Tuesday, 18 September 2012

የፍትሕ ሥርዓቱ በመዳከሙ ሴቶችን ይበልጥ እያጠቃ ነው

የኢትዮጵያዊያት ሴቶች ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማየት እስቲ አንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሳ፡፡

1. ምን አዎንታዊ ነገር አለ?


ችግሮችን ከማየታችን በፊት ሴቶችን የሚመለከት በአገራችን እየታየ ያለውን አዎንታዊ ጎን እንይ፡፡ የሴቶች መብት በሕገ መንግሥት ዋስትናው የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊና አዎንታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በሴቶች መብት ላይ የሚያተኩሩና የሚከታተሉ በመንግሥት በሚኒስቴር ደረጃ፤ በሲቪል ማኅበረሰብ ደግሞ የሴቶች መብት አቀንቃኞችና የሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበራት አሉ፡፡ ይህ አዎታንዊ ነው፡፡

ሴቶችን ራስ ለማስቻልና ወደ ሥራ የሚያስገቧቸው የሴቶች የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራትንና ድርጅቶችን ማቋቋም፣ የሴቶችን እንቅስቃሴ የሚደግፉ የገንዘብ አቅራቢ አካላትን መመሥረት በአዎንታዊ ጎኑ ይታያሉ፡፡ ሴቶች ወደ ቢዝነስ ዓለም በመግባት ራስን ለመቻል የሚያደርጉት ጥረትም አዎንታዊ ነው፡፡

                                                             2. ምን ችግር አለ?
 
ሀ. በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እየተባባሰ ነው


በገጠርም በከተማም በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው አካላዊ ጥቃት ዘግናኝ እየሆነ ነው፡፡ “ሁለት ዓይኖች ተጎለጎሉ” የሚሉ ዜናዎች የተለመዱ እንዳይሆኑ እያሳሰበ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን በከተማና ለመገናኛ ብዙኀን ቅርበት ያገኙ ድርጊቶች ተስተጋቡ እንጂ፣ ያልተሰሙና ያልተስተጋቡ በርካታ ተመሳሳይ ጭካኔዎች በየገጠሩና በሌሎች ከተሞችም እየደረሱ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ በአስቸኳይ መፍትሔ ይፈለጋል፡፡

ለ. ሴት ወጣቶች ለአሰቃቂ ስደት እየተዳረጉ ናቸው

የወጣት ሴቶች ዋናው ችግር ውጭ አገር መሄዳቸው አይደለም፡፡ መሄድ የትም ያለ ነውና፡፡ ለግርድናና ለቤት ሠራተኝነት መሄዳቸውም አይደለም ችግሩ፤ እሱም ሥራ ነውና፡፡ ነገር ግን ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ታዳጊ ሴቶች በኑሮ ችግር ምክንያት ዕድሜ ጨማምረው ሲሰደዱ ይታያሉ፡፡ በሄዱበት አገር ተገቢ ጥንቃቄና ክትትል አይደረግላቸውም፡፡ ለጥቃት፣ ለእስር፣ ለመባረር፣ ለመጥፋትና ለሞት እየተዳረጉ ናቸው፡፡

በሌሎች አገሮችም የሠራተኛ ጉልበት በአግባቡ ወደ ውጭ ይላካል፡፡ መብታቸውና ክብራቸው ተጠበቆ፡፡ ከአገራችን ወደተለያዩ የዓረብ አገሮች የሚሄዱ ሴቶች ግን መብታቸውም፣ አካላቸውም፣ ሥነ ልቦናቸውም፣ ሕይወታቸውም ጠባቂ የለውም፡፡ የሚታረዱት፣ የሚታነቁት፣ የሚወረወሩትና የሚታሰሩት እየበዙ ናቸው፡፡

ተገቢ ትኩረት አልተሰጣቸውም፤ ትኩረት ይሰጣቸው እንላለን፡፡

ሐ. የፍትሕ ሥርዓቱ በመዳከሙ ሙስና ሴቶችን ይበልጥ እያጠቃ ነው

የፍትሕ ሥርዓታችን በሙስና፣ በአቅም ማነስ፣ በማስፈራራት፣ ወዘተ የድርሻውን መጫወት ባለመቻሉ የሴቶች ጥቃት ተባብሷል፡፡ ይህ ችግር በአጠቃላይ ኅብረተሰቡን እየጎዳ ቢሆንም ሴቶችን ይበልጥ እያጠቃ ነው፡፡ በባለገንዘብና በባለጉልበት ተበድለው ፍትሕ ማግኘት እየተሳናቸው ነው፡፡ በፍቺ ወቅት የሚገባቸውን ድርሻ ማግኘት እየተሳናቸው ነው፡፡ የባል የበላይነት እየተንፀባረቀ ነው፡፡ በሥራ ሲበደሉና ሲጠቁም የሚከላከልላቸው ሕግና ሥርዓት ባለመኖሩ በኑሮ ችግር እየተጎዱ ናቸው፡፡

መ. ለዝሙት፣ ለሴተኛ አዳሪነትና ለምግባረ ብልሹነት እየተዳረጉ ነው


በእርግጥ ለሴቶች ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴው ይታያል፡፡ ሆኖም ግን የኑሮ ውድነትና የቤተሰብ ችግር በርካታ ወጣት ሴቶችን ወደ አላስፈላጊ የሥራ መስክ እንዲጎርፉ እያደረገ ነው፡፡ ለውርደትና ለበሽታም እየተዳረጉ ነው፡፡ ለሴተኛ አዳሪነትና ለምግባረ ብልሹነት እየተጋለጡ ነው፡፡ ይህን አስከፊ ችግር መከላከል ካልተቻለ ወደ ወንጀል ሊገፋቸው ይችላል፡፡ የዝሙት ሥራ መኖሩ የሚያስገርም ባይሆንም የመስፋፋቱ አቅጣጫና ፍጥነት በእጅጉ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ረ. አሁንም ተገቢ የሥራና የኃላፊነት ምደባ እያገኙ አይደሉም


የሴቶችን ቁጥርና ተሳትፎ ለማሳደግ ተብሎ በሚኒስትርነትም፣ በፓርላማ አባልነትም፣ በሌሎች የሹመት ቦታዎችም አዎንታዊ ነሮች ይታያሉ፡፡ በመንግሥት፣ በግልና በሲቪል ማኅበረሰብ መሥርያ ቤቶችም የተወሰኑ መሻሻሎች ሲታዩ ይስተዋላል፡፡

ነገር ግን አሁንም ገና ነው፡፡ በአቅማቸው ልክ በትክክል ኃላፊነት ቢሰጣቸው ኖሮ በግልም ሆነ በመንግሥት መሥርያ ቤቶች በተሻለ አቅም ኃላፊነት ሊሸከሙ የሚችሉ በርካታ ሴቶች አሉ፡፡ ካለ ምንም ድጋፍ በአቅማቸውና በብቃታቸው ብቻ የሚመጥኑ ሴቶች አሉ፡፡ ሆኖም ግን በኃላፊነት አሰጣጥ ላይ አሁንም የወንዶች የበላይነት እየታየ ነው፡፡ ይህም ሊሻሻል ይገባዋል፡፡

አዎንታዊውም ሆነ አሉታዊ ችግሩ በዚህ አጭር ጽሑፍ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ለማሳየት እየሞከርን ያለነው በሕገ መንግሥታችን የሴቶች እኩልነት መረጋገጡ ቢሰፍርም በተግባር ግን ገና መሆናችንን ነው፡፡

ኃላፊነቱ ግን ለመንግሥት ወይም ለኃላፊዎች ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደ አገር ልንረባረብበት የሚገባ አጀንዳ ነው፡፡

የሴቶችን መብት ማረጋገጥ ለሴቶች ተብሎ የሚደረግ ስጦታ ወይም በጎ አድራጎት አይደለም፡፡ ሕዝባችንና አገራችን የሚያድጉበት መንገድ እሱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ መብቱ የሚጠበቅለት ዜጋ ለአገር የሚያበረክተው እጥፍ ድርብ ስለሚሆን ነው መብት ይጠበቅ የሚባለው፡፡ የሴቶች ተሳትፎ ለአገር ዕድገት መፍትሔ ስለሚሆን ነው፡፡ ለልማትና ከድህነት ለመላቀቅ ብቸኛው መንገድ ስለሆነ

No comments:

Post a Comment