አዲስ አበባ ታህሳስ 2 2005 ተቋርጦ የነበረውና በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝና በጋዜጣው አሳታሚ ማስተዋል የህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ላይ በመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ወንጀል የተመሰረተው ክስ ተንቀሳቀሰ
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጉዳያቸው የታየው የፌደራሉ አቃቢ ህግ በ11 ሶስተኛ ወር 2005 ላይ ክሱ እንዲንቀሳቀስ ያቀረበውን አቤቱታ ተቀብሎ ነው ።
የተከሳሽ ጠበቆች ከችሎቱ 2ኛ ተከሳሽ ባለመቅረቡ ድርጅቱን ወክላችሁ ምላሽ መስጠት ትችላላችሁ? ወይ ተብለው ተጠይቀውም እንደማይመለከታቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል ።
ጠበቆቹ ምንም እንኳ አቃቢ ህግ ክስ የመመስረት ፣ የማቋረጥና መልሶ የማንቀሳቀስ ሰልጣን እንዳለው በህግ ቢደነገግም አሁን እንዲንቀሳቀስ የተደረገበት አካሄድ ግን ግልፅ አይደለም ብለዋል ።
አቃቢ ህግ በበኩሉ በቂ ተያያዥ ማስረጃዎችን አደራጅቶ የፍርድ ሂደቱ እንዲቀጥል በማሰብ ክሱን ማቋረጡን ያስረዳ ሲሆን የተለያዩ የህግ አንቀፆችን በማጣቀስ ይርጋ እስካላገደው ድረስ በፈለገበት ሰዓት ክሱን ማንቀሳቀስ እንደሚችል ገልጿል ።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ከዚህ በፊት ክሱ ተቋርጦ በነበረበት ወቅት በምን ሁኔታ ላይ ይገኝ እንደነበር እንዲሁም የዋስትና ሁኔታውንም ግልፅ በሆነ ሁኔታ እንዲያስረዳ አቃቢ ህግን ጠይቋል ።
አቃቢ ህግ ክሱ ከተቋረጠ በኋላ ተከሳሹ ግለሰብ ከማረሚያ ቤት በዋስ መውጣታቸውን በማስታወስ ለአሁኑ ጉዳይ ተመጣጣኝ ዋስትና በድጋሚ በማቅረብ ውጭ ሆነው ቢከታተሉ ቅሬታ እንደሌለው አስረድቷል።
በዚሁ መሰረት ችሎቱ ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሽ ተመስገን ደሳለኝ የ50 ሺህ ብር ዋስ ወይም 50 ሺህ ብር በማስያዝ የዋሰትና መብታቸው እንዲከበር በማዘዝ ፥ ሁለተኛ ተከሳሽ ማስተዋል የህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ለጥር 24 2005 ዓመተ ምህረት መጥሪያ ደርሶት እንዲቀርብ በድጋሚ ታዞል።
No comments:
Post a Comment