ላለፉት ሀያ አንድ ዓመታት ግፈኛው የህወሃት/ኢሕአዴግ ሥርዓት በአገራችን ኢትዮጵያና ህዝቦችዋ ላይ ያደረሰውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ በደልና መከራ ሁሉም የሚያውቀው ነው። በአሁኑ ጊዜ ሥርዓቱ “የመለስን ራዕይ እናሳካለን” በሚል መፈክር/ፈሊጥ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣውን እና አምባገነናዊ አገዛዙን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አድማጭ እስኪሰለቸው ድረስ እየለፈፈ ይገኛል። የኢትዮጲያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት በቅርቡ ይህ ዘረኛ ሥርዓት በወገኖቻችን ላይ ያደረሰውን በርካታ ግፍና በደል በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጲያዊያንና ለዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ በማሳወቅ፣ ድርጊቶቹን አጥብቆ እንደሚያወግዝ ይገልፃል። ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምንታት፤ የህወሃት/ኢሕአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ በወገኖቻችን ላይ ካደረሳቸው በርካታ የሰው ልጅ መብት ረገጣዎች፣ ግፍና በደሎቸ መካከል የሚከተሉት በዋናናት የሚነሱና በጥብቅ የሚወገዙ ናቸው::
1. የህወሃት/ኢሕአዴግ ሥርዓት በአገራችን ሕዝብ ላይ የሚያደርገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግልፅ እንዲወጣ ካደረጉት የቅርብ ጊዜ ክስተቶች መሃል ዓብይ የሚባለው፣ በሙስሊም ሀይማኖት ተከታዮች እምነትና የውስጥ አስተዳደር በሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ነው። አክራሪነትን ለመዋጋት በሚል ሰበብ፤ የሀይማኖት መሪዎች እንዴት እንደሚመረጡ በመወስን፣ ይህንን የተቃወሙ አማኞችን በመደብደብ፤ በማሰርና በመግደል፣ “አኬልዳማ” የሚል አሸባሪ የፈጠራ ፊልም በሚቆጣጠረው ቴሌቪዥን በማሳየት፣ መፍትሔ ለመፈለግ የተመረጡትን ግለሰቦች በማሰር፣ የፈለጋቸውን የሀይማኖት መሪዎች በቀበሌ
በማስመረጥና በእስር የሚገኙትን የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ለመጠየቅ የመጡትን ሰዎች በማንገላታት ለማስፈራራት መሞከሩ።
2. የህወሃት/ኢሕአዴግ ሥርዓት፣ የህሊና እስረኞች በሆኑ ወገኖቻችን ላይ በፈጠራ የአሸባሪነት ክስ የተለያየ የእስራት ውሳኔ ከማስተላለፉ ባሻገር፤ በሕገ ወጥነትና በተለመደ ዘዴው ሌሎች ተቃዋሚዋችን ለማስፈራራት የእስክንድር ነጋንና የአንዱአለም አራጌን ንብረት መውረሱ፤ ሥርዓቱ ይቃወመኛል ብሎ የሚያምንበትን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡንም ለመጉዳት፣ በጋራ የተመዘገበን ንብረት መውረሱ ነው።
3. ይህ የግፍኛ አገዛዝ በሕገ ወጥነት ቤትን በመውረስ ብቻ አልተወሰነም። ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች የተሰሩትን ከሰባት ሺህ በላይ የሆኑ ቤቶችን በሕገወጥ መንገድ የተሰሩ ናቸው ብሎ አፍርሷል። በዚህም ምክንያት በብዙ አስር ሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት፣ አዛውንት፣ ሴቶችና ጎልማሳዎች ሜዳ ላይ ፈሰው እንዲቀሩ አድርጓል።
እነዚህ ለብርደና ለውርጭ የተዳረጉት ግለሰቦች መሬቱን ከገበሬ ማህበር እንደተረከቡና በቤታቸውም ከአራት እስከ አምስት ዓመት እንደኖሩበትና ቤታቸውም የፈረሰው በአጭር ማስጠንቀቂያ መሆኑም ተረጋግጧል። ይህ አሳዛኝ ድርጊት “ድህነትን ታሪክ አደርጋለሁ” እያለ በየእለቱ በሚፎክረው ሕገ ወጥ ሥርዓት የተፈፀመ ድርጊት ነው።
4. የህወሃት/ኢሕአዴግ ሥርዓት ሥረ-መሠረቱ ለመበሰበሱ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ በገብሮ ቀበሌ በአንድ የኢሕአዴግ የፍትህና ጸጥታ ሹምና ሶስት ግብረ አበሮቹ አማካኝነት የተፈፀመው እጅግ ኢሰብዓዊና አስፀያፊ ተግባር ዋና ማስረጃ ነው። አንድን ግለሰብና ባለቤቱን ልብሳቸውን በማስወለቅ፣ አደባባይ ላይ እርቃናቸውን በማሰር፣ እንዲሁም ህዝብ
በተሰበሰበበት አደባባይ ከሀገራችን ባህል ውጭ የሆኑ የተለያዩ አስፀያፊ ወሲብነክ ድርጊቶችን እንዲፈፅሙ አስገድደዋቸዋል። ይህ እጅግ የሚያስደነግጥና የሚያሳዝን ተግባር አልበቃ ብሏቸው ነፍሰ ጡሯን ሴት በሰደፍ በመምታት የስድስት ወር ጽንሷን እንድታስወርድ አድርገዋታል።
5. ህወሃት በተለመደው ሁኔታ የራሱን ሕገ-መንግስት በመጣስ ሁለት ተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በመሾም የተለመደውን የአፈና የዘረፋና የግፍ አገዛዙን ለመቀጠል ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።
6. በዚህ ባሳለፍንው ሳምንት ሥርዓቱ፤ የሰላማዊ ፓርቲ መሪዎችና ታጋዮች በነበሩ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የውጭ ቋንቋ መምህርና የመድረክ ፓርቲ አመራር አቶ በቀለ ገርባ፤ የኦህኮ ፓርቲ አመራር አቶ አልባና ሌልሳና እና ሌሎች ስምንት ተከሳሾች ላይ በፈጠራ የሽብርተኝነት ወንጀል በመፈረጅ ከ 3 እስከ 13 አመት እንዲታሰሩ ውሳኔ አስተላለፏል።
የኢትዮጲያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት ይህ ዓይነት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የአጠቃላይ የስርዓት ችግርና ዝቅጠት የሚፈጥረው መሆኑን ለመላው ዓለም ሕዝብ ያሳውቃል። ምክር ቤቱም የህወሃት/ኢሕአዴግ ሥርዓት ተወግዶ፣ በምትኩም በአገራችን ኢትዮጲያ የሰው ልጆች መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት የሚከበርበት ሥርዓት እንዲመሰረት የሚያስፈለገውን ሕዝባዊ ትግል እያካሄደ መሆኑን ያስታውቃል። በአገራችን ኢትዮጲያ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቼ ይቆማል የሚለው ጥያቄ የኢትዮጲያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት እንዲመሠረት ካደረጉት ዋና፣ አንገብጋቢና መንሥዔ ጉዳዮች አንዱ ነው። ምክር ቤቱ ሰፊውን የኢትዮጲያ ሕዝብ በማደራጀትና የትግል ተሳታፊ በማደረግ መርሆ እንደ መመሥረቱ መጠን፣ በማንኛውም ኢትዮጲያዊ ዜጋ፣ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ ሕብረተሰብ ወይም ጎሳ ላይ ግፍና በደል እንዳይደርስ በፅናት ይታገላል። ለወደፊቱም እነኚህ ግፍና በደሎች በማያዳግም ሁኔታ እንዲወገዱ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጲያዊን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ የተቻላውን ጥረት፣ ጫናና ተፅዕኖ እንዲያደርግ ይጠይቃል። ምክር ቤቱም ኢትዮጲያዊያን ይህንን የዘቀጠ የህወሃት/ኢሕአዴግ ሥርዓት የሚቀይሩበትን መንገድ ለመፈለግ፣ የጋራ ትግሉን ለማመቻቸትና በትግሉም የቀጥታ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያላሰለስ ጥረቱን እያካሄደ ነው። እያንዳንዱም ኢትዮጵያዊ፣ በአገርውስጥና በውጭ አገር ያሉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የሁሉም ሀይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማሕበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ እነዚህን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያውግዙ በተጨማሪ ይጠይቃል። እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት፣ ግፈኛውን የህወሃት/ኢሕአዴግ ሥርዓት እንዲያስወግዱ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ይህን ዘረኛ ሥርዓት ለማሰወገድ ቁልፉ የያንዳንዱ ሃገር ወዳድ ዜጋ መሳተፍና መደራጀት ነው። የሽግግር ም/ቤቱ አመራር
No comments:
Post a Comment