የሕዝብን ጥቅም፣ ፍላጎትና ሁለንተናዊ መብቶች መሰረት አድርጎ የሚቀረፅ ህገ መንግስት ለውጤታማና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ስርዓት የታደለ ማህበረሰብ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ያጠናክራል፣ ከፍተኛ አገራዊ ፍቅርን ይላበሳል፣ በብሄር፣ በቋንቋና በባህል የተለያየ ቢሆንም እንኳ በመካከሉ ልዩ የሆነ መተማመንንና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ይገነባል፡፡
ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን የተገነዘበና በእርሱም እምነቱን ያሳደረ ማህበረሰብ በሚኖርባቸው አገራት ውስጥ የሚከሰቱ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለአመጽና ለእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት አይሆኑም፡፡ ስርዓቱ በማህበረሰቦች መካከል የላቀ መተማመንና መተሳሰብን የሚያስከትል በመሆኑ ለሚፈጠሩት ፈተናዎች አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን አይቀስርም፡፡ ከዚህ ይልቅ ፍፁም በሆነ የመተማመንና የመግባባት መንፈስ ማህበረሰቦቹ ለሚገጥሟቸው ችግሮችና ፈተናዎች መፍትሄውን ለማበጀት የሚቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
የዚህ ዓይነቱ ማህበረሰብ የሚመራውን መንግስት ለስልጣን የሚያበቃው በምርጫው በመሆኑ በመንግስቱ ላይም ከፍተኛ እምነትን ይፈጥራል፡፡ ይህም በአገሪቱ ጠንካራ ሰላምና መረጋጋት እንደዚሁም ብሩህ የሆነ የእድገትና ለውጥ ራእይ እንዲኖር፤ ራእዩም በተገቢው መጠንና ፍጥነት እውን እንዲሆን የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በአጠቃላይ አገሪቱ በእኩልነት፣ በፍትህና በጋራ ጥቅም ላይ ጠንካራ እምነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ የሚመራት ትሆናለች፡፡
በተቃራኒው ዴሞክራሲያዊ እሳቤን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋማት በሌሉባቸው አገራት ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን የተላበሰ ማህበረሰብ ማግኘት በእጅጉ ያዳግታል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ በሚታይባቸው አገራት የህዝቦችን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ስርዓት ባለው መልኩ ማስተናገድ ስለሚሳን በህዝቦች እና መንግስታት መካከል ብቻ ሳይሆን በተለያዩት የህብረተሰብ ክፍሎች ጭምር ሁሌም የከፋ ጥርጣሬና አለመተማመን አለ፡፡
በእነዚህ ማህበረሰቦች ውስጥ የሕዝብ ምሬትና ሮሮ ምን ጊዜም አይጠፋም፡፡ ምሬት፣ ቂምና ጥርጣሬ በነገሰበት ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ ምንም ዓይነት የተፈጥሮ ኃብት ክምችት ቢኖር እንኳ የሕዝብን ህይወት ሊያሻሽል የሚችል የኢኮኖሚ እድገት አይታሰብም፡፡ መንግስታቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ የልማት እቅድ ለመተግበር ቢሞክሩም እንኳ የሕዝብ ድጋፍ የራቃቸው በመሆኑ ደካሞች ናቸው፡፡
በእነዚህ ዓይነቶቹ አገራት ውስጥ ዘውትር ስጋት አለ፤ ሰላምና መረጋጋት የለም፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹ ወደእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ድህነትና ችጋር እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ስደት፣ ርሃብና መሰል ማህበራዊ ቀውሶች የእነዚህ አካባቢዎች ዋነኛ መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡
የእነዚህ ዓይነቶቹ አገራት ህዝቦች የታመቀ ምሬትና ብሶት ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም በሆነ አንድ መጥፎ አጋጣሚ ይህ የሕዝብ ምሬት ገንፍሎ በማህበረሰቡ ውስጥ የከፋ ስርዓት አልበኝነት፣ የእርስ በርስ ግጭትና ደም መፋሰስ ይከሰታል፡፡
የዚህ ዓይነቱ የታሪክ ክስተት በተለያዩ የአፍሪካና ሌሎች አገራት ውስጥ ታይቷል፤ በመታየት ላይም ይገኛል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካን ሁኔታ ለዚህ አብነት አድርጎ ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያያ በአሁኑ ወቅት ያለው ህዝብ መብቶቹ የተረገጡበት፣ በምሬት የተሞላና በሆነ አንዳች አጋጣሚ ለአመፅ የሚነሳ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment