Friday, 4 January 2013

ሐና ጎዴፋ የዩኒሴፍ አዲስ የሰብዓዊ መብት አምባሳደር ሆና ተሾመች

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት /ዩኒሴፍ/ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷን ታዳጊ ሐና ጎዴፋን አዲስ የሰብዓዊ መብት አምባሳደር አድርጎ ሾመ።

የ15 ዓመት ዕድሜ ያላት ሐና የሰብአዊ መብት አምባሳደር ሆና መሾሟን የሚያረጋግጥ ስምምነት ፥ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ ሚስተር ሻድራክ ኦሞል ጋር ተፈራርማለች።
ሚስተር ኦሞል በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ፥  ድርጅቱ ሐናን የሰብዓዊ መብት አምባሳደር አድርጎ የሾመበት ምክንያት ለሕፃናት ፣ ለእኩዮቿና ለሴቶች ጥሩ አርአያ በመሆኗ ነው።
ድርጅቱ ሐና በሰብአዊ መብት ሥራ ላይ ባሳየችው ጠንካራ አቋምና ካቋቋመችው የገቢ ማሰባሰቢያ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ሕፃናት በትምህርት ዙሪያ የሚደርስባቸውን ችግር ለማቃለል ያከናወነቻቸው ስራዎች ለአምባሳደርነት እንዳበቋት ገልጿል ።
ሐና ''ሁል ጊዜ ሕፃናትን ለመርዳት አስባለው ሆኖም ግን እንደዚህ ያለ ከፍተኛ ዕድል አጋጥሞች አያውቅም ፥  በጣም ጠቃሚ መልዕክት ለኢትዮጵያ ሕፃናት የማስተላልፈው የትምህርትን ዋጋ ነው ። ትምህርት የውጤት ቁልፍ ነው።" ስትልም ተናግራለች።
ሕፃናት ባለ ብሩህና ጠቃሚ አስተሳሰብ ባለቤት በመሆናቸው በትክክል የትምህርት ዕድል ካገኙ ዓለምን የመለወጥ አቅም አላቸው ፥ ስትል አክላለች ሀና በንግግሯ።
የድርጅቱ አምባሳደር በመሆን በፈቃደኝነት በመሥራት የሕፃናት ትምህርት የማግኘት ፣ የጤና ፣ የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት  ፣ የውኃ ፣ የንጽህና ፣ የእኩልነት ፣ የመጠበቅና የተሳትፎ መብቶቻቸው እንዲሟሉ ጥረት እንደምታደርግም ገልጻለች።
ነዋሪነቷ ካናዳ የሆነው ሐና  ከዚህ በፊት 400 ሺህ እርሳሶችን ከውጭ በማሰባሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናት መርዳቷ የሚታወስ ሲሆን ፥ ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 600 የመማሪያ መጻህፍትንም አበርክታለች።


No comments:

Post a Comment