(አሥራደው ከፈረንሳይ)
ተናገር መጋዶ ተናገር ሻኪሶ ፤
ወርቅ ወዴት ተጋዘ ላንተ አፈሩ ደርሶ ፤
ተናገር ሃዱማ ደግሞም ኡላኡሎ ፤
እነማን ዘረፉት የወርቁን አሎሎ ፧፦
የወርቁን ቡችላ የለገ ደንቢውን ፤
ደብዛውን ንገሩን የደረሰበትን ፧፦
እነማን ዘረፉት ፧ ማንስ ከበረበት ፧፦
እነማን ተዝናኑ፧ ማንስ ጨፈረበት ፧፦
ደሃ በደከመ ደሃ በሞተበት ፤
ጦሙን እንደዋለ አፈር ተንዶበት ፥፥
አካፋና ድማ ይዘው ሳይቆፍሩ ፤
ጨለማ መግፈፊያ ሻማ ሳያበሩ ፤
ጠብ ሳይል ላባቸው ባቋራጭ ከበሩ ፡
ያገር አንጡራ ሃብት እየመዘበሩ፥፥
ዕትብቱ ተቆርጦ ለተቀበረበት፤
ለወርቁ ባለቤት ምንም ሳይሰሩሉት ፤
ጉሮሮውን አንቆ ካፉ በመቀማት ፤
ሃብታም መዘበረ ባዳ ከበረበት ፥፥
አወይ ክብረ መንግሥት እንዴት ነው አዶላ ፧፦
ደሃን እያስራበ ሃብታም የሚያበላ ፦
No comments:
Post a Comment