Thursday, 13 September 2012

የአውጫጭኝ ወጥ

 
By Daniel Kibert

ሴትዮዋ እርሟን አንድ ቀን ወጥ ሠራች አሉ፡፡ ገና ወጡ ከድስቱ ሳይወጣ ጎረቤቱን ሁሉ በነቂስ ጠራችና ወጥ ቅመሱ አለች አሉ፡፡ ሰውም ምን አዲስ ነገር ልታሳየን ይሆን? እያለ ግልብጥ ብሎ ወደ ቤቷ መጣ፡፡ ሴትዮዋም እንጀራውን እያጠፈች ከድስቱ ወጥ እየጨለፈች አቀረበች፡፡

በላተኛውም ግምሹ እያዳነቀ፣ ግማሹም እየሳቀ፣ ግማሹም እየተሳቀቀ፣ ሌላውም በቸርነቷ እያመሰገነ በላ፡፡ እርሷም ከምግቡ በኋላ ቡና አፍልታ የተጋባዦችን አስተያየት ትቀበል ጀመር፡፡ አንዳንዱ በወጡ አሠራር መደነቁን፤ ሌላው በተጠቀመችው ቅመም መማረኩን፤ ሌላውም የጨመረችው ቅቤ ልዩ መሆኑን፤ የቀረውም ሰው በሠራችበት ድስት የተደነቀ መሆኑን ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹እርሟን ጠምቃ ሰጠች ጠልቃ›› ሳይሏት ይህ ሁሉ ጎረቤት ተገኝቶ ይህንን  የርሷን  ግብዣ  ማድነቁ  አስደስቷታል፡፡  ከዚህ  በፊት  በሠፈሩ  ያልተደረገ፤  አዲስ  ነገር  መሆኑንም  ጎረቤቶቿ አድንቀውላታል፡፡


እስከ ዛሬ ድረስ እኔ ነኝ ያሉ አያሌ የወጥ ባለሞያዎች በመንደርዋ ተሠርተዋል፤ እንዲህ እንደርሷ ሰው ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ወጡን የቀመሰለት፤ እንዲህ እንደርሷም ወጡን ለሕዝብ ክፍት ያደረገ ባለሞያም ታይቶ ተሰምቶ እንደማይታወቅ የተናገሩም ነበሩ፡፡  እጅግ የገረማት ደግሞ ከተጠሩት ጎረቤቶቿ በላይ ያልተጠሩት ጎረቤቶቿና አንዳንድ የአካባቢው ሠፈሮች ነዋሪዎች ነገሩን ሰምተው ብቻ ስለ ሁለት ጉዳይ ሲሉ መምጣታቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ ቤቷ ምን እንደሚመስል ለማየት፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዴው ሲፈጥራቸው እበላ ባዮች ነበሩና ለመብላት ሲሉ መምጣታቸው ነው፡፡ በርግጥ ወጥ ለመቅመስ፤ ቀምሶም አስተያየት ለመስጠት የመጡ ባለሞያዎችም ነበሩ፡፡ 

እናም በዚያ ዕለት ቀኑን ሙሉ ቤቷ ወጥ ለመቅመስና አድናቆታቸውን ለመግለጥ በመጡ ሰዎች ተጨናንቆ ዋለ፡፡ አንዳንዱም፣ ሰው ወጥ ለመቅመስ የተሰለፈ መሆኑን አንኳን ሳይሰማ እንዴው ሰልፍ ሲያይ ጊዜ ወይ ቲ ሸርት ወይም ስንዴ ይሰጣል ብሎ በመገመት እንዴው ተቀላቅሎ የገባም ነበረ፡፡  እናም ቀኑ በዚህ መንገድ አለፈ፡፡

ማታ  ሴትዮዋ  ቀኑን  ገመገመችው፡፡  የሕዝቡ  ተሳትፎ  እንዴት  ነበር?  አለች፡፡  የመንደሩ  ሕዝብ  በነቂስ  ወጥቶ አስተያየቱን የገለጠበት ሁኔታ መኖሩንም ተገነዘበች፡፡ በሌላም በኩል የተሠራው ወጥ ማነሱን ከሕዝቡም ቁጥር አንጻር ቅስቀሳ ቢደረግና በሚገባ ቢሠራ ኖሮ ከዚህ በላይ ሕዝብ ሊወጣ ይችል እንደነበረ ተረዳች፡፡  ከዚያም በመንደሩ እኔ ነኝ ያለ ትልቅ ጎላ ተከራየች፡፡ ይህ ድስት በአንድ ጊዜ ከዐሥር በላይ በጎችን ውጦ ዝም ማለት የሚችል ዓይነት ነው፡፡ ምድጃውንም ናቡከደነፆር ሠለስቱ ደቂቅን ከጣለበት ምድጃ እንዳይተናነስ አድርጋ አሠራችው፡፡  ማማሰያውንም  ወጥ  ለማማሰል  ሳይሆን  ነገር  ለማማሰል  በሚያስችለው  መጠን  አስቆረጠችው፡፡ ምንም እንኳን ከዚያ በፊት እንጨት መቁረጥ ለአካባቢ ጥበቃና ለመሬት ለምነት ጎጂ መሆኑን፣ ኅብረተሰቡም
ከዚህ ጎጂ ባሕል መውጣት እንዳለበት በዕድርና በዕቁብ ቢከለከልም እርሷግን ያሳየችው ነገር ለየት ያለ በመሆኑ ተፈቀደላትና ስድሳ ሸክም እንጨት አስቆርጣ ለማገዶ አዘጋጀች፡፡

በዚያ ሰሞንም የመንደሩ ወሬ ሁሉ ተቀየረ፡፡ በልቅሶም በገበያም፣ በሠርግ ቤትም፤ በሻሂ ቤትም፤ በቡና ቤትም ፤ በጠጅ  ቤትም  ወሬው  ሁሉ  ስለ  ሴትዮዋ  ወጥ  ሆነ፡፡  እንዴውም  ስለ  እርሷ  ወጥ  የማያወራ  ሰው  ሁሉ  ወሬ የጠፋበትና አላዋቂ መስሎ እስከሚታይ ድረስ ወሬው ሁሉ ስለ ወጡ ብቻ ሆነ፡፡ የመንደሩ አዝማሪዎች እንኳን
በየጠጅ ቤቱና በየ አረቂ ቤቱ የሚዘፍኑት ዘፈን ሁሉ ስለ ወይዘሮዋ ወጥ ብቻ ሆነ፡፡ የአካባቢው ለማኞች እንኳን ከሕዝቡ  ገንዘብ  የምናገኘው  የሰሞኑን  ወጥ  ስናነሣ  ነው  ብለው  ስላሰቡ፤  ‹‹ስለ  ሰሞኑ  ወጥ››Ž እያሉ  ነበር የሚለምኑት፡፡ አንዳንድ የሠፈሩ ወይዛዝርትም በዚህ ሰሞን የዚህ ወጥ ወሬ ካልቀዘቀዘ በቀር ሌላ ወጥ መሥራቱ
‹‹ሠርቶ እንዳልሠሩ መሆን ነው›› እያሉ ወጥ መሥራቱን ትተውታል ይባላል፡፡

በየጉልት ገበያውና በየመንደሩ ሱቆች፣ በየመንደር መርፌ ወጊዎችና በየመንደር አዋላጆች ዘንድ ወሬው ሁሉ ይህ ብቻ በመሆኑ ሠራተኞቹም ሥራ ፈትተው ወሬ ብቻ ሲያወሩ ይውላሉ ይባላል፡፡ ባለጉዳዮችም የሚያስተናግዳቸው ጠፍቶ እነርሱም አዳዲስ የወጥ መረጃዎችን ብቻ ከየቦታው መሰብሰብ ሆኗል ሥራቸው ይባላል፡፡

‹‹ይህ በእንዲህ እንዳለ አለ ቴሌቭዥን››
‹‹ሴትዮዋ ወጡን ላቅ ባለና የሌሎች መንደሮችንም ተሳትፎ ሊጨምር በሚችል መልኩ ለመሥራት ወስናለችና ዝግጅቱን  አጠናቀቀች››  ሲል  አንድ  የመንደሩ  የኮሙኒኬሽን  ባለሞያ  ገለጠ፡፡  በገለጠውም  መሠረት  ሕዝቡም የተገለጠው ነገር ተግባራዊ እንዲሆን ከጎን ሆኖ ለመንቀሳቀስ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው ይባላል፡፡ በትልቁ ጎላ የዐሥር በግ ሥጋ ተጨመረበት፡፡ ወደ ድስቱ የሚመጣው ውኃም እጥረት እንዳያጋጥመው ሲባል
በቦቴ ታዝዞ መጣ፡፡ የቅቤም እጥረት እንዳይኖር ቅቤ ሻጮች ሁሉ በየቅቤ ማኅበራት ተደራጅተው ቅቤ ወደ ድስቱ እንዲያመጡ ተደረገ፡፡ ላሞች ራሳቸው ተሰብስበው ቅቤውን ለመስጠት በቁርጠኛነት መወሰናቸው ተነግሯል፡፡ እናም አሁን ካለፈው የቅቤ ታሪክ ለየት ያለ ቅቤ ወደ ድስቱ በመግባት ላይ መሆኑንም ወይዘሮዋ ለዜና ሰዎች
ገልጠዋል፡፡

ሽንኩርትና ቃርያም ቢሆን ካለፈው ለየት የሚያደርገው ሻጮቹ ራሳቸው ልጠው፣ ራሳቸው ከትፈው ማቅረባቸው ነው፡፡ ይህም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሳየውን ርብርብ ያሳያል ያሉ አሉ፡፡ በተለይማ የቅመማ ቅመም ነጋዴዎች ተሳትፎ ያልተጠበቀ መሆኑን ከአማሳዮች አካባቢ የተገኘውን መረጃ ጠቅሰው የዘገቡ አሉ፡፡ ቅመሙ እንደሌላው ወጥ እየተመጠነ ሳይሆን፣ ስለ ምግብ አበሳሰል ከተጻፉት መጻሕፍት ድንጋጌ በተለየ መልኩ በኩን ታልም በቁናም እየተጨመረ መሆኑ ታውቋል፡፡ የየአካባቢው ቅመማ ቅመም ሻጮችም እንዴው እንዳገኙት እያመጡ በድስቱ ውስጥ መጨመር እንጂ ከእነርሱ በፊት ተመሳሳይ ቅመም ይግባ አይግባ አይጠይቁም ነበር፡፡ አሁን ስለ ወጡ አሠራር፣ ስለ ቅመሙና፣ ቅቤው፣ ስለ ሽንኩርቱና ቃርያው፣ ስለ ጨውና በርበሬው አስተያየት የሚሰጥ፤ ‹‹ኧረ ይሄ ወጥ በኋላ ይገለምማል፣ ይጎረናል፣ ከልኩ ካለፈ እጅ እጅ ይላል፣ ወጡ ልክና መልክ ይኑረው›› ብሎ የሚናገርም አልተገኘም፡፡ ቢገኝም የማርያም
ጠላት ይሆናል፡፡ 

በተለይ የጨው ነጋዴዎች ድጋፍ ይሁን ተቃውሞ በማይታወቅ ሁኔታ ግማሽ ኩንታል ጨው አምጥተው በድስቱ ውስጥ  መጨመራቸውን  በኩራት  ሲያወሩ  የሰሙ  ሁሉ  የነገሩ  አዝማሚያ  አላማራቸውም፡፡  በርበሬ  ሻጮችስ ቢሆኑ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ሰውን ሁሉ አቃጣይ በርበሬ እየሸጡ ሲያስነጥሱትና ሲያስለቅሱት ከርመው አሁን ደግሞ ዋናው የድስቱ አማሳዮች ሆነው መቅረባቸው አሳዛኝም አስተዛዛኝም ሆኗል፡፡ በሕዝቡ አስተያየት የበርበሬውን ቃጠሎ ያሻሽሉታል ሲባል ያንኑ በርበሬ በባሰ ሁኔታ አምጥተው በድስቱ ውስጥ መጨመራቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህም ተብሎ በዚያ ወጡ በትብብር ተሠራ፡፡

እንደተለመደው ሕዝቡ በነቂስ ወጣ፡፡ ይህንን በትብብር የተሠራ የወይዘሮዋ ወጥ ለመቅመስ ወጣ፡፡ እርሷም ከእንጀራው እያጠፈች ፣ ከወጡም እየጨለፈች ታቀርብ ጀመር፡፡ ውኃው ቧንቧ ውስጥ እንኳን እያለ እንዲህ ያለ ጣዕም አልነበረውም፡፡ ቅመማ ቅመሙ ለሽያጭ የቀረበ እንጂ ሊበላ ድስት ውስጥ የገባ አይመስልም ነበር፡፡ ቅቤውማ ቃናው ብቻ ሳይሆን መልኩም ጭምር ይታያል፡፡ ሽንኩርቱ ለማራቶን የተዘጋጀ እንጂ ወጥ ውስጥ የገባ አይመስልም ነበር፡፡ የበጉ ሥጋማ እዚያው በስሎ በስሎ ሟሙቶ
አልቋል፡፡

አሁን ለቀማሾቹ ችግር የሆነባቸው ወጡ የምን ወጥ እንደሆነ መለየት አለመቻላቸው ነው፡፡ ቅመሙ፣ ቅቤውና ሽንኩርቱ በዛና ወጡ የሥጋ ወጥ መሆኑን ማንም እንዳያውቀው አደነቀው፣ ያጣጣመው፣ ያ መጀመርያ ጨምሩ ጨምሩ እያለ እጁን ጭምር ይልስ የነበረው፤ አሁን ቅመሙም ሲበዛ፤ ቅቤውም ሲበዛ፤ ሠሪዎቹም ከልባቸው ሳይሆን በመመርያ ብቻ ያሻቸውን ሲጨምሩ፤ የወጡን ጣዕም አጠፋው፡፡ አስቀድሞ ያደነቀውና ያመሰገነውም ማማረርና ማቅለሽለሽ ጀመረው፡፡ 

ሴትዮዋም መጀመርያ የሰዎችን ሁሉ አስተያየት በደስታ ትቀበል እንዳልነበረች አሁን ወደ ድግሱ ቦታም ብቅ ለማለት አፈረች፡፡  ድሮም በአውጫጭኝና በመመርያ የተሠራ ወጥ መጨረሻው ይሄ ነው፡፡ እያሉ ተመጋቢዎች በየጠረጲዛው ሥር ይተቹ ጀመር፡፡

©     
   
 

1 comment: