Tuesday, 16 October 2012

ለ እህቶቻችን ልንደርስ የምንችልባቸው ኣምስት መንገዶች!

በኣረብ ኣገራት ለግርድና የሚሄዱትን እህቶቻችንን የሚደርስባቸውን ስቃይ መናገር መነሻዬ ኣይደለም። ያልፍልኛል፣ እናት ኣባቴን እጦራለሁ እያሉ ወደ ሊባኖስና ሌሎች የኣረብ ገልፍ ኣገራት የሚጎርፉት እህቶቻችን ከሰባዊነት ደረጃ ዝቅ ብለው ሲሰቃዩ ሌላው በተለያየ የኣለም ክፍል ያለው ኢትዮጵያዊ ከንፈሩን ከመምጠጥ ያለፈ ብዙ ነገር ሲያደርግ ኣይታይም። እግዚኣብሄር ይባርካቸውና የተለያዩ ሰባዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የቻሉትን ሁሉ እየታገሉ ነው። ግን ኢትዮጵያዊው የበኩሉን ለመወጣት ከማንም በላይ የሞራልም የዜግነትም የውዴታ ግዴታ ኣለበት።
የዛሬው ጽሁፌ በሌላው ኣለም ያለው ኢትዮጵያዊ ምን ሊያደርግ ይችላል? በሚል ተግባራዊ ዘዴዎችን ለመጠቆም ነው።
በመሆኑም ለእህቶቻችን በሚከተሉት መስመሮች ልንደርስላቸው እንችላላን።
1) ለወገን ለሃገር ተቆርቋሪ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ኢሳት ቴሌዚዥን ድርጅት በኣፋጣኝ መቀመጫውን ሊባኖስ ያደረገ የሪፖርተር ቡድን ሊልክ ያስፈልጋል። ይህ ቡድን በየጊዜው የሚደርሰውን በደልና እንግልት እየዘገበ በማጋላጥ ችግራቸውን ሊቀንስ ይችላል። ኣንዱ ትልቁ ችግራቸውም በየሜዳው እየሞቱ ወደ ሚዲያ ስለማይወጣ ነው። ይህ ቡድን በየጊዜው በሚያደርገው ኢንቬስትጌቲቭ ሪፖርት ለኣለም ኣቀፉም ሆነ ለ ኢትዮጵያዊያን ያሳውቃል። ኣንዱ ችግር የኢንፎርሜሽንም ነው። ባለፈው እህታችን ኣለም ደቻሳ የሞተች ጊዜ ነው ትንሽ የተደናገጥነው። ያ ወደ ሚዲያ ስለወጣ እንጂ ሚዲያ ሳያውቃቸው የሚገደሉ የሚሰቃዩ ብዙ ናቸው።
ባለፈው የ ሂውማን ራይት ዎች ባውጣው ዘገባ ላይ እንደሚያሳየው በየ ሳምንቱ ኣንድ የቤት ውስጥ ሰራተኛ ተፈጥሮኣዊ ባልሆነ መንገድ ይሞታል። እንግዲህ ልብ በሉ በሊባኖስ ውስጥ ወደ 200 ሺህ የሚጠጋ የቤት ውስጥ ሰራተኛ ያለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ 60 እስከ 70 ሺህ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ይህ ማለት በየ ወሩ ሁለት የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ወይ ተገለው፣ ወይ ታመው ፣ወይ የሚያሳክማቸው ኣጥተው፣ ወይ ራሳቸውን እንዲያጠፉ ተገደው ይሞታሉ ማለት ነው። ከዚህ የከፋ ነገር የለምና ኢሳት ባስቸኩዋይ ደርሶ ወገንተኛነቱን፣ ኢትዮጵያዊነቱን ማሳየት ኣለበት።
2) በ ኣሜሪካን ኣገር ኣዲስ የተቋቋመው የሴቶች መብት ድርጅት ኣስቸኳይ የቤት ስራው ሊሆን የሚገባው የህግ ባለሙያ የያዘ ኣንድ ቡድን መላክ ነው። በርግጠኝነት ለመብታቸው ለሚሟገት በደላቸውን ወደ ብርሃን ለሚያወጣ ድርጅት ወጪውን እንደሚሸፍኑ እምነቴ ጽኑ ነው። ከሚያገኙዋት ጥቂት ገንዘብ ላይ እያዋጡ ወጪውን ሊሸፍኑ ስለሚችሉ ድርጅቱ በባጀት በኩል ስጋት የሚገጥመው ኣይሆንም። የተጨነቁ እህቶች ኣለን የሚላቸው ካገኙ የሚከፈለውን መስዋእትነት ይከፍላሉ። እነዚህ እህቶች ከ ኤምባሲ ያጡትን የምክር ኣገልግሎትና ፍቅር ይህ ለመብታቸው የቆመ ድርጅት ይክስላቸዋል።
3) ለሲቪክ ማህበራትና ለ ፓለቲካ ድርጅቶች።
ለግርድና የሄደችው እህታችን ስትሰቃይ ዛሬ ስትገደል ከንፈራችንን እየመጠጥን ችግሩ የሚፈታው የችግሩ ምንጭ የሆነው ኣምባገነን መንግስት ሲወገድ ነው ማለት ኣግባባ ኣይደለም። እሱን ማን ኣጣው? ኣሁን በመሃል ግን ድምጻቸው ታፍኖ ተዘልለው የሚያነቡትን እህቶች ኣይዙዋችሁ ማለት ግፋቸውን ማጋለጥ በርግጥ የህዝብ ፍቅር ያለው ድርጅርት ተግባር ነው ። የነሱን መከራና ግፍ ለፓለቲካ ፍጆታ መጠቀም ፈጽሞ ሊሆን ኣይገባም። በመሆኑም ሁለቱም ኣይነት ድርጅቶች በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ይህን በደል ማውጣት ማሳየት ሰላማዊ ሰልፍ ማቀድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሌላው ደሞ ለዚህ የዳረጋቸውን ኣስከፊ ስርኣት ለመለወጥ እንዲችሉ ሊያደራጁዋቸውም ይገባል።
4) ሌላው ከፖለቲካው ተገልሎ ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ በያለበት ድምጹን በተለያየ መንገድ ማሰማት ኣለበት። በፌስ ቡክ በሰልፍ ወዘተ. ተቃውሞውን ማሰማት ኣለብት። ኣንዲት ኣረብ ኣገር የምትኖር እህታችን በስሜት ስትናገር እህቶቻቸውንና ሴቶቻቸውን ኣውጥተው ለግርድና የሰጡ ወንድሞች እንደ ኢትዮጵያዊያን ኣላየሁም ብላለች። ድሃ ኣገር እኛ ብቻ ኣይደለንም ግን እንደኛ ሴቶች ለግርድና ሄዶ የሚሰቃይ የለም ብላለች። በመሆኑም ኣለማቀፋዊ ተቃውሞ በማድረግ እህታችንን ልንደገፍ ይገባናል።
እነዚህ ከፍ ሲል ያነሳሁዋቸው ነጥቦች በውነት በጣም ቀላል ልንሰራቸው የምንችላቸው ናቸው።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

No comments:

Post a Comment