Monday, 24 September 2012

አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ6.5 በመቶ በላይ አያድግም አለ

 
• መንግሥት በአዲሱ ዓመት ከብሔራዊ ባንክ የመበደር ዕቅዱን እንዲሰርዝ ጠየቀ
• የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ መደረግ አለበት ብሏል
• ንግድ ባንክ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሰጠው ብድር 60 ቢሊዮን ብር ደርሷል
 
በጋዜጣው ሪፖርተር ባለፈው ሰኔ ወር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመገምገም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ልዑክ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ6.5 በመቶ በላይ አያድግም ሲል በሪፖርቱ አስታወቀ፡፡ የገንዘብ ድርጅቱን በበላይነት ለሚመራው ቦርድ ሪፖርቱን አቅርቦ አፀድቋል፡፡ ስልሳ ሦስት ገጾች ያሉት ሪፖርት በዋናነት ያተኮረው በዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በገንዘብ ፖሊሲ፣ በበጀት ፖሊሲ፣ በውጭ ምንዛሪ፣ በፋይናንስ ሴክተር፣ በግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴና በአገሪቱ የውጭ ብድር እንቅስቃሴዎች ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡


የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመልክቶ በሚዘረዝረው ክፍል በመንግሥት መሪነት የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች መልካም የኢኮኖሚ ዕድገትን ማስገኘታቸውንና ለድህነት ቅነሳው በጐ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ በዚህም መሠረት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፈው ዓመት በ7.5 በመቶ ማደጉን አይኤምኤፍ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የዓለም ኢኮኖሚ ባጋጠመው ቀውስና ሌሎች መሰል የአፍሪካ አገሮች ካስመዘገቡት ዕድገት አንፃር ሲመዘን አጥጋቢ የሚባል ዕድገት መሆኑን አይኤምኤፍ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ በዚሁ ሪፖርቱ አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠቅሰውን የ11 በመቶ ዕድገት ያልተቀበለው ሲሆን፣ ሌሎች ልማታዊ የሚባሉ የእስያ አገሮች አስመዝገበውት ከነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በንፅፅር ሲታይ የተጋነነ መሆኑን በማመልከት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የዕድገት ስሌቱን መፈተሽ እንዳለበት አይኤምኤፍ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

መንግሥት አብዛኛውን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበው ግዙፍ የመንገድ፣ የግድብና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በማከናወን ሲሆን፣ የእነዚህ ግንባታዎች ወጪ በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዝቅተኛ ወለድ ከሚገኝ ብድርና እስካለፈው ዓመት አጋማሽ መንግሥት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚያገኘው ብድር እንደነበር ያስታወሰው የአይኤምኤፍ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግሥት ብድር የመስጠት አቅሙ እየተዳከመ በመምጣቱና እንዲሁም የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ዕድገት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከ6.5 በመቶ እንደማይዘል የገንዘብ ተቋሙ አስታውቋል፡፡ በዚህ የዕድገት መጠን የአምስት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም እንደታሰበው ላይሆን እንደሚችል አይኤምኤፍ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትን አሁንም ከሚፈታተኑት ዋና ጉዳዮች አንዱ የዋጋ ግሽበት መሆኑን የአይኤምኤፍ ሪፖርት አስረድቷል፡፡ መንግሥት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ብድር በማቋረጡ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን ለባንኮች በመሸጥ በዝውውር ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ለመቀነስ በመቻሉ፣ የዋጋ ግሽበትን በመጠኑም ቢሆን ለመቆጣጠር መቻሉን አይኤምኤፍ የጠቀሰ ሲሆን፣ ይህ የመንግሥት ዕርምጃ በሌሎች ተጨማሪ የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃዎች ማለትም የወለድ ምጣኔን (Interest Rate) ማስተካከልና በመሳሰሉት ያልተደገፈ በመሆኑና እንዲሁም የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በእጅጉ እየሳሳ በመምጣቱ፣ የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት ወደ ነጠላ አኅዝ ለማውረድ የሚደረገው ጥረት ውጤት አልባ እንደሚሆን አይኤምኤፍ አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ግሽበት ዋነኛ መንስዔ ከውጭ የሚገባው (Imported Inflation) መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን፣ ይህም በአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት ላይ የ80 በመቶ ድርሻ እንዳለው ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ገለልተኛ የሆኑ የአገሪቱ ኢኮኖሚስቶች ከውጭ የሚገቡ ምርቶች (Imported Commodities) በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ (GDP) የሃያ በመቶ ድርሻ እያላቸው፣ ከውጭ የገባ የዋጋ ግሽበት ለአጠቃላይ የዋጋ ግሽበት የ80 በመቶ ድርሻ አለው መባሉን ኢ ሳይንሳዊና ትርጉም አልባ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ይወስድ የነበረውንና ባለፈው ዓመት ያቋረጠውን ብድር እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ ለመበደር ማቀዱን አይኤምኤፍ በሪፖርቱ ውስጥ የጠቀሰ ሲሆን፣ ይህ የመንግሥት ዕቅድ የዋጋ ግሽበትን የሚያባብስ አደገኛ ዕቅድ ሲል ነው የኮነነው፡፡ መንግሥት ከዚህ ዕርምጃው እንዲቆጠብም አይኤምኤፍ አስጠንቅቋል፡፡ ስለዚሁ የመንግሥት የመበደር ዕቅድ የጠየቅናቸው ኢኮኖሚስቶች ዕቅዱን በእሳት ላይ ቤንዚን እንደ መጨመር የሚቆጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኅዝ እንደሚወርድ በመተማመን በዘንድሮ የበጀት ዓመት ከብሔራዊ ባንክ ለመደበር ዕቅድ ይዞ እንደነበር ታማኝ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የበጀት ፖሊሲን አስመልክቶ የመንግሥት የበጀት ፖሊሲ አፈጻጸም አጥጋቢ መሆኑን ተቋሙ አመልክቶ፣ ይህም መልካም በሚባል የታክስ አሰባሰብ የተደገፈ መሆኑን አይኤምኤፍ ሲያመላክት፣ የመንግሥት ድርጅቶች በዋናነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮምና ክልሎች ከንግድ ባንክ ያለገደብ የሚወስዱት ብድር የመንግሥት በጀትን ገጽታ የሚቀይር ነው ብሏል፡፡ በባንኩ የገንዘብ ፍሰት (Liquidity) ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን አይኤምኤፍ በሪፖርቱ አስምሮበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የልማት ድርጅቶችና ክልሎች እስካሁን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትና በረዥም ጊዜ ክፍያ የሚከፈለው የብድር መጠን 60 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑንና በባንኩ የገንዘብ ፍሰት (Liquidity) ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፋቸውን የባንኩ ምንጮችም ይናገራሉ፡፡

የመንግሥት የታክስ አሰባሰብ ሥርዓት የተሻሻለ ቢሆንም ለአምስት ዓመቱ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ከሚያስፈልገው የገንዘብ ፍላጐት አንፃር በቂ አለመሆኑን አይኤምኤፍ ገልጾ፣ መንግሥት በዋናነት የአገር ውስጥ ቁጠባን ማሳደግ ላይ አተኩሮ እንዲሠራና እንቅስቃሴው የተገደበውን የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ከፖሊሲና ከአሠራር ማነቆዎች ለማላቀቅ መጣር እንዳለበት አይኤምኤፍ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡

የውጭ ምንዛሪን አስመልክቶ ደግሞ እ.ኤ.አ በመስከረም 2010 የተደረገው የምንዛሪ ማስተካከያ የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ያደረገ ቢሆንም፣ የብድር የምንዛሪ ተመን ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ የዋጋ ግሽበትን መንግሥት ሊቆጣጠር ባለመቻሉ፣ የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርቶች በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንዳልቻሉ አይኤምኤፍ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ሙሉ በመሉ በእርግጠኝነት ወደ ነጠላ አኅዝ ሳያወርድ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስተካከያ በማድረጉ በአገር ውስጥ የብር የመግዛት አቅም ተዳክሟል፡፡

ከዶላር ጋር ባለው ንፅፅር ሲታይ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ማድረጉንና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ካልተቻለ የምንዛሪ ማስተካከያ መደረጉ የማይቀር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን በተመለከተ አይኤምኤፍ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሁለት ወራት መሆኑን ቢያመለክትም፣ አንዳንድ ወገኖች ግን ይህ የክምችት መጠን መቀነሱን ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የአይኤምኤፍ ተወካይ ያን ሚከልሰን በቅርቡ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ የውጭ ምንዛሪው ክምችት ለሁለት ወራት ይበቃል፡፡ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አገሪቱ በቂና አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ እንዳላት ለፓርላማ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የፋይናንስ ሴክተሩን በተመለከተ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የግል ባንኮች እንቅስቃሴ አመርቂ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአስገዳጅነት ያወጣው የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ የባንኮቹን የማበደር አቅም ማዳከሙን አሁንም በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ በዚህ የተነሳም የግሉ ሴክተር ተጠቂ እንደሆነ አይኤምኤፍ አስታውቆ፣ ባንኮቹ ከብሔራዊ ባንክ ቦንድ የመግዛት ግዴታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ግዥው ግን መፈጸም ያለበት ከአጠቃላይ የሰጡት ብድር (Gross Disbursment) ሳይሆን፣ ከተጣራ ብድር (Net Disbursement) ቢሆን የተሻለ መሆኑን አይኤምኤፍ ጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አብዛኞቹ ባንኮች በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰጡት ብድር ከተቀማጭ ገንዘብ አንፃር ሲታይ ከ92 በመቶ በላይ በመሆኑ የገንዘብ እጥረት (Liquidity Problem) ውስጥ እንዳሉ አይኤምኤፍ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ያለበት የፋይናንስ ሁናቴ በትክክል የሚታወቅ ባለመሆኑ፣ በባንኩ የሚቀርቡት የፋይናንስ ሪፖርቶች አጠራጣሪና ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆኑን አይኤምኤፍ አስምሮበታል፡፡ በኢትዮጵያ ያልተሰበሰበ የብድር መጠን ከአንድ በመቶ በታች ነው መባሉ በየትም አገር ያልታየና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አይኤምኤፍ ያመለከተ ሲሆን፣ ይልቁንም የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን የአምስት ዓመት ዕቅድ በማድነቅ የተመዘገበው ዕድገት የሚያበረታታ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን የአምስት ዓመቱን ዕቅድ በታቀደው ሁኔታ ለማስፈጸም ተጨማሪ የገንዘብና የፋይናንስ ፖሊሲ ዕርምጃዎች ካልተወሰዱ አስቸጋሪ እንደሚሆን በመግለጽ፣ አገሪቱ መጠነ ሰፊ የፖሊሲ ማስተካከያ ያስፈልጋታል ብሏል፡፡ በተለይም በገንዘብ ፖሊሲ፣ በውጭ ምንዛሪ፣ በባንኮች ዙሪያና የግል ሴክተሩን በተመለከተ አፋጣኝ ማሻሻያዎች ካልተደረጉ፣ በአዎንታዊነት የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ሊሸረሸር እንደሚችል በመግለጽ ሪፖርቱን ደምድሟል፡፡


Reporter News Paper

No comments:

Post a Comment