26 FEBRUARY 2014 ተጻፈ በ በጋዜጣው ሪፖርተር
በአሁኑ ጊዜ በየቦታው የተጠራቀሙ ብሶቶች ይሰማሉ፡፡ ከመንግሥታዊ ተቋማት የተዝረከረከ አገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ዋናው የአገሪቱ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ድረስ ብሶት በርክቷል፡፡
የኑሮ ውድነቱ አዕምሮውን የሚያናውጠው ሕዝብ፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና የሰብዓዊ መብት መጓደል እያንገሸገሸው ነው፡፡ ሕዝቡ መንግሥት ምን እስኪሆን ድረስ ነው የሚጠብቀው እያለ በየቦታው ያጉረመርማል፡፡ ይኼ አሉባልታ ሳይሆን እውነት ነው፡፡ በተጨባጭ የሚታይ፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የብሶት አቤቱታ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ለተሰገሰጉ ራስ ወዳዶችና ስግብግቦች ላይዋጥላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን እውነቱ ይኼ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲገጥመው፣ ‹‹ይኼ የኪራይ ሰብሳቢዎችና ፀረ ሕዝቦች ሟርት ነው›› እየተባለ ሲድበሰበስ ይሰማል፡፡ ችግሩ አፍጥጦ ወጥቶ መላወሻ ሲታጣ ግን፣ ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ተግተን እንሠራለን›› የሚል ማስተዛዘኛ አይሉት ማደናገሪያ ይቀርባል፡፡ አሁን በተጨባጭ እየታየ ያለው መልካም አስተዳደር የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ መቀለጃ መሆኑ ብቻ ነው፡፡
ሕዝቡ የፍትሕ ያለህ እያለ በየደረሰበት ሲያነባ ላይ ላዩን ችግሩ መኖሩን እያመኑ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ችግሩን ማባባስ የተመረጠ ይመስላል፡፡ በፍትሕ እጦት የሚንገላታው ዜጋ መንግሥት ከዛሬ ነገ መፍትሔ ያፈላልግልኛል ብሎ ሲጠብቅ ውጤቱ በዜሮ ተባዝቶ እየቀረበለት ነው፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የተሰገሰጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝቡን ከማስለቀስ አልፈው ተስፋ እያስቆረጡት ነው፡፡
በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት አቤቱታ ሲቀርብ ፈጽሞ አይፈጸምም በሚባልበት አገር ውስጥ በርካታ እሮሮዎች እየተደመጡ ናቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ ጀምሮ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ ዜጎች በጠላትነት ይፈረጃሉ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ለማስከበር ላይ ታች ሲሉ በሕገወጥ መንገድ ይሰቃያሉ፡፡ መብትን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ከነውር በላይ እየታየ ዜጎችን ወደ ሕገወጥነት የሚመራ አሻጥር ይከናወናል፡፡ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የተሰገሰጉ እነዚህ ኃይሎች ዜጋ በአገሩ እንዳይኮራና ስደት ውስጥ እንዲዘፈቅ እያደረጉ ናቸው፡፡
አገራቸውን በቅንነት ለማገልገል የሚፈልጉ ወገኖች በእንዲህ ዓይነቶቹ ራስ ወዳዶችና ስግብግቦች እየተሸፈኑ ዜጎች ለእንግልት ሲዳረጉ ጠያቂ ያለ አይመስልም፡፡ ለአገራቸው አኩሪ ተግባር መፈጸም የሚችሉ የተማሩና ልምድ ያካበቱ ወገኖች ወደ ዳር እየተገፉ፣ ለጥቅማቸው ብቻ ያደሩ ወገኖች መንበሩን ሲቆናጠጡ አገር እየተጎዳች መሆኗ እየተረሳ ነው፡፡ ሕዝቡ በውስጡ ብሶት ተሸክሞ ሲዞር ችግሩን ከማድበስበስ ባለፈ በግልጽ ለመነጋገርና ለመፍታት የሚሞክር አለመታየቱ ከማስገረምም በላይ ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱ የሕዝቡን ወገብ አጉብጦት መከራ እያሳየው ተገኘ የሚባለው የኢኮኖሚ ዕድገት አኃዝ ብቻ እንዲነገር የሚፈልጉ ወገኖች አሉ፡፡ ዕድገቱ በሕዝቡ ዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ከመታገል ይልቅ የማይጨበጥ ሐተታ ላይ የሚያተኩሩ መብዛታቸው በእጅጉ ያስገርማል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እያለ መንግሥት ሕዝቡ ላይ እንዴት ኢንቨስት ማድረግ ይኖርበታል ከሚለው ወገናዊ መጨነቅ ይልቅ፣ ‹‹ኑሮ ውድነቱ የዕድገቱ ውጤት ነው›› በማለት ግድየለሽ መሆንም በስፋት ይታያል፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው ደግሞ ከራሳቸው ጥቅም ባሻገር መመልከት በተሳናቸው ኃይሎች ነው፡፡
ምንም እንኳ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ቢሆንም፣ በዚህ ዘመን ውኃ እንዴት ለ15 ቀናት ይጠፋል? የኤሌክትሪክ ኃይል በዋና ከተማዋና በሌሎች አካባቢዎች በቀን ሦስትና አራት ጊዜ እንዴት ይቆራረጣል? የሞባይል ኔትወርክና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዴት ብርቅ ይሆናሉ? በተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች የሚሰጠው አገልግሎት ቀርፋፋነትና የጥራት መጓደል እስከመቼ ይቀጥላል? ሕዝቡ በትራንስፖርት እጦት በዝናብና በፀሐይ ሲደበደብ እንዴት ዝም ይባላል? በርካታ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡
የፖለቲካውን አካባቢ ስናየው ደግሞ በጥላቻና በጭፍንነት የተሞላ ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚባለው መታወቂያ ፈጽሞ የተረሳበት ይመስላል፡፡ ምንም እንኳ የፖለቲካ ዋነኛ ግቡ ሥልጣን ነው ቢባልም፣ ፖለቲካው ሠፈር የሚታየው ግን ራስ ወዳድነትና ተራ ብልጣ ብልጥነት ነው፡፡ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሰሶዎች የሚባሉት መሠረታዊ ጉዳዮች ተረስተዋል፡፡ ነፃነትን ማረጋገጥ፣ በምርጫ አማካይነት የሕዝብ ትክክለኛ ተወካዮችን መሰየምና ፍትሕን ማረጋገጥ የተቻለበት አይመስልም፡፡ ይህ ችግር ገዥውን ፓርቲና ተቃዋሚዎቹን የሚመለከት ነው፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ የአገሪቱን የመንግሥት ሥልጣን ሙሉ በሙሉ እንደመቆጣጠሩ መጠን ከችግሩ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በአገሪቱ ተቃዋሚዎች ለምን አልተጠናከሩም ሲባል፣ ችግሩ የእነሱ ብቻ ሳይሆን የገዥው ፓርቲ ጭምር መሆኑን ማሰብ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩ ጠበበ ሲባል እነዚህ ወገኖች የመጫወቻ ሜዳ እያጡ መሆኑን ማመን የግድ ይላል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ የተወጣጠረ ሁኔታ ውስጥ ስለዲሞክራሲም ሆነ ሰብዓዊ መብት ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ፖለቲካው ነፃነትና ዲሞክራሲን ማንፀባረቅ ሲገባው ደም ደም ይሸታል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን እየታየ ካለው የልማት ትሩፋት በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብት በምን ያህል መንገድ ሕዝቡ ዘንድ እየደረሰ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የሕዝብ ውክልና አለኝ የሚል መንግሥት በግልጽ ይህንን ለሕዝቡ ሊያሳየው ግድ ይለዋል፡፡ የተለያዩ አውራ ጎዳናዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር መስመሮች፣ የቴሌኮም ዝርጋታዎች፣ ወዘተ እየተከናወኑ ነው ሲባል ሥርጭታቸው ፍትሐዊ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ስለመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሲነገር የሚሰማ ሕዝብ ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክና መሰል አገልግሎቶች በየቀኑ ሲቆራረጡበት ጥያቄ ያነሳል፡፡ ይህ ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡
በአሁኑ ጊዜ በርካታ ምላሽ ያላገኙ የሕዝብ ብሶቶች ተከማችተዋል፡፡ ሰላማዊና የተረጋጋ ድባብ ቢኖር እንኳን ደስተኝነት የማይሰማው ሕዝብ በሰላም ወጥቶ ስለመግባቱ እርግጠኛ አይሆንም፡፡ የመንግሥታዊ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ‹‹አበረታች›› መሆኑ በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የሚነገረው ሕዝብ በተጨባጭ ካላየው የምሬቱ መጠን ይጨምራል፡፡ ፍትሕ አለ እየተባለ በፍትሕ እጦት የሚንገላታ ሕዝብ ነጋ ጠባ እያለቀሰ እንባውን የሚያብስለት ከሌለ ብሶቱ ይከማቻል፡፡ በገዛ አገሩ ሳይሸማቀቅ የፈለገውን አመለካከት ማራመድ የተሳነው ወገን ብሶቱ ጣራ ይነካል፡፡ በሕግ የተረጋገጠለት መብት በአደባባይ የሚጣስበት ወገን ትዕግሥቱ ይሟጠጣል፡፡ የነፃነት አየርን ማጣጣም እየፈለገ መታፈን የሚሰማው ዜጋ ተስፋ ይቆርጣል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ብሶትን የሚያባብሱ ኃይሎች በርክተዋል፡፡ በፓርቲና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተደላደሉና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድዱ ኃይሎች ሕዝቡን እያስለቀሱ ናቸው፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርት የተዛባ መረጃ እያቀረቡ ተጨባጩን ሁኔታ የሚያድበሰብሱ በዝተዋል፡፡ ከራሳቸው ቡድን ፍላጎት ውጪ ምንም ዓይነት ነገር ማየት የማይፈልጉ ወገኖች የአገሪቱን ገጽታ እያበላሹ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ሕዝቡን እያስለቀሱ ናቸው፡፡ ሃይ ባይ በማጣታቸውም በአገሪቱ ውስጥ ብሶት ተከማችቷል፡፡ ይህ ብሶት ከዕለት ወደ ዕለት እየተወጠረ ነው፡፡ እዚህ ላይ አገራቸውን በቅንነት እያገለገሉ ላሉ ዜጐች አክብሮት እየተቸራቸው፣ እነዚህ ወገኖች ስንዴውን ከእንክርዳዱ እንዲለዩ ጥሪ ይቀርብላቸዋል፡፡ ብሶት እየተከማቸ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል!
No comments:
Post a Comment