Thursday, 11 October 2012

አሜሪካዊው አቃቢ ህግ እና ባለቤታቸው ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ባመጧቸው ህፃናት ላይ ከባድ ጥቃት በማድረስ ተከሰሱ

ዳግላስ ባርበር እና ባለቤታቸው ክሪስቲን ባርበር ባለፈው መጋቢት ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ባመጧቸው ህፃናት ላይ “ከባድ ጥቃት አድርሰዋል” ተብለው ተከስሰዋል፡፡
 
ዳግላስ ባርበር በዩናይትድ ስቴትስ ፔንሲልቬንያ ክፍለ ሀገር ውስጥ ታዋቂ የሆኑ ምክትል ጠቅላይ ኣቃቢ ህግ ናቸው፡፡ የስድስት ዓመቱ ወንድ ልጅ ምግብ ለረጅም ጊዜ ከመከልከሉና ከሌላም አካላዊ ጥቃት የተነሳ ሰውነቱ ከስቶና ተጎድቶ ሆስፒታል ገብቷል፡፡ ሴቷ የዓመት ተመንፈቅ ልጅ ደግሞ በርካታ የአጥንት ስብራት የተገኘባት ሲሆን ዓይኖቿ ላይም ዘላቂ ለሆነ ብርሃን ማጣት ሊዳርጋት ይችላል ብለው ሐኪሞች የሰጉበት ጉዳት ደርሶባታል።

ተከሳሾቹ በጥቂት ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሲሆን በዋስ ተለቅቀዋል። የህፃናቱን ሁኔታ ባዩበት ወቅት ይህ የከፋ ጥቃት ምልክት እንጂ ወትሮ በልጅ ላይ የሚታይ ህመም አይደለም ብለው ካስጠነቀቁት መካከል አንዲቱ ሐኪም ጉዳዩ ገና በክሥ ሂደት ላይ ያለ ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ ሊገቡ እንደማይችሉ አስቀድመው ካሣወቁን በኋላ ልጆቹ ባሁኑ ጊዜ በደህና ሁኔታ ላይ ናቸው፤ የሚያሰጋ ነገር የለም ብለዋል።

የት ናቸው ለሚለው ጥያቄ ግን እዚህ ቦታ ማለት እንደማይችሉ ፣ ነገር ግን ያሉበት የማያሰጋ ቦታ ነው ብለው አጠቃለውታል።ወይዘሮ ለምለም ፀጋው ከጥቂት ወራት በፊት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል መሥራችና የአመራር አባል ናቸው። “ጉዳዩ የሚሰቀጥጥ ነው፤ እኛም ምን መደረግ አለበት የሚለውን እየተነጋገርንበት ነው” ብለዋል ። “በጉዲፈቻ ከኢትዮጵያ ወደየአገሩ የሚወሰዱ ህፃናት ደህንነት ሁላችንንም የሚመለከት ቢሆንም ከየአገሩ የህፃናት ደህንነት አስጠባቂ ተቋማት ጋር ግንኙነት መሥርቶ ደህንነታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ግን በየአገሩ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ኤምባሲ ወይም ቆንስላ መሆኑ ግልፅ ነው ብለዋል።”


No comments:

Post a Comment