Saturday, 15 December 2012

ተዘጋጅተን ጠብቀን ዕድል ሳትመጣ ብትቀር ይሻላል ፡፡

ድህነት ባደቀቃት የሚያሚ ቀዬ የተወለደው ሌስ ብራውን በወላጆቹ ስር ለማደግ አልታደለም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን መንትያ ወንድሙም ከህፃንነቱ ጀምሮ ወላጆቹን አያውቃቸውም፡፡ ሁለቱም በጉዲፈቻ እናታቸው በማሚ ብራውን እንክብካቤ ነው ያደጉት፡፡ ሌስ ቀዥቃዣና ያለ ዕረፍት የሚለፈልፍ ቀባጣሪ ስለነበር ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸው ልጆች በሚማሩበት ልዩ ት/ቤት ነበር ትምህርቱን የተከታተለው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀውም በዚያው ት/ቤት ነበር፡፡ ከዚያም የሚያሚ ቢች ከተማ የፅዳት ሠራተኛ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ የእሱ ህልም ግን ዲጄ መሆን ነበር፡፡ 
  
ማታ ማታ በባትሪ ድንጋይ የሚሰራውን የቤተሰቡን ሬዲዮ ይዞ ወደ አልጋው በመሄድ፣ ከአካባቢው ሬዲዮ ጣቢያ የሚሰራጨውን የዲጄዎች ወሬና ሙዚቃ ያደምጣል፡፡ የወለል ፕላስቲክ ምንጣፉ በተቀደደው ጠባብ ክፍሉ ውስጥ ምናባዊ የሬዲዮ ጣቢያ በመፍጠር፣ የፀጉር ብሩሽ እንደማይክራፎን እየተጠቀመ ዲጄነትን ይለማመዳል - አዳዲስ የወጡ የዘፈን አልበሞችን በህይወት ለሌሉ (ጐስት) አድማጮቹ እያስተዋወቀ፡፡ አሳዳጊ እናቱና ወንድሙ በስሷ ግድግዳ በኩል ስለሚሰሙት “መለፍለፉን ትተህ አርፈህ ተኛ!” እያሉም ይጮሁበት ነበር፡፡ ሌስ ግን ፈፅሞ አይሰማቸውም፡፡ በራሱ አለም ተመስጦ የራሱን ህልም ይኖራል፡፡

አንድ ቀን የከተማውን ሳር አጭዶ ሲያበቃ፣ በምሳ የእረፍት ሰዓቱ በድፍረት ተነስቶ ወደ አካባቢው የሬዲዮ ጣቢያ ይሄዳል፡፡ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ቢሮም ይገባና ዲጄ ለመሆን እንደሚፈልግ ይነግረዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ቁሽሽ ያለ ቱታ የለበሰውንና ኬሻ ባርኔጣ ያጠለቀውን ወጣት ትክ ብሎ እየተመለከተው “ከዚህ በፊት በሬዲዮ ስርጭት ላይ ሰርተሃል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ሌስም “በፍፁም ጌታዬ! አልሰራሁም” በማለት ይመልሳል፡፡
“እንግዲያውስ ላንተ የሚሆን ስራ የለንም” ወጣቱ ሌስ አልተከራከረም፡፡ በትህትና አመስግኖ ከጣቢያው ወጣ፡፡ ሥራ አስኪያጁ ይሄ ወጣት ዳግመኛ ወደ ጣቢያው ድርሽ አይልም ብሎ ገምቶ ነበር፡፡ ግን ተሳስቷል፡፡ ሌስ ግቡን ለማሳካት ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት አያውቅማ! ለነገሩ ሌስ ዲጄ የመሆን ፍላጐት ብቻ አይደለም የነበረው፡፡ ከዚያም የላቀ ነበር - ዓላማው፡፡ በጣም ለሚወዳት አሳዳጊ እናቱ ዘናጭ መኖሪያ ቤት ሊገዛላት ይፈልጋል፡፡ የዲጄ ስራውን የፈለገውም ለግቡ ማሳኪያ ነው፡፡ ማሚ ብራውን ህልሙን እንዲከተልና ያለመውን ከማሳካት ውልፊት ማለት እንደሌለበት ያስተማረችው ገና በልጅነቱ ነበር፡፡ እናም የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ምንም ቢልም በሬዲዮ ማሰራጫው ውስጥ እንደሚቀጠር በእርግጠኝነት አስቧል፡፡ ለዚህም ነው ለአንድ ሳምንት በየቀኑ እየተመላለሰ ክፍት የሥራ ቦታ እንዳለ ሲጠይቅ የሰነበተው፡፡ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ሲታክተው በተላላኪነት እንዲሰራ አስገባው - ያለደሞዝ፡፡ መጀመርያ ላይ ሻይ ቡና በማምጣት፣ ከስቱዲዮው ለማይወጡ ዲጄዎች ምሳና እራት በመግዛት ይላላካቸው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ለስራቸው የሚያሳየው ጥልቅ ጉጉትና ስሜት እንዲያምኑት አደረጋቸው፡፡ እናም እነ ቴምፕቴሽንስ፣ ዲያና ሮዝ እና ሱፕሪምስን የመሳሰሉ ዝነኛ አርቲስቶችን በካዲላክ ወደ ስቱዲዮ እንዲያመጣቸው ይልኩት ጀመር፡፡ እኒያ ከፍተኛ ክብርና ዝና የተቀዳጁ ዝነኞች ግን ወጣቱ ሌስ መንጃ ፈቃድ እንደሌለው ፈፅሞ አያውቁም ነበር፡፡

በጣቢያው ውስጥ የተጠየቀውንና የታዘዘውን ብቻ ሳይሆን ከዚያ የበለጠም ይተጋ ነበር - ሌስ፡፡ ከዲጄዎቹ ጋር አብሮ ሲውልም በመቆጣጠርያ ፓነሉ ላይ እጃቸውን እንዴት እንደሚያንቀሳቅሱት እያየ ራሱን አስተማረ፡፡ በመቆጣጠርያ ክፍሉ ውስጥ ውጣ እስኪሉት ድረስ አብሮአቸው እየቆየ የቻለውን ሁሉ እንደስፖንጅ እየመጠጠ ብዙ ልምዶችን ቀሰመ፡፡ እንደተለመደው ማታ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ደግሞ ዲጄነትን ሲለማመድ ያመሻል - መምጣቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ለሆነበት የሥራ እድል ለመዘጋጀት፡፡ አንድ ቅዳሜ ተሲያት በኋላ ሌስ ጣቢያው ውስጥ ነበር፡፡ ሮክ የተባለው ዲጄ ግን ስቱዲዮው ውስጥ መጠጥ ይጠጣል - ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ፕሮግራም በአየር ላይ ለማሰራጨት እየተዘጋጀ፡፡ በህንፃው ውስጥ ከሮክ ሌላ የነበረው ሌስ ብቻ ነው፡፡ ዲጄው ሰክሮ ችግር ላይ እንደሚወድቅ ሌስ ቀደም ብሎ ተገንዝቧል፡፡ እናም በቅርበት ይከታተለው ጀመር - በዲጄ ቤቱ መስኮት በኩል መለስ ቀለስ እያለ፡፡ ዲጄው ድንገት “ጠጣ… ሮክ… ጠጣ!” እያለ ለራሱ ሲያወራ ማይኩ ክፍት ስለነበር ንግግሩ በአየር ላይ ተሰራጨ፡፡ ሌስ ይሄን ጊዜ ተበሳጨ፡፡ ወዲያው ነበር የስቱዲዮው ስልክ ያንቃጨለው፡፡ ሌስ ማን እንደሆነ አልጠፋውም፡፡ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ነበር፡፡
“ሌስ፤ ሚ/ር ክሌይን ነኝ”
“አውቄአለሁ” አለ - ሌስ
“ሮክ ይሄን ፕሮግራም መጨረስ የሚችል አልመሰለኝም”
“እኔም አልመሰለኝም ጌታዬ”
“አንዳቸው ዲጄዎች ጋ ደውለህ እንዲተኩት ትነግርልኛለህ?”
“እሺ እነግራለሁ!”
ስልኩን እንደዘጋ ግን “እብድ መሰልኩት እንዴ!” አለ - ለራሱ፡፡ ለዲጄዎቹ የመደወል ቅንጣት ታህል ሃሳብና ፍላጐት አልነበረውም - ሌስ፡፡ ሆኖም የስልኩን እጀታ አነሳና ቁጥሮቹን ማሽከርከር ጀመረ፡፡ ሌላ ዲጄ ለመጥራት ግን አልነበረም፡፡ መጀመርያ እናቱ ጋ፣ ከዚያም ፍቅረኛው ጋ በመደወል፤ “ሬዲዮውን ክፈቱት… ድምፄን ትሰሙታላችሁ” አላቸው፡፡ ለ15 ደቂቃ ያህል ከቆየ በኋላ ለሥራ አስኪያጁ በመደወል “ሚ/ር ክሌይን… አንዳቸውንም ላገኝ አልቻልኩም” አለው ሥራ አስኪያጁም፤ “ወጣቱ፤ የስቱዲዮው መቆጣጠርያ ላይ መስራት ታውቅበታለህ?” ሌስም “አዎ ጌታዬ! አውቅበታለሁ” ወዲያው የዲጄ ቤቱ ውስጥ ዘሎ ገባና ሮክን በቀስታ ወደ ጐን ገፍቶ መቀመጫውን ያዘ፡፡ ሌስ እቺን ቦታ ለዓመታት ሲመኛት ኖሯል፡፡ ለዓመታት ሲለማመድና ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ እቺን ቦታ ክፉኛ ተርቧት ነበር፡፡ ማይክራፎኑን ከፈተና መናገር ጀመረ “ጤና ይስጥልኝ… ስሜ ኤልቢ… ትሪፕል ፒ… ሌስ ብራውን… ይባላል፡፡ ፖፕ ሙዚቃ የማጫውትላችሁ ዲጄያችሁ… ነኝ … ከእኔ በፊትም ሆነ ከእኔ በኋላ እኔን የሚመስል አልነበረም፤ አይኖርምም … አንድና ብቸኛ ነኝ… ወጣትና ወንደላጤ፤ ከሰው መቀላቀል የምወድ … ብቃቴ የተረጋገጠ… እውነተኛ የሙዚቃ አጫዋቻችሁ… ለእናንተ እርካታ የምተጋ … ምርጥ ዲጄ ነኝ›› ቅንጣት ያህል ደንቀፍ ሳያደርገው ነበር የተናገረው፡፡ በእርግጥ ሥራው ለሌስ አዲስ አልነበረም፡፡ በየማታው ሲለማመደው የነበረ ስራ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉንም ሰው ያስደመመው፡፡ እቺ አጋጣሚ ናት የሌስን የህይወት አቅጣጫ የቀየረችው፡፡ ከዚያ በኋላማ ማን ይቻለው! በብሮድካስቲንግ ሙያ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካና በፕሮፌሽናል ተናጋሪነትም እጅግ ታዋቂ በመሆን ወደር የለሽ ስኬት ሊቀዳጅ በቃ፡፡ አያችሁ … ዕድል ተዘጋጅተው ለሚጠብቁ ሰዎች ታደላለች፡፡ ዕድል ስትመጣ ተዘጋጅተን ባለመጠበቃችን ከምታመልጠን፣ ተዘጋጅተን ጠብቀን ዕድል ሳትመጣ ብትቀር ይሻላል ፡፡

No comments:

Post a Comment