<<ባለቤቴ ሁለቱም ወላጆቿ የወላይታ ብሄር ተወላጆች ናቸው :: ወላይታ ... በኤርትራ ክልል ውስጥ ነው ካልተባለ በቀር እኔም ባለቤቴም ወላይታና ኢትዮጵያዊያን ነን....>>
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ
ጥያቄ : - ክቡር ጠ /ሚኒስትር አቶ ኃ /ማሪያም አዲሱን ስልጣን እንዴት አዩት ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም : - እንግዲህ ከጌታ ጋር ሁሉንም ለመወጣት ተያይዘናል ያስጀመረን ጌታ ከግቡ ያደርሰናል የሚል ዕምነት አለኝ ::
ጥያቄ : - እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልፎ አልፎ በከባድ ጥበቃ እየታጀቡ ወደ ቤ /ክርስቲያን እንደሚሄዱ ባለቤቴ ትነገረኛለች :: ይህ እውነት ነው ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም : - አዎን ለእኔና ለቤተሰቤ መሰረታችን እምነታችን ስለሆነ የዘውትር ሕይወታችን በቤተክርስቲያን ዙሪያ ነው :: ጊዜ ሳገኝ አልፎ አልፎ እሁድን እንደምንም ቸርች ለመሄድ ጥረት አደርጋለሁ : ካልሆነም ቄሶችና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እኛ ቤት ድረስ እየመጡ የጌታን ቃል ያካፍሉናል :: በቤታችን ውስጥ ግን ማታ ማታ ሁሌም የቤተሰብ ፕሮግራም እናደርጋለን :: እንዘምራለን እናመልካለን :: መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተን ሁላችንም ጥቅሶች አንብበን ተንበርክከን ጸሎት አርገን ወደ መኝታ እንሄዳለን ::
ጥያቄ : - አብረዋችሁ የሚሰሩ የኢሕአዴግ ሰዎች ባልሳሳት ኤትየስት / ኃይማኖት አልባ ናቸው : ሲባል እሰማለሁ ይህ ሁኔታ ለእርሶ በሥራዎት ላይ ፈተና አልሆንቦትም ?
ጠ /ሚ ኃ /ማሪያም :- በኢሕአዴግ ፖሊሲ ኃይማኖትን የግል አርገህ በውስጥህ የምትይዘው ነገር ስለሆነ በአመራር ውስጥ ያለነው የራሳችንን ኃይማኖት በሌሎቹ ላይ ማንጸባረቅ ወይም ጫና ማድረግ ባይፈቀድልንም አንዳንዶቹ ስለእኔ እምነት ለማወቅ የሚፈልጉት ነገር ሲኖር ከመጠየቅ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም :: እኔም በመጠኑ መንገድ ለማስረዳት እሞክራለሁ :: በተረፈ ከሥራ ጓዶቼም ጋር ሆን ብለን በሥራ ቦታ ስለ ግል እምነት አንስተን ተወያይተን አናውቅም :: ይህን ስል በአገሪቱ በኃይማኖቶች ዙሪያ በሚፈጠሩት ችግሮች መንግሥት ምን ማድረግ አለበት በሚለው ላይ አንወያይም ማለቴ አይደለም ::
ጥያቄ :- ለመሆኑ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ስለ ኃይማኖትዎ አንስተው ተወያይተውበት ያውቃሉ ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- ስለ ኃይማኖት አንስተን ተወያይተናል ግን ውይይቱ ጠቅለል ባለ መልክ ስለሁሉም ኃይማኖቶ እንጂ ስለእኔ ወይም ስላንድ ኃይማኖት አይደለም :: እሳቸው ኃይማኖቶች ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖርባትን አገር ማየት ስለነበር ራዕያቸው የኃይማኖት ጽንፈኝነት ሁሌም መዋጋት ያለብን ነገሮች እንደሆኑ ይናገራሉ ::
ጥያቄ :- እንደሚታወቀው ከተማሪነት ዕድሜ ጀምሮ በጣም የተመሰጡ ኃይማኖተኛ ነዎት ፖለቲከኛ ሲሆኑ ብዙ ኃይማኖትን የሚጻረር ውሳኔዎና እርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ በዚህ አንጻር እንዴት ነው ወደ ፖለቲካው መድረክ ሲወጡ ያጋጠምዎት መሰናከል የለም ?
ጠ /ሚ ኃ /ማሪያም :- የኢሕአዴግ ፖሊሲ አብዛኛው ከምከተለው ኃይማኖት ጋር ቢቀራረብ እንጂ አይጻረርም :: ይሄውም አለመስረቅ : አለመዋሸት : ከጉቦኝነት ከአሻጥር በጠራ ሥራ : በቅንነት ወገንና አገርን ማገልገል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው :: መጽሐፍ ቅዱስ ፈርሐ እግዚአብሄር ስንሆንና መልካም ሂሊና ሲኖረን በነገር ሁሉ መልካም ነገርን ማፍለቅ እንደምንችል ይነገረናል ::
ጥያቄ :- አንዳንድ ሰዎች የእርስዎ እዚህ ድረስ መድረስ የእግዚአብሄር ፈቃድ ወይም የእግዚአብሄር ሥራ ነው ይላሉ የእርሶ አስተያየት ምንድ ነው ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- ማንኛውም ሰው አገርን ወደ ሚመራበት ደረጃ ሲደርስ የእግዚአብሄር ፈቃድ አለበት ብዬ አምናለሁ :: ልዩነቱ እግዚአብሄርን የሚያውቅና በልቡ ፈጣሪውን መከታ የሚያደርግ እንዲሁም የእግዚአብሄርን ጥበብና ፊት የሚሻ ሰው በሕይወቱም ሆነ በሥራው ሁሉ እግዚአብሄር ይቀድማል :: እግዚአብሄርን የማይፈራ በራሱ ጥበብ ልንቀሳቀስ ከሚለው ጋር እግዚአብሄር ጋይድ ወይም መሪው ሊሆነው አይችልም :: በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሐዋሪያው ጳውሎስ በዚህ ዐለም ስንኖር በሥጋ ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሄር ጸጋ ጥበብና ቅድስና ስንመላለስ ሂሊናችን ምስክር ነው ትምክህታችንም ደግሞ ይህ ብቻ ነው ብሏልና :: ስለዚህ እኔ አኮንፕሊሽ /አድርጊያለሁ ዓላማዬ ግቤን መታ ልል ምንም ምክንያት የለኝም ይልቁንስ ለአገሬና ሕዝቤ የበኩሌን ምን ላድርግ ብዬ አስባለሁ። ክርስትና በሕይወቴ ብዙ ጥንካሬዎችን የሰጠኝም በብዙ ውጥረቶችና ችግሮች መሓል መንፈሳዊ ጥበቦችን እንድቀስም የረዳኝ ስለሆነ መንፈሳዊ ትምክህት አለኝ፡መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምክህት ከሌላው ዐይነት ትምክህት ለየት ይላል ሌላኛው ዐይነት ትምክህት በእጅ ባለው ነገር ወይም በራስ እውቀት መኩራራት መቦሰት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቡስት ግን በአያሉ አምላክ ፍጹም መታመን ነው ::
ጥያቄ :- ለምሳሌ አቶ መለስ አማኝ ወይም ክርስቲያን አልነበሩምና እሳቸው እግዚአብሄር ጋይድ ሆኖ አይውቅም ማለት ይቻላል ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- እሳቸው ክርስቲያን አልነበሩም ማለት አይቻልም :: የእምነታቸው ጉዳይ የግል ስለሆነ እሱን ከፈጣሪና ከእሳቸው ጋር ያለውን ግኑኝነት ጀጅ ባናደርግ ይሻላል :: በግሌ ግን እንደማምነው እሳቸው ፈርሐ እግዚአብሄር ነበሩ በዚያ ላይ ቅን መሪ ስለነበሩና የኃይማኖት ነጻነት ካለገደብ በመፍቀዳቸው የብዙ መቶ ሺ ቅዱሳን ጸሎት ደግሞ ስለደገፋቸው በሞገስ ሊመሩ ችለዋል ::
ጥያቄ :- ቃለ መሐላ በሚፈጽሙበት ጊዜ <ዘላለማዊ ክብር ለጠ /ሚኒስትራችን > ያሏት ቃል ብዙ ክርስቲያኖችን ያጠያየቀ ጉዳይ ሆናለች ይህችን ቃል ሆን በርግጥም አምነውባት ነው ያሏት ወይስ የተጻፈልዎትን ነው ያነበቧት ?
ጠ /ሚ ኃ /ማሪያም ደሳለኝ :- (ትንሽ ካሰቡ በኋላ ) ያንን ንግግር ያዘጋጁት ንግግር አዘጋጆች ናቸው :: ግን የንግግሩን ጽንሰ ሀሳብ መጀመሪያ እኔ ነኝ የሰጠኋቸው እነሱ ቋንቋውን አሳምረው ቀናንሰውና ጨማምረውበት አሰካክተው ኤዲት አርገው ከጨረሱ በኋላ እኔ ጋ ይደርሳል እኔ ሀሳቤን በትክክል ይገልጻል የሚለውን አንኳሩን ክፍል ብቻ አይቼ ያቺን ቃል ሳላስተውል አመለጠችኝና እናም ምንም አማራጭ የለኝም አልኳት :: ማታ ቤት ስመለስ ባለቤቴና ልጆቼ ሁሉ ገና ከበሩ ጀምሮ አተካራ ገጠሙኝ :: ልጆቼ በተለይ የ 16 ዐመቷ ልጄ ያለችው አባ በምድር አላፊ የሆነ ሥጋ ለባሽ ከኢየሱስ እኩል በላይ ክብር መውሰድ አይገባውም ብለህ ራስህ አስተምረሄን የለም ብላ ስትለኝ በእውነት መልስ አጣሁ :: ትንሽ ፈተና ገጥሞኝ ነበር እልሀለሁ ::
ጥያቄ :- እና ተጸጽተዋል ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- አዎን ... በኋላማ አስቀምጫቸው የሆነውን ነገር ሁሉ አስረጅያቸው በጠረጴዛ ዙሪያ ሰላም ፈጠርን :: ግን አንድ ነገር ቤተሰቤም ሆነ መላ ክርስቲያን ወገኖቼ ይረዳሉ ብዬ ተስፋ የማደርገው ነገር እኔ የትናንቱ የትንሹ ኃ /ማሪያም ቤተሰብ አስተዳዳሪና አንድ ተራ የሐሪያዊት ቤተክርስቲያን አባልና አማኝ ብሆንም ያንን ማንነቴን ምንም የሚቀይር ነገር የለም :: ጌታ እስከፈቀደ አሁንም ወደ ፊትም ያን የትናንቱን አምላክ ማምለኬ እንደ ግለሰብነቴ ተጠብቆልኝ በአንጻሩ ደግሞ የ 80 ሚሊዮን ሕዝብ አደራና ኃላፊነት ስላለ የሁሉንም እምነትና ኃይማኖት የማክበር ግዴታ አለብኝ :: ሌሎቹም እንዲሁ የእኔን ኃይማኖት ለግሌ ነጻነቴን ትተውልኝ በመቻቻል ተያይዘን በወንድማማችነት በጋራ እንደምንኖር መገንዘብ አለባቸው :: ግን ማንም ኃይማኖቱን ሽፋን አርጎ ፖለቲካዊም ሆነ ኃይማኖታዊ አድቫንቴጅ ለመውሰድ የማንንም ሂሊና መጋፋት እንደለለበት አምናለሁ ::
ጥያቄ :- ሌሎች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እርስዎ የሚከተሉት እምነት ማለትም ኦንሊ ጂሰስ ከልት ነው ወይም አሳች ኃይማኖት ነው ብለው ያምናሉ : ምናልባት በየኢንተርኔትና በጋዜጦች ተከታትለው እንደሆነ አላውቅም ሰዎች በየቦታው ማንሳታቸው አይቀርምና ስለዚህ ጉዳይ መልስ ምን ይላሉ ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- አሁን ስለ ኃይማኖት ዲኖሚኔሽንና ዶክትሪን ውስጥ ገብቼ ሀሳብ መስጠት አልችልም :: ምክንያቱም የምነግርህ አንተን ወይም ሌሎቹን የሚያስከፋ ሊሆን የሚችል ሰንሰቲቭ ጉዳይ ስለሆነ እዛ ውስጥ ገብቼ መነጋገር የለብኝም :: ግን አንድ ነገር ማወቅ ያለብህ <ኦንሊ ጂሰስ > ተከታዮች ብቻ የምንባለው ውሸት ነው በመሰረቱ ኢየሱስ የሚል ስም የኃይማኖታችን ዋናው መሰረት ስለሆነ ይህ ስም የተሰጠን እንጂ እኛም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ::
ጥያቄ :- እርግጠኛ ነዎት ? የሰማሁት ግን አባትን ክደው ልጅን ብቻ ያመልካሉ ሲባል ነው ::
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- አዎን እርግጠኛ ነኝ :: ይህን ጉዳይ በጥልቀት ለማወቅ ከፈለክ ቤተክርስቲያናችን ወደ ሚገኝበት ወደ የትም ሄደህ ማረጋግጥ ትችላለህ :: ወይም ... ሳቅ እያሉ ትንሽኛዋ ልጄ ስታገኛት ልታስረዳህ ትችላለች ::
ጥያቄ :- ባለቤትዎ ወ /ሮ ሮማን ከወላይታ ብሄር አባትና እናት የተወለዱ እንደሆኑ እኔም አውቃለሁ ሰሞኑን በኢንተኔት ግን ኤርትራዊት ናቸው ብለው ወሬ እንደሚናፈስ ሰምተዋል ? የአንዷን ልጅዎትን ስም የዋሓና ኃ/ማሪያም ብለዋታል ይህ ማለት በርግጥ የኤርትራ ስም ነው ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- (በጣም እየሳቁ ) እንደዚህ መባሉን ገና ካንተ መስማቴ ነው :: እኔ ግን የሰማሁት እኔን ነበር ትግሬነት አለበት ሲሉ የሰማሁት .... እንግዲህ ባለቤቴን አንተ ካወቅካት ሌላ ምን እልሀለሁ :: እንደገና ግልጽ ማድረግ ካስፈለገ ባለቤቴ ሁለቱም ወላጆቿ የወላይታ ብሄር ተወላጆች ናቸው :: ወላይታ እንግዲህ በኤርትራ ክልል ውስጥ ነው ካልተባለ በቀር እኔም ባለቤቴም ወላይታና ኢትዮጵያዊያን ነን.... ያንን ውዥንብር የሚያናፍሱ የወሬ ፋብሪካዎች መላውን የወላይታ ሕዝብ ዜግነት ጉዳይ ሊወስኑ ነው ማለት ነው :: የሓዋና ማለት የመጽሓፍ ቅዱስ ስያሜ እስከሆነ ድረስ ማንም ባይብል የሚያውቅ ወይም ክርስቲያን የሆነ ሰው መጋራት የሚችል ስም ነው ። እንኳንስ በቋንቋና በባህል አንድ የሆንን ኤርትራዊያን ብቻ ሳይሆኑ ከብዙዎቹ አገሮች ሕዝቦች ጋር ዩኒቨርሳሊ አንድ የሚያደርገን ክርስትና ነው። የዋሓና በሉቃስ ወንጌል ሁሉንም ታሪክ ታገኘዋለህ። የጌታችን ትንሳኤ ካበሰሩት ሴቶች መካከል ከነመግደላዊት ማሪያም ጋር የሓዋና የምትባል ሴትም አብራቸው ነበረች። ትርጓሜውም በእብራይስጥ ቋንቋ የግዚአብሄር ስጦታ ማለት ነው ለዚህ ነው ይህን ስያሜ የመረጥነው።
የዋሓና ኃይለማሪያም የጠ/ሚኒስትሩ ታላቅ ልጅ ሳትሆን 2ኛ ልጅና በአምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ በምንድስሕና 2ኛ ዓመት ተማሪ ነች። የዋሃና በጣም ተግባቢና በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ከመሆኗም ሌላ በምታመልክበት ቤ/ክርስቲያን ከእህቶቿ ጋር ለምእመናኖች ቆሎ ዳቦ ና ሻይ እያቀረቡ <የመክሊት አገልግሎት> ይሰጣሉ። እንዲሁም በቤተክርስቲያናቸው ደንብ መሰረት ቀዳሚ ወይዘሮዋ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እንዲሁም የዋሓናና ሁለቱም እህቶቿ ሜካአፕ ወርቅ የመሳሰሉ ጌጣጌጥ በሰውነታቸው እንደማያጠልቁ ጠ/ሚኒስትሩ ነግረውኛል
ጥያቄ :- ንጉሥ ጦና አያታቸው ከቴምቤን ስለሆኑ ምናልባት የወላይታ ትግሬነት ይኖርብዎታል ብለው እንዳይሆን ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- እኔ ከጦና ጎሣ አይደለሁም :: ንጉሥ ጦና ከሮያል ፋሚሊ ማለትም <ካዎናታ> ከሚባል ጎሣ ናቸው እኔ ግን ከዚያ ጎሣ አይደለሁም ::
ጥያቄ :- ቤት ውስጥ ወላይትኛ ትነጋገራላችሁ? ባለቤትዎና ልጆችዎስ ቋንቋውን በደንብ ይነጋግራሉ ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- ወላይታ ውስጥ ተወልደን እስካደግን ድረስ እኔም ባለቤቴም የዘውትር መግባቢያችን ፕራይሜርሊ ወላይትኛ ቢሆንም ግን ብዙ ጊዜ አፋችን ወደ ሚመራው ቋንቋ እየተጠቀምን እንግባባለን። ሃሳባችንን በትክክል መለዋወጣችን ላይ እንጂ ሆን ብለን ቋንቋ መርጠን አናውቅም:: የምንገለገልበት ቋንቋ ወላይትኛም አማርኛም አንዳንዴም እንግሊዘኛም ሊሆን ይችላል ልጆቻችን የቋንቋችንንና የባህላችን ተካፋይ ሆነው ማደግ ስላለባቸው ቋንቋውን እንዲማሩ ገፋፍተናቸዋል። ምክንያቱም ከገጠር የሚመጡ ዘመዶቻችን ብዙዎቹ አማርኛ የማይችሉ ስላሉ ከነሱ ጋር መግባባት በመቻላቸው በጣም እንዲቀራረቡ አስችሎአችዋል
ጥያቄ :- ባሁኑ ጊዜ በኢህአደግ አመራር ውስጥ የውጭ አገር ተወላጆች አሉ ስለሚባለውስ ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- አሁን አንተ ባለበቴን ይላሉ እንዳልከው ዐይነት አሉባልታ ነው ምንም መሰረት የለለው ተራ አሉባልታ ነው:: በኢሕአዴግ አመራር ውስጥ ያሉ ታጋዮች አገሬ ናት ለማይሉትና ለማያምኑበት ዓላማ መተኪያ የላላትን ሕይወታቸውን አሳልፈው አይሰጡም። ኢሕአዴግ ከትጥቅ ትግል ዘመን ጀምሮ አንድ ይዞ የመጣ ባህሉ ኮራፕት የሆነ አባሉን ካለምንም ምሕረት እያንጠባጠበ ያጭበረበረ ከተገኘ እያሽቀንጠረ እያጣራ ነው የመጣው :: ባንጻሩ ነባር አመራር ሆነ ዝቅ ያለ ደረጃ ያለ በመልካም ሥነ ምግባሩ ከመለካት ባሻገር ማንነቱ ከታወቀ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ሕይወቱን አሳልፎ እስከመስጠት በግንባር የተሰለፈውን ታጋይ በዜግነት ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ የማንንም የዐይን ቀለም የሚመረምርበት ምክንያት የለውም ::
ጥያቄ :- በመጨረሻ ክቡር ጠ/ሚኒስትር የሚወዷትን ጥቅስና መዝሙር ቢነግሩኝ
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- የምወዳት ጥቅስ ሉቃስ ወንጌል10፥5 ላይ ኢየሱስ << ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል።>> ያለው ነው፡ የእግዚአብሄር ሰላም በውስጣችን ካለ ወደ ምንሄድበት ሁሉ እሱ ያስቀመጠልንን ሰላም እየዘራን መሄድ አለብን። የምወዳቸው መዝሙሮች ብዙ ቢሆኑም <ምን ክብር አለኝ ክብሬ ኢየሱስ ነው: ምን ክብር አለኝ ክብሬ ኢየሱስ ነው: በእሱ ክብር ደግፎ ያኖረኝ በምህረቱ እስካሁንም ያቆመኝ ... ክብሬ እለዋለሁ ..... ሞገሴ እለዋለሁ > የሚለው አሁን ምርጫዬ ነው::
No comments:
Post a Comment