የኢንተርኔት መብት አያያዝ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁናቴ በተመለከተ በየዓመቱ ጥናት የሚያደርገው “ፍሪደም ሐውስ” የሚባለው ታዋቂው
የአሜሪካ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የ2012
ዘገባውን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት እንዳላቸው እና ዓመታዊ ሪፖርታቸው በጉጉት እንደሚጠበቀው
“ሒዩማን ራይትስ ዎች”ን እንደመሳሰሉት ድርጅቶች ሁሉ “Freedom House”ም ሚዛን የሚደፋ ሪፖርት በማቅረብ የሚታወቅ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የተቋቋመ የአሜሪካ
ድርጅት ነው።
ሰሞኑን ይፋ ያደረገውን “FREEDOM ON THE NET 2012: A GLOBAL ASSESSMENT OF INTERNET AND DIGITAL MEDIA” የሚለውን ሪፖርት በማገላብጥበት ወቅት ድርጅቱ ጥናት ያደረገባቸው ዐበይት ጉዳዮች አትኩሮቴን ሳቡት። የዚህ ጥናት ዋነኛ ጭብጥ በ47 አገራት ያለውን የ“ኢንተርኔት መብት” ወይም ኢንተርኔትን በመጠቀሙ ሒደት ዜጎች ያላቸውን መብት መዳሰስ መሆኑን ዘገባው በመግቢያው ያትታል። በዚህም መሠረት ሦስት ዓይነት የእገዳ ደረጃዎችን በጥናቱ ማግኘቱን ያመለክታል። እነርሱም፦ የማይፈልጉትን የኢንተርኔት ውጤት ሙሉ በሙሉ የሚያግዱ፣ የማያግዱ እና እገዳ-በመጀመር ላይ ያሉ አገራት/ መንግሥታት በሚል ይከፍላቸዋል።
“አጋጅ አገራት” ያላቸው መንግሥታቱ በተለይም ከተቃዋሚዎቻቸው የሚመጡ አሉታዊ አመለካከቶችን ሙሉ በሙሉ የሚጨፈልቁ እና እገዳ የጣሉ አገራትን ሲሆን ይህንንም ለማድረግ መንግሥታቱ እጅግ ትልቅ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳቸውን ያትታል። በዚህ ዘርፍ ውስጥ “ባህሬን፣ ቻይና፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ቪየትናም፣ ሦሪያ፣ ታይላንድ እና ኡዝቤኪስታን” በቅደም ተከተል ተጠቅሰዋል።
ጥናቱ ስለነዚሁ አገራት ሲያብራራ “አገራቱ የኢንተርኔት ነጻነትን ማፈኛ የተለያዩ መንገዶችን” እንደሚጠቀሙ፣ ለምሳሌ በጦማሪዎች እና በኢንተርኔት ሰጪ ድርጅቶች ላይ ጫና እንደሚያደርጉ፣ ስለ መንግሥታቱ በጎ በጎ ነገር የሚያቀርቡ ሰዎችን በገንዘባቸው እንደሚገዙ/ እንደሚደልሉ፣ አሉታዊ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎችን ደግሞ እንደሚያስሩ፣ አሉታዊ አስተያየቶች እንዳይታዩ ማገጃ ቴክኒኮችን እንደሚጠቀሙ አስረድቷል።
ሁለተኛዎች ዓይነት አገሮች ደግሞ ነጻ የሆነ ኢንተርኔት አቅራቢ ድርጅቶች እንዲኖሩ ይፈቅዳሉ፣ ዜጎችም የፈቀዱትን ሐሳብ ለማንሸራሸር ሳንሱር የማይደረጉባቸው ናቸው። በዚህ ረድፍ ከተጠቀሱት መካከል አዘርባጃን፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ማሌዢያ፣ ቬኔዙዌላ እና ዚምባቡዌ ይገኙበታል። ጥናቱ እንዳመለከተው በነዚህ አገራት ያሉ መንግሥታት የማይፈልጓቸው ጉዳዮች ከኢንተርኔት እንዲከለከሉ እንደሚፈልጉ ቢያሳዩም ፍላጎታቸው በተግባር ተገልጦ ዜጎቻቸው ከኢንተርኔት አልተከለከሉባቸውም።
ጥናቱ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያነሳቸው “ክልከላ ለመጀመር ፍላጎች እንዳላቸው ያሳዩ አገሮች” ደግሞ ቤላሩስ፣ ስሪላንካ፣ ፓኪስታን እና ሩሲያ ሲሆኑ ጉዳዩን ለመተግበር ከመስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሰዋል ይላል። ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ማዕቀቦችን መጣል ቢጀምሩም ክልከላው ስልት ባለው እና ሕጋዊ ማጣቀሻ እየተሰጠው የተደረገ ባለመሆኑ መጠነ ሰፊ አይደለም። ክልከላው በዚህ መልክ የቀጠለ ቢሆንም በነዚህ አገራት ያሉ ዜጎች ኢንተርኔቱን የመጠቀም ደረጃቸውን ከፍ እያደረጉ፣ መብታቸውንም ለማስከበር እየጣሩ መሆኑን ጥናቱ ይጠቅሳል።
ከጥናቱ ሐተታ ውስጥ ቀልቤን የሳበው የከልካይ አገራት የክልከላ ዘዴ እና ሁኔታ የሚለው ክፍል መሆኑን በመግቢያዬ ጠቅሻለኹ። እነዚህኑ በመጠኑ እንመልከት።
ከልካይ መንግሥታቱ ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች የመጀመሪያው “አዳዲስ ሕጎችን በማውጣት በነጻነት ሐሳብን መግለጽን መከልከል እና እንዲህ የሚያደርጉትንም ማሰር” የሚለው ነው። በዚህ ደረጃ ከተጠቀሱት አገራት መካከል ግንባር ቀደም የሆነችው ኢትዮጵያ ጦማሪውን እስክንድር ነጋን ማሰሯ በምሳሌነት ተጠቅሷል። በግብጽም ከሆስኒ ሙባረክ መውረድ በኋላ ብዙ ጦማርያን (ብሎገርስ) መታሰራቸውን አንስቶ በዚህ በኩል መጥፎ ሪኮርድ ካላቸው አገራት መካከል ቻይናን፣ ሶሪያን፣ ቪየትናምን እና ኢራንን አንስቷል።
በሁለተኛነት የተጠቀሰውና የኢንተርኔት ነጻነት ከልካይ መንግሥታቱ ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል የሆነው ጉዳይ ሰዎችን በገንዘብ በመደለል ስለ መንግሥታቱ በጎ ነገር (እንዲጽፉ፣ እንዲናገሩ፣ እንዲያሰራጩ) ማድረግ እንዲሁም አሉታዊ ሐሳብ የሚያስፋፉትን ሰዎች ድረ ገጾች በዘዴ በመስረቅ (hijacking and hacking) በስማቸው ተገቢ ያልሆነ ነገር መለጠፍ የሚለው ነው።
ሰዎችን (Paid Commentators) በገንዘብ መደለል ማለት መንግሥታቱ ባላቸው ኃይል የሕዝቡን ገንዘብ ለዚሁ ጉዳይ በማዋል ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎችን በኢንተርኔት ላይ በማሰማራት የተለያዩ ደጋፊ ሐሳቦችን ማሰራጨት፣ የኢንተርኔት የውይይት አቅጣጫዎችን ማስቀየር፣ ተቃዋሚዎችን በተለያየ መንገድ ማዋረድ እና ክብራቸውን መንካት፣ ስለ ተቃዋሚዎች መሠረት የለሽ አሉባልታዎችን በመንዛት ማሳጣት እና ክብራቸውን መንካት ወዘተ ናቸው። ጥናቱ በምሳሌነት በጠቀሳት በኩባ መንግሥት አንድ ሺህ ብሎገሮችን (ጦማሪዎችን) በመመልመል የተቃዋሚ ጦማሪዎችን ስም በማጥፋት ተግባር ላይ አሰማርቷቸዋል።
ባህሬን እና ማሌዢያን በመሳሰሉት አገራት ደግሞ መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው የሌሎች አገሮች የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሚሠሩ ድርጅቶችን (Public relation Firms) በመቅጠር ስለነርሱ ሆነው እንዲከራከሩላቸው ያደርጋሉ። የሩሲያ መንግሥት አሌክሲ ናቫልኒ የተባለ አንድ ታዋቂ ጦማሪን (ብሎገር) ስም ለማጉደፍ ከ320 ሺህ ዶላር በላይ ሥራ ላይ እንዳዋለ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በቻይና ደግሞ ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው አፍቃሬ መንግሥት ሰዎች (ሕዝቡ “የ50 ሳንቲም ፓርቲ” ይላቸዋል) በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ ሪፖርቱ ያብራራል። በኢራን ደግሞ ከመንግሥት ገንዘብ የሚቀበሉ 40 ኩባንያዎች መንግሥቱን የሚደግፉ የተለያዩ ዘገባዎችን እንዲሰሩ ከ56 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተከፍሏቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህ መንግሥታት በገንዘባቸው ከሚሠሩት አፈና ባሻገር የማይደግፏቸውን ጦማርያን፣ የሚዲያ ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢንተርኔት አድራሻዎች ማለትም ፌስቡክና ትዊተሮችን፣ ድረ ገጾችንና ብሎጎችን በመመዝበርም ይታወቃሉ። ወደ ተቃዋሚዎቻቸው የኢንተርኔት አድራሻዎች ሰብረው በመግባት የማይፈልጉትን ዘገባ፣ ዜና፣ ሐተታ ይለውጣሉ፤ የድረ ገጾቹን ባለቤቶች ሙያዊ ክብር ለማዋረድ እና ተቀባይነት ለማሳጣት የማይሆን ነገር ይለጥፋሉ፤ የሚለዋወጧቸውን ኢ-ሜይሎች ያነብባሉ፤ በክስ ወቅትም ለፍርድ ቤት በማስረጃነት ያቀርባሉ።
ከዚህ ሁሉ የኢንተርኔት ላይ አፈናና መብት ጥሰት በኋላ መንግሥታቱ አሉታዊ አስተያየት በሚያቀርቡባቸው ሰዎች ላይ ግልጽ የአካል ጉዳትም ያደርሳሉ። በቻይና፣ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ሶሪያና ቪየትናም በኢንተርኔት ላይ ሐሳባቸውን የሰጡ ሰዎች ከተያዙ በኋላ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። በባህሬን የኢንተርኔት መወያያ መድረክ አስተናባሪ የሆነ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አካላዊ ሰቆቃ ተፈጽሞበት ተገድሏል።
በኩባ ከማሰር ይልቅ ተቃዋሚዎች ላይ አካላዊ አደጋ ማድረስን መርጠዋል። በቻይና የቱኒዚያን ዓይነት የፀደይ አብዮት ለመቀስቀስ ጥሪ አደረጉ የተባሉ ጦማሪያን (ብሎገሮች)፣ የሕግ ባለሙያዎችና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ላይ ከባድ ሰቆቃ ተፈጽሟል። እነዚህ መንግሥታት የኢንተርኔት ተቃዋሚዎቻቸው ላይ ድብደባ እና ሰቆቃ ከመፈጸም በተጨማሪ ለብቻ በማሰር፣ እንቅልፍ በሚነሳ ዘዴ በማሰቃየት፣ እና ለበሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ በማሰር እንደሚያሰቃዩ ታሳሪዎቹን የጠቀሰው ይህ ጥናት አትቷል።
ጥናቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣ ነው ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደግሞ ጦማርያን እና መንግሥታትን በኢንተርኔት የሚቃወሙ ሰዎች ላይ “ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች” አደጋ ማስጣል፣ በሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወቅት ፖሊሶች ለይተው ጉዳት እንዲያደርሱባቸው ማድረግ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሷል። ለምሳሌ በፓኪስታን የኢንተርኔት ካፌዎችን በቦንብ ማጋየት የተዘወተረ ሆኗል። ከሥራ ማባረር፣ ከትምህርት ማገድ፣ ወደ ውጪ አገር እንዳይሄዱ መከልከል ወዘተ የተለመደ ጉዳይ ነው።
ከዚህ ሁሉ ጋር ኢንተርኔት ላይ ያለው ቁጥጥር፣ እገዳ፣ ክትትል እና መራቀቅ እየጨመረ መጥቷል። ኢ-ሜይሎችን መበርበር፣ በድምጽ የሚደረጉ ንግግሮችን ማዳመጥ/ መቅዳት፣ “ኢንስታንት ሜሴጆች” ልውውጦችን እና ቴክስቶችን መመርመር የመንግሥታቱ የእገዳ አካላት ናቸው።
አፋኝ መንግሥታት በምን ዓይነት የአፈና ጥልቀት እና ምጥቀት ላይ እንዳሉ የጋዳፊ አስተዳደር ሲወድቅ የተገኙ የተለያዩ ማስረጃዎች ይፋ መሆናቸው ይታወሳል። የሆስኒ ሙባረክ መንግሥት ከአውሮፓ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች የገዛቸው ዜጎችን መሰለያ የተለያዩ መንገዶች ተገኝተዋል። ይህ ሁሉ ሆኖም ግን ጋዳፊም፣ ሙባረክም ከመውደቅ አላመለጡም።
“በፍሪደም ሐውስ” ጥናት በኢንተርኔት ነጻነት ረገድ በአፍሪካ ስማቸው የተመሰገኑትና “ነጻ ናቸው” የተባሉት አገሮች ኬኒያ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው። ግብጽ፣ ቱኒዚያና ናይጄሪያ ገሚስ ነጻ በሚለው ዘርፍ ተመድበዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ ከቻይና እና ከሳውዲ አረቢያ እንዲሁም ከኢራን ተርታ “ነጻነት የማይሰጡ” ከሚባሉት ጎራ ተመድባለች።
ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com
No comments:
Post a Comment