- ግብረሰዶም ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ መጠን እየተስፋፋ ነው
- አብዛኞቹ የከተማዋ ማሳጅ ቤቶች የወሲብ ንግድ እንደሚያጧጡፉ ታውቋል
- ከ3600 በላይ ህገወጥ ልማዶችና የወሲብ ድርጊቶች የሚፈፀምባቸው ቤቶች አሉ
- ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ፖሊሶችና ነጋዴዎች የአነቃቂ እፆች ተጠቃሚ ናቸው
- በእርቃን ጭፈራ ቤቶች ደጃፍ ከሚቆሙ መኪኖች አብዛኛዎቹ የመንግስትና የንግድ ታርጋ የለጠፉ ናቸው
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት ይፋ የተደረገው ጥናት “መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ተጽእኖ” በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን ከ3600 በላይ ህገወጥ የወሲብ ድርጊት የሚፈፀምባቸው ቤቶች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡
ወደ 3 ሚሊዮን ከሚጠጋው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ውስጥ 52.4 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ወጣቶች እንደሆኑ ያመለከተው ጥናቱ፣አብዛኞቹ ሴቶችና ወጣቶች ላልተገቡ መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች እየተጋለጡ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ የከተማዋ ሴቶችና ወጣቶች ለሱስ አስያዥ እፆችና ለአልኮል መጠጦች እንዲሁም ለመጤ ባህል ወረርሽኞች ተጋላጭ ሆነዋልም ብሏል፡፡
ለዚህ እንደዋና ምክንያትነት የቀረበው በከተማዋ የቀንና የሌሊት ጭፈራ ቤቶች፣ የራቁት ዳንስ ቤቶች፣ የግብረሰዶም ወሲብ መፈፀሚያ ቦታዎች፣ የሺሻና የጫት ቤቶች፣የቁማር ቤትና ህገወጥ የቪዲዮ ቤቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እያደገ መምጣቱ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በአሥሩም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የፖሊስ መምሪያዎች የተሰበሰበ መረጃ እንዳመለከተው፣ 3691 ቤቶች ለእነዚሁ ተግባራት ተከፍተው በከተማዋ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ቤቶች መበራከትና በስፋት መሰራጨት ሳቢያም በርካታ ወጣቶች ለወንጀል ተግባራት፣ ለአደገኛ እፆች ሱሰኝነት፣ ለዝርፊያ፣ ለስደት ለጐዳና ተዳዳሪነት፣ ለኤችአይቪና ተያያዥ በሽታዎች እንዲሁም ላልተፈለገ እርግዝና ተዳርገዋል፡፡
ትናንት ይፋ የተደረገው ጥናት፤የቀንና የማታ ጭፈራ ቤቶችን፣የእርቃን ዳንስ ቤቶችን፣ የማሳጅ፣ የቪዲዮ፣ የአደንዛዥ ዕጽ መጠቀሚያ፣ የግብረሰዶማውያን ማዘውተሪያ ቤቶችንና የመኪና ላይ ወሲብ መፈፀሚያና ጫት መቃሚያ ቦታዎችን በሚገባ በመቃኘት በተሰበሰበ መረጃ የተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ጥናቱ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የተመሳሳይ ፆታ የወሲብ ግንኙነት ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ ከሚገምተውና ከሚያስበው እጅግ በበለጠ መልኩ ተስፋፍቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርጊቱ እየተስፋፋ በማህበረሰቡ ላይ የስነልቡና፣ የማህበራዊ ግንኙነት፣ የትምህርት ማቋረጥና፣ የጤና ችግር እያስከተለ ነው ተብሏል፡፡
ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት፣ የ2ኛ ደረጃና የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች፣ በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች፣ እንዲሁም በማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች የችግሩ ከፍተኛ ተጠቂዎች እንደሆኑ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር በመሄድ በወሲብ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች ቁጥርም እየተበራከተ መሆኑንና ድርጊቱ በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ ታውቋል፡፡ አዲስ አበባ የጭፈራ ቤቶችና የራቁት ዳንስ ቤቶች ከቀን ወደቀን እየጨመረ የሚሄድባት ከተማ መሆኗን የጠቆመው ጥናቱ፤ በተለይ ከማህበረሰቡ ወግና የአኗኗር ዘይቤ የወጡ፣ ግለሰባዊ ክብርን የሚፈታተኑ፤የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን የሚያጠፉ የእርቃን ጭፈራ ቤቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡
በእነዚህ የእርቃን ዳንስ ቤቶች በራፍ ላይ ከሚቆሙ መኪናዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ የመንግስት ታርጋ የለጠፉ መሆናቸውን ይፋ ያደረገው ጥናቱ፤የግልና የንግድ ታርጋዎችን የለጠፉ መኪኖች በብዛት እንደሚታዩና የተወሰኑ የዲፕሎማትና የእርዳታ ድርጅቶች መኪኖችም እንደሚገኙበት ጠቁሟል፡፡ ከእርቃን ዳንስ ቤቶች ጠባቂዎችና ከእርቃን ደናሾቹ ጋር በተደረገ ኢ-መደባዊ ውይይት በቦታው መጥተው የሚገለገሉም ሆነ በየቤታቸው በግል በማስጠራት አገልግሎት ከሚያገኙት ደንበኞች መካከል የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የውጭ ዲፕሎማቶችና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እንደሚገኙበት የጥናቱ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡
የእርቃን ደናሾቹ ወርሃዊ ገቢ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ሳይጨምር ከ3ሺ-14ሺ ብር እንደሚደርስ የሚጠቁመው ጥናቱ፤ለዚህ ሥራ የሚመለመሉት ወጣት ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅ ያለ፤መልካም የሰውነት አቋም ያላቸው፤ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ከሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች እንደሆኑም ያመለክታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወሲብና ወሲብ ነክ ጉዳዮች የሚፈፀሙባቸው ማሳጅ (መታሻ) ቤቶችን መጠቀም እየተለመደ መምጣቱን ይፋ ያደረገው መረጃው፤ከመታሻ ቤቶቹ አብዛኛዎቹ ደረጃቸውን በጠበቁ ትላልቅ የመኖሪያ ቤቶችና በትላልቅ የንግድ ህንፃዎች ላይ እንደሚገኙና የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡ በእነዚህ ቤቶች በሚሰጠው የመታሸት አገልግሎት ሥር በተለየ ሁኔታ ለምርጫ የሚቀርቡት ድርጊቶች ህብረተሰቡን ከባህልና ሥነምግባር ውጪ ለሆነ ባህርያት እየዳረጉት እንደሆነና የማሳጅ አገልግሎት መስጫ ቤቶቹም ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱ በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
የጥናቱ አዲስ ግኝት ሆኖ የተገለፀው ሌላው ጉዳይ በመኪና ውስጥ የሚፈፀሙ ጫት የመቃምና የወሲብ ድርጊቶች መስፋፋት ነው፡፡ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በቦሌ በሚገኙ ትላልቅ ህንፃዎች፣ ባሮችና ሬስቶራንቶች ሥር፣ በመንገዶች ግራና ቀኝ እንዲሁም በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ላይ በመኪና ውስጥ በተናጥል እና በጥንድ በመሆን ጫት መቃም፣ ወሲብ መፈፀምና ሌሎች ያልተገቡ ተግባራትን መከወን በስፋት እየታየ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ይሄም ተግባር ከተማዋን እጅግ አደገኛ ወደሆነ አደጋ ውስጥ እየከተታት እንደሆነ የጠቆመው ጥናቱ፤በአገሪቱ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በቀጥታ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ለእንዲህ ያሉት ድርጊቶች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጿል፡፡
በሬዲዮ የሚቀርቡና በወሲብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የቀጥታ ውይይት ስርጭቶች ከአስተማሪነታቸው ይልቅ ወጣቶችንና ህፃናትን ለወሲብ ተግባር የሚገፋፉና ያዳመጡትን በተግባር ላይ ለማዋል ከቤት ወይም ከጐረቤት ጀምረው ወደሴተኛ አዳሪዎች እስከመሄድ እያደረሳቸው እንደሆነ የጥናቱ ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡ ሱስ አስያዥ እፆችን መጠቀም፣ ሀሺሽ፣ ሺሻ፣ ሄሮይን እና የአልኮል መጠጦች ለዚህ ተግባር ሰፊ ድርሻ እንዳላቸው የጠቆመው መረጃው፤ ዕድሜያቸው ከ25-30 አልፎ አልፎም በአስራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህፃናት የማሪዋና ወይንም የካናቢስ ተጠቃሚዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጿል፡፡
በመረጃው መሠረት፤ በተለያየ የመንግስት ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ማህበራዊ ደረጃ የሚሰጣቸው ግለሰቦችና በኢኮኖሚው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ባለሙያዎችና የንግድ ሰዎች በዚህ መጤና ያልተገባ ልማድ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ የእነዚህ ግለሰቦች በዚህ ያልተገባ ተግባር መጠመድ አርአያ ሊሆኑለት ለሚገባው ህብረተሰብ የሚያስተላልፈው አፍራሽ መልዕክት ከፍተኛ ነው ያለው ጥናቱ፤ በአገሪቱ እድገትና የልማት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የዝቅጠት አደጋ እያደረሰ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ለህገወጥ ተግባራቱ መስፋፋት በአገሪቱ ያለው ህግ እርስ በርሱ የሚጣረስ መሆኑን ጥናቱ እንደምክንያት አቅርቧል፡፡ “መንግስት በአንድ በኩል ለቪዲዮ ቤቶች ፍቃድ ይሰጣል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጐጂነቱን ያወራል፤በየጊዜው ሺሻ ቤቶችን የማጥፋት ዘመቻ ያካሂዳል፣ሺሻ ማጨሻውን እየሰበሰበ ያቃጥላል፤ነገር ግን ይህንን ሥራ የሚከለክልና የሚቀጣ ህግ ስለሌለ ዕቃውን መልሰው በመግዛት ሥራውን ይጀምራሉ፡፡” ያለው የጥናቱ ሪፖርት፤ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፈቃድ ባገኙበት የሥራ ዘርፍ ስለመሰማራታቸው የሚከታተልና ከመስመር ሲወጡም የሚቀጣ የህግ አግባብ አለመኖሩ ለህገወጥ ተግባራቱ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡
No comments:
Post a Comment