Friday, 12 October 2012

አንድ ገመድ አለኝ

ሁለት ወንድማማቾች እናታቸው ስታርፍ በቤት ውስጥ ያገኙት አንድ ትልቅ ገመድ ብቻ ነበር፡፡ ታላቁ ልጅ እጅግ በመበሳጨቱ ገመዱን ጠቅልሎ ጣራ ላይ ወረወረውና ከቤት ወጥቶ ሄደ፡፡ ታናሹ ግን ምንም ቢሆን ገመዱ የእናቱ ቅርስ ነውና እንደምንም ብሎ ጣራ ላይ ወጥቶ አወረደው፡፡
ከባዱ ጥያቄ ግን ከዚህ በኋላ ያለውን ኑሮ እንዴት መግፋት ይችላል? የሚለው ነበር፡፡ ለብዙ ሰዓታት ተቀምጦ አሰበበት፡፡ ምንም ነገር ሊታየው ግን አልቻለም፡፡ መንገዱ ሁሉ በግንብ የታጠረ ነው፡፡ አስቦ አስቦ ወደ አንድ ጠቢብ ዘንድ ሄደ፡፡
ጠቢቡ ሰው እንዳገኘው የጠየቀው ጥያቄ ‹‹ምን አለህ›› የሚል ነበር፡፡
መልሱም ቀላል ሆነ ‹‹ምንም››
ጠቢቡ ሰውም ‹‹በዓለም ላይ ምንም የሌለው ሰው የለም፡፡ ምናልባት ግን ጥቂት ብቻ ያለው ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ከለምሳሌ አንተ ከወንድምህ በተለየ ጥበብ አለህ፤ ይህ ጥበብህም ነው ወደ ጠቢብ ያመጣህ››አለው፡፡ ልጁ ግን በርግጠኛነት እየማለ ምንም እንደሌለው ተናገረ፡፡


ጠቢቡም ‹‹ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ሰው ሆኖ ምንም የሌለው የለም፡፡ ረስተኸው ነው እንጂ አንዳች ነገር አለህ›› አለው፡፡ ልጁ ቢያወጣና ቢያወርድም ያለውን ነገር ሊያገኘው አልቻለም፡፡ የሚያውቀው ምንም እንደሌለው ብቻ ነው፡፡
ያን ጊዜ ጠቢቡ ልጁን ይዞት ወደ አንድ ክፍል ገባ፡፡ ክፍሉ ሊዳሰስ በሚችል ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ የተሞላ ነው፡፡ ጨለማው ዓይን ሊወጋ ይደርሳል፡፡ ከጠቢቡ ጋር በዚያ ክፍል ውስጥ እንደገቡ ‹‹ምን ይታይሃል?››አለና ጠየቀው፡፡ ልጁም መለሱን ወዲያው ነበር ያገኘው ‹‹ጨለማ››
ጠቢቡ ግን እንደገና ጠየቀው፡፡ ‹‹ሌላ ነገር አለ፤ ፈልገው›› ዘወር ዘወር አለ፡፡ ግን ምንም፡፡
ጠቢቡ እንዲህ አለው ‹‹ና አብረን ቁጭ እንበልና ጊዜ ወስደህ ተመልከት››
ተቀመጡም፡፡
ልጁ በግራና በቀኝ፤ በፊትና በኋላ ማየት ጀመረ፡፡ ለብዙ ደቂቃዎችም አየ፡፡ በመካከል ላይም ‹አሃ›› የሚል ድምጽ ከልጁ ሲወጣ ተሰማ፡፡
ጠቢቡም ‹‹እሺ ምን ተገኘ›› አለው፡፡
‹‹በዚያ በኩል ባለው ቀዳዳ ብርሃን ነገር ይታየኛል›› አለው፡፡
ጠቢቡ አቀፈው፡፡
‹‹አሁን አእምሮህን መጠቀም ጀመርክ፡፡ አእምሮን መጠቀም ማለት ከዓይነ ሥጋ ይልቅ በዓይነ ልቡና ማየት መቻል፣ ከእዝነ ሥጋ ይልቅ በእዝነ ልቡና መስማት መቻል ማለት ነው፡፡ ‹ልብ ካላየ ዓይን አያይም› ሲባል አልሰማህም፡፡ አእምሮውን የሚጠቀም፣ ሰው ሁሉ የሚያየውን ብቻ ሳይሆን የማያውንም ያያል፡፡ ለዚህ ነው አእምሮ ያለው ሰው ተስፋ የማይቆርጠው፡፡ አእምሮ ያለው ሰው በግንብ መካከል በር፣ በጨለማ መካከል ብርሃን፣ በተራራ መሐል መንገድ፣ በሞት መካከል ሕይወት ይታየዋል፡፡
‹‹መንገድ ያለው ከውጭ አይደለም፡፡ መንገድ ያለው ከውስጥ ነው፡፡ የውጭው መንገድ እግር ነው የሚሄድበት፡፡ የውስጡ መንገድ ግን ልቡና ነው የሚጓዝበት፡፡ በልቡናቸው የሄዱ ሰዎች ናቸው በእግራቸው ለመሄድ ፈልገው የእግሩን መንገድ የሠሩት፡፡ ከእነርሱ በኋላ ግን ብዙዎቹ በልቡናቸው ሳያዩ ይጓዙበታል፡፡ መጀመርያ በልቡናቸው የበረሩ ሰዎች ናቸው አውሮፕላንን የፈጠሩት፣ መጀመርያ በልቡናቸው የተገናኙ ሰዎች ናቸው ስልክን የሠሩት፡፡ እናም መንገድ ያለው ውስጥህ ነው፡፡ አንተ ውስጥ መንገድ አለ፡፡
‹‹ምን አልባት ያ መንገዱ አልተጠረገ ከሆነ ጥረገው፤ ተጎድቶ ከሆነ ጠግነው፤ አርጅቶ ከሆነ አድሰው፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ቀላል ነው፡፡ ጊዜ ውሰድ፡፡ ለማየት ጊዜ ውሰድ፡፡ ወሳኙ የጨለማው መጠን አይደለም፡፡ ወሳኙ አንተ የሰጠኸው ጊዜ መጠን ነው፡፡ ለማሰብ የምትወስደው ጊዜና የምታስብበት መንገድ፡፡ ጊዜ ወስደህ ባሰብህ ቁጥር ያለኸው ጨለማ ውስጥ አለመሆኑን ታውቀዋለህ፡፡ እስኪ ትንሽ ጊዜ እንውሰድ››
ሁለቱም ጥቂት ጊዜ ተቀመጡ፡፡
ያ ልጅም ማየት ጀመረ፡፡
‹‹እስከዚያ በዓለም ላይ ታዋቂ የሆነውን ‹የተጠማውን ቁራ ታሪክ› ልንገርህ፡፡ ቁራው ውኃ ጠማውና በአካባቢው ወዲያና ወዲህ እያለ መፈለግ ጀመረ፡፡ ግን አላገኘም፡፡ በመጨረሻም በውኃ ጥም ወደቀ፡፡ ነገር ግን ተስፋ ለመቁረጥ አልፈለገምና እንደምን ብሎ ተነሥቶ አካባቢውን ማማተር ጀመረ፡፡ በሩቁም አንድ ገንቦ አየ፡፡ ወድቆ እየተነሣ ገንቦው ጋ ደረሰ፡፡ ሲያይ ጥቂት ውኃ ውስጡ አለ፡፡ ምንቃሩንን አስገብቶ ሊጠጣ ሲሞክር የገንቦው አንገት ጠባብ ስለነበር አልቻለም፡፡ ገንቦውን ሊያዘነብለው ሲገፋውም ዐቅሙ ተዳክሞ ነበርና ያንን ከባድ ገንቦ መግፋት አልተቻለውም፡፡
‹‹ማሰብ ጀመረ፡፡ መንገድ ከውስጥ ነውና ውስጡ መንገድ ፈለገ፡፡ መንገዱንም አገኘው፡፡ በአካባቢው ያሉትን ጠጠሮች እየለቀመ ወደ ገንቦው ውስጥ መጣል ጀመረ፡፡ ለብዙ ጊዜ ሲጥል ገንቦው በጠጠር እየተሞላ ውኃውም ወደ ላይ እየወጣ መጣ፡፡ በመጨረሻም የገንቦውን ታችኛውን ክፍል ድንጋዩ ሞላውና ውኃው ወደ ገንቦው አፍ ደረሰ፡፡ ቁራውም ጠጣ፡፡››
በታሪኩ ትረካ መካከል ልጁ አንዳች ቅርጽ ያለው ነገር ተመለከተ፡፡ መሥመር ያለው ነገር፡፡ ከወለሉ ጀምሮ ወደ ጣራው የተሠመረ፡፡ ዓይኑን ከታች ወደ ላይ እያንከባለለ ተከተለው፡፡ አንዳች የብርሃን መሥመር፡፡ ቀጭን የብርሃን መሥመር፡፡ ከታች ወደ ላይ ሄደና እንደገና ወደ ግራ ዞረ፤ ተከተለው፡፡ ከግራ ደግሞ ወደ ታች ተጠመዘዘ፤ አብሮትም ሄደ፡፡ ከዚያም ተመልሶ ወለል ላይ ደረሰ፡፡
‹‹ያ የብርሃን መሥመር ምንድን ነው›› አለው ጠቢቡን፡፡
‹‹ጠጋ ብለህ እየው››
ፈራ፡፡
‹‹አትፍራ ጨለማውን ሳትፈራ እንዴት ብርሃኑን ትፈራለህ፡፡ ምንጊዜም የማያውቁት ነገር ያስፈራል፡፡ ሂድ ተጠጋ፡፡
ሄደና ተጠጋ፡፡ የጣውላ በር በሚመስለው ነገር ዙርያ የሚገባ ብርሃን ነው፡፡
‹‹እስኪ ንካው›› አለው ጠቢቡ፡፡ እየፈራ እየደፈረ ነካ አደረገው፡፡ ጣውላ ነገር ነው፡፡
‹‹በምትችለው ዐቅም ሁሉ ግፋው›› አለው፡፡ ላቡ ጠብ እስኪል ገፋው፡፡ ሲጢጢጥ እያለ፤ በመጨረሻ ያ ጣውላ የመሰለ በር ነገር ወደ ኋላው ወደቀ፡፡ ያን ጊዜ በውጭ ያለው ብርሃን ፏ ብሎ ገባ፡፡ ዓይኑን ጨፈን አድርጎ ሲገልጠው በበሩ ፊት ለፊት ሰፊ መንገድ አለ፡፡
‹‹በሕይወትህ ለመለወጥ ከፈለግህ ሦስቱን መሠረታዊ ነገሮች አሁን ተምረሃለል››አለው፡፡
‹‹ምንድን ናቸው?››
‹‹መጀመርያ እምነት ነው፡፡ ምንጊዜም መንገድ አለ፡፡ ሊዘጋ የማይችል፤ ሊታጠር የማይችል፤ መንገድ አለ፡፡ እርሱም አንተ ውስጥ ነው፡፡ ሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ጊዜ ስጥ፡፡ ለማሰብ ጊዜ ይኑርህ፣ ለመፈለግ ጊዜ ይኑርህ፣ ምንጊዜም በፍለጋ ላይ ሁን፡፡ አሁን ያልታየህ ቆይቶ ይታይሃል፡፡ ነገር ለመቁረጥ እንጂ ተስፋ ለመቁረጥ አትቸኩል፡፡‹ገና አላገኘሁትም› በል እንጂ ‹የለም› አትበል፡፡ አለ፤ ግን አልደረስክበትም፡፡ መድረስ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል፡፡ ሦስተኛው ነገር ያገኘኸውን አጋጣሚ ንካው፡፡ ያገኘኸውን ብርሃን ንካው፡፡ ካልነካኸው በሩ ግድግዳ እንደሆነ ይቀራል፡፡ ከነካኸው ግን በሩ መንገድ ይሆናል፡፡ ብርሃን ማየትህ ብቻ ዋጋ የለውም፤ ብርሃኑ በሚገባ እንዳይገባ ያደረገውን ነገር መንካት አለብህ፡፡ እስኪወድቅና ብርሃኑ በሚገባ እስኪገባ፣ መንገዱም ወለል እስኪል መግፋት፡፡
‹‹ሳይነኩት በምኞት ብቻ የሚወገድ ችግር የለም፤ የሚከፈትም በር የለም፡፡ አየህ ማሰብ የብርሃን ጭላንጭልን አሳየህ፤ ጊዜ ሰጥቶ ማስተዋል ይህንን በር ገለጠልህ፤ መንካት ደግሞ መንገዱን አሳየህ፡፡ አሁን አይበቃህም››
‹‹ይበቃኛል››
‹‹ታድያስ አሁን ምን አለህ››
‹‹ገመድ አለኝ››
‹‹ሂድ ጊዜ ሰጥተህ፣ መጣፍ አገላብጠህ፣ ዐዋቂ ጠይቀህ፣ ግራ ቀኙን አስብ፡፡ ይህች ገመድ ሕይወትህን የመለወጫ ምክንያት ትሆንሃለች፡፡ የባለጸግነት መጀመርያ፣ የሥልጣን እርከን፣ የሊቅነት ፋና፣ የጀግንነት መንሥኤ ትሆንሃለች፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ የመታነቂያ መሣርያ ትሆንሃለች፡፡ ሁለቱም በእጅህ ነው፡፡››
አሰናበተውና ሄደ፡፡

No comments:

Post a Comment