ሃሰተኛ ጋብቻ ፈፅማ ዜግነቷን ቀይራለች፤ ፍቺውንም ለ10 ወራት በምስጥር ይዛ ቆይታለች፡፡ ታክስ አጭበርብራለች… - የስዊድን ሚዲያዎች
በትውልድ ኢትዮጵያዊ የነበረችውና ዜግነቷን በመቀየር ስዊድናዊ ሆና በመወዳደር ሁለተኛ ዓመቷን የያዘችው አትሌት አበባ አረጋዊ በትዳሯ ዙርያ በተፈጠሩ አወዛጋቢ ሁኔታዎች በለቅሶ እና ሃዘን መሰንበቷን የተናገረችው በሳምንቱ መግቢያ ላይ ነው፡፡ አትሌቷ ስዊድናዊ ለመሆን ሃሰተኛ የጋብቻ ሰነድ በማስረጃነት በመጠቀም አጭበርብራለች በሚል ዘገባ ከ6 ወራት በፊት ያብጠለጠላት ታዋቂ የስዊድን ጋዜጣ ኤክስፕረሰን፤ በፖላንድ ሳፖት የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቷ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከመጎናፀፏ አራት ቀናት በፊት ባወጣው ልዩ ዘገባ አበባ አረጋዊ ስዊድናዊ ዜግነት ያለውና አሰልጣኟ ከነበረው ሄኖክ ወልደገብሬል ጋር ባለትዳር ያደረጋትን ሃሰተኛ የጋብቻ ሰነድ በማቅረብ ዜግነት መቀየሯን አስታውሶ ፤ ትዳሩ በፍቺ ከፈረሰ 10 ወራት ማለፉን በመጥቀስ የውዝግብ አቅጣጫውን አክርሮታል፡፡ የፍቺው ወሬ በተሰማበት ወቅት በስዊድን ሚዲያዎች አትሌት አበባ አረጋዊ ማብራርያ ስትጠየቅ የግል ህይወቷን ማብጠልጠላቸውን እንዲያቆሙ ተማፅና፤ ስለ ጉዳዩ ብዙም መናገር እንደማትፈልግ በመግለፅ ትኩረቷ በስፖርቱ በመወዳደር ውጤት ማምጣት መሆኑን ተናግራ ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ስዊድናዊ ሆና በ3 ትልልቅ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በ1500 ሜትር 3 የወርቅ ሜዳልያ ድሎች በማስመዝገብ የተሳካላት አትሌት አበባ አረጋዊ በስዊድን ህዝብ የጥረት ተምሳሌት ሆና እንደ ጀግና ስትከበር ብትቆይም፤ በስዊድን ሚዲያዎች እንድትብጠለጠልና ዜግነቷን ተነጥቃ እንድትባረር ዘመቻ የተቆሰቆሰው ከስፖርቱ ጋር ጎን ጎን ሲወሳሰብ በቆየው የትዳር ህይወቷ ነው፡፡ አትሌት አበባ አረጋዊ በፖላንዱ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወቅት በለቅሶ እና በሃዘን እየታወከች ዝምታ ውስጥ ነበረች፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ግን አትሌቷ ዝምታዋን ሰብራዋለች፡፡ ፒ4 ኤክስትራ ከተባለ የስዊድን ሬድዮ ጋር በስፋት ቃለምምልልስ ያደረገችው አበባ አረጋዊ በአወዛጋቢው የትዳር ህይወቷ ዙርያ የቀረቡላትን ከባባድ ጥያቄዎች በልበሙሉነት ምላሽ ሰጥታባቸዋለች፡፡ ለመሆኑ የአበባ አረጋዊን የአትሌቲክስ ገድልና የትዳር ህይወቷን ያወሳሰበው ጉዳይ ምንድነው? እውነት ዜግነቷን ለመቀየር ሃሰተኛ የጋብቻ ሰነድ ተጠቅማ አጭበርብራለች? ከምታገኘው ገቢስ ለስዊድን መንግስት ሆን ብላ የገቢ ቀረጥ አልከፈለችም ወይ? ወደፊት ስዊድናዊ ሆና በዓለም የአትሌቲክስ መድረኮች መወዳደሯን ትቀጥላለች? እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎችን በማስመልከት ስፖርት አድማስ በሞስኮ 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከአትሌቷ ጋር በተያያዘ በግንባር የነበረውን ተመክሮ በመከለስ፤ ባለፉት ሶስት ሳምንታት በስዊዲሽ ቋንቋ ለንባብ ከበቁት የድረገፅ ህትመቶች ኤክስፕረሰንና ስፖርትብሌድን ዘገባዎች ተርጉሞ በማንበብ እና አትሌት አበባ አረጋዊ በፒ4 ኤክስትራ ሬድዮ የሰጠችውን ቃል በመንተራስ ከዚህ በታች የቀረበውን ዘገባ ያቀርባል፡፡
በአበባ ላይ የውዝግብ አጀንዳው በሞስኮ ሲቆሰቆስ
14ኛው የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና ከ6 ወራት በፊት በሞስኮ ሲካሄድ ኤክስፕረሰን የተባለው የስዊድን ጋዜጣ አትሌት አበባ አረጋዊን መውጭያ መግቢያ አሳጥቷት ነበር፡፡ ጋዜጣው በወቅቱ በአትሌቷ ላይ በሰራው ዘገባ ከአምስት ዓመት በፊት ዜግነቷ ወደ ስዊድን ለመቀየር ባስገባቸው ማመልከቻ የስዊድን ዜግነት ካለውና አሰልጣኟ ከሆነው ሄኖክ ወልደገብሬል ጋር በትዳር እንደተሳሰረች በመግለፅ ያቀረበችው የጋብቻ ሰነድ ሃሰተኛ እንደነበር አንድ ፊላንዳዊ የአትሌቶች ማናጀር ያቀረቡትን ማስረጃ ጠቅሶ ነበር፡፡ ያኔ አበባ አረጋዊ ጋብቻ ወረቀት የስዊድን ዜግነት ወስዳለች መባሉን እንደማትቀበለው በመግለፅ የተቆጠበ ምላሽ ሰጥታ ነበር፡፡ በሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አትሌት አበባ አረጋዊ በ1500ሜ ያገኘችው የወርቅ ሜዳልያ የስዊድን ዜግነቷን ባገኘች ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበችው ግዙፍ ውጤቷ ነበር፡፡ ‹‹እኔ ስለማሸነፌ እንጅ ዜግነት ስለመቀየሬ አላስብም፡፡ በማንኛውም ውድድር ማሸነፍ ያስደስታል፡፡ እዚያም ሆነ እዚህ ሁሉም ደስታ ነው፡፡ የሰራሁበትንና የለፋሁበትን ነው ያገኘሁት፡፡ የስራዬም ውጤት ነው። ዜግነት ስለቀየርኩ ብቻ የመጣ ውጤት አይደለም› በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት የሰጠችው ውድድሩን ከጨረሰች በኋላ አትሌቶች እና ጋዜጠኞች በሚገናኙበት ሚክሲድ ዞን በተገኘችበት ወቅት ነበር። በአካባቢዋ የነበርን የኢትዮጵያና የስዊድን ጋዜጠኞች በወርቅ ሜዳልያ ድሏ ተፈጥሮብን የነበረው ድብልቅልቅ ስሜት የሚረሳ አልነበረም፡፡ ከስዊድን የቴሌቭዥን የሬድዮ እና የህትመት ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች አንዳንዶቹ በአትሌቷ ታሪካዊ ስኬት ከፍተኛ ኩራት ቢሰማቸውም የኤክስፕረሰን ጋዜጠኛ ሌሎች ባለሙያዎች ከወርቅ ሜዳልያው ይልቅ ስዊድናዊ የሆነችበት ሁኔታን ለማጥራት ፍላጎት ነበራቸው፡፡ አበባ አረጋዊ በስዊድሽ ቋንቋ እየተንተባተበች የሁሉንም ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሞክራለች፡፡ በወቅቱ የስዊድን ጋዜጠኞች ለአትሌቷ አቅርበዋቸው ከነበሩ ጥያቄዎች የማስታውሰው ከስዊድን ልዑል ጋር ተገናኝታ ምን እንደተባባለች ያነሱባትን ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ካገኘችበት ውድድር በፊት በዋዜማው ቀን ከስዊድኑ ልዑል ጋር በተገናኘችበት ወቅት መልካም እድል በመመኘት ከልባቸው እንዳበረታቷት የተናገረችው አበባ፤ ልዑሉ በማግስቱ በስታድዬም ተገኝተው ስታሸንፍ በመመልከት ደስታቸውን ሲገልፁ ማየቷ እንዳኮራት ገልፃ በስዊድን ዜግነት ለምታመጣው ውጤት ሁሉ የልዑሉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ምላሽ ሰጥታ ነበር፡፡ በወቅቱ የወርቅ ሜዳልያ ለስዊድን ተላልፎ መሰጠቱን በስፍራው ተገኝተን በቁጭት ለታዘብነው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላቀረብናቸው ጥያቄዎች በሳቅ በታጀበና ቁጥብ በሆነ አማርኛ አትሌት አበባ አረጋዊ ምላሽ ነበራት፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ስዊድን ዜግነቷን የተቀየረችበትን ሁኔታ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስታብራራም ‹‹ከለንደን ኦሎምፒክ በፊት ቢያንስ ለ3 ዓመታት ኑሮዬ በዚያው ስዊድን እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንደማንኛውም ሰው ዜግነት እንዲሰጠኝ ያመለከትኩት ብዙም ውጤት ይዤ አልነበረም፡፡ የለንደኑ ኦሎምፒክ 1 ወር ሲቀረው ከስዊድን መንግስት መልስ ተሰጠኝ፡፡ ይሁንና በወቅቱ በኦሎምፒክ መድረክ የትውልድ አገሬን ኢትዮጵያ በመወከል ለመወዳደር የሚያስፈልገውን ሚኒማ አሟልቼ ስለነበር ወደ ስዊድን ዜግነት የመቀየሩን ሁኔታ ከኦሎምፒክ በኋላ እናያለን አልኳቸው፡፡ እናም በኦሎምፒክ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል በመወዳደሬ በሁለቱ አገራት ፌደሬሽኖች መካከል ብዙ ጭቅጭቅ ነበር፡፡ ይህ የዝግጅት ትኩረቴን አዛብቶት ስለነበር በውድድሩ ወቅት ከተሰሩ ስህተቶች ጋር ተዳብሎ ውጤት አሳጣኝ›› በማለት የነበሩትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አስታውሳ ምላሽ ሰጥታናለች፡፡ አበባ አረጋዊ ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ በ2012 ሐምሌ ወር ስዊድናዊ ዜግነቷን ሙሉ ለሙሉ አግኝታ መወዳደር ጀመረች፡፡
በተለይ 2013 የውድድር ዘመን ላይ በ1500 ሜትር የዓለምን ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች ቆየች፡፡ ከሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና 6 ወራት ቀደም ብሎ በስዊድን ዜግነት ለመጀመርያ ጊዜ በተወዳደረችበት አውሮፓ የቤት ውስጥ አትሌቲከስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ መውሰድ የቻለችው አትሌቷ፤ ከዚሁ ድሏ በኋላ የዳይመንድ ሊግ ውድድርን በማሸነፍም ተሸላሚ ሆነች፡፡ ከ6 ወራት በፊት ደግሞ 24 አትሌቶችን ያቀፈው የስዊድን አትሌቲክስ ቡድን በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሞስኮ ላይ በነበረው ተሳትፎ አገሪቱ ከፍተኛውን የሜዳልያ ውጤት የጠበቀችው ከአበባ አረጋዊ ነበር። አትሌቷ ይህን የተሰጣትን ግምት በማሳካት የወርቅ ሜዳልያውን ወሰደች፡፡ ውድድሩበተካሄደበት የሞስኮው ሉዝንስኪ+ ስታድዬምን በመዞር ደስታውን ስትገልፅም ግዙፍ ባንዲራ በመከናነብ ለስዊድን ህዝብ ያላትን ፍቅር ገለፀች፡፡ በውጤቷም በመላው ስዊድን ከፍተኛ ደስታ ተፈጠረ፡፡ በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና ሰሞን በአትሌት አበባ አረጋዊ የትዳር ህይወት ላይ ተነስተው የነበሩ አወዛጋቢ አጀንዳዎች የተድበሰበሱትም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡
የአበባ የሃሰተኛ ጋብቻ፤ የምስጢራዊው ፍቺና የታክስ ማጭበርበር ክሶች?
በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና ሰሞን አትሌት አበባ አረጋዊ የስዊድን ዜግነቷን ለማግኘት በሃሰተኛ የጋብቻ ሰነድ መጠቀሟን በዘገባው አጋልጦ የነበረው ኤክስፕረሰን ፤ ከ6 ወራት በኋላ ደግሞ አጀንዳውን ወደሌላ አቅጣጫ በመውሰድ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውዝግቡን ሲያራግብ ቆይቷል፡፡ አበባ እና ሄኖክ የውሸት ጋብቻቸውን በፍቺ ማፍረሳቸውን ለ10 ወራት ምስጥር ሆኖ መቆየቱን የሚገልፀው ኤክስፕረሰን ፤አበባ እና ሄኖክ በውሸት ትዳር በመመስረት ለጥቅም መመሳጠራቸውን ለማጋለጥ ከሰሞኑ ባቀረበው ሃተታ ሁነኛ ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው የአትሌቷ ማናጀር የሆኑት ሆላንዳዊው ጆስ ሄርማንስ ከሁለት ዓመት በፊት ለዜግነት ቅየራ የሚያመቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሲባል እንጅ አበባ እና ሄኖክ ጋብቻ ስለመመስረታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለፅ ለሃመርቢ አትሌቲክሰ ክለብ ሃላፊዎች የማስጠንቀቂያ መልክት በኢሜል በላኩት ሰነድ ማረጋገጡን ጠቅሶ ነው። ጆስ ሄርማንስ በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ ሲጠየቁ በራሷ ውሳኔ ለፈፀመችው ተግባር ሃላፊነቷ የራሷ ነው፡፡ እኔ አባቷ አይደለሁም ብለዋል፡፡
አበባ አረጋዊ አሰልጣኟ ከሆነው ሄኖክ ወልደገብሬል ጋር የተሳሰረችበትን ጋብቻ እንዳፈረሰች ለማረጋገጥ የተቻለው ለስዊድን የታክስ ተቋም ባስገቡት የፍቺ ሰነድ እንደሆነ የገለፀው ኤክስፕረሰን ፤ የታክስ ተቋሙ ጉዳዩን በምስጥር በመያዙ፤ የምትሰራበት የሃመርቢ አትሌቲክስ ክለብ ፤ ግሎባል አትሌቲክስ በተባለ ድርጅት ማናጀሯ የሆኑት ሆላንዳዊው ጆስ ሄርማንስ ሆነ የስዊድን አትሌቲክስ ፌደሬሽን ስለፍቺው ምንም የሚያውቁት ነገር ሳይኖራቸው ቀርቷል በማለትም አብራርቷል፡፡ ዲኤን ስፖርት ለተባለው የስዊድን ጋዜጣ በክለቧ ሃመርቢ ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጋቫር ኤስትሮም የተባሉ ግለሰብ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት አስተዳደራቸው ሁለቱን የክለቡ አባላት ለዓመታት በከፍተኛ ድጋፍ ሲያግዝ መቆየቱን ገልፀው ትዳራቸውን ስለማፍረሳቸው እነሱ የገለፁልን ሆነ ምንም የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል። ህጋዊ ጋብቻ መስርተናል በሚል አትሌቷ ባገኘችው ስዊድናዊ ዜግነት የገቢ ቀረጥ መክፈል የነበረባት አትሌቷ ፍቺዋን ድብቅ ያደረገችው ታክስን ለማጭበርበር ነው በሚል ውንጀላው በውዝግቡ ያለውን ግልፅ አቋም ማንፀባረቁን የቀጠለው ኤክስፕረሰን በ2012 ብቻ እስከ 290ሺ ብር አለመቀረጧን ገልፆ ባለፈው ዓመት ብቻ አትሌቷ በዳይመንድ ሊግ አሸናፊነቷ፤ በዓለም ሻምፒዮና እና በተለያዩ የስፖንሰርሺፕ ውሎች 2.9 ሚሊዮን ብር ገደማ ገቢ ማስገባቷ ቢገመትም የስዊድን መንግስት በቀረጥ ሊያገኝ የሚገባውን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እየሄደች በመኖር ማጭበርበሯን ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡
በአበባ አረጋዊ ዙርያ የሚራገቡት የውዝግብ አጀንዳዎች ከሳምንቱ አጋማሽ በኋላ አትሌቷ አገር ለቅቃ እንድትወጣ በሚያስገድዱ ሁኔታዎች እየተወሳሰቡ ናቸው፡፡ የሃመርቢ አትሌቲክስ ክለብ ሃላፊዎች ሰሞኑን በጉዳዩ ዙርያ በሁለት ወገን ተከፍለው ሲነታረኩ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ከክለቡ መልቀቅ አለባት ብለው ሲሟገቱ ሌሎች ደግሞ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ የአትሌቷ ንፅህና እንዲረጋገጥ እና በስዊድን አትሌቲክስ በውጤታማነቷ ያላት የተምሳሌትነት ደረጃ እንዲቀጥል መፈለጋቸውን እየገለፁ ናቸው፡፡ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ አበባ አረጋዊ በምትወክለው የስዊድኑ የአትሌቲክስ ክለብ የሚገኙ ባለሙያዎች እና አንዳንድ አመራሮች አትሌቷ በተለያዩ መረጃዎች እና የጋዜጣ ዘገባዎች እንደሚገለፀው ህገወጥ የኮንትራት ቅጥር መፈፀሟ ከተረጋገጠ የክለቡን መተዳደርያ ደንብ በማጭበርበር መጣሷን ስለሚያመለክት እርምጃ እንዲወሰድ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ የአበባ አረጋዊ ሃሰተኛ ትዳር የክለቡን ዓላማ ለሚያጎድፍ ተግባር ምክንያት ይሆናል ያሉት እነኚህ የክለቡ አባላት አትሌቷን የሚቃወም ፊርማ በማሰባሰብ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ክለቡ ባደረገው ስብሰባ ስንብቷን ለማፀደቅ ጥረት አድርገዋል፡፡ አትሌቷ በቅጥር ኮንትራቷ ማጭበርበር ፈፅማ ከሆነ ለክለቡ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትን የሚያስከፋ ተግባር ነው በማለትም የስዊድን አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጉዳዩን በትኩረት እንዲመረምር ጥሪ አቅርበዋል፡፡የሃመርቢ አትሌቲክስ ክለብ ፕሬዝዳንት በአትሌት አበባአረጋዊ የሚሰሟቸው ውዝግቦች ዱብእዳ እንደሆኑባቸው የገለፁ ሲሆን አንድ የስዊድን አትሌቲክስ ፌደሬሽንን የወከሉ ግለሰብ ደግሞ‹‹ አትሌትአበባ አረጋዊ ወደስዊድን መጥታ ቪዛ ጠየቀች። የዓለም ምርጥ አትሌት መሆኗን ተረድተን ዜግነት በመስጠት እንድትወዳደር ደገፍናት›› በማለት የግል ህይወቷ ምንም ትኩረት እንዳማይሰጠው በሚገልፅ አስተያየት በፌደሬሽኑ ላይ እየደረሰያለውን ትችት ተከላክለዋል፡፡ ሮበርት ክሮከንበርግ የተባለ የቀድሞ የአትሌቲክስ ባለሙያ አትሌትአበባ አረጋዊ በሃሰተኛ የጋብቻሰነድ የስዊድን ዜግነት ማግኘቷን በተመለከተ በሰጠው አስተያየት ምናልባት የቢሮክራሲ ውጣውረድን ለማለፍ የፈፀመችው ተግባር ሊሆን እንደሚችል አመልክቶ ግን ሁለቱም ባለጉዳዮች ምስጥር በማብዛት ዝምታ መምረጣቸው እንዳልተረዳው ተናግሯል፡፡ ሚላን ክሮዬፕ የተባለ የቀድሞ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ በበኩሉ ‹‹ አበባ የዓለም ምርጥ አትሌት ናት፤ ለስዊድን ብቻ ለመሮጥ የፈለገችበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ በብዙ አገሮች ዜግነት ሊሰጣት ይችላል›› ብሏል፡፡
የአበባ ቃል
የ23 ዓመቷ አትሌት አበባ አረጋዊ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ‹‹ፒ4 ኤክስትራ ከተባለ የስዊድን ሬድዮ ጣቢያ ጋርባደረገችው ልዩ ቃለምልልስ በሰሞኑ የውዝግብ አጀንዳዎች ዙርያ የተብራሩ ምላሾችን ለመስጠት ሞክራለች፡፡
በመጀመርያ ደረጃ የስዊድን ሚዲያዎች በግል ህይወቷ ላይ ባተኮሩ ጉዳዮች አሉታዊ በሆነ መንገድ ዘመቻ በሚመስል ሁኔታ መንቀሳቀሳቸው አስደንጋጭ እና አሳዛኝ እንደሆነባት የገለፀችው አትሌቷ፤ጋዜጠኞች የተከበረ ውድ ጊዜያቸውን በመሰዋት በሰዎች የግል ህይወት አላይአተኩረው መስራታቸው እንዳስገረማት ተናግራለች፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች ለውድድር ከፍተኛ ዝግጅት በምታደርግበት እና ትኩረት በሚያስፈልጋት ሰዓት ስለጋብቻዋ ሃሰተኛነት፤ የትዳር ህይወቷ በፍቺ ስለመፍረሱ፤ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ጥያቄዎች መውጭያ መግቢያ አሳጥተዋት የሰነበተችው አትሌት አበባ አረጋዊ፤ በግል ህይወቷ ዙርያ እየተፈጠሩ ባሉ ሁኔታዎች ሃዘን ተሰምቷት በየቀኑ እንደምታለቅስ በቃለምልልሷ ላይ ስትናገር ‹‹ አንዳንዶች እኔን በገንዘብ እንደሚገዛ ሸቀጥ መቁጠራቸው አስከፍቶኛል›› ብላለች፡፡ ከሄኖክ ወልደገብሬል ጋር የነበራቸውን ጋብቻ በስምምነት በፍቺ ለመፈፀም የወሰኑት በሞስኮ ከተከናወነው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት እንደነበር በሬድዮው ቃለምልልስ ላይየተናገረችው አትሌት አበባ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት የመገናኛ ብዙሃናት በጉዳዮቹ ላይ ማብራርያ ሲጠይቋት በግል ህይወቷ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲተው በመማፀን ምላሽ ስትሰጣቸው፤ ትዳሯ በፍቺ መፍረሱን በግልፅ አለመናገሯ እንደውሸታም ማስቆጠር የለበትም በማለት አስረድታለች፡፡ ከሄኖክ ጋር የነበራቸው የትዳር ግንኙነት በፍቺ ሊፈርስ መወሰናቸውን እንኳን ለመገናኛ ብዙሃናት ይቅርና ለቤተሰቦቻቸው እና ለቅርብ ወዳጆቻቸውየደበቁት ምስጥ እንደነበር ለፒ 4 ኤክስትራ ሬድዮ ጣቢያ ያሳወቀችው አትሌት አበባ አረጋዊ፤ለፍቺ የበቁት ተጣልተው እንዳልሆነ ስትገልፅ ብዙውን ጊዜ በተለያየ አገር ተራርቀው ለመኖር በመገደዳቸው ለፍቺው ምክንያት እንደሚሆን አስረድታ ሄኖክ በስዊድን እየኖረ እሷ ደግሞ ልምምዷን በመደበኛነት በምትሰራበት ኢትዮጵያ ለመቀመጥ መወሰኗ ልዩነታችንን ፈጥሮታል ብላለች፡፡አንዳንዶቹ ዘገባዎች አትሌት አበባ አረጋዊ ከሄኖክ ወልደገብሬል ጋር የነበራትን ጋብቻ በምስጥር ባደረገችው የፍቺ ስምምነት ከፈፀመች በኋላ ከታዋቂው ኢትዮጵያዊ የማራቶን ሯጭ የማነ ፀጋዬ ጋር ሁለተኛ ትዳር መመስረቷን ይገልፃሉ፡፡
ከፒ4 ኤክስትራ ጋር ባደረገችው የሬድዮ ቃለምምልስ በመደበኛነት ተቀማጭነቷን በኢትዮጵያ ለማድረግ የወሰነችው ከሰሞኑ እንደሚወራው በስዊድን መክፈል የሚገባትን የገቢ ግብር ለማጭበርበር አለመሆኑን የገለፀችው አበባ አረጋዊ፤ ልምምዷን በአዲስ አበባ ለማድረግ የወሰነችው ለዝግጅቷ ምቹ አየር ንብረት እና መልክዓ ምድር በመኖሩ ብቻ ነው ብላለች፡፡ አትሌት አበባ አረጋዊ ዜግነቷን ወደስዊድናዊነት በመቀየሯ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ያልተገደበ ተሳትፎ በማግኘት፤ በምትወክለው የሃመርቢ አትሌቲክስ ክለብ በደሞዝ እና የስልጠና ድጋፎች የምታገኘው ከ1ሚሊዬን 750 ሺህ ብር ገቢ በመጠቀም ፕሮፌሽናል አትሌት ሆና ቆይታለች፡፡
አበባ አረጋዊ ስዊድናዊ ከሆነች በኋላ ብዙ የተለየ ጥቅም አለማግኘቷን በሬድዮው ቃለምልልስ ላይ ስታስረዳ፤‹‹ለገንዘብ ብዬ ዜግነቴን አልቀየርኩም። ኢትዮጵያ ውስጥ ከእኔ የተሻለ ገቢ ያላቸው ጓደኞቼ የሆኑ አትሌቶች አውቃለሁ፡፡ ስዊድናዊ ለመሆን ትልቅ ዋጋ ከፍያለሁ፡፡ የምፀፀትበት ግን አይደለም፡፡ ዛሬም ስዊድናዊ ነኝ፡፡ በርግጥ የትውልድ አገሬ ኢትዮጰያ ናት። በአትሌትክስ የምሮጠው ግን ስዊድንን በመወከል ነው፡፡ የስዊድን ህዝብ በሚሰጠኝ አድናቆት እና ክብር ሁሌም ደስተኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ ወደፊትም ስዊድንን ወክዬ ታላላቅ ታሪኮችን መስራትእፈልጋለሁ ››በማለት ተናግራለች፡፡
ከአበባም በኋላ የቀጠለው ስደት...
በነገራችን ላይ ከሳምንት በፊት ከተጠናቀቀው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተገናኘ አነጋጋሪ ከሆነው የአበባ አረጋዊ አወዛገቢ አጀንዳ ጎን ለጎን በተለይ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚያሳስብ ሁኔታ መስተዋሉ አልቀረም፡፡ ገንዘቤ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያ ባጠለቀችበት የ3ሺ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ ከተሳተፉ አትሌቶች መካከል አራቱ ኢትዮጵያዊነትን በመተው በተለያየ አገራት ዜግነታቸውን ቀይረው የተወዳደሩ ነበሩ፡፡ ለባህሬን የተወዳደሩት ማርያም ዩሱፍ ጀማልን ጨምሮ ሁለት ናቸው፡፡ ለሆላንድና ለኳታር የሮጡትም በትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ከዚሁ ሁኔታ መገንዘብ የሚቻለው ከማርያም ዩሱፍ ጀማል ፤ ከኤልቫን አብይ ለገሰና ከአበባ አረጋዊ በኋላ የኢትዮጵያ አትሌቶች ስደት ተባብሶ መቀጠሉን ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታትወዲህ በተለይ በመካከለኛው ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች ፍልሰት መጨመሩም ይስተዋላል፡፡ አለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍ ዜግነታቸውን በመቀየር ለሌላ አገር ለመወዳደር ህጋዊ እውቅና ያገኙ አትሌቶች ስም ዝርዝር በየዓመቱ የሚያሳውቅ ሲሆን በእነዚህ ሰነዶች ባለፉት 15 ዓመታት ወደ የተለያዩ 10 አገራት ከ25 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አትሌቶች ዜግነታቸውን በመቀየር በሌላ አገር ዜግነት በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉበትን ፈቃድ ማግኘታቸው ተመልክቷል፡፡ በአይኤኤኤኤፍ ይፋዊ መረጃ መሰረት ከ1998 እስከ 2011 እኤአ ድረስ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን በመቀየር ለሌሎች አገራት የሚወዳደሩ አትሌቶች ብዛት 12 ነበር፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ግን በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን የቀየሩ አትሌቶች ብዛት 4 ተመዝግቧል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን 2013 እኤአ ላይ ደግሞ 3 አትሌቶች ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን በመቀየር ለአዳዲስ አገራቸው መወዳደር ጀምረዋል፡፡
አትሌቶቹ ካለፈው የውድድር ዘመን ወዲህ ዜግነቱን ወደ ታላቋ ብሪታኒያ በመቀየር መወዳደር የጀመረው የ21 ዓመቱ ተስፋዬ ሃምዩ፤ ዜግነታቸውን ከኢትዮጵያዊ ወደ ባህሬን በመቀየር ከወር በፊት በዓለም አቀፍ ውድድሮች መሳተፍ የጀመሩት የ21 ዓመቱ አወቀ አያሌው እና የ26 ዓመቱ ዘላለም ባጫ ረጋሳ ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment