀሰው!
ለማንኛውም አብያችን እያኮራን ነው! የአፍሪካ መሪዎችኮ ሰው ሐገር ሲሄዱ ሚጎበኙት ሺሻ ቤት ነው። ጭነው ሚመጡት ደሞ ቫያግራና ብራንድ ሽቶ ነው። ጠሚዶ አብይ  አህመድ ግን ከእስር ቢለቀቁ እንኳ ወደሐገራቸው ሚሳፈሩበት ከሌላቸው ከሐገሩ ምስኪኖች ጋር እየተጋፋ ነው ሚመጣው። አሁንማ ሁሉን ነገር ለመድነው! ነፃነቱንም ለመድነው። የፈለጉትን ለፍልፎ አለመታሰሩንም ለመድነው። ሰው ያሻውን አመለካከት ይዞ ካሻው ፓርቲ ካሻው ሚዲያ እንዲያቋቁም መፈቀዱንም ለመድነው! መሪ ዝቅ ብሎ ሰው ሰው የሚሸት ስራ ሲሰራ ማየቱንም ለመድነው። የትናንቱን ጭቆና፣ የትናንቱን ግፍ፣ የትናንቱን የዲሞክራሲ ረሃብ ሁሉ ረሳን!! ዛሬ አንድ ሰውዬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጥበት ያለውን አዳራሽ ተከለከለ ብለን ኡኡ እንላለን። ትናንት ግን እራሱ ሰውዬው የትኛው እስር ቤት እንኳ እንዳለ አናውቅም ነበር። አረ ከሱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊቀበል የሚሰለፍ ጋዜጠኛም ባገሩ የለም ነበር!
ሳስበው ሳስበው እያደነቅን መቆየት የኛ ተፈጥሮ አይደለም። ኑሯችን ከማማረርና ከጦርነት ጋር የተቆራኘ ስለነበር ካልተቃወምን የተሳሳተ ቦታ ላይ የቆምን ይመስለናል። የተቃወመና ያለቃቀሰ ብቻ ትክክልና እውነተኛ ይመስለናል! ምን ላይ እንደነበርን በአንድ አመት ረስተናል! ትናንት በራሱ አንደበት «ጨለማ ክፍል ለአራት አመት ታስሪያለሁ። መፅሃፍ ቅዱስ እንኳ እንዲገባልኝ ብለምን ተከልክዬ ነበር» ያለው እስክንድር ነጋ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሆኖ መግለጫ እንዲሰጥ ሲለመን እምቢ እያለ አዳራሽ ያማርጣል! ትናንት በፌስቡክ ፅሁፍ ወህኒ ወርዶ እግሩ እስኪላላጥ የተደበደበው እንደስዩም ተሾመ አይነት አክቲቪስት ዛሬ ከንቲባውን ከፍ ዝቅ አርጎ ተናግሮ በማግስቱ ከንቲባው ቢሮ በክብር ለውይይት ተጋብዞ አይተናል! ትናንት ሞት ተፈርዶበት ከየመን ከየት ሃይጃክ ሲደረግ የነበረ ፖለቲከኛ ዛሬ ቤተመንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቁጭ ብሎ ይማከራል!
ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ማንም ሰው ይሄን ስለተናገርክ ወንጀለኛ ነህ ተብዬ እታሰራለሁ ብሎ አይሳቀቅም። ዛሬ የሚሳቀቀው ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሳይሆን ባለስልጣን ሆኗል! በስንት ምህላና ለቅሶ የመጣው ይሄ የነፃነት ጭላንጭል ግን እጃችን ሲገባ ረከሰብን! ሳስበው ሳስበው አብይ ራኒ ጁስ በቧንቧ ቢልክልን ሁሉ የለቅሶ ስታየል እንቀይራለን እንጂ ማልቀሳችንን አናቆምም! ሁሉ ነገራችን ከዚያ ለማኝ ጋር ይቀራረባል
ለማኙ ባጋጣሚ ሎተሪ ይቆርጥና አንድ ሚሊየን ብር ደረሰው አሉ። ጋዜጠኞች ከበውት «አሁን በብሩ ምን ልታረግበት አሰብክ?» ሲሉት
«መኪና እገዛበታለሁ» አለ 
«ከዛስ?» ቢሉት
«በመኪና እየዞርኩ እለምናለኋ!» ብሎ እርፍ!

No comments:

Post a Comment