Monday 6 May 2013

የፌደራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት እንዳሳየን ለአንድ ብር በምንጨነቅበት ወቅት ሚሊዮኖች መቀለጃ ሆነዋል


የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2004 ዓ.ም. ኦዲት ሪፖርት ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ቀርቧል፡፡ ሪፖርት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን በመረጃ በተደገፈ ግልጽ አቀራረብ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የገንዘብ አያያዝና ሪፖርት አደራረግ ያለውን ድክመትና ችግርም በግልጽ አሳይቷል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተርን እናመሰግናለን፡፡ ሒሳባቸውን በአግባቡ የማይዙና ተገቢውን ሪፖርት የማያቀርቡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እንወቅሳለን፡፡ በሪፖርቱ የቀረበው ችግር እጅግ አሳሳቢ ችግር ነውና፡፡ 

የሪፖርቱን ቁም ነገር ስንዳስስ የሚከተሉትን አሳሳቢ ችግሮች እንገነዘባለን፡፡

-    1.4 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ አለ፡፡
-    313.6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ሳይመልሱ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡
-    897.5 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ክፍያና ወጪ ተደርጓል፡፡
-    ያልተወራረደው 1.4 ቢሊዮን ብር በ57 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የታየ ነው፡፡
-    15 ድርጅቶች ወይም መሥሪያ ቤቶች ከልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ምንጮች ገቢ የሚሰበስቡ ቢሆኑም፣ የገቢ ሪፖርት የማያደርጉ በመሆኑ ኦዲት ማድረግ አለተቻለም፡፡
-    በ13 ናሙና መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 132.364 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቧል፡፡
-    22 መሥሪያ ቤቶች 13.8 ሚሊዮን ብር ማስረጃ የሌለው ወጪ አድርገዋል፡፡
-    30 መሥሪያ ቤቶች ደንብና መመርያ በመጣስ 353.568 ብር የሚያወጣ ግዥ ፈጽመዋል፡፡
-    በውሎ አበልና በትርፍ ሰዓት ተመን 11 መሥሪያ ቤቶች 1.4 ሚሊዮን ብር አባክነዋል፡፡
-    በኤርፖርት ተርሚናል የተሰማራ አንድ የግል ድርጅት ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ለመቀበል ፈቃድ ሳይኖረው ከአሥር ዓመታት በላይ እየሠራ እንደሚገኝና ተቆጣጣሪ አካላት ያደረጉት ምንም ነገር የለም፡፡
-    134.7 ሚሊዮን ብር ብድር ያልመለሱ የመንግሥት ድርጅቶች ሲኖሩ፣ የመንግሥት ትርፍ ድርሻ የሆነ 18.549 ሚሊዮን ብር ሳይከፍሉ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ 44.254 ሚሊዮን ብድር ያለባቸው ሲሸጡም የገዛው አካል ለመንግሥት መከፈል የነበረበትን ያልከፈለ መሆኑን፣ ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ.

ይህ አሳሳቢና አስደንጋጭ ሪፖርት ነው፡፡ በትክክልና በግልጽ በመቅረቡ የኦዲት ተቋሙ ሥራውን ሠርቷል ብንልም፣ ሥራቸውን በአግባቡ ያልሠሩ እጅግ በርካታ የመንግሥት ድርጅቶች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡

ይህን ሪፖርት ያዳመጠው ፓርላማ ራሱም ቁጭትና ንዴት የታየበት መስሏል፡፡ ስርቆትና ማጭበርበር ካለ ያሳስበናል ብለው አስተያየት የሰጡ የፓርላማ አባላት አሉ፡፡ ፓርላማውና የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴም ወደ ዕርምጃ ለመግባትና የሚቀጡትን ለማስቀጣት ዕርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

ገንዘቡ ተሰርቆና ተዘርፎ ሊሆን ይችላል፤ ባይሰረቅና ባይዘረፍም ዶክመንት ላይኖረው ይችላል፤ ሁሉም ዓይነት ችግር ከቦት የተከሰተ ነገርም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም አለ በዚያ ግልጽ በሆነ መንገድ የምናስቀምጠው ሀቅ አለ፡፡ የአገርና የሕዝብ ሀብት እየባከነ ነው፤ ክትትልና ቁጥጥር እየጠፋ ነው፤ ኃላፊነት የሚሰጠው ኃላፊ እየታጣ ነው፡፡ 

በእንደዚህ ዓይነት አሠራርና በእንደዚህ ዓይነት አካሄድ ምን ያህል እንጓዛለን? የ2004 ዓ.ም. ኦዲት ችግርን ይህን ያህል ካሳየን ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታትስ ምን ያህል ገንዘብ ባክኗል? ምን ያህል አላግባብ ወጪ ተደርጓል? ምን ያህል በአበልና በመሳሰሉት ወጥቷል? ምን ያህል አለአስፈላጊ ግዥ ተካሂዷል? ምን ያህል ሥርዓት አልባና ሕገወጥ ድርጊት ተፈጽሟል? ምን ያህል የቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል? ከ2004 ዓ.ም. ችግር በላይና የእጥፍ እጥፍ ነው፡፡ 

ከዚህ በመነሳት ከፓርላማና በመንግሥት ሦስት ዓበይትና አስቸኳይ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ እንጠብቃለን፤ እንጠይቃለን፡፡

ዕርምጃ አንድ 

በፌደራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት የቀረቡትን ዝርዝር ችግሮች የሚያይ፣ የሚያጠና፣ ምክንያታቸውን ለይቶ የሚያውቅና የሚያሳውቅ፣ ያስከተሉትን አደጋ በግልጽ የሚያቀርብና መወሰድ ስላለበት ዕርምጃ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ የኦዲት ተቋሙ ያለበትና ሌሎች አካላትን ያካተተ ልዩ ቡድን እንዲቋቋም ማድረግ፡፡ ይህ ካልተደረገ ቀልድና ፌዝ ይሆናል፡፡ የአገር ሀብት ነው፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ የልማት እንቅፋት ነው፡፡ 

ስለሆነም ዝርዝር ሪፖርቱና የሚወሰደው ዕርምጃ ለሕዝብ መቅረብ አለበት፡፡ ይህ ማለት ያጠፉ ግለሰቦች ስም ዝርዝርና ተጠያቂነታቸው ከሚወሰደው ዕርምጃ ጋር ይቅረብ ማለታችን ነው፡፡

ዕርምጃ ሁለት

በዘላቂነት እንዲህ ዓይነት አካሄድ እንዳይደገም ምን ዓይነት ተቋማዊ ሥራ ይሠራ? ምን ዓይነት ሥርዓት እንከተል? የሚል መመርያ መውጣት አለበት፡፡ ከጥፋት በኋላ እዬዬ ከማለት ጥፋት እንዳይፈጸም መከላከሉ ይበጃል፡፡ ስለዚህ በተቋምና በአሠራር ደረጃ ይህንን የሚከላከል አስፈላጊው ነገር ሁሉ ከአሁኑ መዘርጋት አለበት፡፡  

ለግል ድርጅቶች ‹‹ደረሰኝ ሳይቀበሉ አይክፈሉ›› እየተባለ የመቆጣጠሪያ ማሽን እየገባ (ተገቢ ነው!)፣ ለመንግሥት ድርጅት ግን ተቆጣጣሪ የሌለው ሥርዓት አልባ አካሄድ መፍቀድ ተገቢ አይደለምና፡፡

ዕርምጃ ሦስት 

ይህ ችግር የታየው በፌደራል ደረጃ ነው፡፡ በክልል ደረጃ የተደረገው የኦዲት ሪፖርትስ ምን ይላል? ይህ ችግር የለም አንልም፤ ካለማስረጃም መውቀስ አንፈልግም፡፡ ግን በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ሕዝብ የማወቅ መብት አለውና፡፡ ገንዘቡ ነውና፡፡ ስለዚህ በክልል ደረጃም የሁሉም ክልሎች ሪፖርት ለሕዝቡ ይቅረብለት፡፡

ብዙ የሚነሳ ጉዳይ ቢኖርም ለጊዜው እዚህ ላይ እናቁም፡፡ አንድ ብር በሚያሳስበን ጊዜ ሚሊዮኖች መቀለጃ እየሆኑ ነው፡፡


No comments:

Post a Comment