Thursday, 30 May 2013

የግንቦት 7 ንቅናቄ 4ኛ ጉባኤ ህዝቡ ወደ ትግሉ እንዲቀላቀል ጥሪ አቀረበ

የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነት፣ የዲሞክራሲ ንቅናቄ 4ኛ ጉባኤ ከግንቦት 11 – 19/2005 አ/ም በበርካታ ወቅታዊ፣ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት እና የድርጅቱን አዲስ ም/ቤት በመምረጥ ወያኔን በማስወገድ ረገድ ሊከተል የሚገባውን ጠቋሚ አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን ከተሳታፊው በመውሰድ ወሳኝ የሆነ ውይይት አድርጓል።

ንቅናቄው ከተለያዩ አለማት በአባላት የተወከሉ ጉባኤተኞች እና በተለያዩ የስራ ክፍል የሚገኙትን የድርጅቱን አባላት ያሳተፈ፤ ከዚህ በፊት ከተደረጉትም ጉባኤዎች እጅግ የላቀ አባላት የተገኙበት ነበር።
ጉባኤው የነበረውን የም/ቤት ሪፖርት፣ የስራ አስፈጻሚ እንዲሁም የኦዲትና ማናጅመንት ኮሚሽን፣ የግልግልና ዳኝነት ኮሚቴን እና የፋይናንስ ሪፖርቶችን በማዳመጥ ጥልቅ የሆነ ወይይቶች አደርጓል።
የግንቦት 7 ንቅናቄ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች፤ ደርጅቱ የጀመረውን ወያኔን የማስወገድ ትግል በየትኛውም አቅጣጫ አስፈላጊ ሆኖ የታመነበትን ማናቸውም መንገድ ሁሉ በመጠቀም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘረኝነትን ስርአት ድባቅ መምታት፤ አልፎም ዘላቂ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አስቸኳይና ማንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ግዴታው አድርጎ መውሰድ ያለበት አጣዳፊ ስራ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የሰላም አየርና የዲሞክራሲ ጮራ ሁሌም የሚፈነጥቅባት፣ ህዝብ ካለፍርሃትና ሰቀቀን ወጥቶ የሚገባባት፣ ህዝብ በነጻነት የፈለገውን ፓርቲ የሚመርጥበት፣ የሚያወርድበት፣ ስልጣን የህዝብ መሆኑን የሚረጋገጥበት፣ የመንግስት አካላት ለህዝብ ተጠያቂ የሚሆኑበት፣ ነጻ ሚዲያ ለመልካም አስተዳደር ግንባታ የሚያገለግልበት፣ ፍትህ ለሁሉም በእኩል የሚሰጥበት፣ ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክልሎች የመኖር፣ ሀብት የማፍራት፣ ቤተሰብ የመመስረት፤ ከቦታ ወደ ቦታ ያለምንም ገደብ የሚንቀሳቀሱበት መብት እንዲኖራቸው፣ እና የሃይማኖት ነጻነት ይኖረን ዘንድ የድርጅቱ ጉባኤተኞች ሙሉ መሰዋእት ለመክፈል ዝግጁዎች ነን ሲሉ በድጋሚ ቃል በመግባት መራራ የሆነውን ትግል እጅ ለእጅ ተያይዞ ተራራውን ለመውጣት እና ለማቋረጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ከ4ኛ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ጉባኤተኛው የግንቦት 7ን 5ኛ አመት ምስረታ ታሪካዊ ቀን አስቦ ውሏል። በዚህ በግንቦት 7, 1997 ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተሳትፎ ፍትህ፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ በሀገሪቱ ይሰፍን ዘንድ ለዘመናት ተጭኖት የነበረውን ጫና ተቋቁሞ የወያኔን ስርአት በድምጹ የጣለበት ልዩ ቀን ነበር። ግንቦት 7, ሁሌም በታሪክ የሚዘከር ልዩ እለት ነው።
ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያዊ ትውልድ በግንቦት 7 ያሳየውን ልበሙሉነት፣ ጀግንነት፣ መሰዋእትነት፣ አንድነትና ወንድማማችነት ለዘለአለም ሲታወስ ይኖራል። ይህንኑ በ97 የተጀመረው የትግል ፍሬ፤ ውጤት ያፈራ ዘንድ አስፈላጊ ያላቸውን ትግሎችን እያደረገ እንደሆነ ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነት፣ የዲሞክራሲ ንቅናቄ 5ኛ አመቱን ከአባላቱ ጋር ሆኖ ሲዘክር ተወያይቷል። ይህም ታሪካዊ የህዝብ ድል ቀን፤ በጠመንጃ ሃይል የነጠቀውን ወያኔን ለማስወገድ እና የህዝብን ድምጽ ለማስመለስ ድርጅታችን ማናቸውንም መንገድ በመጠቀም የሚያደርገውን የትግል ጅማሮ ግብ ለመምታት አሁን ከአለንበት በተሻለ በመጠናከር መሆኑንም ስምምነት ተደርሷል። ድርጅታችን ካለፈው ጉባኤ ጀምሮ ድርጅቱ ያደረገውን እንቅስቃሴ በስፋት ገምግሞ፤ በስራ ሂደት የታዩ ድክመቶችን አፍረጥርጦ ተወያይቶ፤ የታዩትን ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ የሚጎለብቱበትን ሁኔታ ተመልክቶ፤ በድርጅቱ የእስትራቴጂ አካሄድ ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን አድርጎ፤ እነኝህን የእስትራቴጂ አቅጣጫዎች በተቀላጠፈ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ወሳኝ የመዋቅር ለውጦችን አጽድቆና ይህን አዲስ መዋቅር የሚያስፈጽሙ ያመራር አባላትን መርጦ፤ በከፍተኛ የጓዳዊ መንፈስና ልዩ በሆነ የትግል ወኔ ጉባኤውን በድል አጠናቋል::
በመሆኑም ግንቦት 7፣ በግንቦት 7 የገባውን ቃል ኪዳን ዛሬም ህያው መሆኑን ሲያረጋግጥና ትግሉ ከመቼውም በበለጠ ጽናትና ቁርጠኛነት እንደሚገፋበት ቃል ሲገባ፣ የሀገራችን ህዝብ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ; አዛውንት፣ ወጣት፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ ዘር ቀለም ሳይለያችሁ በግንቦት 7/ 1997 የተሰረቀውን፣ የተነጠቅነውን የህዝብ መንበረ-ድምጽ ስልጣን ወደ ትክክለኛ ባለቤቱ እንዲመለስ የምናደረግውን የትግል ጉዞ ትቀላቀሉ ዘንድ ጥሪያችን ይድረሳችሁ!
የሀገራችን ወጣቶች ሆይ፡ ለነጻነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ቱርፋቶች መሰዋእት ሆናችሁ መሰዋእትነታችሁ በጥቁር ህዝብ የኢትዮጵያ ታሪክ ገድል ውስጥ ለዘላለም ተከትቦ ይቀመጥ ዘንድ ኢትዮጵያዊ የሞራል ግዴታ አለባችሁ፡፡ ግንቦት 7 ትግሉን ጀምሯል። ኑ ተቀላቀሉ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment