Wednesday 20 March 2013

የፓርቲ አባሎቻቸው በሰንሰለት ታስረው እስከሚደሙ መደብደባቸውን፣ የኢሜይል ፓስወርድ አምጡ እየተባሉ መገረፋቸውንና በደል እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል፡፡


የፋሺስት ኢጣሊያ የአዲስ አበባ ገዢ በመሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ላስጨፈጨፈው የጦር ወንጀለኛ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ፣ በአገሩ ኢጣሊያ የተሠራለትን ሐውልትና መናፈሻ ለመቃወም፣ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ሲወጡ መታሰራቸውን የገለጹት ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያምን ጨምሮ፣ ስድስት የሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚዎችና ሌሎች ከ30 በላይ ሰዎች መጋቢት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. በዋስ መለቀቃቸውን ተናገሩ፡፡
‹‹ለፋሽስቱ የጦር ወንጀለኛ ለማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ ክብር መስጠት የአባቶቻችንን መስዋዕትነት ማራከስ ነው›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ሰላማዊ ሠልፍ ያስተባበሩት፣ ባለራዕይ የወጣቶች ማኅበርና ሰማያዊ ፓርቲ ሲሆኑ፣ ዋና ዓላማውም በኢትዮጵያውያን ላይ ሞት፣ እንግልትና ግፍ ለፈጸመው የጦር ወንጀለኛ ሐውልት ሊገነባለትና መናፈሻ ሊሠራለት እንደማይገባና የኢጣሊያ መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ ለማድረግ እንደነበር አዘጋጆቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በመሆኑም ለአሥር ቀናት ሰላማዊ ሠልፉ እንዲሚደረግ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መነገሩንና የሚመለከተው የመንግሥት አካል በደብዳቤ መጠየቁን የገለጹት አዘጋጆቹ፣ ቀኑ ደርሶ ወደ መነሻው የካቲት 12 የሰማዕታት ሐውልት አደባባይ ሲጓዙ የገጠማቸው፣ ሠልፉ ተጀምሮ ወደሚያበቃበት ኢጣሊያ ኤምባሲ መሄድ ሳይሆን በተቃራኒው ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ መላው ዓለም እያወገዘው የሚገኘውን የግራዚያኒ ሐውልት ግንባታና መናፈሻ ሥራ ለመቃወም መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት የካቲት 12 ሰማዕታት ሐውልት አደባባይ መገኘታቸውን የገለጹት ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ በድንገት አንድ የፖሊስ ኃላፊ ደርሰው ‹‹አልተፈቀደላችሁም፤ ሕገወጥ ሠልፍ ማድረግ አትችሉም፤›› በማለት በስፍራው የተገኙትን ዜጎች በመማታት፣ የሞባይል ስልክ በመቀማትና በመጎተት ወደ መኪና ውስጥ አስገብተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው ተናግረዋል፡፡ 

ዶክተር ያዕቆብ እንደገለጹት፣ በሕጉ እንደተቀመጠው ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የሚመለከተው አካል ተጠይቆ 48 ሰዓታት ካለፈው እንደተፈቀደ ይቆጠራል፡፡ ይኼም ተደርጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደ በመሆኑ ፈቃድ አያስፈልገውም፡፡ የተፈቀደ መብት ነውና፡፡ የፖሊስ ኃላፊው ግን ‹‹ይኸ ሕገወጥ ሰልፍ ነው፤ ፈቃድ የላችሁም፤ ካላችሁ አሳዩ›› ከማለት ውጭ ሊሰሙ ፈቃደኛ  ባለመሆናቸው ወደጣቢያ ማምራታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ወደ አራት ፖሊስ ጣቢያዎች ያህል በማዘዋወር ካንገላቷቸውና ቃላቸውን ከተቀበሏቸው በኋላ፣ ቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ማደራቸውን የገለጹት ዶክተር ያዕቆብ፣፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን፣ በአንዲት ጠባብ የማሰሪያ ክፍል ውስጥ ብዙ እስረኞች ታስረው አንዱ ባንዱ ላይ ተዛዝሎ እንደሚያድር መመልከታቸውንና እሳቸውም አንዱ ተኝቶባቸው ማደራቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ታስረውበት ያደሩበት ክፍል የሰብዓዊ መብትን የሚረግጥና ሰብዓዊነትን ዝቅ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ያዕቆብ፣ በማግስቱ ከትናንትና በስቲያ ከታሰሩበት ተጠርተው ጃንሜዳ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የቀበሌ መታወቂያ ያለው ዋስ እየጠሩ መለቀቃቸውን አውስተዋል፡፡ 

እንዲታሰሩ ያደረጉት ‹‹ለኢሕአዴግ አንድ ፋይዳ ያለው ነገር እናድርግ›› በማለት ያሰቡ ዝቅተኛና የሰላማዊ ሠልፍ ትርጉምና ዓላማ ያልገባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሚናገሩት ዶክተር ያዕቆብ፣ ይኼንንም ለማለት ያስቻላቸው ፖሊስ 48 ሰዓታት ጠብቆ ፍርድ ቤት ሳይወስዳቸው በጠዋት ሊለቋቸው የቻለው፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲሰሙ ስህተት መሆኑን ተገንዝበው በመፀፀታቸው ሳይሆን አይቀርም በማለት ነው፡፡ 

ሰላማዊ ሠልፉን ለማዘጋጀትና ለማስተባበር ያነሳሳቸው ዋናው ቁም ነገር፣ አገራዊ አጀንዳ ስለሆነ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ይልቃል ጌትነት ናቸው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ስድስት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚዎች መታሰራቸውን ገልጸው፣ ስለሰላማዊ ሠልፉ ለአሥር ቀናት ሕዝቡን ከመቀስቀሳቸውም በተጨማሪ፣ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ከስድስት በላይ ማኅበራትንም መጋበዛቸውን አስታውሰዋል፡፡ 

‹‹ያልተፈቀደ ሠልፍ ነው›› በማለት ተቆርቋሪ ዜጎችን ማሰር አግባብ አለመሆኑን የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ራሱ መንግሥት ሊያደርገው የሚገባን ተግባር ሌሎች ለምን አደረጉ ወይም ቀደሙኝ ብሎ አላስፈላጊ ተግባር መፈጸም ፍፁም ስህተት መሆኑን በመጠቆም፣ እሳቸውም እንደ ዶክተር ያዕቆብ ድርጊቱን ተቃውመዋል፡፡ 

‹‹መከራ እንደደረሰብን ሳይሆን ማስተማርና ዋጋ መክፈል ስለነበረብን የሆነው ሁሉ ሆኗል፤›› ያሉት አቶ ይልቃል፣ ኢሕአዴግ ሁሉንም ነገር ዝግትግት ከማድረግ ይልቅ፣ ነገሩን ቀለል በማድረግ ፈታ ፈታ ባለ ሁኔታ መንቀሳቀሱ እንደሚጠቅመው መክረዋል፡፡ ሕጉ የሚፈቅደውን ሁሉ እንደሚያደርጉ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀጣይም ሕጉና ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው  መሠረት ሰላማዊ ሠልፍ በመጥራት እንደሚተገብሩትና ለዚህ የሚከፈል ዋጋም ካለ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡ 

ፖሊሶች በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች እያዘዋወሩ ቃላቸውን እንደተቀበሏቸው፣ ዶክተር ያዕቆብ እንዳሉት ባደሩበት ጣቢያ ሰብዓዊ ክብርን በሚነካ ሁኔታ ታስረው ማደራቸውን፣ በርካታ ወጣቶች ታስረው ማየታቸውንና እጅግ ጠባብ ክፍል ውስጥ 38 ታሳሪዎች ተደራርበው ማደራቸውን የገለጹት አቶ ይልቃል፣ እሳቸው ባይደበደቡም የፓርቲ አባሎቻቸው በሰንሰለት ታስረው እስከሚደሙ መደብደባቸውን፣ የኢሜይል ፓስወርድ አምጡ እየተባሉ መገረፋቸውንና በደል እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል፡፡

ሰላማዊ ሠልፉ በየትኛውም ዓለም እንደሚደረግ፣ ከዓላማው ያፈነገጠ ተግባር እንኳን ለማድረግ ቢሞከር በውኃ፣ በአስለቃሽ ጭስና በሌሎች ዜጎችን በማይጎዱ ቁሳቁሶች ሠልፉ እንዲበተን እንደሚደረግ የሚናገሩት ዶክተር ያዕቆብ፣ በዜጋ ላይ ቃታ እንደማይሳብና ወደ እስር ቤት እንደማይወረወር ልምድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ 

ግራዚያኒ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ መርዛማ ጋዝ በመጠቀም የፈጃቸውን ዜጎችና እንስሳት የሚያስታውስና ታሪክን ያነበበ ዜጋ ሁሉ እንደሚቆረቆር እምነታቸው መሆኑን የገለጹት ዶክተሩ፣ በተገነባለት ሐውልትና መናፈሻ ምክንያት በትናንትናው ዕለት በ25 የኢጣሊያ ከተሞች የተቃውሞ ሠልፎች መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኢጣሊያ ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ የግራዚያኒን ድርጊት እንደማይደግፉት መናገራቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

‹‹ኢትዮጵያውያን ግራዚያንን ሊያወግዙ ወጥተው ታሰሩ ሲባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ሊባል ይችላል?›› በማለት የሚጠይቁት ዶክተር ያዕቆብ፣ ኢትዮጵያውያን አሁንም ቢሆን ሰላማዊ ሠልፍ አድርገው ማውገዝ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፖሊሶች ከመከልከል አልፈው ወደ መደብደብና ማሰር የገቡት፣ “ከ97 ወዲህ ሠልፍ ተደርጎ ስለማይታወቅ እስከ መጨረሻው እንዳይደረግና ሕዝቡ ፈርቶ እንዲቀመጥ ሊሆን ይችላል፤” የሚል ግምት እንዳላቸው የሚናገሩት ዶክተር ያዕቆብ፣ ኢሕአዴግ ሰላማዊ ሠልፉን ስለሚፈራ እያደረገው ያለው ነገር የሕዝቡን ብሶት ያባብሰዋል እንጂ ሊያፍነው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ሰው በተፈጥሮ ነፃነት፣ ፍትሕና ክብር ስለሚፈልግ መታፈኑ ለጊዜው ሊገታው ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ የፈጀ የነፃነት፣ የፍትሕና የክብር ፍለጋ ትግል በመሆኑ እንጂ በአፈና ቢሆን ኖሮ  በመንግሥቱ ጊዜ ሊያበቃ ይችል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 

ፖሊስ ሰዎችን ወደ ፍትሕ ቦታ መውሰድ እንጂ መደብደብ እንደማይችል በሕግም ሆነ በፖሊሳዊ ሳይንስ የተከለከለ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተሩ፣ ዜጋው ሥራውን ቢያውከው እንኳን ማስቆም ወይም ወደጣቢያ መውሰድ፣ አልሄድ ቢለው እንኳን ተሸክሞ መውሰድ እንጂ መደብደብ እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡ እንኳን ሰው እንስሳትን እንኳን መማታት እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ 

ፖሊስ አላግባብ እንደደበደባቸው እንዳሰራቸውና በኋላም በቀበሌ መታወቂያ ዋስ እንደለቀቃቸው ስለተናገሩት ዜጎች ማብራሪያ እንዲሰጠን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተን ብንጠይቅም ሊሳካልን ስላልቻለ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ወርራ በነበረበት የአምስት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንንና ከአሥር ሚሊዮን በላይ እንስሳትን መጨፍጨፏ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን የግራዚያኒ ተግባር የሚያሸልምና የሚያስወድስ መሆኑን ለመግለጽ በስተደቡብ በምትገኘው አፊሌ በምትባል የኢጣሊያ ከተማ ሐውልትና መናፈሻ እንደተሠራለት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ተቃውሞው ግን በመላው ዓለም ቀጥሏል፡፡ 

No comments:

Post a Comment