
- ባለፈው ማክሰኞ ሌሊት ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በስተደቡብ የሚገኘው ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ በእስራኤል የሚሳይል ጥቃት እንደተፈጸመበት ከታወቀ በኋላ፣ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን ዜጎችና የፖለቲካ ተንታኞች እያስረዱ ነው፡፡
እስራኤል በዚህ እጅግ ሚስጥራዊ ነው በተባለለት ወታደራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ ላይ ጥቃቱን የፈጸመችው በቅርቡ በሒዝቦላህ የተላከባት ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (Drone) ግዛቷ ውስጥ መትታ ከጣለች በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሰው አልባው የጦር አውሮፕላን የተመረተው በካርቱም የጦር መሣርያ ፋብሪካ ውስጥ መሆኑን፣ በግብፅ በኩል ተጓጉዞ ለኢራን ከደረሰ በኋላ ሊባኖስ ውስጥ ለመሸገው ሒዝቦላህ መሰጠቱን መግለጻቸው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኅን ተገልጿል፡፡
ምንም እንኳን እስራኤል የጦር መሣርያ ፋብሪካውን በሚሳይል ማጥቃቷን በቀጥታ ባታስተባብልም፣ የሱዳን መንግሥት ከጠላቶቿ ጋር እያሴረባት መሆኑን ወታደራዊ ባለሥልጣናቷ እየገለጹ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ የሱዳን መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመችው እስራኤል መሆኑን አስታውቆ፣ ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እወስዳለሁ ብሏል፡፡ በተጨማሪም ለጥቃቱ አፀፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ዝቷል፡፡ የሱዳን መንግሥት የካርቱም የጦር መሣሪያ ፋብሪካው መደብደቡን ማረጋገጡ ለኢትዮጵያና ለአካባቢው አገሮች ጭምር ሥጋት መሆኑን የሚገልጹት ተንታኞች፣ በተለይ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥታ ልትከታተለው ይገባል ይላሉ፡፡

