በዘመነ “ህንፍሽፍሽ” ህወሓት ለሁለት በተሰነጠቀበት ወቅት “በህወሓት የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት መግለጫ አናወጣም” በማለታቸው ከድርጅትና ከሃላፊነታቸው ተባርረው በነበሩት ኩማ ደመቅሳ ጠቋሚነት ጨፌ ኦሮሚያ አዳራሽ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ሆነው በ1997 ዓም የተመረጡት አባዱላ ገመዳ ሥልጣን በያዙ ማግስት የጁነዲንን “አርሲ ተኮር” ካቢኔ ሲንዱት ጁነዲንና ደጋፊዎቻቸው ደስተኛ እንዳልነበሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ።ጁነዲን ስልጣን ባስረከቡ በደቂዎች ውስጥ ከጋዜጠኛ ቀርቦላቸው ለነበረ ጥያቄ “ከስልጣን እንደምወርድ ከሁለት ዓመት በፊት አውቀው ነበር” ብለው መመለሳቸውን በስፍራው የነበሩ ያስታውሳሉ።
በዚሁ ሳቢያ በተፈጠረ መቧደን የነጁነዲን ቡድን አባዱላን ለማሰመታት የተደራጀው በጊዜ ነበር። አባዱላን ለማስወገድ ይቻል ዘንድ ተባራሪው ፕሬዚዳንት ጁነዲን የአባዱላ ምክትል የነበሩትን ሙክታር ከድርን ደጋፊያቸው አደረጉ። ይህ መቧደን በተጋጋለበት ወቅት አባዱላ ከሼኽ መሃመድ አላሙዲ ጋር ከፍተኛ ጸብ ውስጥ ገብተው ነበር። አባዱላ ለበታች አመራሮች አላሙዲ አስፈላጊውን ግብር እንዲከፍሉ፣ ያላለሙትን መሬት እንዲነጠቁና የመሳሰሉትን ርምጃዎች በካቢኔ በማስወሰን ተግባራዊ ያደረጉበት ያ ወቅት አባዱላ በኦሮሚያ ተወዳጅነት ያተረፉበት፣ በተዛማጅ ደግሞ ወንበራቸው መንገዳገድ የጀመረበት ወቅት ስለመሆኑ ሽኩቻውን የሚከታተሉ በስፋት የሚያወሱት ጉዳይ ነው።
የውጥኑ መነሻና መድረሻው የደረሳቸው አባዱላ በኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ የሙስና ጉዳይ ከመነሳቱ በፊት አስቀድመው ሃጢያታቸውን ተናዘዙ። “ይህንን ቤት ይዤ ለመታገል አይመቸኝም” በማለት ጥይት እንዳይበሳው አድርገው ወዳጆቻቸውና “ተጠቃሚዎች” የገነቡላቸውን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ካርታና የባንክ እዳ ለድርጅቱ አበረከቱ። ሌሎቹም ያላቸውን እንዲያስረክቡ ሲጠየቁ ጁነዲን አዳማ ያላቸውን አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እሰጣለሁ አሉ። አዲስ አበባና ለገጣፎ ስላላቸው ህንጻ ዝምታ መምረጣቸውም ይፋ ሆነ። እነ ሽፈራው ጃርሶ፣ ግርማ ብሩ ግን የመንግስት ቤት ውስጥ እየኖሩ በዶላር የሚያከራዩትን ቤት ለማስረከብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ።
በወቅቱ የመለስ ድጋፍ የነበራቸው አባዱላ በግምገማው መጨረሻ እነ ሙክታርን ረቱና ከኦሮሚያ አባረሩ። አካባቢያቸውንም አጸዱ።
አባዱላን ለመምታት የሚደረገው ፍትጊያ ቢያይልም አዲሱ ካቢኔ አባዱላን “ጃርሳው” በማለት ተቀበለ። በጉባኤና በግምገማ “አባዱላን የሚነካ ወዮለት” ማለት ጀመረ። አባዱላም “ልማትን አፋጥኑ እንጂ የፈለጋችሁን አላማና አመለካከት መያዝ ትችላላችሁ። እኔ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ” በማለት በወጣቶች የገነቡትን ካቢኔ ስሜቱን አጋሙት። በዚህ መካከል 2002 ምርጫ ሲመጣ በድንገት አባዱላ ኦሮሚያ ክልል እንደማይወዳደሩ ከላይ መወሰኑ ተሰማ። ካድሬው፣ ምክርቤቱና ካቢኔው ውሳኔውን “አንቀበልም” አለ።
በቆረጣ ባለሃብቱ (አላሙዲ) ላይ ተንጠላጥሎ በሙስና መሽተቱና የባለሃብቱ ታዛዥ እንደሆነ የሚነገርለት ብርሃኑ አዴሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሃላፊነት ሲወገድ ሙክታር ከድር ተክተው ተሾሙ። ሹመቱ የባለሃብቱ እጅ እንዳለበት አብነት ገ/መስቀል ሸራተን አዲስ ስም እየጠራ ወሬውን የአልኮል ቁርስ በማድረግ አስቀድሞ ሲናገር የሰሙ ይመሰክራሉ። በድርጅት ከኢህአዴግ ጋር፣ በጽህፈት ቤት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር የቀረቡት ሙክታር ከድር አባዱላ ገመዳን ለመጎሸም አጋጣሚው ተመቻቸላቸው።
በዚህ መሃል አባዱላ በድጋሚ ክልሉን እንዲመሩ በኢህአዴግ ምክር ቤት የተወሰነውን ውሳኔ የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ከጁነዲን፣ ከሙክታር፣ ከሱፊያንና ከሽፈራው ጃርሶ በስተቀር የተቀሩት ተቃወሙ። ምክር ቤቱም አወገዘው። የበታች አመራር ማብራሪያ ጠየቀ። በዚሁ ሳቢያ በረከት ስምኦን አዳማ ወረዱና የኦህዴድን ጠቅላላ ጉባኤ ሰበሰቡ። ካድሬው ሳይፈራ በረከትን ሞገተ። በረከት የድርጅት ውሳኔ መከበር እንዳለበት በማስፈራራት ተናገሩ። ካድሬው አሻፈረኝ አለ። አባዱላ “እባካችሁ” በማለት ተማጸኑ። በሁለት ስብሰባዎች አልበገርም ያለው የካድሬው ተቃውሞ በሶስተኛ ስብሰባ አባዱላ ተማጽኖ አቅርበው፣ ካድሬው አልቅሶና ፈርቶ አባዱላን ለመሸኘት ተስማማ። በረከት ስምዖንና ህወሓት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቂም እንደያዙ ስለቆዩ ኦህዴድን ለማጥራት አሁን አጋጣሚው እንደተመቻቸላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
አሁን በኦህዴድ ውስጥ ተፈጠረ የተባለው ቡድን ሲወርድና ሲንከባለል ቆይቶ መለስን በሚተካው አመራር ማንነት ላይ የድርጅቱ ምክር ቤትና ካድሬ ተቃውሞውን በግልጽ አወጣው። ህወሓቶችም በዚህ መልኩ መቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ። ሁለት ተጻራሪ ቡድኖች የሚያካሂዱት አይነት የመደብ ትግል እየተደረገ መሆኑ ይፋ ሆነ። ለህወሓት ትዕዛዝ እንደቀድሞው መታዘዝ ያቆመው ኦህዴድ ይህንን አቋም ከየት አመጣው?
አዲሱ ኦህዴድ
ቀደም ሲል ከነበረው ኦህዴድ ይልቅ አባዱላ ያደራጁት ኦህዴድ በወጣቶች የተገነባ፣ በካቢኔ ደረጃ አንደኛና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውና ቀደም ሲል በኦነግ አስተምሮ የበቁ እንደሆኑ ይነገራል። ስለድርጅቱ በቅርበት የሚያውቁ እንደሚሉት አዲሱ ኦህዴድ በማክረር ፖለቲካ የተለከፈ አይደለም። ነገር ግን ኦሮሞ አገሪቱን መምራት አለበት የሚል፣ የመለስ ሂሳብ ባስቀመጠው ስሌት መሰረት ጠ/ሚኒስትርነቱን ያለማቅማማት መረከብ አለብን የሚል አቋም ያራምዳሉ።አሮጌው ኦህዴድ ኦነግን መታገል ባለመቻሉ አዲሱ ኦህዴድ የኦነግና የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረንስ የወጣት ክንፍ አባል የነበሩትን በማስኮብለል አባል ማድረጉ ድርጅቱን እንደበረዘው ጭምጭምታ ይሰማ ነበር። እነ ጁነዲን ድርጅቱን ልቅ በማድረግ ለዚህ አደጋ የዳረጉት አባዱላ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም አባዱላ ለህወሓት ባለስልጣኖች፣ ለአዜብ፣ ለመለስ ጠባቂዎች፣ ለደህንነት ሰዎችና አስፈላጊ ናቸው ለሚባሉት ሁሉ የክልሉን መሬት በንግድ ስምና በመኖሪያ ቤት ስም በማደል ስለተወዳጁ፣ በሌላ አነጋገር ስላነካኳቸው ክሱ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆየ።
አዲሱ ኦህዴድና አመራሮቹ ሁሉንም አካሄድ ስለሚያውቁና የአባዱላ ውሳኔ አስፈጻሚዎች በመሆናቸው ሌሎች በመሬት ንግድ ገንዘብ ሲያፍሱ “እኛስ” በማለት በጋራ ገንዘብ ወደ ማምረቱ አተኮሩ። የሚፈሩ የነበሩ የህወሓት ባለስልጣናት መሬት ፍለጋ በየማዘጋጃ ቤቱ ደጅ ሲጋፉ መናናቅ ተፈጠረ። ህወሓት ገንዘብ ሲያሳድድ ቀደም ሲል የነበረውን ስም አጣ። ኦህዴዶች በስም እየጠሩ ለህወሓቶች ምጽዋት እንደሚሰጡዋቸው ይናገሩ ጀመር። ቀደም ሲል ከነበረው ፖለቲካ እምነት ጋር ተዳምሮ ህወሓት ተናቀ፤ ተጠላ – በተለይም በኦህዴድ። ኦህዴድ የአመራሩ ባለቤት መሆን እንዳለበት ካድሬው በግልጽ ያወራ ጀመር። በዚሁ ሳቢያ በርካታ አዳዲስ የካቢኔ አባላት በሙስና ስም እንዲታሰሩ ተደረገ። ኩማ ደመቅሳ ቡራዩ በተካሄደ ዝግ ስብሰባ ተልዕኳቸውን አሳኩ። አዲሱ ኦህዴድ አጥብቆ የሚጠላቸው ኩማ መጨረሻቸው ባይታወቅም ከፊት መስመር ሆነው የማስተናበሩን ስራ እየመሩ ነው። አዲሱ ኦህዴድ ከሞላ ጎደል ይህ ነው። በሙስና የሸተተ፣ በአመላካከት የተሻለ፣ ዥንጉርጉር አቋም ያካተተ፡፡
“በአንድ ድርጅት ውስጥ የመደብ ትግል ካለ መተላለቅ ተጀምሯል ማለት ነው”
ኦህዴድ እንደ ድርጅት ሊቀጥል የማይችልበት ደረጃ መድረሱን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው። በአንድ ፓርቲ ውስጥ “የመደብ ትግል” የተባለ ግምገማ መካሄዱን ተከትሎ ከህወሓት መሰንጠቅ ቀጥሎ በኢህአዴግ ታሪክ ትልቅ የተባለ የማጥራት እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ተገምቷል። ጉዳዩን አስመለክቶ ያነጋገርናቸው “የመደብ ትግል ካለ መተላለቅ ተጀምሯል ማለት ነው” ብለዋል።በልዩ ጥበቃ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ለአራት ቀናት በተካሄደው የኦህዴድ ምክር ቤት ግምገማ ድርጅቱ እንደ ድርጅት መቀጠል የማይችልበት ደረጃ መድረሱና፣ ለድርጅቱ የተቀመጠው መስመር መጣሱ በዋናነት የተነሱ የግምገማው መነሻ ጉዳዮች መሆናቸውን የጎልጉል ምንጮች ገልጸዋል።
በየሳምንቱ ረቡዕ የሚታተመው ሰንደቅ የተባለው ጋዜጣ “ የሰላ መደባዊ ትግል” መካሄዱን አስነብቧል። በረከት ስምዖን ከኋላ ሆነው የሚመሩት ሰንደቅ ጋዜጣ “ስርዓቱን ለማኖር ሲባል የድርጅቱን መስመር በርዘው በሚንቀሳቀሱት አመራሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ የሚወሰድበት ትግል” ሲል ባልተለመዱ የግምገማ ቃሎች ኦህዴድ ውስጥ የተከሰተውን ችግር ይፋ ያደረገው ዜና ችግሩን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ጋር አያይዞታል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ምንጮች እንደሚሉት ግን ኦህዴድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት መቀመጫው እንዲሰጠው አለመጠየቁ ካድሬዎቹን አበሳጭቷል። በበታች አመራሮች አማካይነት የተነሳውን የቆየ ጥያቄ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ በኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ያቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ አለማቅረቡ አሁን ይፋ ለወጣው “የመደብ” ችግር ዋና መንስዔ ነው።
በኦህዴድ ምክር ቤት ደረጃ አቋም የተያዘበትን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ለሃይለማርያምና ለደመቀ ድምጽ በመስጠት የተመለሰው ሥራ አስፈጻሚ የልዩነት አቋም አራምደዋል በተባሉት በምክርቤቱ አባላት፣ በበታች አመራርና ካድሬዎች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል። በዚሁ ሳቢያ የቆየው ክፍፍልና ቁርሾ ይፋ ሊወጣ ችሏል።
ከሥራ አስፈጻሚው ጀምሮ በተዋረድ ባለው መዋቅር እስከ ቀበሌ የደረሰው የልዩነት ደረጃ በመካረሩ “የመደብ ትግል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ግምገማ እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል። ጎልጉል ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ “በአንድ መስመር ላይ ሆነው በሚሰሩ የአንድ ድርጅት አባላት መካከል የመደብ ልዩነት ሊከሰት አይችልም። ከተከሰተም ልዩነቱ እስከመጫራረስ የሚያደርስ ይሆናል” ሲሉ የግምገማው ውጤት መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ያስረዳሉ።
“የመደብ ትግል” አሉ አስተያየት ሰጪው “የመደብ ትግል ከሁለት በላይ በሆኑ ተጻራሪ ሃይሎች መካከል የሚካሄድ አሸናፊና ተሸናፊ ያለው ትግል ነው። ኦህዴድ ውስጥ በትክክል የመደብ ትግል የሚባል ግምገማ ከተነሳ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። የመደብ ትግል ብሎ ግምገማ ስለሌለ ድርጅቱ ከፍተኛ አደጋና የህልውና ቀውስ ይገኛል ማለት ነው። ኦህዴድ በመደብ ልዩነት ችግር ከተመታ ፓርቲው እንደ ፓርቲ መቀጠል አይችልም ማለት ነው። ቀውሱ ወደ ሌሎቹም ድርጅቶች የመዛመት ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ይሆናል” በማለት አስተያየታቸው ሰጥተዋል።
መለስ የቆፈሩዋቸው ጉድጓዶች በሚል ርዕስ ስማቸው ለጊዜው እንዳይጠቀስ ጠይቀው ከጎልጉል ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኢህአዴግ ሰው ከወር በፊት“የወንበር ጥያቄው መነሳቱ አይቀርም። ካድሬውና የበታች አመራሩ ድሮም ጀምሮ ሃሳቡ አለው። ግምገማ እየተባለ በሰርጎ ገቦች እየተሰለሉ እየተወገዱ እንጂ እስከዛሬም አይቆይም ነበር። ያም ሆነ ይህ መለስ ስለሌሉ የወንበር ቡቅሻው የማይቀር ነው። በየድርጅቱ አመራሮች ዘንድ የሌባና ፖሊስ፣ የሃይል ሚዛንና ቅኝት፣ አሰላለፍን የማሳመር ሰልፍ እየታየ ነው። አሁን በዝርዝር የማልናገረው አንዳንድ የመናድ ምልክቶችም አሉ” በማለት ቅድመ ትንበያቸውን አስቀምጠው ነበር።
የግምገማውን ውጤት አስመልክቶ በማስጠንቀቂያ የሚታለፉ፣ በህግ የሚጠየቁ፣ የፖለቲካ ውሳኔ የሚተላለፍባቸው እንደሚኖሩ ይጠበቃል። የበረከት ጋዜጣ ሰንደቅ እንዳለው መሸፋፈንና ማድበስበስ የለውም በተባለለት “እርቅ የሌለው ትግል” ሲጠናቀቅ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ለህግ የሚቀርቡ አሉ። የጎልጉል የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት የኦህዴድ ሰዎች በፓርላማና በድርጅት ለመለስ እያጨበጨቡ፣ እያንቀላፉ ባጸደቁት ህግ መቀጣታቸው አይቀሬ ነው።
ከፖለቲካው በተጨማሪ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ “አሸባሪነትን ለሚቀሰቅሱና አገሪቱ በሸሪዓ ህግ እንድትመራ ለመጠየቅ እቅድ ከያዙ ክፍሎች ጋር በማበርና ዓላማቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ውስጥ ውስጡን የማሳለጥ ስራ ሲያከናውኑ ነበሩ” የተባሉም አሉ። ምንጮቻችን እንዳሉት ኢህአዴግ የሙስና ፋይል የሚከፍትባቸውም አይታጡም።
ህወሓቶች የሚመሩት የስለላው ሃይል አባላቱ ለሚከሰሱበት ክስ ሰነድ አዘጋጅቶ እንደጨረሰ ያስታወቁት ክፍሎች ከኦህዴድ አመራሮች መካከል ቀደም ሲል በጁነዲን ሳዶ፣ አባዱላ ገመዳና አሁን ደግሞ ኩማ ደመቅሳ መካከል ያለውን አሰላለፍና ልዩነት ሲከታተል ነበር። በዚሁ መሰራት ስም ባይዘረዝሩም እርቅ የሌለበት ግምገማ ሲጠናቀቅ ቀደም ሲል ጀምሮ የነበሩ ጉዳዮች እንደ አዲስ እንደሚነሱ የጎልጉል ምንጮች አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment