Saturday, 29 September 2012

አንድ ምሁር በገበሬው ፊት


አንድ በእርሻ ላይ የሚሠራ ዪኒቨርሲቲ መምህር በገበሬው ዙርያ ጥናት ለመሥራት ወደ ገጠር ወጡ፡፡ የአካባቢው የገበሬዎች ማኅበርም በአካባቢው የሚኖሩትን ገበሬዎች ለጥናቱ እንዲተባበሩ ለማድረግ ስብሰባ ጠራ፡፡ ምሁሩም ከገበሬዎቹ ፊት ለፊት ተቀመጡና ስለመጡበት ሥራና ከገበሬዎቹ ስለሚጠበቁ ነገሮችም ማብራራት ጀመሩ፡፡
 
‹‹ጉድ አፍተርኑን፤ እዚህ የመጣነው ፍሮም ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከእናንተ  ጋር ሚት ማድረጋችን ጉድ ኦፖርቹኒቲ ነው፡፡ ኦፍ ኮርስ እዚህ ለመምጣት ያሰብነው ቢፎር ኤ ይር ነበር፡፡ በት አንዳንድ ፐሮሲጀሮችን ለማሟላት ሃርድ ስለሆነብን ትንሽ ሌት ሆነናል፡፡ ሶሪ፡፡
 
‹‹የኢትዮጵያ ሜይን ኢንካሟ አግሪካልቸር መሆኑን አንደርስታንድ ታደርጋላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አግሪካልቸር ዋን ኦፍ ዘ ሜይን የሰው ልጆች አንሸንት አክቲቪቲዎች ነው፡፡ ኢን ኢትዮጵያ ደግሞ ሎንግ ሂስትሪ አለው፡፡ በትአግሪካልቸራችን አንደር ደቨሎፕ ሆኗል፡፡ ፋርሚንጋችን ፖር ነው፡፡ አክቲቪቴያችን  ሌበረስ ነው፡፡ ገበሬው ሳይንቲፊክ ዌይ አይጠቀምም፡፡ ፋርሚንጋችን ሜካናይዝድ አይደለም፡፡ ገበሬው ኢንፎርሜሽን እንደልቡ አያገኝም፡፡ 
ናው እኛ ሪሰርች የምንሠራበት ኤርያ ገበሬው ሃው ካን አቺቭ ዘኒው ቴክኖሎጂ በሚለው ዙርያ ነው፡፡ ከእናንተ ፉል ፓርቲሲፔሽን እንፈልጋለን፡፡ አይ ሆፕኮኦፐሬቲቭ ትሆናላችሁ፡፡ ያዘጋጀናቸው ኩዌሽነሮች አሉ፡፡ ለእነዚህ ኩዌሽነሮች ኢንፎርሜሽን ትሰጡናላችሁ፡፡ ከእናንተ መካከል ራንደምሊ ኢንፎርማንቶችን እንወስዳለን፡፡ ሳም ኦፍ
ዩ ሳትመረጡ ብትቀሩ ደስፐሬት እንዳትሆኑ፡፡ ኢን አዘር ዌይ እናገኛችኋለን፡፡
 
እነዚህን ኢንፎወሜሽኖች ወሰደን ዳታዎቹን የእናንተን ላይፍ ለማስተካከል እንጠቀምበታለን፡፡ ኢሪጌሽን ላይና አኒማል ሀዝባንደሪ ላይ ለመሥራት እየተዘጋጀን ነው፡፡ አፍተር ዛት ደግሞ ሌሎች ላይ እንሄድባቸዋለን፡፡ 

ታንክ ዩ ለትብብራችሁ፡፡ 

ገበሬዎቹ አላጨበጨቡም፤ ራሳቸውንም አልነቀነቁም፡፡
 
የገበሬ ማኅበሩ ሊቀ መንበር ‹‹እስኪ ጥያቄ ያላችሁ?›› አሉ፡፡ ገበሬዎቹ ዝም አሉ፡፡ ሊቀመንበሩ ደጋግመው ቢጎተጉቱም ገበሬዎቹ ጸጥ አሉ፡፡
 
በመካከል አንዲት እናት ተነሡና፡፡

‹‹እስኪ የመጡት ሰውዬ ይናገሩና እንጠይቃለን›› አሉ፡፡

ሊቀ መንበሩ ግራ ገባቸውና ‹‹እርሳቸውማኮ ተናገሩ›› አሉ፡፡ 

‹‹እኛ ግን አልሰማናቸውም›› አሉ እኒያ እናት፡፡

‹‹ታድያ እስካሁን ምን ያደረጉ ነው የመሰላችሁ›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡

‹‹እኛማ በማናውቀው ቋንቋ የመክፈቻ ጸሎት እያደረሱ ነው የመሰለን›› አሉ፡፡
 
(መስከረም 17 ቀን በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ቀርቦ በነበረ ዝግጅት ከኢትዮጵያ የመጡ ምሁር በአማርኛ ማስረዳት ሲያቅታቸው ጋዜጠኛውም በአማርኛ ሲተረጉም ለተሰማው ነገር መታሰቢያ ነው)
Daniel Kibert



 

No comments:

Post a Comment