This Blog Is Intended To Raise Platform For Dialoguing And Discussing The Practical Issues Related With Women And Children in Ethiopia.
Wednesday, 26 December 2018
Wednesday, 19 December 2018
አሜሪካዊው ቢሊየነር ስቲቭ ጆብስ፣ በህይወቱ መጨረሻ ሰዓት ላይ ያስተላለፈው መልዕክት።
[ስቲቭ ጆብስ በ56 አመቱ ያረፈ አሜሪካዊ ቢሊየነር ሲሆን፣ ህይወቱ ያለፈው በካንሰር በሽታ ነው።]
"በንግዱ አለም ውስጥ የመጨረሻ ከፍታ ጫፍ የሚባለው ቦታ ደርሻለሁ፣ ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ሀብት ደስታን ማግኘት አልቻልኩም። በልፋቴ ካከማቸሁት ሃብት ያገኘሁት ደስታ እዚህ ግባ የማይባል ነው። አሁን፣ በህይወቴ የመጨረሻው ሰዓት አካባቢ፣ አልጋ ላይ ሆኜ ያሳለፍኩትን ነገር ሁሉ ወደኋላ ሳስበው፣ እኮራበት የነበረው ሀብቴና ዝናዬ ከንቱ እና ትርጉም አልባ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ አንድን ሰው መኪና እንዲነዳልህ ወይም ሰርቶ ገንዘብ እንዲያስገባልህ ልትቀጥረው ትችላለህ፣ እየተሰቃየህበት ያለውን ህመም እንዲሸከምልህ ግን ልትቀጥረው አትችልም፡፡
ምድራዊ የሆኑ ቁሳቁሶች ሁሉ ሊጠፉ፣ ዳግም ሊገኙም ይችላሉ፥ አንድ ጊዜ ካመለጠ ደግመህ ልታገኘው የማትችለው አንድ ነገር ግን አለ… እርሱም ህይወትህ ነው! አንድ ሰው የቀዶ ጥገና ወደሚደረግለት ክፍል ሲገባ አንብቦ ያልጨረሰው አንድ መጽሃፍ ትዝ ቢለው የመጽሐፉ ርዕስ "ጤናማ ህይወት የመኖር ሚስጥር" የሚል ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ በየትኛውም የህይወት ከፍታ ላይ ብንሆን የህይወታችን መጋረጃ የሚዘጋበትን ቅጽበት ፊት ለፊት የምንጋፈጥበት አንድ ቀን መምጣቱ አይቀርም፡፡
ለቤተሰብህ፣ ለትዳር አጋርህ እና ለጓደኞችህ የፍቅርን ውርስ አስቀምጥላቸው፡፡ ራስህን ተንከባከብ፣ ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት ይኑርህ። እያደግን ስንሄድና የህይወት ትርጉሙ ሲገባን፣ ውድ ሰዓትም አሰርን ርካሽ ሰዓት፣ ሁለቱም የሚነግሩን ጊዜ እኩል መሆኑ ይገባናል፡፡ በኪሳችን ውድ ቦርሳም ያዝን ርካሽ ቦርሳ፣ በውስጡ የሚኖረውን የገንዘብ መጠን አይቀይረውም፡፡
የአንድ ሚሊየን ብር መኪናም ነዳን የሶስት መቶ ሺህ ብር መኪና፣ የመንገዱ ርዝመት አይቀየርም፣ አቅጣጫውም ያው አንድ ነው፥ የምንደርሰውም ያው እዚያው ቦታ ነው፡፡ ውድ መጠጥም ጠጣን ርካሽ መጠጥ፣ ስካሩና አድሮ የሚያመጣው ራስ ምታት ለውጥ የለውም፡፡ ሰፊ ግቢ ውስጥ ኖርንም ጠባብ ቤት፣ ብቸኝነቱ ያው እኩል ነው፡፡ የውስጥ ደስታ በቁሳቁስ እንደማይገኝ ያን ጊዜ ይገባሃል። አውሮፕላን ላይ የክብር ቦታም ተቀመጥክ ወይም ተራ ቦታ፣ አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ እኩል ቁልቁል ትወርዳለህ።
እውነተኛው ደስታ የሚገኘው ከቤተሰብህ፣ ከጓደኞችህ፣ ከዘመዶችህ ጋር በሚኖርህ ውብ ጊዜዓት ብቻ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር በምታሳልፈው ጊዜ፣ በምትጫወተው ጨዋታ፣ በምትዘምረው መዝሙር፣ በምትስቀው ሳቅ እውነተኛ ደስታን ታገኛለህ፡፡ ሊካዱ የማይችሉ የህይወት እውነታዎች ግን አሉ ልጆችህ ሀብታም እንዲሆኑ አታስተምራቸው፥ ይልቅ እንዴት ደስተኛ መሆን እንደሚችሉ አስተምራቸው፡፡ ሲያድጉ የነገሮች ዋጋ ሳይሆን ጥቅማቸው ይገባቸዋል፡፡ ምግብህን እንደ መድሃኒት ውሰድ ካልሆነ መድሃኒት እንደምግብ ትወስዳልህ፡፡ የሚወድህ ሰው በቀላሉ አይለይህም፣ ከአንተ ለመለየት 99 ምክንያት ቢኖረው እንኳ መለየት በማይችልባት አንዲት ነገር ላይ ፀንቶ ይቆማል፡፡
"ሰው ሆኖ በመፈጠር"ና "ሰው በመሆን" መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፥ ይህ የሚገባቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ስትወለድ ውድ ነበርክ፣ ስትሞትም ውድ ትሆናለህ፣ በመካከል ያለውን ማስተካከል ያንተ ፋንታ ነው፡፡ በፍጥነት ለመሄድ ከፈለክ ብቻህን ሂድ፣ ሩቅ ለመድረስ ከፈለግህ ግን ከሌሎች ጋር አብረህ ተጓዝ፡፡
በዓለም ላይ ያሉ ስድስቱ ፈዋሽ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው…
★የፀሃይ ብርሃን
★እረፍት
★ስፖርት
★ጥሩ ምግብ
★በራስ መተማመን እና
★ጓደኛ
እነዚህን አጥብቀህ ያዝ፥ ደስተኛ ህይወትን አጣጥም!
Saturday, 15 December 2018
Friday, 14 December 2018
Wednesday, 12 December 2018
Tuesday, 27 November 2018
Thursday, 1 November 2018
ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክና መልክ እንደቂጣ ጠፍጥፎ የሚጋግራት የግል ርስት ሳትሆን፣ ዘመናትን ያስቆጠረች፣ ታላቅ ሕዝብ የመሠረታት፣ ታላቅ ሀገር መሆናን ነው።
ዶር አብይ በጀርመን ያደረጉት ንግግር (ሙሉ ንግግር)
...............................................
አይነን ሾነን ጉተን ታግ!
ኤይቶፒሼ ዲያስፖራስ ኢን ዶችላንድ ኡንት ኤይሮፓ!
ክቡራትና ክቡራን!
ከመላው አውሮፓ የተሰበሳባችሁ የሀገሬ ልጆች ሆይ፣ የማይንን ወንዝ ተገን አድርጋ በተቆረቆረችው፣ የገንዘብና የኢንዱስትሪ ማዕከል በሆነችው ፍራንክፈርት ተናኝተን በአይነ ሥጋ መተያየታችንንን እንደ ታላቅ እድል እቆጥረዋለሁ።
ከሀገር የወጣችሁበት ዘመንና ምክንያት እንደ ቁጥራችሁ ብዙ፣ እንደየመጣችሁበት ሀገር ለየቅል መሆኑ ግልፅ ነው። ለትምህርትም ይሁን ለሥራ፣ በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ የተሰደዳችሁ ወገኖቼ… ከምንወዳት ሀገራችን እና ሁሌም ከምትናፍቁት ህዝባችን እጅግ የከበረ ሰላምታ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደዛሬው ከኋለኛው ተርታ ተመድባ በችግሯ ከመታወቋ በፊት ከአውሮፓ አገራት ጋር ታሪካዊ የሆነ ግንኙነት ነበራት። ከእንግሊዝ ጋር በትምህርት፣ ከፈረንሳይ ጋር በባቡር ሀዲድ፣ ከፖርቱጋል- በጦር ትብብር፣ ከቱርክና ከግሪክ በንግድ፣ ከስዊድን በጤናና በአየር ሀይል፣ ከሩሲያና ከሌሎች የምስራቅ አውሮጳ ሀገራት ጋር በተለያዩ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የነበረን ታሪካዊ ተዛምዶ እስከዛሬም የቀጠለ የወዳጅነታችን መሠረት ነው። ከጀርመንም ጋር ቢሆን ጠንካራ ትስስር ነበረን።
አምስተኛዋ ግዙፍ የጀርመን ከተማ ፍራንክፈርት፣ የታዋቂው ደራሲ ዮሐን ዎልፍ ጋንግ ቮን ጎይተ ከተማ ናት። በዚህ ታላቅ የጥበብ ሰው ስም የተቋቋመ ስመ ጥር ኢንስቲቲዩት በአገራችን ከመኖሩ በተጨማሪ የጀርመን የባህል ማዕከልና ትምህርት ቤት መቋቋሙ ጠንካራ ትስስርና ወዳጅነት ስለመኖሩ አንዱ ማሳያ ነው። እንደ አገር ከጀርመን ጋር፣ እንደ አጠቃላይ ደግሞ ከአውሮፓ ጋር ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ተመሳስሎም አለን።
እንደምታውቁት፣ ለእኛ የቅርብ ጊዜ እውነታ በሆነው ጦርነትና ግጭት ውስጥ ያላለፈ የአውሮፓ ሀገር የለም። ለምሳሌ ያህል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእጅጉ ከተጎዱት የአውሮፓ ከተሞች መካከል አንዷ ፍራንክፈርት ናት። ብዙ ሕዝብ አልቆባታል፤ መኖሪያ ቤቶቿ የሙታን መንደሮች መስለው ነበር፤ አያሌ የንግድና የገበያ ሥፍራዎቿ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ታዋቂ የነበረውና በወቅቱ ከጀርመን በታላቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ዋናው የንግድ መናኸሪያዋ ወድሟል። ሆኖም ግን፣ የማይበገሩትና ለችግር የማይረቱት ፍራንክፈርቶች ከተማቸውን እንደገና ገንብተው የአውሮፓ የፋይናንስ ማዕከል ለማድረግ ዐርባ ዓመት እንኳ አልፈጀባቸውም። ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው።
ሃያ ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የዓለማችን ታላላቅ ጦርነቶች የማስተናገድ ክፉ ዕጣ በላያቸው ላይ የተጫነባቸው አውሮፓውያን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦቻቸውን አጥተዋል፤ ለዘመናት የተገነባ ታሪካቸው አመድ ሆኗል፤ የልዩነት ግንብ በመካከላቸው ተገንብቶ ቆይቷል። በዘመኑ፣ አውሮፓውያን እንኳንስ ለሌሎች ሕዝቦች መጠጊያ ሊሆኑ ይቅርና በገዛ ሀገራቸው ተስፋ ቆርጠው ስደትን የመረጡ ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም። ያ ሁሉ አበሳ የመጣው በጥቂቶች፣ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ በግል ጥቅማቸው በታወሩ መሪዎች እና የእኛ ዘር ከሁሉም ይበልጣል ባይ ደመ-ነፍሳውያን ቅዠት መሆኑ በጸጸት የሚታወስ ክፉ የጦርነቱ ጠባሳ ነው። የዚህ አሰቃቂ ጥፋት የፍጻሜ ትርፉ ድህነት፣ ጉስቁልና፣ ስደት፣ ወረርሽኝና እልቂት ብቻ ነበረ።
ሆኖም ግን፣ ጠንካሮቹ አውሮፓውያን ከአንደኛውና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እጅግ በፈጠነ ጊዜ አገግመው፣ ዛሬ ላይ እናንተን ጨምሮ ከመላው አለም ሚሊዮኖችን እስከማስጠለል ደርሰዋል። እርስበርስ መሸናነፍን ትተው አለምን ማሸነፍ ችለዋል። ይሄን ያሳኩት በአጋጣሚ አይደለም። ወገባቸውን አሥረው፣ ተስፋ መቁረጥን አባርረው፣ የደረሰባቸውን መከራ ሁሉ ለነገ ሲሉ ታግሠው፣ ለአገራቸው አንድ ሆነው በትጋት ስለሠሩ ብቻ ነው።
እዚህ ቦታ በፊታችሁ ስቆም ሀገራችን በኢኮኖሚ በልጽጋ፣ ሰላማችን ሙሉ በሙሉ ተሟልቶ፤ ግጭት ጠፍቶ፣ ዴሞክራሲ ጎልብቶ፣ ሰብአዊ መብት በላቀ ሁኔታ ተከብሮ ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር። ግን አይደለም። አሁን በእጃችን ያሉን ሁለት ነገሮች ናቸው። ነጻነትና ተስፋ። እነዚህን ሁለቱን ይዘን በትብብርና በአንድነት ከሰራን የምንሻት ኢትዮጵያን ከመፍጠር የሚያግደን የለም።
ከጦርነቱ ማግስት አውሮፓውያን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከመገፈታተር ይልቅ ትብብርን የመረጡት ጥቅሙ ስለገባቸው ነው። ሕዝቡ ጦርነትን አምርሮ ቢጠላ ገፈት ቀማሽ ሆኖ ስላየው ነው። ዘረኝነትንና የበላይነት አባዜን አምርሮ የተዋጋው ካደረሰበት ውድመትና ጥፋት ስለተረዳው ነው።
ይህ፣ እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠን ትምህርት ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ብዙዎቹ የለውጥ ጅምሮች በመሳሪያና በአመጽ ተጀምረው፣ በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በማሳደድና በመሰደድ የተደመደሙ መሆናቸው ለሁላችን ግልፅ ነው። አዲስ የሰላምና የእርቅ ምዕራፍ ከመሆን ይልቅ የሌላ ዙር ውጊያ እና አመጽ መጀመሪያ የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ እንደነበር የትናንት ታሪካችን ምስክር ነው። አሁን፣ ያላየነውን የምናይበት፣ ያልሞከርነውን የምንሞክርበት ዘመን ነው። ምቾታችንን ተወት አድርገን፣ መከራዎቻችንን ታግሰን፣ ጥርሳችንን ነክሰን የምንሰራበት፤ ለአገራችን በተባበረ ክንድ የምንተጋበት ወቅት ነው። በየጎራው ያሉ ሀይሎች አሸናፊ የሚሆኑበትን የፖለቲካ ባህል ከአውሮፓ ተምረን እንደ አገር አሸናፊ የምንሆንበትን መንገድ መያዝ አለብን፤ ይገባናልም።
የተከበራችሁ ወገኖቼ!
ከሩቁ ሆናችሁ ስለ ሀገራችሁ ስትሰሙ በአንድ በኩል ትደሰታላችሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትከፋላችሁ። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ታደርጋላችሁ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተስፋ ትቆርጣላችሁ። ግን ርግጠኛ መሆን ያለባችሁ አንድ ነገር፣ ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክና መልክ እንደቂጣ ጠፍጥፎ የሚጋግራት የግል ርስት ሳትሆን፣ ዘመናትን ያስቆጠረች፣ ታላቅ ሕዝብ የመሠረታት፣ ታላቅ ሀገር መሆናን ነው። ‹እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው› እንደተባለው፣ አንቀላፍታ ይሆናል እንጂ አልሞተችም፤ ደክማ ይሆናል እንጂ አልተሸነፈችም፤ ቀጥና ይሆናል እንጂ አልተበጠሰችም። ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ሳንከፋፈልና ጊዜያችንን የማይጠቅም ነገር ላይ ሳናባክን ወገባችን አጥብቀን ከሠራን አገራችንን ታላቅ ማድረግ የሚከብድ አይሆንም።
መቼም፣ ኢትጵያዊ ሆኖ የኢትዮጵያን ክፉ ማየት የሚመኝ ጤነኛ ሰው አለ ብዬ አላምንም። እዚህ ከተሰበሰባችሁ ያገሬ ልጆች መሀል የሀገሩ ነገር ሆዱን የማይበላው ውስጡን የማያንሰፈስፈው ሰው አይኖርም። ኢትዮጵያዊነትን ከቃላት በዘለለ እና ከስሜት በተሻገረ መልኩ በስራ የምናሳይበት ዘመን ላይ ስለሆንን ለጊዜው የማይጠቅመውን ትተን፣ የሚያስፈልገንን አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል።
ወደድንም ጠላንም እንደ ሀገር ልንሸሻቸው በማንችላቸው ሦስት መሰረታዊ የጊዜ ማዕዘኖች መካከል ላይ እንገኛለን። ከትናንት ስህተቶቻችን የምናስተካክለው፣ ዛሬ ተግተን ልንሠራው የሚገባን፣ ለነገ ደግሞ የምንገነባው ሁነኛ መሠረት አለ። እነዚህን ሦስቱን አጣጥመን ለመሄድ በምናደርገው ትግል አንዳንድ ጊዜ ወደ አንዱ መጎተታችን አይቀሬ ነው። ከትናንት አያሌ መልካም ነገሮችን እንደወረስን ሁሉ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮችንም ወርሰናል። ፍትሕን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን፣ የዳበረ የሥራ ባሕልን፣ በሕግና በሥርዓት መኖርን፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጥን፣ ረሐብና ድህነትን ማስወገድን በተመለከተ ገና ብዙ የሚቀሩን ሥራዎች አሉ።
እነዚህን የምናሳካው በማንመልሰውና በማንቀይረው ትናንት ላይ እየተጨቃጨቅን፣ ወርቅ እድላችንንና ጊዜያችንን በማባከን ወይም ጥቂቶች በሚያዘጋጁልን አጀንዳዎች በመተራመስ ሳይሆን ልቦናችን የሚያውቀውን በጎ ሀሳብ ወደ ተግባር በመቀየር ነው። ጊዜውን መጣያ እንዳጣ ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥደን ውድ እውቀታችንና ጉልበታችንን በማፍሰስ ሳይሆን ትርጉም ያለው ስራ ላይ በመሰማራት ጭምር ነው። ጨለማውን ለመግፈፍ ሻማ ማብራት እንጂ የጨለማውን ክብደትና ጽልመት መስበክ መፍትሄ አይሆንም። እኔ ለሀገሬ ምን ሠራሁ በማለት እንጂ እነ እገሌ አገሬን ጉድ ሰሯት እያልን መዓት ብናወራ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም። ይሄንን ማድረግ ካልቻልን ለሀገራችን ያለን ጥልቅ ፍቅር በግብር የሚገለጸው እምኑ ላይ ነው?
ክቡራንና ክቡራት
ፍትሕና ዴሞክራሲ ስለተፈለጉ ብቻ አይገኙም። በሰላማዊ ሰልፍና በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጠዋት ተዘርተው ማታ የሚያፈሩ ዛፎችም አይደሉም። እነርሱን የሚያበቅሉ፣ አብቅለውም ማሳደግ የሚችሉ ተቋማትን ይፈልጋሉ። እነዚህ ተቋማት ባልተገነቡበት፣ ተገንብተውም ባልዳበሩበት ሁኔታ የምንመኘውን ፍትሕንና ዴሞክራሲን ሳይሆን የጠላነውንና የሸሸነውን ሥርዐት አልበኝነትና አፋኝነት አጭደን ምርቱን ማቀፋችን አይቀርም። እህሉን ስለፈለግነውና ስለዘራነው ብቻ አይበቅልም። መሬቱ እህሉን ለማብቀል የሚችል፣ ሰብሉም ተገቢው እንክብካቤ የሚደረግለት ከሆነ ብቻ ነው፣ ዛሬ ቡቃያ ሆኖ የሚያጓጓን የለውጥ ሰብል ነገ ሁላችንን ስንመኘው የኖርነውን የሥልጣኔና የብልጽግና ነዶ ሊያሳቅፈን የሚችለው።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተከለ ያለው አዲሱ የለውጥ እርምጃ አቅጣጫው በዚሁ የሚመራ ነው። ፍትሕንና ዴሞክራሲን ሊሸከሙ፣ ሊያሳልጡ፣ ሊያሰፍኑና ሊያስከብሩ የሚችሉ ተቋማትን በመገንባት ላይ እንገኛለን። በተጓዳኝም ለተቋማቱ የሚመጥን አመለካከት ያላቸው ባለሞያዎችንና ቢሮክራቶችን መምረጥ፣ ማሠልጠንና መመደብ የሳንቲሙ ሌላኛው ገፅታ ነው። ውጤታማነትና ቅልጣፌን የሚያረጋግጥ ተደርጎ ሰሞኑን ያዋቀርነው አዲስ ካቢኔም ከዚሁ ዓላማና ግብ በመነጨ ነው። ምርጫ ቦርድ ነጻ፣ ተአማኒና ገለልተኛ እንዲሆን ለማድረግ የሕግና የመዋቅር ማሻሻያ እየሠራን ነው። የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት በሠለጠነ መንገድ የዜጎችን መብትና ክብር ጠብቀው የሚፈለግባቸውን ሥራ እንዲሠሩ ጠንካራ ሪፎርም በማካሄድ ላይ እንገኛለን። መከላከያችን በሁሉም መልኩ ኢትዮጵያን የሚወክልና የሚመስል፤ የዘመነና ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ሀገሪቱን ሊጠብቅ በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ የበኩላችንን እየሰራን ነው። የፍትሕ ተቋማት ለዜጎች መብት መከበር የሚሠሩ፣ በገለልተኝነት፣ በሕግ-የበላይነትና በኅሊናቸው ልዕልና ብቻ እንዲዳኙ፣ በሕዝቡም ዘንድ የሚከበሩና የሚታፈሩ ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ የዚህ ዓመት አንዱና ዋናው ሥራችን ነው። በቅርቡም በፍትህ ዘርፉ ተከታታይ እርምጃዎች የሚወሰዱ ይሆናል።
የትምህርት ሂደቱን የተሻለና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶለት በሚመለከታቸውም አካላት እንዲታይ ሠፊ የተግባር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን።
የትናንቱን ዝንፈት ከመጠገንና በጠንካራ መሰረት ላይ ከማነጽ ጎን ለጎን የዛሬው ግንባታ ከሥር ከሥሩ እንዲፋጠን፣ አሁን ላለው ትውልድ ሥራ መፍጠር፣ ኢኮኖሚው በሚገባ እንዲያንሠራራ ማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን መቋቋም፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማብረድና እንዳይከሠቱ ማድረግ፣ የውጭ ግንኙነታችንን ውጤታማ ማድረግ፣ ለነገ ፋታ የማይሰጡን ተግባራት ናቸው። ለነገው ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ደግሞ ከፊታችን ተዘርግቷል።
የአገሬ ልጆች
በሶስት ግንባር ከከፈትነው ጦርነት ጋር የምናደርገው ትግል መደምደሚያው በድል እንደሚጠናቀቅ በፍጹም አልጠራጠርም።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጄኔራል ፓርክ፣ በጀርመን ሀገር በነርስነትና በመአድን ቁፋሮ ሥራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ የዴያስፖራ ዜጎቻቸውን ደሞዝ በመያዣነት በመጠቀም ብድር መጠየቃቸው ይታወሳል። በሂደትም ተመፅዋች ሀገራቸውን ዛሬ ከእድገት ማማና ለጋሽ ሀገር ማድረግ ችለዋል።
የእኛ ትውልድ የምታኮራና አንጸባራቂ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ግዙፍ ኃላፊነት ከፊታችን ተዘርግቷል። ምናልባትም የሚነሳው ቁልፍ ጥያቄ ይሄንን ማድረግ ይቻለናል ወይ? የሚል ነው።
ያለጥርጥር አዎ! ይቻለናል! ነው መልሱ።
ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ ሀገር፣ ባለ ክቡር ታሪክ፣ የጠቢባንና የሊቃውንት መፍለቂያ ምድርን፣ የማይበገርና የማይናወጥ ሕዝብ ይዞ መሸነፍ የማይታሰብ ነው። ከተባበርንና አንድ ከሆንን፤ በትንንሾቹ ጉዳዮች ላይ የተጣዱ ትኩረቶቻችንን ወደታላላቆቹ ቁምነገሮች መልሰን ትልቁ ሥዕል ላይ ካተኮርን፣ ዛሬን ለነገ ስንል ችለን፤ ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ለመገንባት ከቆረጥን፤ ጉልበታችንን በማይረቡ ነገሮች ላይ ካላፈሰስን፣ ምንጮቹን ጅረቶች፣ ጅረቶቹን ወንዞች፣ ወንዞችንም ባሕሮች ለማድረግ ቆፍጠን ብለን ከሠራን ድላችን ሩቅ አይሆንም፣ ይቻላል። የድል ነጋሪትም ይጎሠማል።
የተከበራችሁ የሀገሬ አምባሳደሮች
እኔ ዛሬ እዚህ የቆምኩት እናንተ በአውሮፓ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንድሆናችሁ ከልቤ ስለማምን እና ከኮሪያውያን ስለተማርኩም ጭምር ነው። የሀገራችሁ ነገር ስለሚያሳስባችሁ ቀን በሥራ ብትደክሙም ሌሊቱን በሀሳብ ተጉዛችሁ ስለ ሀገራችሁ ስትብሰለሰሉና ላይ ታች ስትሉ እንደምታድሩ በሚገባ አውቃለሁ። እዚህ ማስናችሁ ከምታገኙትን፣ ሀገር ቤት ያለው ዘመዳችሁ እኩል ተካፋይና የወዛችሁ ተጠቃሚ መሆኑም ድንቅ ነው። ለራሳችሁ በኪራይ ቤት እየኖራችሁ የወላጆቻችሁን ቤት ትሠራላችሁ። እናንተ ለመማር ያላችሁን ዕድል አሳልፋችሁ ቀን ከሌት እየለፋችሁ ታናናሾቻችሁን ታስተምራላችሁ። ይህንን ሁሉ የምታደርጉት በእርግጥ ሀገራችሁን ስለምትወዱ ነው። ስለዚህም አምባሳደሮች ብላችሁ አይበዛባችሁም።
ኢትዮጵያውያን ከአውሮፓ ጋር ያላቸው ትውውቅ ከ 500 ዓመታት በላይ ዕድሜ ማስቆጠሩን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። በዚህ ዕድሜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በተደራጀና በአሰራር በተደገፈ መልኩም ባይሆን ለሀገራቸው የሚሆን ብዙ ነገር እየቀሰሙ በነጠላና በቡድን በመሆን ወደሃገራቸው ተመልሰዋል። እናንተም እንደነርሱ ለሀገራችሁ የሚበጀውን ሥራ ሁሉ ለመስራት መትጋት ይኖርባችኋል። ዕውቀትን አሻግሩ። ለሀገራችሁ የገቢ ምንጭ ፍጠሩ። አዳዲስ አሠራሮችን አምጡ፤ እንዲሆን የምትመኙትን በጥልቅ መረዳት ጨብጣችሁ ወደሃገራችሁ ኑና ተግባራዊ አድርጉት። ከማንም አትጠብቁ። ኢትዮጵያ የእናንተ ናት። ማንም ቢሆን የእናትና የአባቱን ቤት በማገዝ እንጂ በማማረር ለውጦ አያውቅም። ኢትዮጵያም ይሄንኑ ትፈልጋለች። ማን ለማን ቅሬታ ያቀርባል? ሁላችንም እኛው ነን። ማን ማንን ያማርራል? ሁላችንም እኛው ነን። ማን ለማን ሥራውን ይተወዋል? ሁላችንም እኛው ነን። አንድ ቤተሰቦች ነን።
አምባሳደሮቼ ሆይ!
አሁን በአውሮፓ ቅዝቃዜው እየጀመረ ነው። ከክፍለ ዘመናት በፊት በድፍን አውሮፓ በቅዝቃዜው ጦስ ብዙ ሕዝብ ያልቅ ነበር። የሕልውና ጉዳይ ነውና በችግሩ ከመረታት ይልቅ፣ ችግሩ ወደ ብልሃት መራቸው። የበረዶውን ወቅት በማሞቂያና በበረዶ መጥረጊያ የሚያልፉበትን ብልሃት ቀየሱ። የሀሩሩንም ግለት ለማብረድ የአየር ማቀዝቀዢያን ፈለሰፉ። በችግር መቆዘምና ማማረር ሳይሆን ችግርን እንደ ዕድገት መሰላልና ድልድይ በማየት ጉዞን በፍጥነት ወደ ላይና ወደ ፊት ማድረጉ ይበጃል። ስለዚህ፣አንድ ሆነን ዛሬ እንነሣ! የምንተኛበት ሳይሆን የምንነቃበት… የምንከፋፈልበት ሳይሆን ያለንንና የሆነውን ሁሉ በአንድነት አጣምረን የምንነሳበት ጊዜ ነው። ትናንት ከኛ ውጭ ነው። ቆርጠን ከተነሳንና ከተጠቀምንበት ያለንም ያለነውም ዛሬ ላይ ነው። የማግለል ሳይሆን የማቀፍ፣ የመንቀፍ ሳይሆን የማበረታታት፣ ሁሉን ለኔ የሚል ሳይሆን የመተሳሰብ ባህል ከፈጠርን ደግሞ ገና ያልተነካው ነገም አንጡራ ሀብትና ወርቃማ ዕድል ሆኖ ከፊታችን ይጠብቀናል። ዛሬ ላይ በርትተን በመሥራት የነገን የሰለጠነ ማህበረሰብና የበለጸገች ውብ ኢትዮጵያን አብረን እንገንባ።
ከዐሥር ዓመት በኋላ ችግሮቿን ሁሉ ትዝታ ያደረገች፣ የማትፈርስ፣ የማትቀለበስና ወደ ኋላ የማትመለስ… ለሁላችንም የምትበቃ፣ ለሌሎች የምትተርፍ፣ የአፍሪካ ኩራት፣ የዓለም ፈርጥ የሆነች ኢትዮጵያን አያለሁ።
ተስፋ አደርጋለሁ።
በስደትና በተለያዩ ምክንያቶች ሀገርና ቀያቸውን ጥለው በየሰዉ ሀገር የተበተኑ ህዝቦቿ በሀገራቸው በፈቀዱበት ቦታና መንገድ በፍቅርና በመልካም ጉርብትና በሀገራቸው ዘና ብለው የሚኖሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ተስፋ አደርጋለሁ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች አውሮፓ መጥተው ለማግኘት ለሚያልሙት ያልርተረጋገጠ ቀቢጸ ተስፋ የሰሀራን በርሃ አቋርጠው፣ የሜዲትራኒያንን ባህር ከፍለው የሚነጉዱበት ዘመን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከትማል። ፍሰቱ ወደ አውሮፓ መሆኑ ቀርቶ ወደ ኢትዮጵያ ይቀለበሳል። ልጆቻችን ወደ አውሮፓ ለጉብኝት እንጂ ለስደት የሚመጡበት ጊዜ ያበቃል።
ተስፋ አድርጋለሁ።
ዛሬ በመረጥነው በጎ ጎዳናና በፈጸምነው ሰናይ ምግባር ልጆቻችንም በክብር ስማችንን እንደሚያነሡ አምናለሁ።
ተስፋ አደርጋለሁ።
ይሄ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በእግራችን እየተራመድን የዛሬዋን ቀን በደስታ አስታውሰን እንኳንም ለዚህች ታላቅ ሀገር ደከምን ብለን ደስ የሚለን ቀን ይመጣል።
ተስፋ አደርጋለሁ።
ሁላችንም ወደ ልቡናችን ተመልሰን፣ የትናንቱን በዕርቅና በይቅርታ ዘግተን፣ የነገውን በተስፋና በፍቅር ሰንቀን፣ የምንኮራባትን ልዩ ሀገር እንገነባለን።
ተስፋ አደርጋለሁ። አምናለሁም።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
አመሠግናለሁ
ኢሽ ዳንከ ኢኔን!Tuesday, 30 October 2018
ዶ/ር ዓቢይ ከሥልጣን ይውረድ!
ሙአዘ ጥበብ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አንድ ባልና ሚስት ነበሩ። ሴትየዋ ሙያ ሚባል ነገር አልፈጠረባትም። ሁልጊዜ ንፍሮ እየቀቀለች ነው ምታቀርበው። እሱም በጣም ከመልመዱ የተነሳ እንግዳ እንኳን ሲመጣ “እስቲ ያን እጅ ሚያስቆረጥም ንፍሮ ቀቅይላቸው” ነው ሚለው።
አንድ ቀን ታድያ ይቺ ሙያ የሌላት ሚስቱ ጥላው ትሄዳለች። እጅግ በጣም መጎዳቱን ያዩት ጎረቤቶቹ ሌላ ሚስት ያመጡለታል። እሷንም ባገባ በመጀመርያው ቀን የተለያየ አይነት ምግብ ሠርታ ቡፌ ደርድራ ታቀርባለች። ይሄ ምንድነው? ይላል በመደነቅ፤ እርሷም ምግብ ነዋ ትለዋለች።
በጣም እየተገረመ “ለካ እንደዚህም አለ” እያለ እስኪጠግብ ከበላ በኋላ በሩን ዘግቶ በአለንጋ ይገርፋት ጀመር። ጩኸቷን የሰሙ ጎረቤቶች ተሯሩጠው ይመጡና “ምን ሆነሃል? ሚስት እንድትሆንህ እንጂ እንድትደበድባት አይደለም’ኮ ያጋባንህ!” ይሉታል።
እሱም “እስከዛሬ ድረስ በንፍሮ ስቀቀል የት ነበረች?” አለ ይባላል።
ብዙዎቻችን አዲስ ለውጥ የሬት ያህል ይመረናል። ቀድሞ የተጸናወተን የጠባብነት ባህል/አስተሳሰብ አዲሱን ለውጥ መሸከም እንዲከብደን ያደርገናል። በዚህም ጊዜ ራሳችንን ከለውጡ ጋር ለማጣጣም ከመጣር ይልቅ በለውጡና ለውጡን ያመጡ ሰዎች(ቡድኖች) ላይ የስድብ /የተቃውሞ/ ውርጅብኝ ማውረድ ይቀናናል።
በዶ/ር ዓቢይ አሕመድ ላይ የተከፈቱ አንዳንድ ዘመቻዎች ከዚህ የተለዩ አይደሉም። ባርነትን የለመደ ነፃነትን ከባርነት በላይ ይጸየፋልና ከለውጡ ጋር መራመድ ያቃታቸው በቁማቸው ያንቀላፉ አንዳንድ ብሔርተኞችና የቀድሞው ሥርዓት ልዩ ተጠቃሚዎች አፋቸውን ሞልተው “ዓቢይ ከሥልጣን ይውረድ” የሚል አሳፋሪ ዘመቻ መክፈታቸው አስገርሞኛል።
አያቶቻችን “ሞኝ እርሱ ባያፍር ዘመዱ ያፍር” የሚሉት ብሂል አለ። እናም በእነዚህ ሰዎች ሥራ እነርሱ ባያፍሩም እኛ ወገኖቻቸው እናፍራለን አፍረናልም። ኢትዮጵያም አፍራለች።
ሁሌም ስንራመድ እያስተዋልን ቢሆን ለእኛ መልካም ነው።
Thursday, 25 October 2018
የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ ብሄር - ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ፣
የካቲት፣ 1942 አዲስ አበባ ውስጥ የተወለዱት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ እድገታቸውም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡
ወ/ሮ ሳህለወርቅ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ሲሆኑ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡
ከፈረንሳዩ ሞንተፔለ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ የተመረቁት ወ/ሮ ሳህለወርቅ እ.ጎ.አ ከ1989 እስከ 1993 ባሉት ዓመታት ተቀማጭነታቸውን ሴኒጋል ውስጥ በማድረግ የጊኒ ቢሳው፣ የጋምቢያ፣ የማሊ፣ የኬፕ ቨርድ እና የጊኒ አምባሳደር በመሆን ማገልገላቸውን ተመልክተናል፡፡
እ.ጎ.አ ከ1993-2002 በጅቡቲ አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ቋሚ ተወካይም ነበሩ።
እ.ጎ.አ ከ2002-2006 በፈረንሳይ አምባሳደር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ተወካይ ሆነው ሰርተዋል።
በመቀጠልም፣ በተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ውስጥ የተቀናጀው የሰላም አስከባሪ ሃይል ተወካይ በመሆን በሴንትራል አፍሪካ(BINUCA) ኃላፊ በመሆን ማገልገላቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡
ወ/ሮ ሳህለወርቅ፣ በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ውስጥ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ በመሆን እንዲሁም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው አገልግለዋል፡፡
እ.ጎ.አ በ2011 የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ የነበሩት ባንኪ ሙን፣ በኬኒያ የተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተር ጄነራል አድርገው ሾመዋቸው አገልግለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመው እንደነበር ለማወቅ ችለናል፡፡
...
ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፣ በሥራ ዘመናቸው ስለሰላም ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የተናገሩት ርዕሰ ብሄሯ፣ “ሥር የሰደደውን ጥላቻ፣ መናናቅና አልፎ አልፎ የሚታየውን ጠብ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ በዳበረ የቤተ እምነቶች ጥበብና የሽምግልና ሥርዓት ከወዲሁ በመግታት ለራሳችንም ሆነ ለትውልድ የምታኮራ ሐገር መፍጠር ይኖርብናል” ሲሉ ተናግረዋል
Tuesday, 16 October 2018
ትዳር ነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም፡
Dsniel Kibert
“ትዳር ነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም፡፡ ልምድ ማስቆጠሪያ እንጂ፡፡ ትዳር በሁሉም ነገር መግባባትን፣ መተማመንንና መስማማትን አይጠይቅም፤ ከተለያዩ በታዎች በመጡ፣ በጾታም በማይገናኙ ሁለት ሰዎች የሚመሠረት ነውና፡፡
ትዳር የተለያዩ ሰዎች ያዘጋጁዋቸው ሁለት ፈትሎች እየተገመዱ የሚሄዱበት ሽመና ነው፡፡ ሲጀመር ጫፍና ጫፉ ይያያዛል፣ በሂደት ግን ካልተገመደው የተገመደው እየበለጠ ይሄዳል፡፡ ግመዳው ግን እንዲህ በቀላሉ የሚከወን አይደለም፡፡”
ትዳርን የተቃናና የተሳካ ለማድረግ በሁለት ባላዎች ላይ መትከል ያሻል ይላሉ፤ ሊቃውንቱ፡፡ በመማርና በመማር፡፡ ሰው ሌላውን ሥራ ሁሉ የሚሠራው አንድም ተምሮ አንድም ለምዶ ነው፡፡ ትዳር ሲመሠርት ግን ትምህርትም ልምድም የለም፡፡
ትዳርን እንደ ትምህርት ዓይነት መርጦ፣ ከፊደል እስከ ዳዊት ደግሞ፤ አድርሶ አስመስክሮ የተመረቀ የለም፡፡እዚህም እዚያም ትዳርን የተመለከተ ንባብና ሐሳብ ይገኝ ካልሆነ የትዳር ዲፕሎማና ዲግሪ፣ ማስተርስና ዱክትርና የለም፡፡ ሌላውን ሞያ ለተግባሩ ተመሳሳይ በሆነ አምሳያ ተግባር(ዎርክ ሾፕ/ሲሙሌተር) ልምምድ ማድረግ ይቻላል፡፡
ትዳርን ግን በአምሳያው ላይ ልምምድ ማድረግ አይቻልም፡፡ ‹እገሌ ይህን ያህል ዓመት ትዳርን በተመለከተ ልምድ አለው› ብሎ መጻፍ የሚችል መሥሪያ ቤትም የለም፡፡ ለዚህ ነው በትዳር ጉዞ ውስጥ ‹መማር› ወሳኝ የሚሆነው፡፡ ትዳር ማለት ጥቂት ዕውቀትና ጥቂት ሐሳብ ይዘው ገብተው፣ እየኖሩ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስለ ዋና በሚገባ ማወቅ የሚቻለው እየዋኙ እንደሆነው ሁሉ፣ ስለ ትዳር በበቂ መማር የሚቻለው እየኖሩ ነው፡፡
ሁለቱም በተለያዩ ቤተሰቦች ባሕልና መርሕ ያደጉ፣ አንዱ ለሌላው ተብሎ በዕውቅ ያልተሠሩ፣ በነጠላ ተወልደው በድርብ የሚኖሩ ናቸውና፡፡ በትዳር መርከብ ውስጥ ከሌላው ጋር ሲኖሩ ሊከሰቱ የሚችሉትን የአስተሳሰብ፣ የፍላጎት፣ ጠባይና የአካሄድ ለውጦች አስቀድሞና አስረግጦ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡
እንኳን አንዱ ስለሌላው ስለራሱም ለውጥ ቀድሞ መተንበይ ይከብደዋል። ይባስ ብሎም ከዚያ በፊት ያልነበሩ ሦስት ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ በየራሳቸው ሲወስኑና ሲያደርጉ የኖሩት ወንድና ሴት በጋብቻ ምክንያት ሥልጣናቸው የጋራ፣ ኃላፊነታቸው የጋራ፣ ውሳኔያቸውም የጋራ ይሆናል።
መመካከር፣ መግባባትና መጋራት የግድ ይሆናል፡፡ በአንድ ዙፋን ሁለት ነገሥታት ይነግሣሉ፡፡ በእዝ ሠንሠለት ሁለት ሰዎች ለአንድ ሰው ተጠሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንድ ሰው ግን ለሁለት ሰው ተጠሪ አይሆንም፡፡ በትዳር ውስጥ ግን ይከሰታል፡፡ አንድ ልጅ፣ አንድ የቤት ሠራተኛ፣ አንድ በቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ለሁለት ሰዎች ተጠሪ ይሆናል፡፡
በሁለቱ ጋብቻ ምክንያት ሌላ ማኅበረሰብ ይፈጠራል፡፡ ሲለጥቅ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሚተቃቀፉ፣ አንዳንድ ጊዜም የሚገፋፉ ሁለት ቤተሰቦች ከሁለቱ ጀርባ ይመጣሉ፡፡ መጥተውም ወይ ጸጥ ያለ፣ አለያም ማዕበል የበዛበት ውቅያኖስ ይፈጥራሉ፡፡ ይህን የቤተሰብ ውቅያኖስ ማስተዳደር ለተጋቢዎቹ አዲስ ነገር ነው፡፡ ሲሠልስ ደግሞ ከሁለቱ ኑሮ ልጆች ይወለዳሉ፡፡
ይህን አዲስ የተፈጥሮ ስጦታ መቀበል፣ ተቀብሎም ማስተዳደር ዕውቀት፣ ብስለትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡
በዚህ ሁሉ ጉዞ ውስጥ ብልህ ይማራል፣ ሞኝ ያማርራል፡፡ ብልህ ከምን ይማራል? ቢሉ ከሦስት ነገሮች ይማራል፡፡ ከራሱ ጉዞ ይማራል፤ ከትዳር አጋሩ ጉዞ ይማራል፤ ከሁለቱም ጉዞ ይማራል።
ቀድሞ የሚያውቃቸውን፣ ይሆናሉ ብሎ ሲገምታቸው የኖሩትን፣ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸውንና እንዲያደርጋቸው የተመከረውን በትዳር ውስጥ ይሞክራቸዋል፡፡ የተሳካ ውጤት ካመጣለት፣ እሰየው ብሎ መመሪያው ያደርጋቸዋል፡፡ ችግር ከተፈጠረበት፣ ይቅርታ ብሎ ያርማቸዋል፡፡ እየተሞረደና እየተሳለ፣ እያወቀና እየበሰለ፣ እየታረመና እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡
ለዚህም ነው የተሟላ ባል ማግኘት አይቻልም፤ የሚሟላ ባል እንጂ፣ የተሟላች ሚስትም ማግኘት ከባድ ነው፣ የምትሟላ ሚስት እንጂ የሚባለው፡፡ ብልህ ከትዳር አጋሩም ይማራል፡፡ የትዳር አጋርን በእጮኝነት ጊዜ ማየት ፀሐይን በሩቁ እንደማየት፣ በትዳር ጊዜ ማየት ደግሞ ፀሐይን ቀርቦ እንደማየት ነው ይባላል፡ አንዳንድ ጊዜ ከምናስበው የተለየ ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ መሆኑን ቀድሜ ባውቅ ኖሮ አላገባትም/ አላገባውም ነበር ያሰኛል፡፡
ሊቃውንቱ ‹እንዳውቅህ ተገለጥ› ይላሉ፡፡ የአንድን ሰው ጠባይ፣ ሐሳብና አቋም መገለጡን አንጥላው፡፡ባወቅነው መጠን እንዴት መያዝ፣ እንዴትስ ማሸነፍ እንደምንችል እናውቃለንና፡፡ ከማያውቁት ነገር ጋር መኖር እንጂ ካወቁት ነገር ጋር መኖር አያስፈራም። ከትዳር አጋርህ ጋር ይበልጥ አብረሃት በኖርክ ቁጥር ይበልጥ ታውቃታለህ፤ ይበልጥ ባወቅካት ቁጥርም ይበልጥ አብረሃት ትኖራለህ፡፡
ብልህ ባል ከብርታቷም ሆነ ከድካሟ፣ ከትዕግሥቷም ሆነ ከንዴቷ፣ የሚወስደው ትምህርት አለ፡፡ ብልህ ሚስትም እንዲሁ፡፡ ትዳር ማለት ምርቃት የሌለበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ እንደ ጎበዝ የአብነት ተማሪ ሲቀጽሉ መኖር፡፡ አብረው መዝለቅ የቻሉ ባለትዳሮች በሚገባ እየተማሩ፣ የሰለጡ ባለትዳሮች ይሆናሉ፡፡
በትዳር መማር ብቻ ሳይሆን መማማርም አለ። ከየራሳቸውና ከአጋራቸው ብቻ ሳይሆን ከጋራ ኑሯቸውም ይማራሉ፡፡ ጋብቻ ማለት በትዳር ላይ ሥልጣንና ኃላፊነት የሚረከቡበት ቀን ነው፡፡ ጋብቻ በሰጣቸው ሥልጣን ብቻ የሚጠቀሙ ባለትዳሮች ፍቻቸው ቅርብ ነው፡፡ ጋብቻ በሰጣቸው ኃላፊነት ብቻ የሚጠቀሙ ባለትዳሮችም ምሬታቸው ቅርብ ነው፡፡ ጋብቻ ሥልጣንና ኃላፊነት ነው፡፡
ትዳር የሠመረ የሚሆነው እነዚህ ሁለቱ ሚዛን ሲሠሩ ነው። ትዳር ማለት የሥልጣንና የኃላፊነት አማካዩ ነው፡፡ኃላፊነት በተሞላበት ስሜት ሥልጣንን ለመጠቀምና ሥልጣን ባለው መንገድ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚችሉበትን ዘዴ የሚያገኙት አብሮ በመኖር አብሮም በመማማር ነው፡፡ እየተማማሩ በሄዱ ቁጥር ሥልጣናቸውን የጋራ፣ ኃላፊነታቸውንም የጋራ ያደርጉታል፡፡
ትዳርን የሚያቆመው ሌላው ባላ ደግሞ ‹መማር› ነው፡፡ ይቅር ማለት፡፡ ይቅር ማለት ‹ለይቅርታ የተዘጋጀ ልብ› ይፈልጋል፡፡ ይቅር ማለት ሽማግሌ ገብቶ፣ ዕርቅ ወርዶ ይቅርታ ሲጠየቅ ‹እሺ ይቅር ብያለሁ› ማለት አይደለም፡፡ ነገሮችን ለማለፍና ለማሳለፍ፣ ራስ ምክንያት ሰጥቶ ይቅር ብሎ ለማለፍ ዝግጁ መሆን ነው፡፡
ነገሮችን በክፋትና በተንኮል ከማየት ይልቅ ከልምድ እጥረት፣ ከጊዜያዊ ስሜት፣ከማይታወቁ መነሻዎችና ከድካም ሊመጡ እንደሚችሉ በመረዳት ቀድሞ ይቅር ማለት፡፡ ቀድሞ ይቅር የሚል ሰው መፍትሔው ላይ እንጂ ችግሩ ላይ አይቆዝምም፤ነገሩን ከመፍተል ይልቅ መፍትሔውን ይሸምናል፡፡
ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው› ብሎ ስለ ሰቃዮቹ ለምኗል፡፡ ሰቃዮቹ ‹የምናደርገውን ስለማናውቅ ይቅር በለን› አላሉትም፡፡ እርሱ ራሱ የቅድሚያ ምክንያት ሰጥቶ ‹የሚያደርጉትን አያውቁም› አለላቸው እንጂ፡፡ የይቅርታ ልብ ማለት ይህ ነው፡፡
በማናቸውም ጊዜና በማናቸውም ሁኔታ እያስተሠረዩ መጓዝ፡፡ ትዳር ነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም፡፡ ልምድ ማስቆጠሪያ እንጂ፡፡ ትዳር በሁሉም ነገር መግባባትን፣ መተማመንንና መስማማትን አይጠይቅም፤ ከተለያዩ በታዎች በመጡ፣ በጾታም በማይገናኙ ሁለት ሰዎች የሚመሠረት ነውና፡፡
ትዳር የተለያዩ ሰዎች ያዘጋጁዋቸው ሁለት ፈትሎች እየተገመዱ የሚሄዱበት ሽመና ነው፡፡ ሲጀመር ጫፍና ጫፉ ይያያዛል፣ በሂደት ግን ካልተገመደው የተገመደው እየበለጠ ይሄዳል፡፡ ግመዳው ግን እንዲህ በቀላሉ የሚከወን አይደለም፡፡ ውስጡ ሕመም አለው።
ያንን ሕመም መጀመሪያ ማከም፣ በኋላም ማዳን የሚቻለው በይቅርታ ነው፤ በመማር፡፡ ውይይቱና ክርክሩ እንኳን ውጤት የሚያመጣው በሁለቱም ልብ ውስጥ የይቅርታ ልብ ካለ ብቻ ነው፡፡ ውጤቱ መሸናነፍ ሳይሆን መተራረም ከሆነ፡፡ መማር ‹ይቅር ብያለሁ› ማለት አይደለም፡፡
መተውና መርሳት ጭምር እንጂ፡፡ ፋይል እየሰበሰቡና በትናንቱ እርሾ የዛሬውን ሊጥ እያቦኩ መሄድ አይደለም፡፡ በትዳር መጋገር ያለበት አፍለኛ እንጀራ ነው፡፡ ከትናንቱ ተምሮና ምሮ መሄድ እንጂ፣ አምርሮና አማርሮ መሄድ ትዳርን ይበክለዋል፡፡
መማርና መማር – ለተቃና ትዳር፡፡
Friday, 12 October 2018
አነጋጋሪዉ የአቶ ልደቱ አያሌዉ ቃለምልልስ- ያልተነገሩ የ1997 ምርጫ ምስጢሮችና ሌሎችም
የ1997 ምርጫ ምስጢሮች (ክፍል 1)
የ1997 ምርጫ ምስጢሮች (ክፍል 2)
Monday, 8 October 2018
Friday, 5 October 2018
Thursday, 4 October 2018
Tuesday, 2 October 2018
Wednesday, 19 September 2018
የድኅረ ወሊድ ጭንቀት (postnatal depression)
የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) እናቶች ከወለዱ በኋላ የሚያጋጥማቸው፣ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ሊዘልቅ የሚችል የጭንቀት ዓይነት ነው፡፡ ልጅ መውለድ የሚያስከትለውን አዲስ ሁኔታ፣ ጠባይ፣ የሰውነትና የስሜት ለውጥ ለማስተናገድ በሚደረገው እናታዊ ትግል ምክንያት በመጀመሪያዎቹ ቀናት የጠባይ ልውጠት(baby blues) ይከሠታል፡፡ ይህ ግን ለሁለትና ለሦስት ቀናት የሚቆይ ነው፡፡ ነገሩ ከእነዚህ ቀናት በላይ ከዘለቀ ወደ ጭንቀት ያድጋል፡፡ እርሱም የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) ይባላል፡፡ በዚህ ዓይነት ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ እናቶች ‹ሙዳቸው› ይጠፋል፤ የተሸናፊነት ስሜት ይሰማቸዋል፤ ተስፋ ቢስነት ይነግሥባቸዋል፤ ስለ ተወለደው ሕጻን አብዝተው ይጨነቃሉ፤ አንዳች የሆነ ነገር ልጃቸውን የሚነጥቃቸውና የሚገድልባቸው ወይም የሚያሳምምባቸው ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ፈልገው የሚያመጡት ጠባይ ሳይሆን ወሊድ የሚያመጣባቸው ክስተት ነው፡፡
የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ቁጣን ያስከትላል፣ ያነጫንጫቸዋል፣ ተናጋሪ አንዳንዴም ጯሂ ያደርጋቸዋል፡፡ እጅግ የሚገርመው ደግሞ የሚቆጡትም፣ የሚነጫነጩትም፣ የሚናገሩትም፣ የሚጮኹትም በሚወዱትና በሚቀርባቸው ሰው ላይ ነው፡፡ ይህም መውለድ ያመጣው የጠባይ ለውጥ እንጂ ውሳጣዊ የልቡና ለውጥ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የሚነጫነጩበትን፣ የሚቆጡበትንና የሚጮኹበትን ብቻ ለተመለከተ ሰው ትዳሩ የፈረሰ፣ ቤተሰቡ የታመሰ ሊመስለው ይችላል፡፡ ግን በውስጣቸው ፍቅር አለ፡፡ ለዚህም ነው በሚቀርቡትና በሚወዱት ሰው ላይ ብቻ የሚያደርጉት፡፡
በዚህ የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ውስጥ ያሉ እናቶች ከምንም ጊዜ በላይ ክብካቤ፣ ፍቅርና እገዛን ይፈልጋሉ፡፡ ከምንም ነገር በላይ የሚረዳቸው፣ የሚገነዘባቸው ሰው ይሻሉ፡፡ ባሎቻቸው፣ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውና ጠያቂዎቻቸው ሳይረዷቸው ከቀሩ ጭንታቸው ይበልጥ ይጨምራል፡፡ ይህ ችግር የቤተሰባቸውን መረዳትና እገዛ ካገኘ በቶሎ የሚጠፋ መሆኑን የሚያውቁ ብልሆች ጊዜውን በትዕግሥት፣ በአርምሞ፣ በመቻልና በማሳለፍ ይሻገሩታል፡፡ የማይረዱ ቤተሰቦች ግን መልሰው ይጮኹባቸዋል፤ ይቆጧቸዋል፤ ያኮርፏቸዋል፤ ይርቋቸዋል፤ ከዚህም አልፎ ይፈርዱባቸዋል፡፡ በተለይም ወንዶች በዚህ ይታማሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለውጥንና ተስፋን ወልዳ አሁን የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ላይ ናት፡፡ ስለዚህም በሕዝቡ ላይ ንጭንጭ፣ ተሥፋ መቁረጥ፣ ስሜታዊነትና ቁጣ ይታያል፡፡ ይህንን የሚገልጠው ደግሞ በሚያደንቀው፣ በሚወደውና በሚያከብረው ላይ ነው፡፡ ይህ ግን የሚያልፍ ጠባይ ነው፡፡ ልጁ እያደገ፣ እናቲቱም እየበረታች ስትሄድ ጭንቀቷ ወደ ደስታ፣ ንጭንጯም ወደ ሳቅና ጨዋታ ይቀየራል፡፡ ነገር ግን ይህን ወቅት በሚገባ የሚረዳ የቅርብ ቤተሰብ ያስፈልጋታል፡፡ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የሕዝብ መሪዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ሹማምንትና የሐሳብ መሪዎች ይህንን የድኅረ ወሊድ ጭንቀት ጠባይ መረዳት፣ ለአንዲት ወላድ እናት ሊደረግ የሚገባውን ክብካቤ ማድረግ፣ በወሊድ ምክንያት የሚከሠቱ የጠባይ ለውጦችን ዐውቆ የተጠናና ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ሁሉም ተናዳጅ፣ ሁሉም፣ ተሥፋ ቆራጭ፣ ሁሉም ጯሂ፣ ሁሉም ተነጫናጭ፣ ሁሉም አፉ እንዳመጣለት ወርዋሪ፣ ሁሉም ልቡ ያጎሸውን ሁሉ ተናጋሪ ከሆነ የእናቲቱ ጭንቀት እየጨመረ፣ ጤንነቷ እየተቃወሰ፣ የልጁ ጤንነት እየተበላሸ፣ የቤተሰቡ ሰላም እየተናጋ፣ በመጨረሻም ለደስታና ለእልልታ የተወለደው ልጅ ለመከራና ለጭንቀት ይሆናል፡፡
እንረጋጋ፣ እናረጋጋ፤ ሀገር የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) ላይ ናት፡፡
Tuesday, 11 September 2018
Saturday, 8 September 2018
የኢ/ር ስመኘው ገዳዮች ጄ/ል ክንፈ እና ዶ/ር ደብረፂዮን ናቸው!!
From Seyoum Teshome Facebook page
የኢንጂነር ስመኘውን አሟሟት አስመልክቶ ፖሊስ ያቀረበውን የምርመራ ውጤት እንዳለ እንቀበለው። እሺ…እንጂነር ስመኘው ራሱን አጥፋ። ይህ ሰው ራሱን ያጠፋበት ምክንያት ምንድነው? የሀገሪቱን ትልቅ የግንባታ ፕሮጀክት በኃላፊነት ሲመራ የነበረ ሰው ነው። መስቀል አደባባይ ላይ ራሱን ከማጥፋቱ በፊት ፍላሚንጎ ወደሚገኘው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ቢሮ እየሄደ ነበር። የሚሄደው ስለ ህዳሴው ግድብ ግንባታ አጠቃላይ ሂደት መግለጫ ለመስጠት ነው።
ከዚያ ቀደም ብሎ ጠ/ሚ አብይ አህመድ የህዳሴው ግድብ ግንባታ አሁን ባለው አካሄድ በአስር አመት ውስጥ እንደማይጠናቀቅ መናገራቸው ይታወሳል። ኢ/ር ስመኘው ግን “የግድቡ ግንባታ ከ60% በላይ ደርሷል” እያለ መግለጫ ሲሰጥ ኖሯል። ይህ ሰው እንዲህ ያለ የውሸት መግለጫ ሲሰጥ የኖረበት ምክንያት አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ከዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ጋር ያደረገውን የኢሜል ልውውጥ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻለል። እነ ዶ/ር ደብረፂዮን እና ጄ/ል ክንፈ ለህዳሴው ከተመደበው በጀት ውስጥ ወደ 70 ቢሊዮን የሚሆነውን ሙጥጥ አድረገው ሲዘርፉ ኖረዋል። በተለይ ለሜቴክ የተሰጠው ስራ ግን ገና 30% ላይ ነው። 30% የሚሆነውን ሥራ ሳይሰሩ 90% የሚሆነውን በጀት የበሉት የሜቴክ እና ህወሓት ባለስልጣናት ኢ/ር ስመኘውን እያስገደዱ “የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ60% በላይ ደርሷል” እያለ እንዲናዘዝ ሲያደርጉት ኖረዋል።
በድንገት ዶ/ር አብይ መጣና በህዳሴው ግድብ ጉብኝት ያደርጋል። በቦታው ያለውን የውሸትና የሌብነት ክምር ከተመለከተ በኋላ “ይህ ውሸትና ሌብነት ማብቃት አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ እውነታውን ማወቅ አለበት። የህዳሴው ግድብ ገና 30% ላይ ሲሆን 90%ቱ በጀት ተዘርፎ አልቋል ብለህ እቅጩን ተናገር” የሚል መመሪያ ይሰጡታል። ከጉብኝቱ መልስ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከምሁራን ጋር ባደረጉት ስብሰባ “የህዳሴው ግድብ አሁን ባለው አካሄድ በ10 አመት ውስጥ እንኳን አይጠናቀቅም” ብለው ተናገሩ።
የሀገር ውስጥና የውጪ ሚዲያዎች ወደ ኢ/ር ስመኘው ስልክ በመደወል “ይሄ ነገር እንዴት ነው?” ብለው ጠየቋቸው። ሰውዬው በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ሆነው “ቆይ ከመንግስት ኮሚኒኬሽን ጋራ ተናጋግሬ ምላሽ እሰጣለሁ” ማለት ጀመሩ። በቀጣይ ቀናት ወደ አዲስ አበባ መጡ። ዋና ዋና የመንግስት ሚዲያዎችን ጠርተው ፍላሚንጎ ወደሚገኘው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ፅ/ቤት በመሄድ ላይ ሳሉ መስቀል አደባባይ ራሳቸውን አጠፉ።
ኢ/ር ስመኘው የሚሰጡት መግለጫ ምን የሚል ነበር? “የግንባታ ሥራው ገና 30% ላይ እያለ 90% በጀት መዘረፉን ደብቄ ሥራው ከ60% በላይ ደርሷል እያልኩ የሌቦችን ስራና ዘረፋ ስደብቅ፣ ሀገርና ህዝብን ስዋሽ…ስዋሽና ስዋሽ ኖሬያለሁ” የሚል ነው። ይሄ “Professional Suicide” ይባላል!!! ኢ/ር ስመኘው ላለፉት 6 አመታት ሙያዊ ኃላፊነቱን መወጣት የተሳነው፣ ሀገርና ሕዝብ ሲያዘርፍ የኖረ ሙያዊ ክብርና ስነ-ምግባሩ የተገፈፈ “ተራ” የዘራፊዎች መጨዋቻ እንደነበር በራሱ ላይ ከሚመሰክር ራሱን ቢያጠፋ ይመርጣል። በዚህ መሰረት ኢ/ር ስመኘው ራሱን አጠፋ!!!
ኢንጅነሩ ራሱን ሲያጠፋ ከሁሉም ቀድመው የአዞ እምባ ማንባት የጀመሩት ገዳዮቹ ናቸው። የኢ/ር ስመኘው ገዳይ ሽጉጥ አይደለም። ራሱ ግለሰቡም አይደለም። ከዚያ ይልቅ እጁን የኋሊት ጠፍሮ በጉልበት እያስፈራራ ሲያስዋሸዋ የኖረው ጄነራል ክንፈ፣ ለሙያው እንዳይገዛ ከላዩ ላይ የዕብሪት ትዕዛዝ ሲያዘንብበት የነበረው ዶ/ር ደብረፂዮን ናቸው። በዚህ መልኩ ህሊናዉን ሸጦ፣ ውሸት እየተናገረ፣ የእነሱን ዘረፋ እየደበቀ እንዲኖር ያደረጉት፣ ሙያዊ ክብርና ዝናውን የገፈፉት፣ በመጨረሻም ራሱን እንዲያጠፋ ያደረጉት ጄ/ል ክንፈ እና ዶ/ር ደብረፂዮን ናቸው።
Friday, 7 September 2018
.እውነት ለመናገር እኛ ኦሮሞዎች ጥበብ እና ጀግንነት አይወድልንም: :
እንደዚህ አይነት የበሰለ ሰው ደስ ይለኛል በግሌ:-
የአመቱ ምርጥ ኮሜንት!!!
ይህ አስተያየት የተሰጠው ለእቴጌ ጣይቱ ሐውልት የመሰረት ዲንጋይ ለመጣል ከተዘጋጀ በሁዋላ በኦሮሞ አክቲቪስቶች ጫጫታ የተነሳ የመሰረት ድንጋዩ ሳይጣል መቅረቱን ተከትሎ በOMN በተሰራ ዘገባ ስር @YAYESHHULU YINBEREKEKILISHAL በመሚል አካውንት የተሰጠ አስተያየት ነው*****
#እንደዚህ_ይላል........
1.እውነት ለመናገር እኛ ኦሮሞዎች ጥበብ እና ጀግንነት አይወድልንም: : ጠበብን እና ጀግነትን ተገንዝበን አያከብርም:: ጣይቱም ትሁን ምንሊክ ከ50% በላይ ኦሮሞ ናቸው:: ነገር ግን ኦሮሞ ሞኝ ነን ; ብዙ ግዜ በ inferiority compex ወደ ሃላ እንቀራለን:: አማራ የወደደው እና ያደነቀው ነገር ሁሉ የአማራ ይመስለናል:: በዚህም ጀግኖቹን እና ጠቢባኑን መጠቀም ሳይችል: ;ለሌሎች አሳልፎ ይሰጣ ; ጀግኖቻችን እና ጠቢባኖቻችን በሌሎች hijacked ይደረሉ::
2.አማራ ብልጠቱ ከየትም ብሄር ብትሆን ; ጀግና እና ብልህ ወይም አዋቂ ከሆንክ ይወድሃል:,ያከብርሃል የራሱ እስክትመስለው ያቀርብሃል:: Because they give high values for knowledge , wisdoms, leadership and heroism . ሞኝ ,ተላላ , አላዋቂ , ፈሪ ከሆነ አማራ የራሱንም መሪ ቢሆን አያከብርም አያደንቅም::
3. በትንሹ ለምሳሌ መንግስቱ ሀይለማሪያም በእናቱም ይሁን በአባቱ ኦሮሞ ነው ; የሚወደው እና ሚደነቀው ግን በአማራ ነው:: ሌሎችም እጅግ ብዙ አሉ እንደእነ ሎሬት ፀጋየ ገ/መድህንም 100% ኦሮሞ ናቸው ; በጥበባቸው የሚወደዱት እና ሚከበሩት ግን በእማራው ነው::
4.እዩዋቸው አቢይ አህመድ እና ለማ መገርሳን ; አማራ እንዴት እንዳነገሳቸው ,እንደወደዳቸው, እንዳከበራቸው , ህይወቱን አሳልፎ እንደ ሚስጥላቸው ::
5. እነሱ ግን ከኦሮሞ እናት እና አባት ተገኝተው , የኤሮሞን ወተት እና ውሃ ጥጥተው አድገው ሳለ ; አማራ ያየው ብሄራቸውን አይደልም ; ድፍረታቸውን ,leadership አሰጣጣቸውን , ብልህነታቸውን እና ቅንነታቸውን ነው:
6. የኦሮሞ ችግሩ በድሮው አባገዳ ደረጃ የሚወደሰውን እና የሚደነቀውን ; ከብት ጠባቂ ጀግና(0ld fashion warriors)ወይም local heroes እንጅ ; ለnational ጀግና ክብር አይሰጥም:: በዚህም የተነሳ የኦሮሞ ተወላጅ ዘመናዊ መሪዎቻችንን ብዙ እርቀት ሄደው ሀገር የመምራት እንዳይችሉ እንቅፋት እንሆናለን::
7. አሁን ለምሳሌ ኦሮሞ ቄሮ ጅዋር መሃመድ እንወድዋለን እናከብረዋለን እንበል; ጅዋር መሀመድ በ National ደረጃ በአማራ እና በትግራይ በሌላውም ብሄር ተቀባይነት ቢኖረው ; እኛ ኦሮሞዎች ጅዋር ኦሮሞ አይደለም እንላለን ; ምክንቱም ጅዋር local ብቻ ሆኖ ; ኦሮሞ ኦሮሞ እያለ ብቻ እንዲቀር እንፈልጋለን::
8. ለዚህም ነው ምእራብያውያን ; የአንድን ማህበረሰብ ስነልቦና እና የእውቀት ደረጃ ; ወይም values ለማወቅ ወይም ለመረዳት ከፈለግክ ; ማህበረሰቡ የሚያደንቃቸው ጀግኖቻቸውን ወይም icons ቸውን ቀርበህ ተመልከት ወይም አድምጥ የሚሉት::
9. ምሊክንም ይሁን ጣይቱን ያስተዳደሩት ትምህርት በሌለበት ,ሚድያ በሌለበት ,ፌስቡክ በሌለበት የዛሬ 200 አመት ነው ; ስለዚህ በድሮው ዘመን የንጉሳዊ አገዛዝ አስተሳሰብ እንዳኛቸው::
እንግሊዝ አውሮጳም ቢሆን በዚያ ዘመን ; አንድ ግዛት አልገብርም ብሎ ካስቸገረ ; ለምን የእናቱ ልጆች አይሆኑም ; ለ 2 ግዜ ወይም 3 ግዜ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከንጉሱ ከቤተመንግስት ይላክ እና ; አሁንም አሻፈረኝ ካለ ተንቂያለው ብሎ የማስፈራሪያ እርምጃ ; አልገብርም ብሎ ባስቸገረው በግዛቱ ህዝብ ላይ ይወሰድበት ነበር: “”nothing is personal or hatred”
10. እነሱ አልከተልም ወይም አልገብርም ያላቸውን ህብረተሰብ ; እንደነ ጅዋር 6 አመት ሙሉ በፌስቡክ ህዝብን ለማሳመን ; እንደ ለማ መገርሳ ለማግባባት ምንም ዘመናዊ የመረጃ ማስተላለፊያ እና ሚድያ ሳይኖራቸው ; ሰው ቢገድሉ ወይም ቢያስፈራሩ ምን ይገርማል ;
እኛ አለን አይደል በዘመናዊው ዘመን ተምረን እና ተፈጥረን የዛሬ 20 ቀን ; የደቡብ ልጅ እንደኛ ኦሮምኛ አልተናገረም ብለን ;በዚህ በሰለጠነ ዘመን በኮምኔኬሽን ማሳመን አቅቶን inocent ሰው ሻሸመኔ ላይ ዘቅዝቀን የገደልን እና ያቃጠልን:: በምንሊክ ከተናደድን እኮ ከምንሊክ መማር ነበረብን; እውነተኛ ከሆን where is our practical justification ?
Let’s set our standards higher and push forward our Oromo leaders to the national and global levels by admiring them. ር ል
ስለተመቸኝ ሼር አርኩላችሁ
ከወደዳችሁት ሼር አርጉት
Monday, 3 September 2018
Friday, 31 August 2018
Monday, 27 August 2018
Sunday, 26 August 2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ እሁድ በመኖሪያ አቅራቢያቸው በድህነት የሚኖሩ አንዲት አዛውንትን ጎብኘ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ እሁድ በመኖሪያ አቅራቢያቸው በድህነት የሚኖሩ አንዲት አዛውንትን በመጎብኘት በላያቸው ላይ እየፈረሰ ያለ ደሳሳ ቤታቸው በጎረቤቶች ትብብር ዳግም እንዲስራ ቤቱን የማፍረስ ስራ አስጀመሩ፣ በእማሆይ ቤትም በህብረት ቁርስ ተመግበዋል ::
መላው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እና የኢትዮጵያ ህዝብ በአዲሱ አመት የወደቁ ወገኖቹን የማንሳት ተመሳሳይ ተግባራትን እንዲፈጽሙ በዚህ መልክ በመደመርና በፍቅር አዲሱን አመት እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል::
መላው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እና የኢትዮጵያ ህዝብ በአዲሱ አመት የወደቁ ወገኖቹን የማንሳት ተመሳሳይ ተግባራትን እንዲፈጽሙ በዚህ መልክ በመደመርና በፍቅር አዲሱን አመት እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል::
Saturday, 25 August 2018
Friday, 17 August 2018
Friday, 10 August 2018
Thursday, 9 August 2018
ባንዲራ የማስረዘም ፉክክር
ሰሞኑን የማያቸው ሁለት ነገሮች ግርርርርም ይሉኛል
ባንዲራ የማስረዘም ፉክክር ይገርመኛል
አንዳንዱ ባንዲራ ከመርዘሙ የተነሳ ፤ተሸንሽኖ፤ ሱሪና ቀሚስ ሆኖ ቢሰፋ አንድ የገጠር መንደር አመት ያለብሳል፤
የጦቢያ ፖለቲካ የተራቀቀ አይደለም፤ ለብር እና ለክብር የሚደረግ ትግል ነው፤ ከላይ ያሉት ጮሌዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ፤ በተራበ ሰው ስም፤ በተፈናቀለ ሰው ስም፤ነፃነት በጠማው ሰው ስም ፤ በግዜር ስም፤ በናት ሀገር ስም፤ በናት ጎሳ ስም፤ ሀብት ፤ ስልጣንና ዝና ይሰበስባሉ፤
ከታች ያለው ጎበዝ የኔ ባንዲራ ቁመት ካንተ ባንዲራ ቁመት ይበልጣል፤ በሚል ሀሳብ ተጠምዶ ድርሻውን ሳይጠይቅ፤ ክሬም እድሜውን ያባክናል ፤ አንድ ቀን ባንኖ ሲነቃ በጁ ምንም የለም፤ ሰው መሆን አይቀርምና ላመፅ ያቆበቁባል፤ ይህን ጊዜ ተጠባባቂው ጮሌ ከሰገነቱ ወርዶ ለጭፍራነት ይመለምለዋል፤የምድር ወገብ የሚያክል ባንዲራ ያሸክምና በግሩ ፈንጅ ያስጠርገዋል፤
ካርታ በመሳል ሰመመን ጦዘው የሚውሉ አሉላችሁ ደግሞ፤ ድሮ አገር ለመያዝ ያማረው ብዙ ድካም ነበረበት፤ ፈረስ መግዛት ፤ጭፍራ ማደራጀት፤ ግብር ማብላት፤ መድማት መራብ መጠማት እንቅልፍህን እና ህይወትህን መሰዋት ይጠበቅበት ነበር፤ አሁን አገር ማቅናት አልጋ ላይ ተንበልብሎ ላፕታፕ ላይ ካርታ ከመሳል አያልፍም፤ እያንዳንዱ ጎራ የሚስለው ካርታ አንድ የሚያስቅ ተመሳሳይነት አለው፤ ወደ አጎራባች ባህር ወይም ክልል ዘልቆ የሚገባ ሾጠጥ ያለ ነገር አለው፤ያ ሾጣጣ ነገር ያባት አገር ብልት ይሆን? ለማንኛውም ካርታ ስንስል ፤ ጊዜው፤ የመነጋገር፤ የማሽኮርመም፤በፍቅር የመማረክ እንጂ አስገድዶ መድፈር እንዳልሆነ እናስብ፤
የለማ ቡድን የፍቅር የትህትናንና የታታሪነትን ዋጋ ለማሳየት የሚያደርገው ሙከራ የሚደነቅ ነው፤ ግን ሌላው ተምሳሌትነቱን ካልተከተለው በቀር፤ ለውጥ አይታሰብም፤ አሁን አሁን፤ ተምሳሌትነት አጠገብ ቆሞ ፎቶ መነሳት እንጂ ተምሳሌትነትን መከተል ብዙ አይታይም፤
እዚህ ላይ የቀበጢቱ ታሪክ ትዝ አለኝ፤
አንዲት ከመዘነጥና ሞባይሉዋን እንደ ልጅ ራስ ከመደባበስ ውጭ፤ ስራ በደረሰበት የማትደርስ ቀበጥ ልጅ ነበረች፤ታላቅ ወንድሙዋ እና እናቱዋ የልጂት ባህርይ አሳሰባቸው፤ እስቲ ስራ እንድትለምድ አንድ ነገር እናድርግ ተባባሉ፤ለምን አርአያ ሆነን አናሳያትም? ያኔ ህሊናዋ ወቅሱዋት መስራት ትጀምራለች ብለው እቅድ ነደፉ፤
አንድ ማለዳ ላይ፤ ቀበጢት መስታወት ፊት ቆማ ፤ፊትዋን በፓውደር ስትጠበጥብ ፤ እናት አጠገቡዋ ያለውን ወለል መጥረግ ጀመሩ፤ ልጅ እየሮጠ ደረሰና “ እማየ እኔ እያለሁማ በደካማ ጉልበትሽማ አትጠርጊም” ብሎ መጥረጊያውን ለመቀማት ይታገል ጀመር፤እናት በበኩላቸው “እኔ እናትህ ክንዴን ሳልንተራስማ አንተ አትጠርግም” ብለው መጥረጊያውን ሰንገው ያዙ፤በዚህ አይነት ሲፋለሙ ቀበጢቱ ፊትዋን ከመስታውቱ ሳትነቅል እንዲህ ስትል ተሰማች፤
“ሽሽሽሽሽሽስ ! እየረበሻችሁኝ ነው ተራ በተራ ጥረጉ!”
Bewketu Seyoum
Bewketu Seyoum
Saturday, 4 August 2018
Thursday, 2 August 2018
Tuesday, 31 July 2018
አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም
አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ህልፈተ ህይወቱን ሰማን፡፡ በበርካታ የኪነጥበብ ስራዎቹ የምናውቀው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በወሎ ሲሪንቃ ቅድስት አርሴማ ፀበል ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ አመሻሽ ለይ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡
Monday, 30 July 2018
በእውቀቱ ስዩም
ባገራችን ባሁኑ ጊዜ ብዙ ተከታይ ያለው ሃይማኖት ብሄርተኝነት ይባላል፡፡የብሄርተኝነት ምእመን ከሆንክ የነፍስ አባት ይኖርሀል፣በጭፍን የምትቀበለው ቀኖና ይኖርሀል፣ነገ የምትገባባት የተስፋ ምድር ይኖርሀል፣ከሁሉ በላይ ደግሞ ብርቱ ችግርህን የምትደፈድፍበት የመስዋእት በግ ይኖርሀል፡፡
ሃይማኖቶች ምእመናንን ብቻ ሳይሆን መናፍቃንንም ያፈራሉ፡፡ብሄርተኞች በስሜት የሚነድደውን ምእመን ብቻ ሳይሆን የኔ ቢጤውን መነፍቅም እንደሚያፈሩ አንርሳ፡፡በነገራችን ላይ ሃይማኖትን መካድ ማለት ሃይማኖት የሚያነሳቸውን አብይ ጥያቄዎች መካድ ማለት አይደለም፡፡እንዲሁም፣ ብሄርተኝነትን መካድ ማለት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ህልውና መካድ ማለት አይደለም፡፡በዚህ ጉዳይ ፣መናፍቅ መሆን ማለት፣ የብሄርተኛ ነቢያት ሰለ ጭቆና ስለ ነጻነት ብሎም ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀርቡትን አጉል እምነት መጠራጠር ማለት ነው፡፡
ከኢትዮጵያዊነት እንጀምር
ከዘመናችን የብሔርተኝነት ነቢያት አንዱ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ከእንቁ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ላይ ስለኢትዮጵያዊነት የሚከተለውን ይላል፡፡
‹‹…ኢትዮጵያን የመሠረታት የሶሰትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡በአማራው፣በኦሮሞው፣በትግሬው ግብግብ ውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡በዚህ የተነሳ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭት እና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡…የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት የምንለው የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው››
ጃዋር የኢትዮጵያን መሠረት የሦስት ብሄረሰቦች የስልጣን ግብግብ አድርጎ ወስኖታል፡፡ በመጀመርያ፣ ሌሎች ብሄረሰቦች በግብግቡ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አድርጎ ማቅረቡ አንድ ጉድለት ነው፡፡ ግን ዋናው ቁምነገር ይሄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የግጭት ውጤት ብቻ እንደሆነች አድርጎ ማቅረቡ ነው ትልቁ ስሕተት፡፡ ሲጀምር፣ የግብግብ ታሪክ መሠረት ይንዳል እንጂ መሠረት አይገነባም፡፡ እንደኔ ግምት፣የኢትዮጵያ መሠረት የሆነው ብሄረሰቦች ለጋራ ሕልውና ሲሉ የሚያደርጉት የመደጋገፍ ታሪክ ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ፣ ታሪክ ከላሾች፣የብሄሮችን የ‹‹ግብግብ››ታሪክ ሞቅ አድርገው፣አኳሽተው ሲጽፉ፣የብሄሮች መደጋገፍ ታሪክን ግን ቸል ይሉታል፡፡ አለያም እጅግ በቀዘቀዘ ስሜት፣ በጥቂት መስመሮች ብቻ ጨረፍ አድርገው ያልፉታል፡፡ለነገሩ፣ከፋፋይነትን ብቸኛ ያስተዳደር ፈሊጥ አድርጎ የሚቆጥር ሰው በታሪክ ገጾች ውስጥ መመልከት የሚፈልገው ክፍፍልን ብቻ ነው፡፡ታሪክ ግን ብዙ በጎ የትብብር ገጠመኞችን መዝግቧል፡፡ለምሳሌ ጀግናው አጼ ዮሐንስ አራተኛ በበዛሬይቱ ኤርትራ የግብጽን ወራሪ ጦር ድል የነሡት የትግራይ ጀግኖችን ብቻ አሠልፈው አልነበረም፡፡ በዚህ ጦርነት ከግብጽ ጎን ሆኖ፣የተዋጋው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይ እንደመሠከረው ወልቃይቶች፣ጥልጣል የተባሉ የአፋር ንኡስ ክፍሎች፣የወረኢሉ ኦሮሞዎች ለንጉሰነገስቱ ድጋፍ ለማድረግ ተሸቀዳድመዋል፡፡በራስ ወሌ የሚመሩ የአማራ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡የጎንደር ቀሳውስት ለጦርነቱ ድጋፍ ለማድረግ አድዋ ገብተዋል፡፡ የጎጃሙ ራስ አዳል የደርሼልሀለሁ አለኝታቸውን አሳይተዋል፡፡ የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ሳይቀር በመቶ የሚቆጠሩ በቅሎዎችንና ማበረታቻ ልከዋል፡፡ ዝርዝሩን ማንበብ ለሚፈልግ Muslim Egypt Christian Abyssinia የተባለውን የዚህ ደራሲ ማስታወሻ ገጽ 291-292 ያንብብ፡፡ መጽሐፉን በኢንተርኔት ቤተ-መጻህፍት ውስጥ በብላሽ ማግኘት ይቻላል፡፡
ከተለያየ መአዘን የመጡ እኒህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ቃላት ይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደ አረቄ ይወጣል፡፡ ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹‹የአማራ ባህል ››ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለው አይመስለኝም፡፡
ጃዋር‹‹አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭትና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች›› በማለት ሳይወሰን ‹‹የኢትዮጵያ አገራዊ መለያ ማንነት የምንለው አማራ ብሄራዊ ማንነት ነው›› ሲል ይጨምራል፡፡ ጎበዝ ኧረ በህግ አምላክ!!! የኢትዮጵያ ባህልኮ ካንድ አለት የተጠረበ ሕንጻ አይደለም፡፡ ከብዙ የመዋጮ ጡቦች የተገነባ ነው፡፡ ጃዋር እያንዳንዱን ጡብ ቀርቦ ቢመረምረው እዚህ የደረሰበት እርግጠኝነት ውስጥ የሚደርስ አይመስለኝም፡፡
እስቲ ከደቃቅ ምሳሌ እንጀምር፡፡ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡና ስነ-ስራታችን ነው፡፡ አንዲት ጠይም ፣ባለሹርባ ሴት፣ያበሻ ቀሚስ ለብሳ ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስል በየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ይህ ችክ ያለ ምስል በስነ-ስእል ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ቢዮንሴና ጆን ኬሪ አገራችንን በጎበኙበት ሰአት የቡና ስነስርአት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡና ስርአታችንን እንደ ኢትዮጵየዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው፡፡ ለዋለልኝ መኮንን እና ለጃዋር መሀመድ ይህ የአማራ ባህል መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ እይታ ይመስላል፡፡ ጉዱ ዝርዝሩ ላይ ነው፡፡ የሴትዮዋ ሹርባ ከሐማሴን ወይም ከተንቤን ሴቶች ልማድ ጋር ስምም ነው፡፡ ያበሻ ቀሚሱን የሽሮሜዳ ጋሞ የሸመነው ሊሆን ይችላል፡፡ ጀበናው የጂማ ሙስሊም ኦሮሞዎች ያስተዋወቁት ነው፡፡ አቦል ቶና በረካ አረብኛ ወይም የተወላገደ አረብኛ የተገኙ ቃላት ናቸው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ትንሳኤ በአል በሉባንጃ የሚታጀብ ቡና የማያፈላ ክርስትያን ኢትዮጵያዊ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ከጥቂት መቶ አመታት በፊት ግን ቡና የእስላም ልማድ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ የቡና ትርኢት የሙስሊም አበው በኢትዮጵያ ባህል ላይ የጨመሩት በጎ መዋጮ እድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ጊዜ በተባለው አናጢ ከብዙ ጡቦች የተገነባች ናት የምንለው ለዚህ ነው፡፡
ጃዋር አማራው የራሱን ባህል በኦሮሞው ላይ እንደጫነ ሲያምን ተገላቢጦሹ ያለው አይታየውም፡፡ ኦሮሞ በረጅም ዘመን፣በሠፊ ምድር፣ ሰፍሮ የመኖሩን ያክል በጎረቤቶቹና በወደረኞቹ ላይ የባህል ተጽእኖ አላሳደረም ማለት ብርቱ ባህል የለውም ከማለት አይለይም፡፡ ባገራችን ዋና ዋናዎቹ የባህል ቀራጺዎች ጦርነትና ሐይማኖት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፣ጀግኖችን እና ነገስታትን አባ በዝብዝ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኘው አባ ነጋ ወዘተ እያሉ መሰየም ገናና ኢትዮጵያዊ ባህል መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ብዙዎቻችን የማናውቀው ይህንን ባህል ያስተዋወቁት ለግማሽ ምእተአመት ያክል ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ቼ በለው በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እንዲህ በማለት ያረጋግጣሉ- ‹‹ነገስታቱ በ‹‹አባ›› ወይም የእገሌ ባለቤት በሚል ቅጽል ስም መጥራት የጀመሩት የኦሮሞዎችን ወይም የወረሸሆችን ልምድ በመከተል ነው ከ1838 ዓም ወዲህ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ወትሮ ግን በተለይም 1474-1713 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ቅብዓ መንግሥቱ በሚደረግላቸው ሰአት ይወጣላችው የነበረው የግርማ ስም ወይም ስመ መንግስት ‹‹ሰገድ›› የሚል ኃይለቃል በመጨመር እንደነበር ቀጥሎ ያለው ያረጋግጣል፡፡ ወናገድ ሰገድ፣ አጽናፍ ሰገድ፣ አድማስ ሰገድ፣ መለክ ሰገድ፣አድያም ሰገድ ሉል ሰገድ››በማለት ይዘረዝራሉ፡፡
ከጥቅሱ ሦስት ፍሬ ነገሮችን መረዳት ይቻላል፡፡
1- ይህ ባህል ባንድ የዘመን ምዕራፍ ላይ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የመነጨ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡
2- ባህሉ ብርቱ ተጽእኖ ከመፍጠሩ የተነሳ አማራና ትግራይ ነገስታት ለረጅም ዘመን ይጠቀሙበት የነበረውን የስያሜ ዘይቤ ሽሯል፡፡
3- አማራው ታሪክ ጸሀፊ ለባህሉ አስተዋዋቂዎች የባለቤትነት እውቅና ሰጥተዋል፡፡
በሃይማኖት ረገድም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚገጥመን፡፡ ለምሳሌ አቴቴ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድ ሲተረጉሙ ‹‹ዛር፣በሴት ስም የምትጠራ፣ ውቃቤ ፣ አማሮች ከኦሮሞዎች የወረሷት ጨሌ የሚያጠልቁላት አቴቴ ጊንቢ ሐራ አቴቴ ዱላ እያሉ እንቀት የሚቀቅሉላት አምልኮ ባእድ፣ትርጓሜ ጠባቂ ማለት ነው››ይላሉ፡፡
‹‹አምልኮ ባእድ ››የሚለውን አሉታዊ ሐረግ፣የክርስትያን አድልኦ ያለበት ፍርድ አድርገን እንለፈው፡፡ ዋናው ፍሬ ነገር፣ የአሮሞው ባህል በአማራው ባህል ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ማወቃችን ነው፡፡ ይህም አንዱ ብሄረሰብ ሁልጊዜ ጫኝ ፣ ሌላው ብሄረሰብ ሁልጊዜ ተሸካሚ እንደነበረ አድርገው ሊነግሩን የሚፈልጉትን ሰዎች ያስተባብላል፡፡ በሁለቱ ግዙፍ ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ግኑኝነት የእኩዮች ልውውጥ ነው፡፡ የባህሎች ውርርስ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ የማንኩሳ ዘመዶቼ የሚያስደነግጥ ነገር ሲገጥማቸው ‹‹አቲቲን ወሰድከው›› ይላሉ፡፡ ቀልቤን ገፈፍከው ለማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ባህላዊ ተጽእኖ በወለጋ ድንበር ላይ ቆሟል ያለው ማነው?
ስለጉዲፈቻ ባህል ብዙ ሰዉ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ በጦርነት ወቅት ምርኮኞችን ባርያ ማድረግ ወይም መግደል በብዙ ማህበረሰቦች የተለመደ ነው፡፡ በኦሮሞ አበዋዊ ባህል ውስጥ ግን ምርኮኞች በልጅነት ይታቀፋሉ፡፡ ከሌላ ብሄረሰብ ቢመጡም የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚያገኘውን መብት ሳይነፈጋቸው ያድጋሉ፡፡ ይህንን ልማድ በአማራው ማህበረሰብ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በጎጃሙ ንጎስ ተክለይማኖትና በወለጋ መሳፍንት መሀል በተደረገው ጦርነት የተማረከው ብላቴና ነገሮ ዋቅጅራን እንደልጅ አሳድገውታል፡፡ ክርስትና አስነስተው ተክለኢየሱስ አሰኝተውታል፡፡ ራሱ በጻፈው ማስታወሻ ‹‹በጠጅና በስጋ አደግሁ›› በማለት የመሳፍንት ልጆች ያገኙት የነበረውን ምቾት ሳይነፈገው ማደጉን ይመሰክራል፡፡ ነገሮ ፣ ከማእረግ ወደ ማእረግ እየወጣ የንጉሱ ጸሐፌ ትዝዛዝ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ተመሳሳይ መልኩ በሸዋ ምርኮኛው ቆሴ ዲነግዴ በቤተመንግስት እየተቀማጠለ አድጎ ሐብተጊዎርጊስ በሚል ስመ ክርስትና የኢትዮጵያ የጦር ምኒስትር እስከመሆን ደርሷል፡፡ ሰዎችን በልዩ ቋንቋቸው ምክንያት ባይተዋር ማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህል አልነበረም፡፡ እኩዋን ባህላችን አማርኛችን እንኳ የጉራማይሌነታችን ምስክር ነው፡፡ አሁን ኦሮምኛ ያልተነካካ አማርኛ ማግኘት ይቻላል?፡፡ እሰቲ ለናሙና ያክል ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› ከተባለው የዮሐንስ አድማሱ ምርጥ የአማርኛ ግጥም ውስጥ ጥቂት መስመሮች ልቆንጥር፡፡
1) ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ
2) ሜዳና ተራራ በመሐል ሸለቆ ጨፌውና መስኩ በኒህ ተደብቆ
3) ሐቀኛ ጠፍቶበት በዋለበት መልቲ ጌጥ ነው ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ
4) ብልጭ ብሎ ጠፋ ተወርዋሪ ኮከብ የሐሳብ አንጋፋ በመረጥኳቸው መስመሮች ውስጥ የሚገኙት ‹‹ይፋ፣ ጨፌ፣ መልቲ፣ ሎቲ፣ አንጋፋ፣›› የተባሉት ቃላት ኦሮሚኛ ናቸው፡፡ ካንድ የአማርኛ ግጥም ይህን ያህል ኦሮሚኛ ከተገኘ በሙሉ መዝገበ ቃላት ውስጥ ምን ያህል ሊገኝ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህን ያክል ነው የተዋሀድነው፡፡
የኢትዮጵያ ባህል የተውጣጣ ባህል እንጂ ጃዋር እንደሚለው የአማራ ባህል ብቻ አለመሆኑን በመጠኑም ቢሆን ያሳየሁ ይመስለኛል፡፡ ጃዋርን እዚህ ላይ ላሰናብትና ለማጠናቀቂያ የምትሆን አንዲት አንቀጽ ልጨምር፡፡
ባህልን ማክበር ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በስሜት ሚነድደው የብሄርብሄረሰብ ፖለቲካችን፣ ዜጎች ለባህል ያላቸውን ፍቅር ወደ ጭፍን አምልኮአዊ ፍቅር እያዘቀጠው ነው፡፡
ባባቶቻችንና በእኛ መካከል የባህል ፋይዳ ልዩነት ያለ ይመስለኛል፡፡ አባቶች ባህላቸውን ያገኙት በኑሮ ጣጣ አስገዳጅነት ነው፡፡ ለምሳሌ የኔ አያት ቁምጣ ሱሪ የሚታጠቀው ከሌሎች ብሄረሰቦች ለየት ብሎ ለመታየት አይመሰለኝም፡፡ በቂ አቡጀዲ ስላላገኘ ነው፡፡ ወይም ለስራ እንዲያመቸው ባጭር መታጠቁ ይሆናል፡፡ እኔ ግን የብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ቁምጣ ለብሼ ራሴን በማስጎብኘት እንድኮራ ይጠበቅብኛል፡፡ ጉድ እኮ ነው!!! ጋቢ በጥንት ጊዜ የሙቀት ምንጭ ነበር፡፡ ዘንድሮ የኩራት ምንጭ ሊሆን ይቃጣዋል፡፡
የዛሬዎቹ ባህል አምላኪዎች ባህል ሲያስቡ ለውጥን ይረሳሉ፡፡ ባንድ ወቅት የሚያኮራው ያንድ ብሄረሰብ ባህል በሌላው ወቅት ይናቃል፡፡ ባንድ ወቅት የሚያስሸልመው በሌላ ጊዜ ያስቀጣል፡፡ ከጥቂት መቶ አመት በፊት ዝሆን መግደል በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የሚያጎናጽፍ ተግባር ነበር፡፡ ዝሆን የገደለ ልዩ አምባር ክንዱ ላይ ያጠልቃል፡፡ እስኪ ዛሬ ያባቶቼን ባህል ለማክበር ነው ብለህ ፓርክ ውስጥ አርፎ የተኛውን ዝሆን ግደል፡፡ በአምባር ምትክ ካቴና ይጠልቅልሀል፡፡
የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት የተባለውን የተደጋገመ ግን ያልታሰበበት ቃል ከዚህ አንጻር ቃኙት፡፡ ሲጀምር ፣ዛፍ እንኳ ቅርፊቱን በሚቀያይርበት ዓለም፣ብሄር ብሄረሰቦች በየጊዜው አልባሳታቸውን አይቀያይሩም ወይ?፡፡ የብሄረሰቡ አልባስ ሲባል በየትኛው ዘመን የሚለበሰው ነው? የእንዳለጌታ ከበደ እናት ሲነግሩን፣ ዛሬ በጉራጌ ዘፈን ላይ በቲቪ የምናየው የሴቶች ሻማ ቀሚስ በደርግ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ሸማ ነው፡፡ ከሸማው በፊት ደግሞ የቆዳ ቀሚስ ይለበስ ነበር፡፡
ሌላው፣ አንድ ማህበረሰብ አልባሳት በየማእረጉ ልዩ ልዩ ልብሶች ይኖሩታል፡፡ ወታደሩ ያባ ገዳውን ልብስ የሚለብስ አይመስለኝም፡፡ ባሮች ከጌቶች ልብስ ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንዲለብሱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ በፊውዳል ማህበረሰብ ከላይ አስከታች መልበስ መከናነብ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ ይህንን በሸዋና በትግራይ ብቻ ሳይሆን በቅድመ ምኒልክ ከፋ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ባንጻሩ፣ባሮች በከፊል ተራቁተው መታየት አለባቸው፡፡ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አለባበስ በበሄረሰብ ላይ ሳይሆን በመደብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ የብሄር አልባሳት የሚባለው እንደ ማንኛውም ሾላ በድፍን ሐሳብ በጥርጣሬ መታየት አለበት፡፡
ትውልዱ የባህል ፈጣሪ መሆን ሲገባው፣የባህል ሙዚየም ሆኖ ተተክሏል፡፡አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ባንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ካባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ፣ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል››
ማሳረጊያ
ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ያቆያት የነገስታቱ ጉልበት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያ የተሸመነችበትን ውስብስብ ክር ማየት ያልታደሉ ናቸው፡፡ዛሬ ኢትዮጵያን በታትነን ክልላችንን እናድናለን ብለው ባደባባይ ሳያፍሩ የሚናገሩ ሰዎችን የምናይበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ ማእበል ከበረታባት እንደ ታይታኒክ ትሰጥም ይሆናል፡፡ግን መርከቢቱ ስትሰጥም የመርከቢቱ ሳሎን ብቻውን አይንሳፈፍም፡፡የመርከቢቱ ጓዳ ብቻውን አይተርፍም፡፡ኢትዮጵያ ስትከስም ብሄሮች ተነጥለው ይለመልማሉ ማለት ተፈጥሮ አመሏን እንደ ግትቻ የትም ጥላለች ማለት ነው፡፡
Friday, 27 July 2018
Thursday, 26 July 2018
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል። ያልታደለች ሀገር… ዕንቁ ኢንጅነሯን አጣች፡፡ የገዳዮች ማንነትና ከገዳዮች ጀርባ ማን እንዳለ ባይረጋገጥም…. በሰው እጅ እንደተገደሉ ግን ታውቋል፡፡ የሸሚዝ ኮሌታቸው ተቀዶ በግራ ጆሯቸው እየደሙ እንዳዩአቸው እማኞች ተናግረዋል። ከሕሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ብዙ ምሥጢር ስለያዘ ግድያው ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ኢንጅነሩ ሁሌም ለገብርኤል በዓል… በዓልይ ንግሥ ሲሆን ግቢ ገብርኤል ያስቀድሳሉ። እኔም ሁለት ጊዜ በዓይኔ አይቻቸዋለሁ። ዛሬም የተገደሉት ወደ ገብርኤል ንግሥ እየሄዱ ሳለ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ለንግሥ እንደማይቀሩ ይታወቃልና።
ትጉሁ ሰው፣ ጠቢቡ መሐንዲስ፣ ትሁቱ ክርስቲያን ኢንጅነር ስመኘው ሞቱ ሲባል ሰማይ ምድሩ ነው የዞረብኝ። በአካል ከ4 ጊዜ በላይ አግኝቻቸዋለሁ። ፈገግታ የማይለያቸው ትሁት ሰው ናቸው። እና ሞቱ? እኔ አላምንም። እንባየን ማቆም አልቻልሁም።
የበረሃው ትጉህ ሰው ሞቱ። “የሕዳሴው ግድብ እንዳለቀ ብሞት አይቆጨኝም” ይሉ የነበሩት ተስፈኛ መሐል ላይ ቀሩ። “ይህ ግድብ የቀደሙ አባቶቻችን ድል ማስታወሻ ነው። አድዋ ላይ ሞተው የቀሩህ ጀግኖች ሕይወት ማስታወሻ ነው። እነርሱ የሞቱት ልጆቻቸው ይህን መሰል ታሪክ እንድንሰራ ነው። ይህ እንደ አድዋ ሕዝቡን በአንድነት ያዘመተ ታሪክ ነው።” እያሉ ሕዝቡን ያጽናኑ የነበሩት ባለ ብሩህ አእምሮውና ትሁት ሰብዕናን የተላበሱት ጀግና በጨካኞች ሞቱ። ምን አይነት አረመኔነት ይሆን? እንዴት ያለ ጭካኔ የተላበሰ ሰወ በላ በእኝህ ዕንቁ ሰው ላይ ሞት ፈረደ??? ያማል። የምር ያማል።
Tuesday, 24 July 2018
የበቅሎዋ ጥያቄ
አንዲት ግልገል በቅሎ እናቷን እንዲህ ብላ ጠየቀቻት፡፡
‹‹እማዬ እኔ ግን ማነኝ››
እናቷም ገረማትና ‹አንቺማ በቅሎ ነሽ፤ ግን ለምን ጠየቅሽኝ››
ግልገሏም ጥቂት ጊዜ ዝም ብላ ከቆየች በኋላ፤ ‹‹መጀመሪያ ግን አህያ
ነበርኩ ወይስ ፈረስ›› አለቻት፡፡ እናቲቱምአንገቷን ነቅንቃ ‹‹እንስሳ ነሽ ልጄ፤ እንስሳ፡፡ ፈረስም አህያም እንስሳ ነው፡፡ ስንፈጠር እንስሳ ነበርን፡፡ የቤት የዱር፣ የሸክም የግልቢያ፣ የእርሻ የሜዳ፣ የንጉሥ የባሪያ የሚለው በኋላ የመጣ ነው፡፡ አዳምኮ ሲፈጠር ቤት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የቤት እንስሳ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ሁላችንም ይህቺን ምድር እንደልባችን እንጠቀምባት ነበር፡፡ ነገር የመጣው በኋላ ነው፡፡ ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው ይህንን አሁን ያለንበትን ሁኔታ የፈጠረው፡፡››
‹‹ጓደኛዬ የአንቺ አያቶች ጨቁነውናል አለኝ፡፡››
‹‹እንዴት አድርገው ነው የጨቆኑት፤ ለመሆኑስ የአንቺ አያቶች ስንት ናቸው?
እርሱ የተነገረውን ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ያልተነገረውስ? ከታሪካችንኮ በጣም ጥቂቱ ነው የተጻፈው፤ ከተጻፈውም በጣም ጥቂቱ ነው የተነገረው፡፡ ባልተጻፈው ታሪካችን ውስጥ ማን ምን እንደነበረ ማን ያውቃል?
ለምሳሌ በሀገረ እሥራኤል አህዮች እጅግ የሚወደዱ የቤት እንስሳት ነበሩ፡፡ ነገሥታቱም፣ ካህናቱም፣ ነብያቱም ዘመኑ ዘመነ ሰላም ሲሆን በአህያ ነው ይሄዱ የነበሩት፡፡ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በአህያ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ወደ ግብጽ የተሰደደችው በአህያ ነው፡፡ በጥንታውያን ግብጾች ዘንድ አህያ የመኳንንትና የነገሥታት ሀብት ማሳያ ነበር፡፡ የናርማር ወይም የሖር – አሃመቃብር እንደሆነ በሚታመነው ቦታ ላይ በተደረገ ቁፋሮ አህዮች ከነገሥታቱ ጋር በክብር ተቀብረው ተገኝተዋል፡፡ በዚያ ጊዜ አህዮች የቤተ መንግሥቱን ምግብ እየተመገቡ፣ በቤተ መንግሥቱም እየተሸለሙ ኖረዋል፡፡ በሌላው ዘመን ደግሞ ይህንን ፈረሶቹ ወስደውታል፡፡››
‹‹ወደኋላ ተመልሰሽ ሁሉን እንስሳት ብታያቸው ታሪካቸው እንደዚሁ ነው ልጄ፡፡ በዘርሽ አትጨቁኝም፤ በዘርሽም አትጨቆኝም፡፡ የጭቆና መሠረቱ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ አቤልን የገደለውኮ ቃየል ነው፡፡ የአንድ ማኅፀን ልጆች ናቸውኮ፡፡ ቃየል አቤልን የገደለው ለጥቅም ሲል ነው፡፡ እስኪ የሰዎችን ታሪክ እይው አፍሪካውያንኮ በራሳቸው በአፍሪካውያን ይጨቆኑ ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ሰው መሰሎቹን ይሰበስብና ሌሎቹን የሀገሩን ልጆች ይጨቁናል፡፡ መጀመሪያ የገዛ ወገኖቻቸውን ለዐረቦች በባርነት ሲሸጡ የነበሩት የሀገራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አፍሪካውያን በባርነት ተሽጠው አሜሪካ ሲሄዱ ደግሞ ነጮቹ ጥቁሮቹን መጨቆን ጀመሩ፡፡ አየርላንዳውያን በእንግሊዞች መከራቸውን አይተዋል፡፡ ዓረቦች በዓረቦች ተሰቃይተዋል፡፡ አየሽ ቤተ መንግሥቱ ላይ ስትቀመጭ ሌላውን ለማግለል ሳጥን ትከፍቻለሽ፤ ከዚያ ሁሉንም በየሳጥኑ ታስቀምጭዋለሽ፡፡
የእምነት፣ የዘር፣ የመልክ፣ የአካባቢ፣ የቋንቋ ሳጥኖችን ከፍተው ሁሉንም እዚያ ስላስቀመጧቸው ተቀማጮቹ ሳጥኑን እንዳለ ተቀበሉት፡፡ ማንነታቸውም አደረጉትና ሳጥኑን ለማስቀረት ከመታገል ይልቅ ራሳቸውን ብቻ ከሳጥኑ ለማውጣት ይታገሉ ነበር፡፡ በሳጥኑ ዛሬ አህዮች ይገቡበታል፤ ነገ ፈረሶች፣ ከነገ ወዲያ ግመሎች፣ ከዚያም በጎች፣ ከዚያም ፍየሎች እየገቡበት ይቀጥላል፡፡ እኛም ዛሬ ያለሳጥን መኖር ከማንችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ እኔን ሲያገኙኝ እንስሳ መሆኔን አይደለም የሚያዩት፤ የትኛው እንስሳ? ይላሉ፡፡ – ፈረስ፡፡ በዚህ አያቆሙም፡፡ ከዚያ ደግሞ የትኛው ፈረስ? የዱር ወይስ የቤት? ይቀጥላል፡፡ -የቤት፡፡ ለጭነት ወይስ ለግልቢያ? መቋጫ የለውም ልጄ፡፡ በትልቁ ሳጥን ውስጥ ራሳችን የሠራናቸው ትንንሽ ሳጥኖችም አሉ፡፡ በእነዚያም ውስጥ ሌሎች ትንንሽ ሳጥኖች አሉ፡፡››
‹‹ ለአንድ የገጠር ጉዞ በእኔ ላይ ይሄድ የነበረ አንድ ሰው ሲናገረው የሰማሁትን ታሪክ ልንገርሽ፡፡ ሰውዬው የከባድ መኪና ሾፌር ነበረ፡፡ ድሮ አሰብ እየተመላለሰ ዕቃ ይጭን ነበር፤ አንድ ጊዜ ወደ አሰብ ሲሄድ በረሃው ላይ መኪናው ይበላሽበታል፡፡ ከዚያም እዚያው ማደር ስለነበረበት ለምግቡ የሚሆን ፍየል ከአካባቢው የአፋር ሰው ይገዛል፡፡ አፋሩ ሰውዬው ፍየሏን መሸጥ ብቻ ሳይሆን አርዶ፣ ጠብሶ ያቀርብለታል፡፡ ሾፌሩ ምግቡን እየበላ የሸጠለትን የአፋር ሰው ‹‹እንግዲህ ትቼህ መብላቴ ነው፤ እንብላ እንዳልልህ የክርስቲያን ሥጋ አትበላም ብዬ ነው›› ይለዋል፡፡ አፋሩ ሰውዬ ይገርመውና ‹‹እኔው አዋልጄ፣ እኔው አሳድጌ፣ እኔው አርጄ፣ እኔው ጠብሼ ያመጣኋትን ፍየል ምንጊዜ ክርስቲያን አደረግካት?›› አለኝ ብሎ ሲያወራ ሰማሁት፡፡ አየሽ ሌላን ማግለል ስትፈልጊ የሆነ ነገር ትፈጥሪያለሽ፡፡ ማቅረብም ስትፈልጊ እንደዚያው፡፡› ‹‹ብዙ ዓይነት ነጻ አውጭዎች አሉ፡፡ እኔ አሁን የፈረስ ነጻ አውጭ ውስጥ ልግባ ወይስ የአህያ? ወይስ የበቅሎ?›› አለቻት ግልገሏ፡፡ ‹‹የእንስሳት ነጻ አውጭ ካለ እዚያ ግቢ፡፡ አንቺ እንስሳ ነሽ፡፡ የቀረው ከመኖር የመጣ ስም ነው፡፡ እንስሳት ሁሉ ነጻ ሳይሆኑ በቅሎ ተለይታ ነጻ ልትሆን አትችልም፡፡ አንድን አካባቢ ብቻውን ንጹሕ ማድረግ አትችይም፡፡ ምክንቱም ዝንቧ ከወዲያኛው ማዶ ትመጣለችና፡፡ ከእኛም ወገኖችኮ ሜዳ በመኖራቸው የተነሣ ‹የሜዳፈረስ›› ተብለው የቀሩ አሉ፡፡ እኛ ከሰው ተጠግተን ‹የቤት ፈረስ›› ለመሆን ቻልን፡፡ ‹‹የቤት አህዮች›› አሉ፡፡ ‹‹የሜዳ አህዮች››ም አሉ፡፡ የስም ጉዳይ ነው፡፡ የአኗኗር ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ መንግሥት ከነገሥታት ጋር የሚኖር አንበሳ ነበርኮ፡፡ የነገሥታቱ ዙፋን እንዲያውም የአንበሳ ቅርጽ ነበረው፡፡ በዚያው ዘመን ግን ንጉሡ ጫካ ወጥተው ሌላ አንበሳ ገድለው እየተዘፈነላቸው ይመጣሉ፡፡ ጀርባሽን ለመጋለብ ምቹ ካደረግሽው ምንጊዜም የተሻለ ተወዳጅ ትሆኛለሽ፡፡
እንግሊዞች ‹‹Better to ride on ass that carries me, than on a horse that throws me –
የምትገለብጠኝን ፈረስ ከምጋልብ፣የምትሸከመኝን አህያ ብጋልብ ይመረጣል›› ይላሉ፡፡ ቤት የቀረው ውሻ ዱር ከቀረው ውሻ ጋር በመለያየታቸው ዛሬ አንዱ አንዱን እንደ ጠላት ያባርረዋል፡፡ ሰው ብልጥ ነው፡፡ አንዱን ወደ ራሱ አቅርቦ ውሻ አደረገውና ‹‹ቦቢ›› እያለ በማቆላመጥ ነጻ የወጣ አስመሰለው፤ ሌላውን ደግሞ ቀበሮ፣ ተኩላ ብሎ ጫካ ተወውና እርሱን መግደል ጀግንነት እንዲሆን አደረገው፡፡ አሁን ውሾቹ የሠለጠኑና ነጻ የወጡ መስሏቸው ተኩላና ቀበሮ ሲያብርሩ ይኖራሉ፡፡ አየሽ ጉዳዩ የዘር አይደለም፡፡ በዘር ከሰው ተኩላ ለውሻ ይቀርበዋል፣ ቀበሮ ይዛመደዋል፡፡ ጉዳዩ የጥቅም ጉዳይ ነው፤ የመደብ ጉዳይ ነው፡፡ ከቀበሮውና ከተኩላው መካከል ደግሞ የተወሰነውን ይወስዱና ፓርክ ውስጥ አስገብተው ያለፈለት ያስመስሉታል፡፡ እርሱም ማግኘት የሚገባውን ሳይሆን ራሱን ከጫካው ኑሮ ጋር ስለሚያነጻጽር ‹ተመስገን› እያለ ይኖራል፡፡››
‹‹ነጻነት የፍጡር ሀብት ነው፡፡ ለእነ እገሌ ተብሎ የሚቆረስ አይደለም፡፡ ጨቋኙም ተጨቋኙም ነጻ ካልወጣ ሙሉ ነጻነት አይገኝም፡፡ ጨቋኝነት ከአስተሳሰብ ባርነት የሚመጣ ነው፡፡ ከአመለካከት ድህነት የሚከሰት ነው፡፡ ሙሉ ነጻነትን ለማግኘት እርሱን ነጻ ማውጣት አለብሽ፡፡ ካልሆነ ግን ጉዞው አንዱን ጨቋኝ በሌላ ጨቋኝ መተካት ነው የሚሆነው፡፡
( ኤነር ደብረ መንከራት ቅዱስ አማኑኤል ገዳም )
አንዲት ግልገል በቅሎ እናቷን እንዲህ ብላ ጠየቀቻት፡፡
‹‹እማዬ እኔ ግን ማነኝ››
እናቷም ገረማትና ‹አንቺማ በቅሎ ነሽ፤ ግን ለምን ጠየቅሽኝ››
ግልገሏም ጥቂት ጊዜ ዝም ብላ ከቆየች በኋላ፤ ‹‹መጀመሪያ ግን አህያ
ነበርኩ ወይስ ፈረስ›› አለቻት፡፡ እናቲቱምአንገቷን ነቅንቃ ‹‹እንስሳ ነሽ ልጄ፤ እንስሳ፡፡ ፈረስም አህያም እንስሳ ነው፡፡ ስንፈጠር እንስሳ ነበርን፡፡ የቤት የዱር፣ የሸክም የግልቢያ፣ የእርሻ የሜዳ፣ የንጉሥ የባሪያ የሚለው በኋላ የመጣ ነው፡፡ አዳምኮ ሲፈጠር ቤት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የቤት እንስሳ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ሁላችንም ይህቺን ምድር እንደልባችን እንጠቀምባት ነበር፡፡ ነገር የመጣው በኋላ ነው፡፡ ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው ይህንን አሁን ያለንበትን ሁኔታ የፈጠረው፡፡››
‹‹ጓደኛዬ የአንቺ አያቶች ጨቁነውናል አለኝ፡፡››
‹‹እንዴት አድርገው ነው የጨቆኑት፤ ለመሆኑስ የአንቺ አያቶች ስንት ናቸው?
እርሱ የተነገረውን ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ያልተነገረውስ? ከታሪካችንኮ በጣም ጥቂቱ ነው የተጻፈው፤ ከተጻፈውም በጣም ጥቂቱ ነው የተነገረው፡፡ ባልተጻፈው ታሪካችን ውስጥ ማን ምን እንደነበረ ማን ያውቃል?
ለምሳሌ በሀገረ እሥራኤል አህዮች እጅግ የሚወደዱ የቤት እንስሳት ነበሩ፡፡ ነገሥታቱም፣ ካህናቱም፣ ነብያቱም ዘመኑ ዘመነ ሰላም ሲሆን በአህያ ነው ይሄዱ የነበሩት፡፡ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በአህያ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ወደ ግብጽ የተሰደደችው በአህያ ነው፡፡ በጥንታውያን ግብጾች ዘንድ አህያ የመኳንንትና የነገሥታት ሀብት ማሳያ ነበር፡፡ የናርማር ወይም የሖር – አሃመቃብር እንደሆነ በሚታመነው ቦታ ላይ በተደረገ ቁፋሮ አህዮች ከነገሥታቱ ጋር በክብር ተቀብረው ተገኝተዋል፡፡ በዚያ ጊዜ አህዮች የቤተ መንግሥቱን ምግብ እየተመገቡ፣ በቤተ መንግሥቱም እየተሸለሙ ኖረዋል፡፡ በሌላው ዘመን ደግሞ ይህንን ፈረሶቹ ወስደውታል፡፡››
‹‹ወደኋላ ተመልሰሽ ሁሉን እንስሳት ብታያቸው ታሪካቸው እንደዚሁ ነው ልጄ፡፡ በዘርሽ አትጨቁኝም፤ በዘርሽም አትጨቆኝም፡፡ የጭቆና መሠረቱ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ አቤልን የገደለውኮ ቃየል ነው፡፡ የአንድ ማኅፀን ልጆች ናቸውኮ፡፡ ቃየል አቤልን የገደለው ለጥቅም ሲል ነው፡፡ እስኪ የሰዎችን ታሪክ እይው አፍሪካውያንኮ በራሳቸው በአፍሪካውያን ይጨቆኑ ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ሰው መሰሎቹን ይሰበስብና ሌሎቹን የሀገሩን ልጆች ይጨቁናል፡፡ መጀመሪያ የገዛ ወገኖቻቸውን ለዐረቦች በባርነት ሲሸጡ የነበሩት የሀገራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አፍሪካውያን በባርነት ተሽጠው አሜሪካ ሲሄዱ ደግሞ ነጮቹ ጥቁሮቹን መጨቆን ጀመሩ፡፡ አየርላንዳውያን በእንግሊዞች መከራቸውን አይተዋል፡፡ ዓረቦች በዓረቦች ተሰቃይተዋል፡፡ አየሽ ቤተ መንግሥቱ ላይ ስትቀመጭ ሌላውን ለማግለል ሳጥን ትከፍቻለሽ፤ ከዚያ ሁሉንም በየሳጥኑ ታስቀምጭዋለሽ፡፡
የእምነት፣ የዘር፣ የመልክ፣ የአካባቢ፣ የቋንቋ ሳጥኖችን ከፍተው ሁሉንም እዚያ ስላስቀመጧቸው ተቀማጮቹ ሳጥኑን እንዳለ ተቀበሉት፡፡ ማንነታቸውም አደረጉትና ሳጥኑን ለማስቀረት ከመታገል ይልቅ ራሳቸውን ብቻ ከሳጥኑ ለማውጣት ይታገሉ ነበር፡፡ በሳጥኑ ዛሬ አህዮች ይገቡበታል፤ ነገ ፈረሶች፣ ከነገ ወዲያ ግመሎች፣ ከዚያም በጎች፣ ከዚያም ፍየሎች እየገቡበት ይቀጥላል፡፡ እኛም ዛሬ ያለሳጥን መኖር ከማንችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ እኔን ሲያገኙኝ እንስሳ መሆኔን አይደለም የሚያዩት፤ የትኛው እንስሳ? ይላሉ፡፡ – ፈረስ፡፡ በዚህ አያቆሙም፡፡ ከዚያ ደግሞ የትኛው ፈረስ? የዱር ወይስ የቤት? ይቀጥላል፡፡ -የቤት፡፡ ለጭነት ወይስ ለግልቢያ? መቋጫ የለውም ልጄ፡፡ በትልቁ ሳጥን ውስጥ ራሳችን የሠራናቸው ትንንሽ ሳጥኖችም አሉ፡፡ በእነዚያም ውስጥ ሌሎች ትንንሽ ሳጥኖች አሉ፡፡››
‹‹ ለአንድ የገጠር ጉዞ በእኔ ላይ ይሄድ የነበረ አንድ ሰው ሲናገረው የሰማሁትን ታሪክ ልንገርሽ፡፡ ሰውዬው የከባድ መኪና ሾፌር ነበረ፡፡ ድሮ አሰብ እየተመላለሰ ዕቃ ይጭን ነበር፤ አንድ ጊዜ ወደ አሰብ ሲሄድ በረሃው ላይ መኪናው ይበላሽበታል፡፡ ከዚያም እዚያው ማደር ስለነበረበት ለምግቡ የሚሆን ፍየል ከአካባቢው የአፋር ሰው ይገዛል፡፡ አፋሩ ሰውዬው ፍየሏን መሸጥ ብቻ ሳይሆን አርዶ፣ ጠብሶ ያቀርብለታል፡፡ ሾፌሩ ምግቡን እየበላ የሸጠለትን የአፋር ሰው ‹‹እንግዲህ ትቼህ መብላቴ ነው፤ እንብላ እንዳልልህ የክርስቲያን ሥጋ አትበላም ብዬ ነው›› ይለዋል፡፡ አፋሩ ሰውዬ ይገርመውና ‹‹እኔው አዋልጄ፣ እኔው አሳድጌ፣ እኔው አርጄ፣ እኔው ጠብሼ ያመጣኋትን ፍየል ምንጊዜ ክርስቲያን አደረግካት?›› አለኝ ብሎ ሲያወራ ሰማሁት፡፡ አየሽ ሌላን ማግለል ስትፈልጊ የሆነ ነገር ትፈጥሪያለሽ፡፡ ማቅረብም ስትፈልጊ እንደዚያው፡፡› ‹‹ብዙ ዓይነት ነጻ አውጭዎች አሉ፡፡ እኔ አሁን የፈረስ ነጻ አውጭ ውስጥ ልግባ ወይስ የአህያ? ወይስ የበቅሎ?›› አለቻት ግልገሏ፡፡ ‹‹የእንስሳት ነጻ አውጭ ካለ እዚያ ግቢ፡፡ አንቺ እንስሳ ነሽ፡፡ የቀረው ከመኖር የመጣ ስም ነው፡፡ እንስሳት ሁሉ ነጻ ሳይሆኑ በቅሎ ተለይታ ነጻ ልትሆን አትችልም፡፡ አንድን አካባቢ ብቻውን ንጹሕ ማድረግ አትችይም፡፡ ምክንቱም ዝንቧ ከወዲያኛው ማዶ ትመጣለችና፡፡ ከእኛም ወገኖችኮ ሜዳ በመኖራቸው የተነሣ ‹የሜዳፈረስ›› ተብለው የቀሩ አሉ፡፡ እኛ ከሰው ተጠግተን ‹የቤት ፈረስ›› ለመሆን ቻልን፡፡ ‹‹የቤት አህዮች›› አሉ፡፡ ‹‹የሜዳ አህዮች››ም አሉ፡፡ የስም ጉዳይ ነው፡፡ የአኗኗር ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ መንግሥት ከነገሥታት ጋር የሚኖር አንበሳ ነበርኮ፡፡ የነገሥታቱ ዙፋን እንዲያውም የአንበሳ ቅርጽ ነበረው፡፡ በዚያው ዘመን ግን ንጉሡ ጫካ ወጥተው ሌላ አንበሳ ገድለው እየተዘፈነላቸው ይመጣሉ፡፡ ጀርባሽን ለመጋለብ ምቹ ካደረግሽው ምንጊዜም የተሻለ ተወዳጅ ትሆኛለሽ፡፡
እንግሊዞች ‹‹Better to ride on ass that carries me, than on a horse that throws me –
የምትገለብጠኝን ፈረስ ከምጋልብ፣የምትሸከመኝን አህያ ብጋልብ ይመረጣል›› ይላሉ፡፡ ቤት የቀረው ውሻ ዱር ከቀረው ውሻ ጋር በመለያየታቸው ዛሬ አንዱ አንዱን እንደ ጠላት ያባርረዋል፡፡ ሰው ብልጥ ነው፡፡ አንዱን ወደ ራሱ አቅርቦ ውሻ አደረገውና ‹‹ቦቢ›› እያለ በማቆላመጥ ነጻ የወጣ አስመሰለው፤ ሌላውን ደግሞ ቀበሮ፣ ተኩላ ብሎ ጫካ ተወውና እርሱን መግደል ጀግንነት እንዲሆን አደረገው፡፡ አሁን ውሾቹ የሠለጠኑና ነጻ የወጡ መስሏቸው ተኩላና ቀበሮ ሲያብርሩ ይኖራሉ፡፡ አየሽ ጉዳዩ የዘር አይደለም፡፡ በዘር ከሰው ተኩላ ለውሻ ይቀርበዋል፣ ቀበሮ ይዛመደዋል፡፡ ጉዳዩ የጥቅም ጉዳይ ነው፤ የመደብ ጉዳይ ነው፡፡ ከቀበሮውና ከተኩላው መካከል ደግሞ የተወሰነውን ይወስዱና ፓርክ ውስጥ አስገብተው ያለፈለት ያስመስሉታል፡፡ እርሱም ማግኘት የሚገባውን ሳይሆን ራሱን ከጫካው ኑሮ ጋር ስለሚያነጻጽር ‹ተመስገን› እያለ ይኖራል፡፡››
‹‹ነጻነት የፍጡር ሀብት ነው፡፡ ለእነ እገሌ ተብሎ የሚቆረስ አይደለም፡፡ ጨቋኙም ተጨቋኙም ነጻ ካልወጣ ሙሉ ነጻነት አይገኝም፡፡ ጨቋኝነት ከአስተሳሰብ ባርነት የሚመጣ ነው፡፡ ከአመለካከት ድህነት የሚከሰት ነው፡፡ ሙሉ ነጻነትን ለማግኘት እርሱን ነጻ ማውጣት አለብሽ፡፡ ካልሆነ ግን ጉዞው አንዱን ጨቋኝ በሌላ ጨቋኝ መተካት ነው የሚሆነው፡፡
( ኤነር ደብረ መንከራት ቅዱስ አማኑኤል ገዳም )
Subscribe to:
Posts (Atom)