Thursday, 3 January 2013

ይህች ሃገር የሊቀ ሊቃውንቶች ወይስ የአምባገነኖች ?

  • እጅግ የተከበሩ የዓለም የሥነ ጥበብ ሊቀ ሊቃውንት የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ሐውልታቸው እስካሁን አለመሠራቱ ቅሬታ ፈጥሯል
  • እንኳን የራሱን ሐውልት የሀገር ሐውልት ሊያሠራ የሚያስችል ገንዘብ ያለው ሰው ነው፡፡ እስካሁን ሐውልቱ አለመሠራቱ ግን በጣም ያሳፍራል በዓለም ደረጃ ትልቅ ክብር የተሰጠውን ሰው ትንሽ ሐውልት ሳንሠራ ሜዳ ላይ ሲወድቅ በጣም ያሳፍራል
  • ለሞያው ክብር ሲታገል የነበረ በመሆኑ ሊከበር ይገባል”
  • በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ስም የሚሰየም ፋውንዴሽን ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ በመጠናቀቁ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
 
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሊቀ ሊቃውንት የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ጥቅምት 13 ቀን 1925ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ በምትገኘው የሸዋ ነገሥታት ከተማ አንኮበር ላይ ጥቅምት 13 ቀን 1925 ዓ.ም. ከአባታቸው ከአቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ተወለዱ።

 የዓለም የሥነ ጥበብ ሊቀ ሊቃውን የነበሩት እጅግ የተከበሩት  አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፤ ከልጅነታቸው ጀምሮ የጋለ የሰዓሊነት ስሜት ያደረባቸው  በትምህርት ቤት ይሰጡ በነበሩት እንደ ኬምስትሪ፣ ሂሳብና ታሪክ በመሳሰሉ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት እንኳን ዘወትር በእርሳስም ሆነ በብዕር፣ ንድፎችንና ሥዕሎችን በመተለምና በመሳል ሥራ ተጠምደው ይታዩ እንደነበር ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለ ሰዓሊው ሥራዎች በፃፉት መጣጥፍ ላይ ጠቁመዋል፡፡ ገና ሕፃን ሳሉ በጣሊያን ወረራ ወቅት አደጋ የደረሰባቸው እኚህ ሰው ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ ከሌሎች የአርበኞች ልጆች ጋር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወደ አርበኞች ትምህርት ቤተ ተላኩ። በወቅቱ በኮተቤ በተከፈተው አዲሱ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ።

1940 .ም እንግሊዝ አገር ሄደው ትምህርት እንዲከታተሉ አፈወርቅ ተመረጡ። የኢትዮጵያ መንግሥት የላካቸው የማዕድን ኢንጅነር እንዲሆኑ ነበር። ሆኖም ሲልቪያ የአፈወርቅን ፍላጎትና ዝንባሌ በመገንዘባቸው ወደ ኢትዮጵያ ደብዳቤ ተጻጽፈው ሥዕል እንዲያጠኑ አስፈቀዱላቸው፡፡ ፍቃዱም ከተገኘ በኋላ Central school of Arts & Crafts ተመዝግበው ገቡ:: ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ለከፍተኛ ጥናት በስመ ጥሩው የሎንዶን ዩኒቨርሲቲ  ኪነ ጥበብ ማዕከል Faculty of Fie Arts at Slade የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ተማሪ በመሆን ገቡ። እዚህ በስዕል፣ ቅርጽ እና በስየቃ (architecture) ጥናቶች ላይ አተኩረው ተመረቁ የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ በየጠቅላይ ግዛቶቹ እየተዘዋወሩ፣ በየቦታው እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና የብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆዩ። “ምኞቴ በዓለም የታወቀ ኢትዮጵያዊ የኪነ ጥበብ ምሑር መሆን ስለነበር፣ የአገሬን ወግና ባሕል ጠንቅቄ ማወቅና ማጥናት እንዳለብኝ አውቄያለሁ። ሥራዬ የዓለም ንብረት ይሆናል ነገር ግን በአፍሪቃዊነት ቅመም የጣፈጠ ሥራ ነው የሚሆነው።” ይሉ ነበር።
ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላም በ1946 .ም የመጀመሪያውን የግል የሥዕል ትዕይንት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ለሕዝብ አቅርበዋል። ከዚያም በኋላም በፋሽስት እጅግ የተጎዳውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊ እምዕላፍ ህሩይ ጋር በመሆን አስጊጠዋል።
1950 .ም ደግሞ ሠዓሊው የአፍሪካ አዳራሽን  የአገሪቱና የአፍሪካ ኩራት የሆነውን 150 ካሬ ሜትር በላይ የሚሸፍነውን አፍሪካ የቀኝ አገዛዝ ውስጥ መኖሯንና ኀዘኗን ከዚያም የልጆቿን ትግልና አዲስ ተስፋቸውን የሚያመለክት የመስታወት ሥዕል አበርክተዋል።
የዓለም የሥነ ጥበብ ሊቀ ሊቃውን የነበሩት እጅግ የተከበሩት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ1961 .ም ያስገነቡት ቪላ አልፋ የአክሱም፣ የጎንደር፣ የላቢላ፣ የሶፍኡመር ዋሻ ተምሳሌት ተደርጎ የተሠራ ሲሆን ቪላው የአርቲስቱ የጥበብ መፍጠሪያ፣ የጥበብ ማሳያና መኖሪያ ቤትም ጭምር ነበር።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ የራሳቸውን ምስል ያሰፈሩበት ሥዕል የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሠዓሊ ሥዕል ተብሎ በጣሊያን አገር ፍሎረንስ ከተማ በዝነኛው ኡፊትዚ ጋለሪ ተቀምጧል። በቋሚነት ከሚገኙ ስብስቦችም አንዱ ነው። ሠዓሊው ልዩ የንድፍና የሥዕል ቅብ ስጦታ ያላቸው ከመሆኑም በላይ አስደናቂና ዘርፈ ብዙ ሠዓሊ ነበሩ፡፡
ለአርቲስቱ የተሰጡትን ሽልማቶች ዘርዝሮ መጨረስ ያስቸግራል። ሁሉም የተሰጡት ላበረከቱት የሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸው ነው፡፡ በሀገር ውስጥ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ከውጭ ከፈረንሳይ ከሩሲያ ከአሜሪካ፣ ከጣሊያን፣ ከሴኔጋል፣ ከቼኮዝላቫኪያ፣ ከግብጽ፣ ከቡልጋሪያ፣ ከእንግሊዝና ከሌሎች አገሮች ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ 200 ታላላቅ የአገር መሪዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ደራሲያንና ሠዓሊያን ተመርጠው የአገራቸውን ስምና አጭር የሕይወት ታሪካቸው ተጽፎ ወደ ጨረቃ ሲላክ የአርቲስቱ ስምም ሰፍሮ ወደ ጨረቃ ተልኳል። ግልባጩም በቤታቸው ውስጥ ይገኛል።
እኒህ ታላቅ ሰው ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ከፍተኛ የሥዕል ገፀ በረከት አበርክተዋል። ዓለምም አክብሯቸዋል። ሚያዝያ 2 ቀን 2004 .ም አርቲስቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የኢትዮጵያ መኩሪያና መከበሪያ የሆኑት የዓለም የሥነ ጥበብ ሊቀ ሊቃውን የነበሩት እጅግ የተከበሩት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መቃብር ሐውልት እስካሁን አልተሠራለትም። እስካሁን ሐውልት አለመሠራቱ በጣም እንዳሳዘናቸው የአርቲስቱ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት ፀሐፊ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላት ይናገራሉ። «ለሀገሩ ለቆመ ሀገሩም ለእሱ መቆም አለበት። እሳቸው ለሀገራቸው አምባሳደር ነበሩ። ለሀገራቸውም በሙያቸው ትልቅ ሥራ ነው ያከናወኑት። « እንኳን የራሱን ሐውልት የሀገር ሐውልት ሊያሠራ የሚያስችል ገንዘብ ያለው ሰው ነው፡፡ እስካሁን ሐውልቱ አለመሠራቱ ግን በጣም ያሳፍራል፡፡ ብዙ ሰው እየታዘበን ነው ያለው። በዓለም ደረጃ ትልቅ ክብር የተሰጠውን ሰው ትንሽ ሐውልት ሳንሠራ ሜዳ ላይ ሲወድቅ በጣም ያሳፍራል። ብዙ ፈረንጆች እየመጡ እሳቸው ያረፉበትን ይጎበኛሉ። በዚህ ሁኔታ መታየቱ ሁላችንንም መንግሥትን ጨምሮ በጣም ያሳፍራል። ስለሆነም ቶሎ ሐውልቱ መቆም አለበት። ይህ የአገር ገበና ነው። መንግሥት ሐውልታቸውን  በአስቸኳይ መሥራት አለበት ይላሉ
 
የኢትዮጵያ ሠዓሊያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሠዓሊ ሥዩም አያሌው በመቃብራቸው ላይ «እስካሁን ሐውልት አለመቆሙ ደስ የማይል ነው» ይላል። ለቀብራቸው የተቋቋመው ኮሚቴ ከዚህም ባለፈ የመቃብር ሐውልታቸውን ለመሥራት አስቦ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ «ወዳጆቻቸውና ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ ሰዎችም ለማሠራት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን በህግና በመንግሥት  የሚወሰኑ ነገሮች አሉ፡፡ በመንግስት በኩል ድጋፍ አልተገኘም  ተጨባጭ ሥራ አልጀመረም
 
የአርቲስቱ ቤት በንጉሡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተሠራ ሲሆን ደርግ ወርሶት ወታደሮች ይኖሩበት ነበር። ቤቱ ለአርቲስቱ የተመለሰውም በዚህ ሥርዓት ነው። አሠራሩ ለመኖሪያነት ሳይሆን ለሕዝብ አገልግሎት በሚውል መልኩ የተደራጀ በመሆኑ ለሥዕል  ለሙዚየም የሚሆን አሠራሩም የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያንፀባርቅ፣ ሥራዎቻቸውም የሀገር ሀብት ስለሆኑ ቤታቸውን ወደ ሙዚየምነት በመቀየር በዚያው ቢጠበቁና ለሕዝብ ክፍት ቢሆኑ መልካም ነው የሚል ሃሳብ አላቸው አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአገር ፍቅርን የሚያስተምሩ ታላቅ ጠቢብ ነበሩ።



 



 
 
 





No comments:

Post a Comment